Saturday, 03 August 2019 14:05

‹‹ፓርቲያችንም ሆነ የዎላይታ ሕዝብ፣ በኢትዮጵያ አንድነት አይደራደርም››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  • ጠ/ሚኒስትሩ የሕዝቡን ጥያቄ በማዳመጣቸው የመሪነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል
                     • በክልልነት ጥያቄ የሚፈጠር ግርግር ፈጽሞ አይኖርም፤እስካሁንም የለም

         ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም፣ ‹‹በአረንጓዴ አሻራ ቀን›› በወላይታ ተገኝተው ችግኝ ተክለዋል፡፡ ሕዝባዊ
ውይይትም አድርገዋል፡፡ ጠ/ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ወላይታን ሲጎበኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ውይይት ምን አንኳር ጉዳዮች ተነሱ? የዎላይታ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ መነሻው ምንድን ነው? ጥያቄው ወደ ረብሻና ግርግር እንደማይሄድ ምን ዋስትና አለ? ክልል ከመሆን
ሕዝቡ ምን ያገኛል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርቡ ከተመሰረተው ‹‹የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን)›› ም/ሊቀመንበር አቶ ሃይለ ሚካኤል
ለማ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል።



             የዎላይታ ሕዝብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረገውን ውይይት እንዴት አገኙት?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ወላይታ ሲመጡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይሄ ሁለተኛው ነው፡፡ ባለፈው አመት በሰኔ ወርም መጥተዋል፡፡ በወቅቱ ተመልሼ መጥቼ ተጨማሪ ውይይት እናደርጋለን ብለው ነበር፡፡ ያንን ቃላቸውን ጠብቀው ነው መጥተው ሕዝቡን ያነጋገሩት፡፡ ከ8 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ድረስ ሰፊ ውይይት ነበር የተደረገው፡፡ በውይይቱ ላይ ነጋዴዎች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የወላይታ ወጣቶች ተገኝተዋል፡፡
በዋናነት የተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
በዋናነት በውይይቱ የተነሳው የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ነው፡፡ በርካቶች የጠየቁትም ይሄንኑ ጉዳይ ነው፡፡ ከሥራ አጥነትና ከልማት ጋር በተያያዘም የቀረቡ አሉ፡፡ የክልልነት ጥያቄውን ተገቢነትና በምን መነሻ ተጠየቀ የሚለውን በተመለከተ የተለያዩ ሰዎች ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ እሳቸው ለዚህ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ‹‹እኔ የክልልነት መብት መስጠትም መከልከልም አልችልም፤ እናንተ ከፈለጋችሁ በህገ መንግስቱ መብታችሁን መውሰድ ትችላላችሁ:: ነገር ግን ክልል መሆን ይጠቅማል አይጠቅምም የሚለውን በሚገባ ምከሩበት አስቡበት›› የሚል ነው፡፡ ተሰብሳቢውም፤  ከቀበሌ ወረዳ ጀምሮ እስከ ዞን ም/ቤት ድረስ የተመከረበትና እንደ ሕዝብ ሙሉ አቋም የተያዘበት ጉዳይ መሆኑን ለማስረዳት ሞክሯል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ምከሩበት ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? እናንተ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት፤ ምንድን ነው ከዚህ ምላሻቸው የተረዳችሁት?
