Saturday, 03 August 2019 13:58

‹‹አሁንም ጨለማ ቤት የታሰረ የለም፤ ሰው አይገረፍም፤ ጥፍር አይነቀልም››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)


              የሰኔ 15ቱ የባለስልጣናት ግድያና ጥቃት በስልጠናዎች የታገዘና አስከፊ አደጋን የሚጋብዝ እንደነበር ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ያብራሩት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ተጨማሪ ባለስልጣናትንና የጦር ጀነራሎችን ለመግደልም ታቅዶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ወንጀል ጋር ተያይዞ በተጠርጣሪነት የተያዙ ሰዎች ሰብአዊ መብት እየተከበረ መሆኑን ‹‹ጨለማ  ቤት የታሰረ የለም፣ ሰው አይገረፍም፣ ጥፍር አይነቀልም›› ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡  
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን አቅልሎ ማየት ተገቢ አይደለም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን አስቀድሞ መቆጣጠር ባይቻል ኖሮ ሃገሪቷ ወዳልተፈለገ አዝማሚያ ታመራ ነበር ብለዋል፡፡
ክስተቱን ተከትሎ ስለተወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎችም ያስረዱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘ ከባህር ዳርም ከአዲስ አበባም 350 ያህል ሰዎች ታስረው እንደነበር ጠቁመው ከእነዚህ ውስጥ 120 ያህሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ መፈታታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከድርጊቱ ጋር ተያይዞ መንግስት የወሰደው እርምጃ ጥንቃቄ የታከለበት መሆኑን ሲገልፁም፣ የተለያዩ ሀገራት እንዲህ ያለው ክስተት ሲያጋጥማቸው የወሰዷቸውን የጅምላ እርምጃዎች በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ ከወንጀሉ ጋር በተገናኘ በ24 ሰዓት ውስጥም 1ሺህ 200 ያህል ጥቆማዎች ደርሰዋቸው እንደነበርና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
ወንጀሉን ለመፈፀም ከውጭ ሀገር በመጡ ባለሙያዎች ጭምር ስልጠናዎች የወሰዱ ሰዎች እንዳሉ የሚያሳዩ መረጃዎች ማግኘታቸውን በመግለጽም፤ ድርጊቱ የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ወደ ኋላ ለመመላለስ የታቀደበት ነበር ብለዋል፡፡ የታሠሩትም ሆነ በህግ ተጠያቂ እየተደረጉ ያሉት በጉዳዩ ተሳትፎ ይኖራቸዋል ተብለው ከሚጠረጠሩት በጥቂቱ መሆኑን ገልጸዋል -ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
ጀነራል ሰአረ መኮንን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው ጠባቂያቸው አንገቱ ላይ በመመታቱ ከጉዳቱ አገግሞ መናገር ባይጀምርም በስልክ ይገናኛቸው የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው አስፈላጊ መረጃዎች መሰብሰባቸውንም ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የሰኔ 15ቱን ክስተት መነሻ አድርጐ መንግስት የተቃውሞ ድምፆቻችንና መገናኛ ብዙሀንን ለማፈን እየሞከረ ነው በሚል የሚቀርቡ ትችትና ወቀሳዎችን በተመለከተም የተጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው በራሱ ያረጋገጠውን መብት ከዜጐች ላይ መልሶ እንደማይነጥቅ፣ የሰዎችን ድምጽ የማፈን ፍላጐት እንደሌላው የታሰሩ ሰዎች የሰብአዊ መብት አያያዝን አስመልክቶም ሲመልሱ፤ ‹‹መፈንቅለ መንግስት ተሞከረ ተብሎ እንደከዚህ ቀደሙ ልምድ የተረሸነም የተሠቀለም የለም›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ተገቢው የሰብአዊ መብት ጥብቃ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
‹‹በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ያለን አቋም አልተቀየረም አሁን ጨለማ ቤት የታሠረ የለም፣ አሁን ሰው አይገረፍም፣ ጥፍር አይነቀልም” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡  በቀጣዩ አገራዊ ምርጫን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡ ኢህአዴግ ቀጣዩ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ አቋም ይዞ በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይሁን እንጂ ምርጫው ይካሄድ አይካሄድ የሚለውን እንደዚህ ቀደሙ ኢህአዴግ ብቻውን የሚወስነው አይሆንም፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ህዝቡም የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው ብለዋል፡፡ ምርጫውን በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ለማካሄድ ኢህአዴግ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ዐቢይ፤ ለምርጫው ከፍተኛ በጀት በመመደብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምርጫ ህጐችም ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራንን ባሳተፈ መልኩ መዘጋጀቱንም በመግለጽ፡፡


Read 11986 times