Saturday, 03 August 2019 13:57

የምርጫና የፓርቲዎች አዋጅ በፓርላማ እንዳይፀድቅ ፓርቲዎች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

የአዋጁ 20 አንቀጾች እንዲሰረዙ፤ 15 ያህሉ እንዲሻሻሉ ይፈልጋሉ

            የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች መተዳደሪያ ረቂቅ አዋጅ በፓርላማው እንዳይፀድቅ 33 የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ የጠየቁ ሲሆን የአዋጁ 20 አንቀፆች እንዲሠረዙና 15 ያህሉ ደግሞ እንዲሻሻሉ ይፈልጋሉ፡፡
ረቂቅ አዋጁ በአፋኝና አፍራሽ አንቀፆች የተሞላ ነው ሲሉ የተቹት ፓርቲዎቹ፤ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የህግ ማሻሻያ ም/ቤቱንም ሆነ የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ላይ ምክክር በተደረገበት ወቅት ማሻሻያ ሃሳቦችን በጽሑፍ አቅርቡ ተብሎ አቅርበናል፤ ነገር ግን ቦርዱ የማሻሻያ ሃሳባችንን ሳያካትት እንዲፀድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ልኮታል ያሉት ፓርቲዎቹ ያቀረብናቸው የማሻሻያ ሃሳቦች ባለመካተታቸው ረቂቅ አዋጁ የኛን ሃሳብ ያገለለ በመሆኑ መጽደቅ የለበትም ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርላማው እንዲፀድቅለት ያቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከስምምነታችን ውጪ ስለሆነ እንደገና በስፋት እንድንወያይበት ይደረግልን ያሉት ፓርቲዎቹ፤ የሚኒስትሮች ም/ቤትም ቅሬታቸውን በጽሞና ተመልክቶ አዋጁ እንዳይፀድቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ረቂቅ ህጉ እንዳይፀድቅ በአጽንኦት የጠየቁት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፤ ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ይዘት የዜጐችን የመደራጀት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚገድብና የህዝብን ጥቅምና መብት የሚጋፋ ነው በማለት ክፉኛ ተችተውታል፡፡
በዋናነት ፓርቲዎቹ ቅሬታ ያቀረቡባቸው አንቀፆችም ለፓርቲዎች ምዝገባ መመዘኛነትና ለእጩ ተወዳዳሪዎች የቀረበውን መስፈርት መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ በረቂቅ ህጉ የቀረቡ መስፈርቶች የምርጫውን አሸናፊ አስቀድሞ የሚበይን በመሆኑ አገሪቱን ወዳልተፈለገ የፖለቲካ ውዝግብ የሚወስድ ህግ ነው ብለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ እንዲሰረዙ አቤቱታ ካቀረቡባቸው የአዋጁ አንቀፆች መካከልም ከ5ሺህ ብር በላይ እርዳታ የሰጠ ደጋፊ ስሙ እንዲገለጽ የሚያስገድደው አንቀጽ ተጠቃሽ ሲሆን ይህም ደጋፊን የሚያሸማቅቅ ስለሆነ ነው የምንቃወመው ብለዋል፡፡
የአባላት ዝርዝርና አድራሻ በግልጽ መታወቅ አለበት እንዲሁም አንድ የፓርቲ አባል የሆነ እጩ ተወዳዳሪ፣ በሚወዳደርበት አካባቢ 3ሺህ ድምጽ አስቀድሞ ማሰባሰብ አለበት የሚሉት አንቀፆችም ፓርቲዎቹ እንዲሠረዙ ከጠቀሷቸው መካከል ይገኙበታል፡፡
ፓርቲዎቹ ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል ካሏቸው አንቀጾች መካከልም አንድ ሀገር አቀፍ ፓርቲ 10ሺህ ድምጽ ለምስረታው ማሰባሰብ አለበት የሚለው ተጠቃሽ ሲሆን ይህም የፓርቲዎችን አቅም ያላገናዘበ ነው በማለት 3ሺህ ድምጽ በቂ ነው የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
በመንግስት ስራ ላይ እያለ ለምርጫ የሚወዳደር ግለሰብ፣ በመጀመሪያ በጊዜያዊነት ከደሞዙም ከስራውም ይለቃል የሚለው አንቀጽም፣ ፍቃድ ላይ ሆኖ ደሞዝ እየተከፈለው መወዳደር እንዲችል መደረግ አለበት ሲሉ ፓርቲዎቹ በማሻሻያ ሃሳባቸው ጠይቀዋል፡፡
መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ይህን አቤቱታቸውን እንዲያደምጡና በጐ ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቁት 33ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ መንግስት ለአቤቱታቸው በጐ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ በቀጣይ በሚያደርጓቸው ትግሎች ላይ በጋራ መክረው አቋማቸውን እንደሚያሳውቁም ገልጸዋል፡፡
መኢአድና ኢህአፓን ጨምሮ የተለያዩ ሀገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች የተሰባሰቡበት ይህ 33 የፓርቲዎች ቡድን፣ በጋራ ጉዳዮች ላይም በህብረት የመስራት እቅድ እንዳለው ተነግሯል፡፡


Read 10991 times