የሳቸው መነሻ እኛ እንደገባን፣ ደኢህዴን ሐምሌ 8 ቀን 2011 የወሰነውን ውሳኔ  አለ፡፡ በዚያ ውሳኔ ላይ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ተመልሶ ሌላው ግን በአንድነት እንዲቀጥል የመፈለግ ሁኔታ ታይቷል:: ይሄ የዎላይታን ሕዝብ ያስቆጣ ነው፡፡ በአግባቡ የተጠየቅን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በዚህ መልኩ ለማስፈር መሞከር ተገቢ አይደለም፡፡ ወላይታ በአንድ ወቅት የራሱ መንግስታዊ አስተዳደር የነበረው ሕዝብ ነው፡፡ አሁንም እየጠየቀ ያለው የራስ በራስ የማስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ምከሩት ሲሉም፤ የደቡብ ክልል እንዳይፈርስ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል፡፡ እሳቸውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እመክርበታለሁ ብለውናል፡፡ በእኛ በኩል ግን ሕዝብ ከስር ጀምሮ እስከ ላይኛው አመራር በሚገባ መክሮ የወሰነው ጉዳይ ነው፡፡ በእርጋታ መክሮበታል፤ ሰላማዊ ትግልም እያደረገ ነው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ተደጋግሞ በስብሰባው ሲቀርብላቸው የነበረው፣ በጉዳዩ ጥልቅ ምክክር እንደተደረገበትና ሕዝቡ በአንድ ልብ እንደወሰነበት ነው፡፡ ስለዚህ ምከሩ ሲሉ እሳቸው፤ የደቡብ ክልል እንዳይበተን ካላቸው ፍላጎት አንጻር ነው፡፡
በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ መቅረቡን ተከትሎ ወላይታን ጨምሮ ሌሎችም ፉክክር በሚመስል መልኩ የክልል እንሁን ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ጥያቄ በዚህ ወቅት ማቅረብ ለምን ተፈለገ? የዎላይታ ሕዝብ ከዚህ ቀደም ክልል የመሆን ጥያቄ አቅርቦ ያውቃል? የዎላይታ ክልል የመሆን ፍላጎት ከምን የመነጨ ነው?
የኛ የክልልነት ጥያቄ ታሪካዊ መነሻ አለው:: የዎላይታ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ የራሱ አስተዳደር፣ የራሱ ንጉስ፣ የራሱ መተዳደሪያ የነበረው ሕዝብ ነው:: አንደኛው ታሪካዊ መነሻው ይሄ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ በታሪክ ሂደትም፣ በየጊዜው ክልል ለመሆን ሲጠይቅና ሲታገል ነው የኖረው፡፡ ለምሳሌ በ1983፣ በሽግግሩ ወቅት ዎላይታ ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆን ተወስኖ ነበር፡፡ በኋላ ሕዝቡ ሳይመክር ነው ሀሳቡ ታጥፎ፣ ደቡብ ውስጥ እንድንጨፈለቅ የሆንነው፡፡  በወቅቱ ዎላይታ ዞን ጥምር እንዳይሆን ተደርጎ ነበር መዋቅሩ የተሰራው፡፡ ከዚያ በኋላ በ1992 ዓ.ም እኛ ‹‹ዋጋ ጎዳ ሪጅሉሼን›› እያልን የምንጠራው ለሁለት ወራት ያህል የስራና ትምህርት እንቅስቃሴ ቆሞ ከፍተኛ ትግል ተደርጎ ነበር፡፡
ምንድን ነው ትግሉ? ምን ነበር ጥያቄው?
ዞን ወይም ክልል የመሆን ጥያቄ ነበር፡፡ በወቅቱ ዞን እንኳ አልሆነም ነበር፡፡ በኋላ በዚህ ትግል ዞን መሆን ተችሏል። በወቅቱ ግን የክልልነት ጥያቄውም ተይዞ ነበር፡፡ በየጊዜውም በተለያየ አግባብ ምክክር ሲደረግበት የቆየ ነው፡፡ እኛ ክልል ለመሆን ስንጠይቅ፤ ሌላኛው ምክንያት የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው፤ የዎላይታ ወጣቶች በመላ ኢትዮጵያ ተበትነው፣ ጠንካራ ሠራተኛነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው፡፡ በዚያው ልክ መብታቸው በሚገባ እየተከበረ አይደለም፡፡ ላልተገባ የጉልበት ብዝበዛ ጭምር እየተዳረጉ ነው:: ይህ ሁሉ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በራሱ ልማት ሰርቶ፣ ወጣቶቹን ተጠቃሚ ማድረግ ባለመቻሉ ነው፡፡ ለራሱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነፃነት ያለው