Saturday, 27 July 2019 14:18

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)


             ታላቁ አምላክ ዚየስ መፈንቅለ መንግሥት ሊካሄድበት እንደተወጠነ ሰማ፡፡ ወሬውን ችላ ብሎ በየዓመቱ ሳያስተጓጉል እንደሚያደርገው ወደ ኢትዮጵያ ምድር ወረደ… ሊዝናና፡፡ የተባለው አልቀረም፡፡… ኩዴታው ተካሄደ፡፡ ለአዲሱ አለቃ የድጋፍ ሰልፍ በላይ በላዩ ተዥጎደጎደ፡፡ እሱ ግን ቁጡና ሃይለኛ ሆነባቸው፡፡ ዚየስ ክፉ ባይሆንም ከሱ የባሰ ይመጣብናል ብለው አላሰቡም፡፡ ግራ ሲገባቸው የሰማዩን ሠራዊት ሁሉ ሰብስበው፡- አዲሱን አምላክ፡-
‹የታዘዝነውን እየፈፀምን ሳለን ስለ ምን ትጨቁነናለህ?” በማለት ጠየቁት፡፡
‹‹ለዚየስ ያልሆናችሁ ለኔ አትበጁኝም›› አላቸው
‹‹አንተ ማን ስለሆንክ ነው? ምንድንስ ትፈልጋለህ?››
‹‹እኔማ ዚየስ ነኝ፣ የምፈልገውን ማድረግ እችላለሁ፣ ከናንተ የምጠብቀው የሰጠኋችሁን ታማኝነት ነበር… መታመን አልቻላችሁም፡፡ ስለዚህ መልሼ ወስጄዋለሁ››
‹‹ዚየስ… አንተ?››
‹‹አዎ ነኝ››
‹‹እንዴት ይሆናል? እሱ በሌለበት ተገልብጦ ምድር ላይ ቀርቷል››
‹‹ካ!ካ!ካ! … ዋናውን ነገር አላወቃችሁምና!››
‹‹ዋናው ነገር ምንድነው?››
‹‹አብ ‘ራ አ›› አላቸው፤ በቋንቋቸው፡፡ ሁሉም በፊቱ ተንበረከኩ፡፡… ምን ብሏቸው ይሆን?
*   *   *  *   
ወዳጄ፡- አማልክት ከሰማየ ሰማያት እየወረዱ፣ በምድር ላይ ጥሩ ጊዜ እንደሚያሳልፉ ሆሜር ጽፏል - በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ!!
ክቡር ሃዲስ አለማየሁ፤ መጋቢት 19 ቀን 1985 ዓ.ም በዳግማዊ ሚኒሊክ ት/ቤት አዳራሽ በተደረገ ስብሰባ ላይ ‹‹ኢትዮጵያዊነት በኔ አመለካከት›› በሚል ርዕስ ባሰሙት ንግግር፤ ሆሜር ስለ ኢትዮጵያ የተቀኛቸውን መወድሶች ከመጽሐፍቶቹ ከኢሊያድና ኦዴሲ ተርጉመው አንብበዋል፡፡ ለተረታችን ማዋዣ ጥቂት መስመሮችን ተውሰናል፡-
ይወርዳሉ እግዜሮች
አብሯችሁ ሊዝናኑ
በናንተ አደባባይ
‘ዜውስ’ እንኳ ሳይቀር
የሰማያት ንጉሥ
የሁሉም የበላይ…
ወዳጄ፡- የአማላክት እንግዶች፣ የነቢዩ መሃመድ መልዕክተኞች፣ የ‘ዐድዋ አርበኛ’ የምንለውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ አርስቶትል፣ ክርስቶፈር ዳጋማ፣ አርተር ራሞልና ሌሎች ብዙ፣ ብዙ ‘እንግዶች’ ወደ ሃገራችን መጥተዋል - … ወደ ሉሲ እናት ምድር
በተለያዩ የጠላት ወረራዎች ወቅትም አገራቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ከጎናችን የተሰለፉ፣ በጦር ሜዳዎች የተዋደቁ የውጭ አገር ዜግነት የነበራቸው ወዳጆቻችን አያሌ ናቸው፡፡ እራሳችን ለራሳችን፣ የራሳችንን ታሪክ መጻፍ አልቻልንም፡። እነሱ ግን በቋንቋቸው ጽፈውልን በዓለም አሳውቀውናል፡፡… ምስጋና ለአሳታሚዎቹና ለተርጓሚዎቹ!!
ባለፈው ሰሞን ደግሞ ከሌሎቹ ለየት ያለች፣ በጥይት ተመታ ያልወደቀች ጀግና መጣችልን፡፡ ጥቁር እንግዳ፡፡ ዓለም በአንድ ህፃን፣ በአንድ ብዕርና በአንድ መጽሐፍ ሊቀየር እንደሚችል አስረዳችን፡፡ እውነቷን ነው፡፡ እሷ አድርጋዋለች!!
ወዳጄ፡- በሃይማኖት ሽፋን ጨቋኝና ጊዜ ያለፈባቸው አስተሳሰቦችን በሌሎች ላይ በግድ ለመጫን በሚንቀሳቀሱ አክራሪ ሃይሎች፤ “ለምን ትማሪያለሽ? ለምን ታውቂያለሽ?›› ተብላ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 9 ቀን 2012 ፓኪስታን ውስጥ በጥይት የተመታችው ሕጻን አዲስ አበባ ነበረች፡፡ አሁን የሃያ ሁለት ዓመት ወጣት ናት፡፡ ‹‹በደረሰብኝ ጥቃት የሁሉም አገር ዜጎችና ኢ-አማንያንን ጨምሮ የሁሉም እምነት ተከታዮች ተቆጥተዋል፡፡ አብረውኝ ቆስለው፣ አብረውኝ ታመው፣ አብረውኝ ድነው ለዚህ በቅተናል፡፡ አለም አቀፋዊ ሰው የመሆን እዳ አለብኝ፡፡ በድሃና ጎታች ልማድ ባላቸው አገራት የሚገኙ ሕጻናት በተለይ ደግሞ ሴቶች የሆኑትን ወገኖች እንደኔ የመማርና የማወቅ መብት እንዲያገኙ እታገላለሁ፡፡ ትምሀርትና ንባብ የዓለምን ገፅታ እንደሚቀይር፣ መጽሐፍ መያዝ ጦር መሳሪያ ከመሸከም የበለጠ ጉልበት እንዳለው ማወቅ አለባቸው፡፡›› ትላለች - ውዷ ልጅ!!
