Saturday, 27 July 2019 14:09

የአለማየሁ ገላጋይ ቀንዶች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)


            ሀገሬ እንደ ጎመን ምንቸት ያለቦታው ወዝታ፣ ጎመን ስትቀቅልበት ቆይታ ነበር፡፡ በኋላ ግን ወደ ምድጃው አናት ወጥቶ ጮማ ማብሰል ጀመረ፡፡ አለማየሁ ገላጋይ ‹‹አጥቢያ›› የተሰኘችው መጽሐፉን አደባባይ ይዞ እስኪወጣ፣ የሰው ሲፈትል ኖሯል፡፡ መጽሐፉ፤ የአራት ኪሎን ገመናና ህይወት፣ የቀጣይ ዘመንዋን ዕጣ ፈንታ ሳይቀር ተነበየና የብዙዎቻችንን ቀልብ ሳበ፡፡ በተለይ የማህበራዊ ህይወት ጥልፍልፉ፣ የሥነ ልቡናዊ ህመምና ስቃዩን ጥዝጣዜ፣ ነፍሳችን ላይ ጥዶ ሲያንተከትከው፣ የጥያቄያችንን ጉድጓድ አሰፋውና አወዛወዘን፡፡
ከዚያ በኋላ አለማየሁ፣ ያለ ማቋረጥ የአጫጭር ልቦለድና የረዥም ልቦለድ፣ አልፎ አልፎም ኢ-ልቦለዳዊ ሥራዎቹን ለአንባቢያን አደረሰ፡፡ እኔም እንደ አንባቢ፣ “አጥቢያ”ን እንደ ጠዋት ፀሐይ ሞቅኋት፡፡ እንደ በዐሉ ግርማ፤ ‹‹ደራሲው›› ልቤን እየቧጨረች፣ ስትጣፍጠኝ ደጋግሜ አነበብኳት፡፡ ከዚያም ሁለት ጋዜጦች ላይ ዳሰሳዬን ሰራሁ፡፡ ዛሬም ድረስ ‹‹አጥቢያ›› ከቅርቤ አትጠፋም፡፡ ከዚያ በኋላ የመጡት  እንደ”ወሪሳ” ያሉት ተመሳሳይ ስሜት ስለሰጡኝ፣ ወደ ጋዜጣ ይዣቸው ብቅ አልኩ፡፡ እንደ ‹‹በፍቅር ስም” ቅር ያሰኙኝን ደግሞ ተውኳቸው፡፡
አሁን ደግሞ ‹‹ታለ በእውነት ስም›› ሲታተም፣ በአጋጣሚ አንዳች ችግር ውስጥ ሆኜ ሳላየው ዘገየሁ:: ከዚያም በኋላ፣ በትኩሱ ስላላነበብኩት፣ አለማየሁ በመጽሐፉ እንዳለው የፓስከልን ‹‹ልማድ ሁለተኛ ተፈጥሮ ነው!›› እየዘመርኩ ዘገየሁ፡፡ ምናልባትም ገጸ ባህሪው ረድ ሠርዌ፣ ደግሞብኝ ይሁን? ብቻ ደንዝዤ ቆየሁ፡፡ መጽሐፉን ስጀምረው ብቅ ያለው፣ ከጠቢቡ ሰለሞን የግጥም - ፍልስፍና መጽሐፍ የተወሰደው፣ ‹‹ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም›› የሚለው የከንቱነት ነጋሪት ሆነና ዝም ብዬ ተከተልኩት፡፡ ገፀ ባህሪው ታለ፤ “እኔና  ጠቢቡ ሰለሞን በአንድ ጉዳይ ተመሳስለናል” እያለ አወራልንና ሰማነው፡፡ ይሁንና ታለ ለሁለት ዓመታት በፍቃዱ የታሰረ፣ መጻሕፍት እንደ ጡጦ ከንፈሩ ላይ ያንጠለጠለ ሰው ነው፡፡ የውጭውን ዓለም ጠልቶታል፤ ወይም ፈርቶታል፡፡
በዚህች ጭራሮ ሀገር፤ በዚህች እሳት የምትልስ ነገረኛ ምድር፣ ለመንደድ መጣዱን ሳይ ዘገነነኝ፡፡ ብዙ ልጆቹዋን በየጓዳውና በአደባባዩ ላይ የበላች ቀበኛ አገር፣የመንደር ፈላስፋ ውጣ ማግሳት ብርቋ አይደለም ብዬ ለታለ አዘንኩ፡፡ ሀገሩ፣ ሆዳቸው የሰፋ፣ ራሳቸው የጠበበ፣ ከልባቸው ሳይሆን ከከንፈራቸው ማር የሚዘንብ ሸንጋዮች፤ ሜዳውን ሞልተውባት ያለፉ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት እንዴት ደበቁት? ብዬ ተሳለቅሁ!
