Saturday, 27 July 2019 14:19

ደራሲ ሕይወት እመሻው - ከ‹‹ማታ ማታ…,, ጋር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 ከዩኒቨርስቲ የተመረቀችው በፖለቲካል ሳይንስ ነው፡፡ በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ሰርታለች:: አሁንም እየሰራች ትገኛለች፡፡ ለበርካታ ዓመታት በፌስቡክ ላይ በምትጽፋቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ መጣጥፎቿ፤ አያሌ አንባቢዎችንና አድናቂዎችን ጭምር አፍርታለች - ደራሲ ሕይወት እመሻው ….፡፡
በተለያዩ ወቅቶች እንደ ዘበት በፌስቡክ ላይ የፃፈቻቸውን ታሪኮች አሰባስባ ሁለት መፃሕፍት ለማሳተም የበቃችው ደራሲዋ፤ ሰሞኑን ደግሞ ‹‹ማታ ማታ እና ሌሎችም ወጎች›› የተሰኘውን ሦስተኛ መጽሐፏን ለምርቃት አድርሳለች፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከደራሲ…ሕይወት እመሻው ጋር በአጭሩ እንዲህ አውግታለች፡፡


           የመጀመሪያ መጽሐፍሽ ‹‹ባርቾ›› በፌስቡክ የጻፍሻቸው አጫጭር ታሪኮች ስብስብ መሆኑ ይታወቃል፡፡  ‹‹ፍቅፋቂ›› የተሰኘው ሁለተኛው መጽሐፍሽም ተመሳሳይ ነው፡፡ የአሁኑስ የፌስ ቡክ ጽሑፎችሽ ተሰባስበው የታተመ ነው?
የአሁኑ ‹‹ማታ ማታ እና ሌሎችም ትረካዎች” የተሰኘ መጽሐፌ፤ በፌስ ቡክ የጻፍኳቸውን ታሪኮች ብቻ አሰባስቤ ያሰናዳሁት አይደለም፡፡ በተወሰነ መልኩ በፌስ ቡክ የጻፍኳቸውን አካትቻለሁ፡፡ በአብዛኛው ግን አዳዲስ ታሪኮች ናቸው - ፌስቡክ ላይ ያልወጡ፡፡
አዲሱ መጽሐፍሽ ከቀድሞዎቹ በምን ይለያል?
አዲሱ መጽሐፌ ከቀደሙት መጽሐፎቼ በቅርጽም በይዘትም የተለየ ነው፡። በ‹‹ባርቾ› እና ‹‹ፍቅፋቂ›› መጽሐፎቼ፤ ወጎች፣ ልቦለዶች እንዲሁም ‹‹መሻገሪያ›› ብለን ያስገባናቸው አራት አምስት መስመር የሚሆኑ አጫጭር ጽሑፎችን ያካተቱ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ግን አጫጭር ልቦለዶች ብቻ ናቸው የተካተቱት፡፡ ከዚያ በተጨማሪ፣ በአጠቃላይ 23 ታሪኮች ናቸው:: በርከት ያሉ ናቸው ማለት ነው፡፡ 281 ገፅ ነው ለእኔ ትልቁ መጽሐፌ ነው! ታሪኮቹ በፊት ከተለመደው ለየት ይላሉ፡፡ እኔ ስጽፍ በጣም አጫጭር ታሪኮችን ነበር፡፡ አሁን ግን አንዱ ታሪክ በአማካይ 11 እና 12 ገጽ ያህል ነው፡። በቅርጽም በርዝመትም ለየት ይላሉ፡፡ ይበልጥ ደፋር ናቸው ብዬም አስባለሁ - ታሪኮቼ።
የቀደሙት ሁለቱ መጻሕፎችሽ፤ በአንባቢያን ዘንድ የነበራቸው ተቀባይነት እንዴት ነው? አሁን ያለው አንባቢ ሌላ ለመጻፍ የሚያበረታታ ነው ወይስ…?
