Print this page
Saturday, 03 August 2019 13:40

የአንድ ሺ ቀናት መዘዝ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

 በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ እጅግ ወሳኝ ጊዜያት ከጽንሰቱ እስከ ሁለተኛ ዓመት ልደቱ ድረስ ያሉት አንድ ሺ ቀናት ናቸው፡፡ እነዚህ ጊዜያት ለአንድ ሰው ቀጣይ አካላዊና አዕምሮአዊ ዕድገት ላይ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
አንዲት ነፍሰጡር እናት በማህፀኗ ለተሸከመችው ጽንስ አካላዊና አዕምሮአዊ ዕድገት የሚረዱ የተለያዩ ምግቦችንና መድሃኒቶችን ማግኘት ይጠበቅባታል፡፡ ከወለደች በኋላም እስከ ስድስተኛ ወሩ ድረስ ለልጇ ከጡቷ ሌላ ምንም አይነት ተጨማሪ ምግብ መስጠት አይገባትም፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ግን ለህፃኑ ዕድገት የሚረዱ የተመጣጠኑ ምግቦችን ለልጇ መመገብ ይኖርባታል፡፡
ይህ ሳይሆን ሲቀር ህፃኑ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ተጋላጭ ይሆናል፡፡ ከእነዚህ የጤና ችግሮች መካከል አንደኛው መቀንጨር ነው፡፡
መቀንጨር ከአምስት አመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ የሞት አደጋን በማስከተል የሚታወቅና በአገራችን በስፋት እየታየ ያለ ችግር ነው፡፡ በኢትዮጵያ በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው ህይወታቸው ከሚያልፈው ህፃናት መካከል ግማሽ ያህሉ ለመሞታቸው ምክንያት የሚሆነው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው፡፡ ከሞት የተረፉትም ቢሆኑ ለአዕምሮ ዕድገት ውስንነት የሚጋለጡ ከመሆኑም በላይ የመማር፣ የማሰብ፣ የመረዳትና የማስታወስ ችሎታቸው ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
መቀንጨር በአገሪቱ አመታዊ የምርት መጠን ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር ሲሆን፤ በየዓመቱ ከአጠቃላዩ የአገሪቱ አመታዊ ምርት 16.5 በመቶ ኪሳራ እንደሚደርስ ‹‹ዘ አፍሪካን ሪፖርት ኦን ቻይልድ ዌልፌር ዌልቢንግ 2018›› ሪፖርት ያመለክታል፡፡
በአገራችን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ በሚከሰት የመቀንጨር ችግር ከሚጠቁ አካባቢዎች መካከል የሱማሌ ክልል ዋነኛው ሲሆን፤ አማራ ክልልና ትግራይ ክልልም ችግሩ ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሰሞኑን ችግሩ በስፋት በሚታይበት የሱማሌ ክልል ጐዴና ቀብሪደአር ከተሞች በመሄድ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ የጤና ችግር ለተጋለጡ ህፃናትና እናቶች ሴቭ ዘ ችልድረን በተባለ መንግስታዊ  ድርጅት እየተከናወነ ያለውን የነፍስ አድን ተግባር ተመልክተናል፡፡
በሱማሌ ክልል ውስጥ የምትገኘው ታሪካዊቷ የቀብሪደሃር ከተማ ለነዋሪዎቿ የገነባችው ሪፈራል ሆስፒታል ደረጃውን የጠበቀ ነው፡፡ ሆስፒታሉ ለከተማው ነዋሪዎችና ከአጎራባች ወረዳና ከተሞች ለሚመጡ ህሙማን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ከሚሰጡ አገልግሎቶች ደግሞ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ለሚከሰተው የጤና ችግር ሆስፒታሉ ሴቭ ዘ ችልድረን ከተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በትብብር የሚሰጠው የህክምና የምግብና መድሃኒት አቅርቦት ሥራ ነው፡፡ በሆስፒታሉ የህጻናት ህክምና ክፍል ውስጥ ያየኋቸው ህጻናት ያሳቅቃሉ፡፡ አብዛኛዎቹ እጅግ የከሳና የመነመነ ሰውነታቸው፣ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ፊታቸውና ክንዶቻቸው ላይ የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ተገጣጥመው ማየቱ ልብ ይሰብራል፡፡ የሕጻናቱን ዕድሜ በማየት መገመቱ ከስህተት ላይ ይጥላል:: የወራት ዕድሜ ቢኖረው ነው ብለው የገመቱት ሕጻን፤ ሶስተኛ ዓመቱን ካሳለፈ ወራት እንደተቆጠሩ ሊነገርዎት ይችላል፡፡  ችግሩ በአካባቢው እጅግ የተለመደና ለሕፃናት ሞት ዋንኛ መንስኤ እንደሆነ በሆስፒታሉ የኒውትሪሽናል ዋርድ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር መሀመድ ኑር ነግረውናል፡፡ እንደ ሃኪሙ ገለጻ፤ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ሕሙማንን ሁሉ የሚያመሳስላቸው አንድ ጉዳይ፣ ሁሉም በምግብ እጥረት ሳቢያ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች የተጎዱ መሆናቸው ነው፡፡ በብዙ ቦታዎች ይህ ችግር ወቅታዊ ችግር ነው የሚሆነው ያሉት ዶ/ር መሀመድ፤ በዚህ አካባቢ ግን አመት እስከ አመት የማይለወጥ ቋሚ ችግር ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሕጻናቱ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት በጣም ከተጎዱና ለሞት ከተቃረቡ በኋላ እንደሆነ የነገሩኝ ዶ/ር መሀመድ፤ ይህንን አክሞ ማዳኑ እጅግ ከባድ ፈተና እንደሚሆንባቸው ገልጸውልኛል፡፡
በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ሕጻናትና ነፍሰጡር እናቶችን ሕይወት ለመታደግና አስተማማኝ ሕክምናና እንክብካቤ ለማድረግ ሴቭ ዘ ቺልድረን የተባለው ድርጅት፤ የራሱን ባለሙያ በመመደብ፣ የሕክምና መሳሪያዎች፣ መድሃኒትና ሕይወት አድን ምግቦችን በማቅረብ በሆስፒታሉ እየተከናወነ ያለውን ሕይወት አድን ተግባር በመደገፍ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በሆስፒታሉ እያደረገ ያለውን የነፍስ አድን ተግባር አሁንም ሊቀጥልበት ይገባል ያሉት ዶክተሩ፤ ያለ እነሱ እገዛ እኛ የትም መድረስ አንችልም ብለዋል፡፡
በወር ከ1200 እስከ 1300 የሚደርሱ በምግብ እጥረት ሳቢያ የተጎዱ ሕጻናት ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ ያሉት ዶ/ር መሀመድ፤ እነዚህን ሁሉ ሕጻናት ተቀብሎ ማስተናገድ የተቻለው ድርጅቱ ባደረገልን እገዛና ድጋፍ በመሆኑ ልናመሰግነው ይገባል ብለዋል፡፡
በሆስፒታሉ ውስጥ ያገኘኋቸው ወ/ሮ ቡሽራ አህመድ ከወለዷቸው መንትያ ልጆች መካከል አንደኛው በተለያዩ በሽታዎች በየጊዜው እየተጠቃና ሰውነቱ እየተመናመነ በመሄዱ ወደ ሆስፒታሉ ይዘውት እንደመጡ ነግረውኛል፡፡ ከወራት በፊትም ወደዚህ ሆስፒታል በመምጣት ልጃቸው ህክምና እንዲያገኝ ያደረጉ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሩ ተመልሶ በመምጣቱ በድጋሚ መምጣታቸውን ገልጸውልኛል፡፡ ከሆስፒታሉ ድነው ከወጡ በኋላ ተመልሰው የሚመጡ ሕሙማን እንዳሉ በመስማቴ ዶ/ር መሀመድን ጠየቅኳቸው፡፡ በሆስፒታሉ ሕክምናና ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይተው ድነው ከወጡ በኋላ ተመልሰው የሚመጡ ሕሙማን ከጠቅላላው 10 በመቶ ያህል እንደሚሆኑ የነገሩኝ ዶ/ሩ፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ ሕጻናቱ ድነው ወደየ ቤታቸው ከሄዱ በኋላ ቤተሰቦቻቸው በቂ ጥንቃቄና እንክብካቤ ስለማያደርጉላቸው ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የልጆቹ አንጀት ከሚችለው በላይ የግመል ወተትና መሰል ምግቦችን ስለሚሰጧቸው ልጆቹ ተመልሰው ለህመም ይዳረጋሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሕጻናቱን ቤተሰብ ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥ ዋንኛ ሥራችን ነው ይህ ደግሞ ጊዜ የሚፈልግ ጉዳይ ነው›› ብለዋል - ዶ/ር መሃመድ፡፡