የክልል መዋቅር ሳይፈጠር በመቅረቱ ነው ለዚህ ችግር የተዳረገው፡፡ ሌላው ጥያቄ የቋንቋ ጉዳይ ነው:: እኛ እንደ ፓርቲ ከያዝነው የመታገያ አጀንዳ አንዱ፤ የዎላይተኛ ቋንቋን የፌዴራል የስራ ቋንቋ ማድረግ ወይም ማስደረግ ነው፡፡ ጥያቄውንም አቅርበናል፡፡ የዚህ መነሻው ደግሞ ዎላይተኛ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ወይም ከኢትዮጵያ ሕዝብ  አንድ አስረኛው የሚናገረው ቋንቋ ስለሆነ ነው፡፡ የብሄራዊ ሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ እስካሁን የአገር አቀፍ ሚዲያ ቋንቋ መሆን አልቻለም፡፡ ክልል መሆን የምንፈልገው ከዚህም አንጻር ነው፡፡ በአጠቃላይ ያለው ችግር ከፍተኛ ነው፡፡ ጥያቄያችንን ስናቀርብም፣ ከሌሎች ጋር ለመፎካከር ወይም ሌሎች ስለጠየቁ አይደለም፤ ለመጠየቅ የሚያስገድዱ ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች ስላሉን ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ ደግሞ ከዚህ በፊትም ሲነሳ የነበረ ነው፡፡
10 ሚሊዮን የሚለውን የሕዝብ ብዛት ከየት አመጡት? ማረጋገጫዎ ምንድን ነው? በ1999 በተደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ የዎላይታ ሕዝብ ብዛት 2.3 ሚሊዮን ነው የሚለው…
እንደውም እኛ ሌላው ጥያቄያችን፣ የ1999 ዓ.ም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት እንዲሰረዝ ነው፡፡ የዎላይታን ሕዝብ ብዛት የሚገልፁ ግምቶችም ሆኑ ቆጠራዎች ትክክል አይደሉም፡፡ የዎላይታ ሕዝብ ቁጥር ከ10 ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ ሆን ተብሎ ቁጥሩ እንዲያንስ ተደርጓል፡፡ እኛ ግን ከ10 ሚሊዮን በላይ ይሆናል ብለን ነው መረጃ የያዝነው፡፡
10 ሚሊዮን የሚለውን ከየት አመጣችሁት?
በተለያየ አግባብ የተለገፁ ቁጥሮች አሉ፡፡ እነሱን መነሻ አድርገን፣ በራሳችን ግምት ያስቀመጥነው ነው::
ከ25 ዓመት በላይ በደቡብ ክልል ውስጥ ቆይቶ ድንገት ዛሬ ክልል ካልሆንን የሚል ጥያቄ ማቅረብ ምን ያህል አሳማኝ ምክንያቶች አሉት ትላላችሁ? ይሄ ወቅት ለምን ተፈለገ?   
ጥያቄው በተለያየ አግባብ ሲቀርብ የቆየ ነው፡፡ ነገር ግን ያኔ በመሣርያ ሃይል የታፈነ ስለነበር ነው:: አሁን አንጻራዊ መብት ስላለ፣ ሕዝቡ መብቱን ተጠቅሞ የበለጠ ነፃነቱን ለማጣጣም ነው ጥያቄውን በዚህ ወቅት እያቀረበ ያለው፡፡ ሌላም አጣዳፊና ገፊ ምክንያቶች አሉት፡፡ እንደሚታወቀው የዎላይታ ተወላጆች፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ በእርግጥ ይሄ ጥቃት አሁን ቆሟል፡፡ ነገር ግን ባለፈው ዓመት ደቡብ ክልል ሃዋሳ ላይ የተፈፀመው ድርጊት፣ እጅግ አስነዋሪና ዎላይታ ትግሉን የበለጠ ማሳደግና ራሱን የቻለ ክልል መሆን እንዳለበት ያመላከተ መነሻ ጉዳይ ነበር፡፡ የሃዋሳው ድርጊት እጅግ ክብር ነው::  ከድርጊቱ በኋላ በተደረጉ ውይይቶች፣ የዎላይታን ሕዝብ መብት እንዴት ማስከበር ይቻላል የሚለው ሰፊ ቦታ የያዘ ጉዳይ ነበር፡፡ ከዚያ ውይይት ውስጥ ነጥሮ የወጣው አንዱ ጉዳይም፤ ራሱን የቻለ የተወላጆቹ የሆነ ጠንካራ ክልል መፈጠር አለበት የሚለው ነው፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ችግር ላይ ከሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል አካላት ጋር መወያየት እንኳ አልተቻለም ነበር፡፡ ይሄ የውይይት እድል አለመገኘቱ ሕዝቡን ከፍተኛ ብሶት ውስጥ ነው የከተተው፡፡ ከዚህ መነሻ የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ ደግሞ አንድም ብርጭቆ እንኳ ሳይሰበር ነው እየተጠየቀ ያለው፡፡ የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ አንዱ መነሻ መገፋት ነው፡፡
ክልል ከመሆን ምን የሚገኝ ጥቅም አለ?