አምስት ሚሊዮን መሃይም ሕጻናት፣ አስራ አንድ ሚሊዮን ስራ አጥ ሰዎችን በየጓዳችን ሸሽገን፣ ከትምህርትና ከልማት የበለጠ፣ በጎጥና በጎሳ ለመነታረክ ቅድሚያ መስጠታችን አሳፋሪ መሆኑን ነግራናለች፡፡
ኦ! ማላላ! ላንቺ የኖቤል ሽልማት ሲያንስ ነው፡፡ አንቺ በሰው ልጆች ልቦና ላይ በደምሽ መጻፍ የቻልሽ የስልጣኔ ትርጉም ነሽ፡፡ አዲስ አበባ ላይ አንቺን ማየት ለኛ ክብር ነው!
ቢሊ አሺን፤ ‹‹ችግር ሲበረታ ብርቱዎች ይራመዱታል›› (When the going gets tough get going) በማለት ያቀነቀነው እንዳንቺ ላሉ አይበገሬዎች ነው፡፡ የዚየስ ልጅ ማላላ፤ እንኳን ደህና መጣሽ!!
ወዳጄ፡- ‹‹ጀግና ማለት ፍርሃት አልቦ ማለት አይደለም፤ ከፍርሃት በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንዳለ የተገነዘበ እንጂ!›› (Courage is not the absence of fear but rathe the judgment that something else is more important than fear.) ይልሃል - አምብሮይዝ ሬድሙን!!
ማላላ… ዛሬ የአክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ናት፡፡ ኦክስፎርድ የወጣቶች ህልም ነው ይባላል፡፡ ትላልቅ ወረቀት የተሸከሙ ትንንሽ ጭንቅላቶችን ሳይሆን ትልልቅ ጭንቅላት የተሸከሙ መፍጠር የሚችሉ፣ ታላላቅ ጠቢባንና ሳይንቲስቶችን አፍርቷል፡፡ ከዓለም የዕውቀት ሰሌዳ ላይ የተፋቁ የሚመስሉት የኛ ኮሌጆች በአብዛኛው ያፈሩልን ‹ፊደላውያን› ግን… የጎሳ ፖለቲካ ተጋጣሚዎችን፣ አራጋቢዎችን፣ ዳኞችንና አጨብጫቢዎችን ነው፡፡ እውነተኛዎቹ ምሁራን ደግሞ ተመልካችና ገለልተኛ ሆነዋል ወይም ሜዳው ውስጥ የሉም፡፡
የትምህርት ጉዳይ ከተነሳ አይቀር እ.ኤ.አ በጥር ወር 2018 በተከታታይ የታተሙት የኒውስ ዊክ መጽሔቶች ስለ አሜሪካን ኮሌጆች የተደረገውን ጥናት በሰፊው ዘግቧል፡፡ ጥናቱ የሚያሳየው የአገሪቱ `credential inflation” እያሻቀበ ስለመጣ ተማሪዎችን ወደ ኮሌጅ መላክ የገንዘብና የጊዜ ብክነት እንደሆነ ነው፡፡ ጥናቱን ካደረጉት አንደኛው የጆርጅ ማሰን ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ብራያን ካፕላን እንደሚሉት፤ ‹‹የአሜሪካ ህልም መሆን ያለበት ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ጥሩ ስራ ላይ በማሰማራት፣ የተሻለ ዓለም መፍጠር መቻል ነው፡፡ ሁሉም ባለ ዲግሪ ከሆነ፣ ማንም ምንም የለውም ባይ ናቸው፡፡  
ወዳጄ፡- የኛ አገር “Inflation” ደግሞ የተገላቢጦሽ እንደሆነ አገራችን ያለችበት ሁኔታ ምስክር ነው፡፡ አንድ ጊዜ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፡- ‹‹ዕውቀት ያለው ወረቀት ላይ ሳይሆን ጭንቅላት ውስጥ ነው›› ብለው ነበር፡፡ አልሆነላቸውም እንጂ!!
ወደተረታችን ስንመለስ ፡- ‹‹ዋናውን ነገር አላወቃችሁም” ያልከን ስለምን ቢሆን ነው?›› ተብሎ በሰራዊቱ ሲጠየቅ፤ የአማላክቱ አለቃ ዚየስ የመለሰላቸው በአጭሩ ነበር - ‹‹አ ብ ‘ራ አ›› በማለት፡፡ ወደኛ ስንመልሰው፤ ‹‹አምላክ ብዙ ፊት አለው›› ማለት ነው፡፡ “ፊቴን ለወጥኩ እንጂ እኔው ራሴ ነኝ ያለሁት… ታዘብኳችሁ›› ማለቱ ነበር ዚየስ!!
ሰላም!!


Read 544 times