መጽሐፉን በተመለከተ የሰዎች አስተያየት የጨለመ ድባብ ፈጥሮብኝ ስለነበር አየመረመርኩ አነበብኩት፡፡
ሲፈን፣ የታለ፣ የሁለት ዓመት ጓዳ መሞሸር መሪ ተዋናይ ናት፡፡ በክህደት ጦሩን ሲወረውር የሳታት አይመስልም፡፡ እንደዚያ ቢሆን የሳኦል ጦር እንደ ሳተው ንጉሥ ዳዊት፣ ዝማሬው አገር ይሞላ ነበር፡፡
ሁለት ክንፎቹን ከዚያና ከዚህ ተጨምድዶ የሚወራጨው ጠና ጋሻውም፣ ከእርሱ የባሰ ውጥረት ውስጥ ሆኖ የሚንደፋደፍ ነው፡፡ ስምረት ባንድ በኩል፣ ረቂቅ በሌላ ሆነው፣ ነፍሱን እየላጡ፣ ያኝኳታል፡፡
ድርሰቱ፤ እንደ ጅረት ከድንጋይ ድንጋይ እየዘለለ፣ በዜማ አጀብ የሚያወራ አይደለም፡፡ ፀጥ ብሎ በርጋታ እንደሚፈስስ ጥልቅ ወንዝ እንጂ፡፡ ድምፅ ሳያሰማ ብዙ ሀሳብ ይዞ፣ አንገቱን ደፍቶ ይሄዳል፡፡ እርምጃው እንደ አዞ፣ መሬት ይዞ ነው፡፡ ግን ነፍስን የሚያገኝበት ትልልቅ ሹል ጥርሶች አሉት፡፡ አፉ ውስጥ ለገባለት ቀስ እያለ ያደቃታል፡፡ እንደ ቀዘቀዘ የእንጀራ ምጣድ ያለ ሙቀት፣ ይጀምራል፡፡ ታሪኩ ውሎ ሲያድር ግን ዐይን እያወጣ፣ መዐዛ እየፈጠረ ይነጉዳል፡፡ ወይም እንደ ባቡር የተለያዩ ፉርጎዎችን ይዞ፣ አንዳንዱን እያሻገረ ሌላውን እያስቀረ ይቀጥላል፡፡ ‹‹የት ቀረ?” ለማለት ሥልጣን አይሰጥም፡፡ የሥነ ጽሑፋዊ ቅርፁ የተበታተነ፣ የፈራረሰ፣ ተጨባጭነትን ያስፈነጠረ ነው - ማንም ስለ ትልሙ፣ የቱም ጠቢብ፣ ስለ ምክንያታዊነቱ ሊጠይቀው አይችልም፡፡
ስለዚህ ረቂቅና ስምረት እንደ ጆፌ የሚሻሙትን ጠና ጋሻውን (ጠኔን)፤
 ለምን እንዲያ አደረጉት? በገፀ ባህርያት አሳሳል ውስጥ አንድ ክብ የሆነው ሞራላዊ እሴት የታለ? ብንል ደራሲው መብቱ ነበር፡፡ አንባቢው ደግሞ የበለጠ ሥልጣን አለው፡፡ ‹‹ደራሲው ሞቷላ!›› እንዲህ ሊል አስቦ ነው፤ እያሉ፤ ማሰብ የለም፣ ፍልጡን መሰንጠቅ፣ ድፍኑን መዘርዘር የአንባቢው ድርሻ ነው:: Localization - ነው፡፡ የፍርዱ ወንበር በየቤቱ፣ በየጠረጴዛው ነው፡፡ ዋናው ነገር ወደ እውነታ ሳይሆን ወደ ኢ-ተጨባጭነት ውቅያኖስ ውስጥ መጥለቅ ነው፡፡ መጠየቅ መፍተል ነው፡፡ “It concerns with questions of on the onthology”  