Saturday, 03 August 2019 13:54

በአዲስ አበባና በድሬደዋ ምርጫ መራዘም፤ ፓርቲዎች የተለያየ አቋም ይዘዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)


                  • ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ምርጫ ማድረግ ብጥብጥን መጋበዝ ነው›› - ኢዜማ
                  • ‹‹ምርጫውን ለማራዘም የቀረቡ ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም›› - አብን


          ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቂ ዝግጅት አላደረግሁም በማለቱ በተራዘመው የአዲስ አበባና የድሬደዋ ም/ቤቶች እንዲሁም የአካባቢና ማሟያ ምርጫ ጉዳይ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለያየ አቋም ይዘዋል፡፡
ምርጫዎቹ መራዘም ጉዳይ ላይ አዲስ አድማስ ካነጋገራቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የዜግነት ፖለቲካን እናራምዳለን የሚሉት፣ ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነው ሲሉ በብሔር ማንነት የተደራጁት ደግሞ መራዘሙ ተገቢ አይደለም፤ ምርጫውን ማካሄድ ይቻል ነበር የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ፓርቲያቸው ከምርጫ በፊት የሀገር መረጋጋት ይቀድማል የሚል ጽኑ አቋም እንዳለው የገለፁት የኢትዮጵያ ዜጐች ንቅናቄ ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ም/ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ ምርጫ ቦርድ በቂ የህግ፣ መዋቅርና ሎጀስቲክስ ዝግጅት ባላደረገበት ሁኔታ ምርጫውን ማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ወደ ክልሌ አትምጡ የሚል ሃይል በበዛበት ሀገር ምርጫ ይካሄድ ቢባልስ እንዴት ነው የሚካሄደው?›› የሚል ጥያቄ ያነሱት ዶ/ር ጫኔ፤ ሀገሪቱ ወደ መረጋጋትና የሃሳብ ፖለቲካ መስመር ውስጥ ሳትገባ የሚደረግ ምርጫ ውጤቱ መልካም አይሆንም ይላሉ፡፡
ሠላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም ያሉት የኢዜማ ም/ሊቀመንበር፤ አዲስ አበባ ላይ የባለቤትነት ውዝግብ፣ ድሬደዋ ላይም የብሔር የስልጣን ክፍፍል ቀመር ባለበት ሁኔታና ባልተረጋጋ ድባብ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ብጥብጥን የሚጋብዝ ነው የሚሆነው፤ ምርጫው እንዲራዘም መደረጉ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ፤ የሀገር መረጋጋት ሳይኖር ስለ ምርጫ ማሠብ በራሱ ተገቢ አይደለም የሚል አቋም እንዳለው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አቶ ሙሉጌታ አማረ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንኳስ የሁለቱን የከተማ አስተዳደርና የማሟያ ምርጫ ቀርቶ ብሔራዊ ምርጫም ማካሄድ አዳጋች ነው ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ድርጅታቸው ከምርጫው ይልቅ ለሀገር መረጋጋትና ለሕግ የበላይነት መስፈን ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል፡፡
በምርጫዎቹ ለመወዳደር ዝግጁ እንደነበሩ የጠቆሙት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (አፌኮ) ደግሞ የሁለቱ ከተማዎች ም/ቤት ምርጫ መራዘሙን አይቀበሉትም፡፡ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ሊካሄድ ይገባው ነበር በማለት በሁለቱም ከተማዎች ላይ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉ በግምገማችን ተገንዝበናል ያሉት የአብን ም/ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ፤ ምርጫዎቹን ለማራዘም የቀረቡ ምክንያቶችም አሳማኝ አይደሉም ብለዋል፡፡
በአንፃራዊነት ሁለቱ ከተሞች በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ በለጠ፤ ምርጫ ለማካሄድ አዳጋች ሁኔታዎች ባለመኖራቸው የምርጫው መራዘም ተገቢ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
የአፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ በሰበብ አስባቡ የከተሞች ም/ቤቶቹ ለተጨማሪ ሁለት አመታት እንዲራዘሙ መደረጉ፣ የህዝብን ስልጣን መጋፋት ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡
ፓርላማው የህዝብን ስልጣን ነው እየተጋፋ ያለው የሚሉት አቶ ሙላቱ፤ ምርጫዎቹን ለማካሄድም አዳጋች ሁኔታዎች አሉ የሚል እምነት ፓርቲያቸው እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡
መንግስት የቁርጠኝነት ማጣትና ዳተኝነት ይስተዋልበታል ያሉት የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር፤ በእጁ ያለን የፀጥታ ሃይል፣ ህግና ሎጀስቲክስ ተጠቅሞ ሀገርን በማረጋጋት የህዝብን መብት የማስከበር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባና የድሬደዋ ም/ቤት እንዲሁም የአካባቢና ማሟያ ምርጫ መካሄድ የነበረባቸው በ2010 ዓ.ም የነበረ ሲሆን በወቅቱ በከተሞቹ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ የለም በሚል በ2011 እንዲካሄድ ተወስኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዘንድሮ እንደሚካሄድ ሲጠበቅ የነበረው ምርጫም፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሄድ ያለው (የአመቱ) ጊዜ አይበቃኝም በማለቱ፣ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በቀጣይ ከሚደረገው አገራዊ ምርጫ ጋር አብሮ እንዲካሄድ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡    

Read 10101 times