ኦ… በጣም ያበረታታል፡፡ አንቺም እንዳልሺው… የእኔ መነሻ ፌስ ቡክ ነው፡፡ እነዚህ የፌስ ቡክ አንባቢዎቼ ናቸው ጽሑፎቼ ተሰባስበው መጽሐፍ እንዲሆኑ፣ ሲገፋፉኝና ሲያበረታቱኝ የነበሩት፡፡ ጽሑፎቹ ተሰባስበው በመጽሐፍ ሲታተሙ ይበልጥ ለታሪክም ይቆያል ብለው ሲመክሩኝ የነበሩት አንባቢዎቼ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ 95 በመቶ ያህሉ አንባቢያን፤ ገንቢ አስተያየት ነው የሚሰጡኝ፡፡ በእነሱ ገንቢና አበረታች አስተያየት ነው፣ ዛሬ ለ3ኛ መጽሐፌ የደረስኩት፡፡ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ አንዳንዴ ‹‹ይሄ ለምን መጽሐፉ ውስጥ ገባ? ለመጽሐፉ አይመጥንም ወይም ይሄንን ብታስገቢበትና ብትጨምሪበት›› የሚሉ አስተያየቶችም ይሰጡኛል፡፡ እኔም ብሆን ‹‹አዎ ይህን ባደርግ፣ ይሄ ቢወጣ›› ብዬ ራሴን እንድገመግም የሚያደርጉኝ ጠንካራ ፀሐፊዎችና አንባቢዎች አሉ፡፡ የምትሰሪው ስራ የማይጥመውም ይኖራል፡፡ ያንንም ተቀብዬ… አስማምቼ፣ መጓዝ የኔ ፋንታ ነው፡፡
ለመፃፍ የምትነሳሽው (የሚነሽጥሽ) መቼ ነው? በምን ዓይነት ሁኔታ? በምን ስሜት?...
ው… በጣም ከባድ ጥያቄ ነው ይሄ እንግዲህ የኔ መነሻ ፌስ ቡክ እንደመሆኑ፣ ከዘመኑ ጋር ነው አብረን የምንሄደው፤ እና በነፈሰበት አብረን የመንፈስ ነገር አለ፡፡ በተለይ ላለፉት አራት ዓመታት፣ አገራችን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የነበረችው። በ‹‹ባርቾ››ም ሆነ ‹‹ፍቅፋቂ›› ላይ ስንመለከት፣ የዚያ የፖለቲካ አሻራ በጣም ከፍተኛ ነው፡። ተፅዕኖ እንዳሳደረብኝ በሚያስታውቅ ሁኔታ የፖለቲካውን ጊዜ የሚዋጁ ነበሩ፡፡ የአሁኑ ‹‹ማታ ማታ እና ሌሎችም ትረካዎች›› መጽሐፌ ለየት ከሚልበት አንዱ፣ ከፖለቲካ ሙሉ በሙሉ ወጥቶ፣ የፍቅር ታሪኮች ላይ ትኩረት ማድረጉ ነው፡፡ ይሄ ስለኔ ምን ይናገራል? አላውቅም። ያው ፌስ ቡክ ላይ የፖለቲካውን ሁኔታ እጽፋለሁ፡፡ ግን መጽሐፉ ላይ እንዲገቡ ያደረግሁት የፍቅር ታሪኮችን ብቻ ነው፡፡ ምናልባት ያለሁበት ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እንደ ጸሐፊ የማየው፣ የማነብበውና የማሰላስለው ወይም ደግሞ በምናብ የምስለው ነገር ነው… እንድጽፍ የሚያነሳሳኝ ማለት ነው፡፡
አሁን ሰዎች ወዲያው የሚያስቡትን ነገር ፌስ ቡክ ላይ የመጻፍ እድሉ አላቸው፡። ብዙ አጫጭር ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ቶሎ ቶሎ ይጻፋሉ:: አንዳንድ የሥነ ጽሁፍ ተቆርቋሪዎች ይህ ሁኔታ… (ፌስ ቡክ ላይ መጻፍ) ሥነ ጽሑፉን አቀጭጮታል - ይላሉ፡፡ ‹‹ቢታሰብበት… ጊዜ ቢሰጠውና ቢበስል… ትልቅ ሀሳብ ይወጣው የነበረው ጉዳይ… በአጭር ይቀጫል›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ አንቺስ ይሄን ሃሳብ ትጋሪዋለሽ?