የሚባለው ለዚህ ነው::  “Fragmentation, paradox,”   ይባላልም፡፡ ይህ ጉዳይ ዕውቀት የሁሉም ነገር ምንጭና መታመኛ ያደረገው ዘመናይነት፤ የሰውን ልጅ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያሳደሩ አገዳ ነው ብሎ የተፈጠረ ማፈንገጥ ነው ይባላል፡፡ ሀቅ ያልናቸው ብቻ ሀቅ አይደሉም! የተሰባበሩና የፈራረሱ ሀቆች ተገጣጥመው፣ አንድ ሀቅ ይሆን ዘንድ አይገደዱም፣ ለየብቻቸው የየራሳቸው ፍካሬ አላቸው፡፡
የአለማየሁ ድርሰቶች ቀድሞ እንደ ሩሲያ ደራሲያን ወደ ዝቅተኛው የማህበረሰብ ክፍል ጎራ ይላሉ፤ እንደ እነ ጎርኪ፡፡ እንደነ ቼኮቭ፣ እንደነ ዶስትየቭስኪ፣ ድንግርግር ውስጥ ለመግባት እግሩን የሰደደው “ወሪሳ” ላይ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ወሪሳ›› ብዙ ቅርፆች ያጣቀስ ይመስለኛል፡፡ እንደ አቅለ ፈሰሰ - ብዥታ ነገር አለው፡፡ እንደ ቨርጂንያ ዎልፍ አካሄድ አይነት:: ይህ ማለት ደግሞ ‹‹ህልማዊነት››ን ይጨምራል፡፡ ህልማዊነት ከእነ ፍሮይድ ሳይኮኢናሊስስ ጋር ትከሻ ለትከሻ ተያይዞ፣ የመጣው አዲስ መንገድ ነው፡፡ ያ መንገድ ይፋ የሆነውም በዊልያም ጀምስ ነበር:: ለዚህ ደግሞ በ1760ዎቹ መነሻ የሆነ ሌላ ሥራ አለ:: ጎተን፣ ማርክስን፣ በርናንድ ሾውን፣ ፍሮይድን ያቀበጠና ያቀለጠ ነበር፡፡
አሁን ግን አለማየሁ፣ እንደ አየርላንዳዊው ጀምስ ጆፍ ቨርጂኒያ ዎልፍ፣ ቧጥጠውት ዐቅለ ፈሰስ፡፡ ድልድይ አድርጎ በመጣው የድህረ ዘመናይ ቅርፅ ውስጥ መዋኘት ጀምሯል፡፡ ሁለቱም ቅርፆች ለስሜት አይመቹም፤ እንደ ባቡር ሀዲድ ብረት ነክሰው አይሽከረከሩም፤ አንዳንዴ ይፈነጠራሉ፤ ያፈነግጣሉ!! ስለዚህ እንደተለመደው የሥነ ጽሑፍ ‹‹አላባ››፣ ታሪክ ፍለጋ መባተት ወይም (Story Hunter) መሆን አይቻልም፡፡
አለማየሁ፤ በጠቢቡ ሰለሞን ዝርወ ግጥም ሲነሳ እንደ ልማዱ የችግር ጎጆ ገብቶ፣ ሊያለቃቅስ ብቻ መስሎኝ ነበር፡፡ በምሬት ውስጥ ባለች አገር ነፍሴን ሬት ሊያልሳት ነው ብዬ የምላሴን ጫፍ አዘጋጅቼ ነበር፡፡ ወደ ኋላ ከሸኘሁት ምሬቱን ያጣጥምብኛልና!