የፖለቲካዊ ነፃነት ይኖረዋል፤ የራስን ችግር በራስ መፍታት ያስችላል፡፡ ይሄ ደሞ የፌዴራል መንግስትን ጭምር ማገዝ ነው፡፡ ከኢኮኖሚ አንጻር በርካታ በተነሳሽነት የሚሰሩ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ ስለዚህ ጠቀሜታው ከዎላይታም አልፎ ለአገር ነው:: ከማኅበራዊ ጠቀሜታው አንጻር ደግሞ አስቀድሜ እንዳልኩት፤ እኛ ቋንቋችንን ማበልፀግ ማሳደግ እንፈልጋለን፡፡ ታሪካችንንም በራሳችን ማሳደግ እንፈልጋለን፡፡ ዞን ሆነን የራሳችን ሚዲያ ኖሮን፣ ቋንቋችንን ማሳደግ አንችልም፡፡ ክልል ከሆንን ግን ይሄን ማድረግ ያስችለናል፡፡ አቅሙም ይፈጠራል፡፡ የተወላጆቹን መብትም በድርድርና በውይይት ከአቻ ክልሎች ጋር ተነጋግሮ ማስከበር ይቻላል፡፡ ዞን ሆነን ይሄን ማድረግ አልቻልንም፡፡ የደቡብ ክልል የሚባል ረጅም ቢሮክራሲያዊ አካሄድ አስቸጋሪ ሆኖብን  ነው የቆየው፡፡ ከዚህም አንፃር የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ የቅንጦት አይደለም፤ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ እኛ የክልልነት ጥያቄ ስናነሳ፣ ኢትዮጵያን ወደ ጎን ትተን አይደለም፡፡ የዎላይታ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱና በኢትዮጵያ ጉዳይ ቅንጣት ጥርጣሬ የለውም፡፡ ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ይጠብቃል፡፡ ለዚህም ቅድሚያ ሰጥቶ ይቆማል፡፡ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ፀብ የለውም፡፡ እንደውም የታሪኩ አካል ነው፡፡ የዎላይታ ተወላጆች ትናንት አድዋ ላይ፣ ባድመ ላይ፣ ካራማራ ላይ ሞተዋል፡፡ ስለዚህም የአገር ግንባታን ሂደት በጽኑ ይደግፋል፡። ለድርድርም አያቀርብም፡፡ የዎላይታ ሕዝብ የኢትዮጵያን አንድነት መቼውንም ቢሆን ለድርድር አያቀርብም፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ አይደራደርም፡፡ ክልል ሲሆንም የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከሩ ላይ ነው ተግቶ የሚሰራው፡፡
ዎላይታ ክልል ቢሆን ሌሎች በውስጡ ያሉ ህዝቦች ምን ዋስትና አላቸው?
የዎላይታ ሕዝብ ሌላውንም አቃፊ ሕዝብ ነው:: ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብሮ ነው የሚኖረው፡፡ አንድም ሰው በብሔሩ ምክንያት በዎላይታ ምድር ጥቃት ተፈፅሞበት ተፈናቅሎ አያውቅም፡፡ እስካሁን ባካሄድነው ሰልፍም ሁሉንም ያሳተፈ እንቅስቃሴ ነው የተደረገው፡፡ በዚህ ሰልፍ የስልጤ፣ የአማራ፣ የጉራጌ የሌላውም ተወላጆች አብረውን ተሳትፈዋል፡። ለነገሩ አሁን እንደዚህ እንላለን እንጂ… እኛ የምናምነው፣ እነሱም የሚያምኑት፣ በስነ ልቦናቸው፣ ዎላይታዎች እንደሆኑ ነው፡፡ ይሄ ዎላይታ ውስጥ ያለ ሃቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ከትግራይ የመጣ ትግረ የሚባል ጎሳ አለ፡፡ ወላይታ ሆኖ ነው የቀረው፡፡ ከአማራ የመጡ ሶስት ጎሳዎች ወላይታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ከኦሮሞ የመጡ ከሦስት በላይ ጎሳዎች ዎላይታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ዎላይታ እንዲህ ነው የተሠራው፡፡ የዎላይታ ሕዝብ ራሱን ብቻ አጥሮ አይኖርም፤ አቃፊ ሕዝብ ነው፡፡ ዎላይታ በመላ አገሪቱ ተንቀሳቅሶ ሠርቶ የሚያድር ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ከሁሉም ጋር አብሮ ተባብሮ መኖር ያውቅበታል፡፡
የክልልነት ጥያቄው ከቀረበ 8 ወር ሞልቶታል ተብሏል፡፡ ትንሽ ቆይቶ ‹‹አንድ ዓመት ሞልቶናል›› በሚል ግርግርና ረብሻ እንዳይፈጠር ብለው የሚሰጉ ወገኖች አሉ፡፡ እናንተስ ይሄን ስጋት ትጋሩታላችሁ?