የቀብሪደአር ከተማ 04 ቀበሌ ነዋሪዋ ወ/ሮ ማልታለ አህመድም ወደዚህ ሆስፒታል የመጡት የሁለት ዓመት ልጃቸው ክፉኛ በመታመሙ ሳቢያ ነው፡፡ የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ማልታለ፤ በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ በመሆኑ ለስድስት ልጆቻቸው በቂ ምግብ ለማቅረብ ባለመቻላቸው ሕጻን ልጃቸው ለከፍተኛ ችግር እንደተጋለጠባቸውና በዚህ ሆስፒታል ይሰጣል የተባለውን የነፃ ሕክምና ለማግኘት መምጣታቸውን ነግረውኛል፡፡
ልጃቸው በተደረገለት ሕክምና ጤናው በመመለሱ ቦታውን ለተረኛ ለቀው እንደሚሄዱ ያውቃሉ፡፡ ሲወጡ ግን ልጃቸውን ምን አበላው ይሆን? የሚለው ጭንቀት ሆኖባቸዋል፡፡
‹‹በሴቭ ዘ ችልድረን ኢትዮጵያ›› የጎዴ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱራዛቅ አህመድ እንደሚሉት፤ አካባቢው ከፍተኛ የዝናብ እጥረት የሚስተዋልበት ሥፍራ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚከሰት የጤና ችግር ያጠቃዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ በአብዛኛው ኑሮውን በከብት ማርባት ላይ ያደረገ አርብቶ አደር ሲሆን የዝናብ እጥረት በሚያጋጥመው ጊዜ እንስሳቱ ስለሚሞቱበትና የምግብ ፍላጎቱን ለማሟላት አቅም ስለሚያንሰው ለምግብ እጥረት ችግር ይጋለጣል:: ችግሩ ደግሞ ቀላል የምግብ እጥረት ሳይሆን የተወሳሰበና የሕጻናት ዕድገት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሴቭ ዘ ችልድረን›› ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመተባበር፣ የሕጻናቱንና በምግብ እጥረት ሳቢያ ለጉዳት የሚጋለጡ ነፍሰጡር እናቶችን ለመታደግ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው የሚታየውን በምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግር ከመሰረቱ ለማጥፋት ሁሉም አካል በጋራና በትብብር ሊሰራ ይገባል ያሉት አቶ አብዱራዛቅ፤ ጉዳዩ መሰረታዊ ሥራ የሚፈልግና የሁሉንም ርብርብ የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ያየሁትና ያስገረመኝ ሌላው ጉዳይ፣ በሆስፒታሉ - ውስጥ ያየኋቸው ሁሉም እናቶች ገና 30ኛ ዓመት ዕድሜያቸውን በቅጡ ሳይደፍኑ ስድስትና ከዚያ በላይ ልጆችን የወለዱ መሆናቸው ነው፡፡ እነዚሁ እናቶች የልጆቻቸው ቁጥር በዚህ ተገድቦ እንዲቀር የማይፈልጉና ሌላ ተጨማሪ ልጆችን የመውለድ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን መስማቴም አስገርሞኛል፡፡
ለመሆኑ የቤተሰብ ምጣኔ ላይ ምን እየሰራችሁ ነው ስል ዶ/ር መሀመድን ጠየቅኋቸው፡፡ በአካባቢው የቤተሰብ ምጣኔ ጉዳይ የባህልም የሃይማኖትም ጉዳይ በመሆኑ ሕብረተሰቡን መለወጡና ማስተማሩ ረዥም ጊዜ እንደሚወስድ ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡ የቤተሰብ ምጣኔን እየተገበረ ነው ለማለት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም፣ የአንድ ሺ ቀናት መዘዝ በሰው ልጅ አካላዊና አዕምሮአዊ ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ዶ/ር መሀመድ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡     

Read 1807 times