ይሄ አስቸጋሪ ነገር፤ ነው፡፡ በዚህ ሀሳብ ላይ እስማማለሁም አልስማማም፡፡ የምስማማበት አንድ ነገር ፌስ ቡክ ጥሞናን ይከለክላል፤ ይህ ግልጽ ነው:: ሰው የመጣለትን ሀሳብ ጊዜ ወስዶ፣ አብስሎና አሰላስሎ እንዲጽፍ አይፈቅድም፡፡ ወይም ደግሞ እኛ በዛ ወጀብ ውስጥ ስለምንገባ፣ ራሳችንን በየደቂቃው፣ በየሰዓቱ፣ በየቀኑ… መግለጽ እንዳለብን ይሰማናል:: ስለዚህ በአንድ በኩል ስትመለከቺው፤ ከጊዜው ጋር ለመሮጥ ወይም ሰው ካለበት የስሜት ሁኔታ ጋር ለመጓዝ፣ ምናልባትም አንዳንዴ የምንጸጸትበት… (‹‹ምናልባት ጊዜ ወስጄ ብጽፈው የተሻለ ይሆን ነበር›› የምንልበት ማለቴ ነው።) ጽሑፍ እንጽፋለን:: በአንጻሩ ደግሞ አዲስ የጽሑፍ ቅርጽም ሰጥቶናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አዳዲስ አንባቢያንን የፈጠረም ይመስለኛል - ፌስ ቡክ፡፡ እኔ አሁን ይሄን የምልሽ… ከዚህ በፊት በአማርኛ ቋንቋ መጽሐፍ አንብበው የማያውቁ ብዙ ልጆች አውቃለሁ፡፡ - ልጆች ስልሽ… በ12 እና 13 አመት ዕድሜ ላይ ያሉ፡፡ እናም ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ መጽሐፍ ያነበብኩት ‹‹ባርቾን›› ነው” ብለው ይነግሩኛል፡፡ ለምንድነው ይሄ የሆነው ብዬ ስጠይቃቸው፤ “ጽሑፉ አጫጭር ስለሆነ አይከብደንም፤ አይሰለቸንም” ይላሉ፡፡ “አማርኛውም አያስቸግረንም፤ አይፈትነንም” ነው የሚሉት፡፡ ስለዚህ ፌስ ቡክ አዳዲስ አንባቢያንን ያመጣ ይመስለኛል:: በተጨማሪ ስነ - ጽሑፍ ማደግ፣ መሻሻልና አዲስ ቅርጽ መያዝ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እኛ… የድሮ ደራሲ እንደምንወደው፣ እንደምናከብረውና እንደምናደንቀው ሁሉ፣ የራሳችንን ዘመን የሚዋጅ የስነ ጽሑፍ ቅርጽና ቀለም ማምጣት ተገቢ ነው ብዬ ስለማምን፣ ሁለቱን አጣጥሞ መሄድ ከተቻለ፣ ብዙ የሚያሳስብ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
በቀደሙት መጽሐፎችሽና በፌስቡክ ላይ ወቅታዊ ፖለቲካን የተመለከቱ ሃሳቦች… ሽሙጦች… ስላቆች በንቃት ስትጽፊ ነበር፡፡ አሁን “ደግሞ አገሪቱ ምጥ ላይ ናት ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት ፖለቲካዊ ትኩሳቱን ችላ ብለሽ በፍቅር ጉዳይ ላይ ብቻ የተጠመድሽበት ምክንያት ምንድን ነው?
‹‹አገር ምጥ ላይ አይደለችም›› በሚል አይደለም የፖለቲካ ትኩሳቱን በመጽሐፌ ላይ ለማሳየት ያልሞከርኩት፡፡ የአገሪቷም ሁኔታ ሳያሳስበኝ ቀርቶ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ያንን የማሳይበት ሌላ ቦታ አለ ብዬ ስለማምን ነው፡፡ የግድ መጽሐፍ ላይ መውጣት የለበትም፤ ምክንያቱም  ከዚህ በፊት አድርጌዋለሁ፡፡ በአገሪቱ ወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከኔ የተሻለ እውቀትና የትምህርት ደረጃም ሆነ ብስለት ባላቸው ሰዎች በርካታ መጽሐፍት ተጽፈዋል፡፡ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በተለያየ መልኩ ለመተንተን እየሞከሩ ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ የሚፈልገው የአገሪቱን የፖለቲካ መረጃና ትንተና፤ ከሌሎች በርካታ መጽሐፍት ማግኘት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው ማለት ነው፡፡ እኔም በበፊቶቹ መጽሐፎቼና በሌሎች መድረኮች የማደርገው አስተዋጽኦ በቂ ነው ብዬ ስለማምንም ነው፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ አለመካተቱ፣ ወቅቱ ስሜት ስለማይሰጠኝ ወይም ስለማያሳስበኝ አይደለም፡፡ የአገሪቱን ሁኔታ እንዴት ታይዋለሽ ላልሽኝ፣ እኔ እንደ ማንኛውም ሰው ነው የማስበው፤ ነገር ግን ሁሌም ስለ ኢትዮጵያ አልሰጋም፡፡
እንዴት ማለት?
