Saturday, 03 August 2019 13:48

መልክቶቻችሁ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ዝርፊያ በአደባባይ ያሳፍራል!


      በቅርብ የምናያቸው ነገሮች በሁለት አቅጣጫ ይቀየራሉ፡፡ አንዳንዶቹ የተሻለ እመርታ ሲያሳዩ፣ ሌሎቹ ከነበሩበት እየባሱና እየዘቀጡ ይሄዳሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ለውጡ ከመጣ በኋላ በርካታ ደስ የሚያሰኙ ነገሮች የተፈጠሩትን ያህል፣ ግርግሩን በሚጠቀሙ ስግብግቦች ባሉበት የረገጡና ወደባሰ ችግር ገብተው ሕብረተሰቡን ያስመረሩ ነገሮች በከተማና ከከተማ ውጭ እየታዩ ነው፡፡
ለኔ - የሕዝቡን ስሜት በእጅጉ እያሳዘኑ ካሉ ነገሮች፣ የትራንስፖርቱ ዘርፍ በእጅጉ አስከፊ ነው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት ችግር መዘርዘር መጽሐፍ የመፃፍ ያህል ሰፊ ቢሆንም፣ ዐቢይ የሚባሉት ችግሮች ግን ከወንበር በላይ መጫንና ያለ ተቆጣጣሪ ታሪፍ መጨመር ናቸው፡፡ ይሁንና እንዲህም ሆኖ የአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊሶች በፀሐይና በዝናም ሳይታክቱ፣ የትራፊኩን ፍሰት ለማሳለጥ ለሚከፍሉት ዋጋ አድናቆት ይገባቸዋል፡፡ በፆታ መለየቱ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ ቢሆንም ለኔ እንስት ትራፊኮች በአመፀኛ የታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የተሻሉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡
ለዛሬ ትዝብቴ ምክንያት የሆነኝ ግን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ያሉት የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ጉዳይ ነው፡፡
በተደጋጋሚ ታዘብኩት የደቡብ ኢትዮጵያ ጉዞዬ፤ ‹‹እዚህ አገር መንግስት የለም?›› የሚያሰኘኝ የትራንስፖርቱ ዘርፍ ነው፡፡ በኔ ገጠመኝ የሚሰሩ ከአዲስ አበባ ወደ ሆሳዕናና ወላይታ ሶዶ በሚያልፈው መንገድ ላይ የተደረደሩት ትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ጉዳይ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንዳስተዋልኩት፣ ከአዲስ አበባ ሆሳዕና፣ ከአዲስ አበባ ቡታጅራና ከአዲስ አበባ ወራቤ የሚጭኑት ሚኒባሶች የሚጭኑ ያለቅጥ ነው፡፡ ከዕቃ መጫኛው ውጭ ሰውን እንደ ዕቃ ባገኙበት ክፍተት ቦታ ሁሉ ይደረድራሉ:: ተሳፋሪውም ተላምዶት እንዳደረጉት ይሆናል:: ምናልባት የሚነጫነጨው አዲስና እንደኔ የመስመሩን ዐመል ያላወቀ ሰው ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ትርፍ መጫን ብቻ ሳይሆን ያለ ታሪፍ መጫኑ ነው፡፡ የአዲስ አበባውን መናኸሪያ፤  እንተወው! አለቃ ያለበት፣ መንግሥት የሚያውቀው አይመስልም፡፡ የመንግሥት ሥራ ግን ምን ይሆን?
እንግዲህ ከአውቶቡስ መናኸሪያ ተጭኖ የወጣ ሰው፤ ጉድ የሚያየው መንገድ ላይ ነው፡፡ አንድ ሰው ከአዲስ አበባ ሆሳዕና ወይም ቡታጅራ፣ ወራቤ እስኪደርስ ድረስ በየመንገዱ ለቁጥጥር ቆመዋል የተባሉ ሰዎች እያስቆሙ፣ ለደንቡ ያህል መውጫ ይጠይቃሉ፡፡ በአጋጣሚ ጋቢና የተቀመጠ ሰው፤ ሾፌሩ ደጋግሞ ሲወርድ፣ የመኪናው ረዳት አሳንሶ በአራት ማዕዘን የጠቀለለትን የሃምሳ ብር ኖት ከመውጫው ጋር ይዞ አቀብሎ ሲመለስ ማየት የተለመደ ነው:: አንዳንዴም በየመንገዱ ሲበዙበትና ሾፌሩ ሲነጫነጭ ይታያል፡፡ እናም ትራፊክ ፖሊሶችና ተቆጣጣሪዎች ለኪሣቸው ቀረጥ ለመቀበል እንጂ ለሕዝቡ መብት ምንም ሲጠቅሙ አይታዩም:: መንግሥት ለራሳቸው ቀረጥ የሚሰበስቡ መኳንንት ከሚቀልብ አልፎ አልፎ ትራፊክ ከመመደብ ባለፈ ዘራፊ ቢተወውስ?
ገና ከአዲስ አበባ ከተማ መውጫ ላይ የሚጀመረው ሕገወጥ የእጅ መንሻ እንዲቆም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የደቡብ ክልላዊ መንግሥት አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል:: የመንገድ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ስራስ ምን ይሆን? የሚገለፀው በምድር ይሁን በሰማይ ግራ ያጋባል! ለመሆኑ ይሄን ጉድ ያየና የሚያውቅ ይኖር ይሆን? መክሸፍ እንደ መንገድ ትራንስፖርት ቢባል ይበዛበት ይሆን? በአደባባይ ዝርፊያ ያሳፍራል!
ራህማቶ ሁሴን  

Read 10849 times