በመጀመርያ ደረጃ ጥያቄያችን ከ8 ወር በፊት በክልሉ ም/ቤት ትኩረት ባያገኝም ጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄያችንን በቀናነት ማየታቸው ለኛ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በቀጣይም ቀና ምላሽ ይሰጠናል የሚል እምነት ነው ያለን። ቢዘገይም እንኳን፣ የዎላይታ ሕዝብም ሆነ ፓርቲያችን ሰላምን ነው የምናስቀድመው፡፡ ህገ መንግስታዊ ጥያቄያችንን፣ መብታችንን በሕግና በሥርዓት ነው እስከ መጨረሻው የምናቀርበው፡፡ የዎላይት ሕዝብም ወጣቶችም፣ ይሄን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ መቀጠል አለባቸው፡፡ እኛ ባለን ግምገማ፤ ሕዝቡ ሁሉንም ነገር በሰላማዊ መንገድ ለማከናወን ሰፊ ስነ ልቦናዊ ብቃትና ዝግጅት አለው፡፡ የኛም ዝግጅት በዚሁ መልክ ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ለሚታዩ የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄው ምንድነው ትላላችሁ?
አገሪቱ ውስጥ ያለመረጋጋት አለ፡፡ በየቦታው መጠናቸው ይስፋ ይነስ እንጂ ግጭቶች… አለመተማመኖች ይታያሉ፡፡ መንግስትም የሚችለውን መፍትሄ ለመስጠት እየሞከረ ነው:: አሁን ትልቁ ችግር ያለመረጋጋት ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ችግር ግን ወታደር አሰማርቶ ምላሽ መስጠት ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም፡፡ የችግሮቹ ዋና ምንጭ ፖለቲካዊ ነው፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች ደግሞ መፍትሄው ፖለቲካዊ ነው መሆን ያለበት፡፡ ጥልቅ ግምገማ ተደርጎ፤ በየአካባቢው ጥያቄዎች ሳይውል ሳያድር፣ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል፡። ሌላው የህግ  የበላይነት ጉዳይ ነው፡፡ የህግ የበላይነት የሚመጣው በፍትህ ነው፡፡ ስለዚህ ፍትህ ማስፈን ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይ የጠ/ሚኒስትሩን የሰሞኑን ጉብኝት እንዴት አገኛችሁት?
ለሁለተኛ ጊዜ ነው መጥተው ያነጋገሩን:: መደመጥ ትልቅ ነገር ነው፡። ስላደመጡን ደስ ብሎናል፡፡ ሕዝቡን በማዳመጣቸው እንደ መሪ ግዴታቸውን ተወጥተዋል ብለን ነው የምናስበው፡፡ የሕዝቡን ጥያቄዎችም በአግባቡ ሰምተዋል፡፡ ምላሽ ያሏቸውንም በአግባቡ ሰጥተዋል፡፡ የክልል ጥያቄ ነው በአመዛኙ የቀረበላቸው፤ ለሱም የመሰላቸውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እሱን እናከብራለን፡፡ ነገር ግን የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ፤ የህልውና ጥያቄ ሆኖ ነው አሁን እየቀረበ ያለው፡፡ ጥያቄችን ግን አሁንም ሰላማዊ ነው:: በዚህ ጥያቄ የሚፈጠር ግርግር ፈጽሞ አይኖርም፡፡ እስካሁንም የለም፡፡ ለወደፊትም እንዲኖር አንፈልግም፡፡ ሰላማዊ ትግላችን፤ በእርግጥም ሰላማዊ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

Read 1430 times