አንዳንድ ጓደኞቼ በዚህ አስተሳሰቤ ይስቁብኛል:: ምክንያቱም አንድ ፖለቲካል ሳይንስ ከተማረ ሰው እንዲህ አይነት የዋህነተ አይጠበቅም ይላሉ፡፡ እኔ ግን ከልቤ… አልፈራም፡፡ የማየው ነገር ስለማያሳዝነኝ፣ ልቤን ስለማይሰብረው ወይም ስለማያስጨንቀኝ ግን አይደለም፡፡ አገር ከዚያ በላይ ናት ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ “አገሬ ግንድ ናት” የሚል አንድ ጽሑፍ አለኝ:: አሁን አገሪቱ ላይ የምናየው ምጥና ችግር ሁሉ ቅርንጫፍ ላይ ያለና እየረገፈ የሚሄድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ብዙ መናወጦች አሉ፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ያንን የማለፍ አቅምና መሰረት አላት፤ የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
ግን ይህንን ምጥና መናወጥ እንዴት ነው የምናልፈው? ምጡ ብዙ እንዳይቆይ ምን መደረግ አለበት ትያለሽ? ከምጡ መቼ የምትገላገልስ ይመስልሻል?
ነገ ዛሬ ብሎ ለመናገር ከባድ ነው፤ ነገር ግን ብዙ መስዋዕትነት ሳንከፍል፣ ከዚህ የከፋ ችግር ውስጥ ሳንገባ ነገሮች ቢስተካከሉ፣ የሁላችንም ምኞትና ፍላጐት ይመስለኛል፡፡ አሁን እርግጥ ነው ዋጋ እየከፈልን ነው፡፡ ከዚህም በላይ የህይወት መስዋዕትነት፣ ከዚህ በላይ በታሪካችን የማንረሳቸው ታሪኮችና ጠባሳዎች ሳይፈጠሩ ከጭንቁ ብንወጣ ጥሩ ነው፡፡
ከዚህ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት ላልሽው፣ አሁን የምነግርሽ ጉዳይ ብዙ ተደጋግሞ የተባለና የተለመደ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁላችንም በየቀኑ የምናደርገውንና የምንኖረውን ነገር መፈተሽ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ እኔ ፀሐፌ ነኝ፤ ፌስ ቡክ ላይ የምጽፈውና በህይወቴ የምኖረው ነገር፣ እውነት ለሀገሬ የሚጠቅም ነው ወይ? ውስጤ ጥላቻ አለ ወይ? የእከሌ ብሔር፣ ከዚህ ብሔር ይበልጣል ያንሳል የሚል ጥላቻ አለኝ ወይ? ብለን ራሳችንን መፈተሽ አለብን፡፡ የመጀመሪያውም ጦርነት የሚኖረው ከራሳችን ጋር ይመስለኛል፡፡ ስብሰባ ላይ ወጥቶ ጥሩ ነገሮችን መናገር ቀላል ነው፤ ግን ወደ ቤታችን ስንመለስ የተናገርነውን እንኖረዋለን ወይ? ክብሪት ለኳሽ አይደለንም ወይ? የሚለውን… ለራሳችን ጠይቀን፣ ህሊናችን ተለውጧል ወይ ማለት አለብን፡፡
በሌላ በኩል፤ ባለንበት መስክ ደግሞ፣ የግል ታሪካችን ምንም አይነት ቂም ውስጥ፣ ምንም አይነት አመለካከት ውስጥ ብንሆን፣ ‹‹ከኔ የሚበልጥ ነገር አለ፤ ሀገር ይበልጣል፤ የሰው ህይወት ይበልጣል” ብለን ማሰብ አለብን፡፡ አንዳንዴ ዝም ማለትም አስተዋጽኦ ነው፡፡ ጥሩ ነገር ማለት ካቃተን፤ ዝም ብንል፣ መገንባት ባንችል ባናፈርስ፤ ይህንን ካደረግን በቂ ነው፡፡ አሁን ችግር የሆነው መድረክ ላይ አንድ ነገር? አውርተን፣ ከኋላ ሌላ ዳባ የምንሰራ ሰዎች መሆናችን ነው፡፡
አንብበሽ የወደድሽው የመጨረሻ መጽሐፍ ምንድን ነው?
አንብቤ የወደድኩት የመጨረሻ መጽሐፍ የአለማየሁ ገላጋይ “ታለ በእውነት ሥም” ይመስለኛል፡፡   


Read 1767 times