በኔ መረዳት የጠቢቡ ሰለሞንና ጥበብ ነው የሚባለውን የጥንቆላ፣ አስማትና መተት ጫፍ ለመያዝ መሰለኝ፡፡ ይህ ደግሞ በኋላ ሳይንስና አመክንዮ ተቃቅፈው ለሚለፉበት ቀጣይ ሀሳብ ድንቅ መሰረት ነው፡፡
የታለ እናት ጉልት ነጋዴ ናቸው፡፡ እህቱ ረቂቅ ጥሩ ሀብት አላት፡፡ ስምረት ደግሞ የጠና ጋሻው የአደባባይ ሚስት፤ ግን ላለመነጠቅ የምትወራጭ፣ የተቧጠጠ ሥነ ልቡና ያላት ናት፡፡ ሁለቱም አፈንግጠዋል፤ ሁለቱም ደግሞ ታስረዋል፡፡ ባንድ ወገን የባህልና የእምነት ቅጥራችንን ዘልለዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠፍንገዋል፡፡ ረቂቅ ለጊዜያዊ ድል የመለመለችውን ባልዋን አባራለች፡፡ ያንኑ ልቧን ደግሞ ለትዝታ ማሰሪያ፣ ለሰቀቀን ድርቆሽ አውላለች፡። ጨለማም ውስጥ፣ ብርሃን ውስጥ- የሉም፡፡
የታለ እናት በተስኪያን ሳሚ፣ አማልክት አድናቂ ናቸው፤ በዚያው ደርበው ደግሞ ለደብተራ ሽር ጉድ ይላሉ፡፡ ረድ ሠርዌን እንደ መሪ ጌታ፣ እንደ ፈጣሪ ወይም አንዳች ሃይል እንዳለው አምላክ ወኪል አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ስለዚህ ቤት ተከራይ ቢሆንም ራሱ ካልወጣ አይጠየቅም፣ ቢያስፈልግ እንኳ ልቀቅ አይባልም! እንደ እግዚአብሔር ታቦት ይፈራል፡፡ ኦዛን እንደ ቀሰፈ፣ አንዳች መዓት የሚያመጣ ያህል ይቆጠራል፡፡
ረድ ሠርዌ፤ የኢትዮጵያን ባህላዊና ሃይማኖታዊ መልኮች፣ የተተበተበበትን ስነ ልቡናዊ ገመዶች ያሳያል፡፡ ታለ፤ መጻሕፍት የበላ፣ ያኘከና ያላመጣ አይነት ተደርጎ የቀረበ፣ አሮጌውን አስተሳሰብ የሚሟገት ነው፡፡ እንደ ዳኛቸው ወርቁ ‹‹አደፍርስ››፣ ባንድ ቀን ሁሉ ይለውጥ ብሎ ቡራ ከረዩ ባይልም! ጠና ጋሻውም የእርሱ ቢጤ ነው፡፡ ሰማይ ላይ ማማ መሥራት ያምራቸዋል፡። ሌላ ፍልስፍና ሌላ ህልም! Unreliable narriate የሚባለውም ይኸው ነው፡፡
ረድ ሠርዌና ታለ የሚያደርጉት የካብ ለካብ ፍልሚያ፣ የአሮጌውንና የአዲሱን ትውልድ፣ የተለያየ ፍልስፍናና እምነት ሲያሳዩ፣ እናቱ በገላጋይነት የሚያደርጉትን መደባበቅ፣ በይሉኝታና በኋላ ቀርነት የታጀለውን ማንነታችንን የሚያሳዩ ይመስለኛል:: አንባቢውና የተማረው ሲባንን፣ በቀድሞው አቁማዳ ወይኑን ለማስቀመጥ፣ ሽንቁሩን ለመክደን የሚጣጣሩትን ሰነፎች ያመላክታል፡፡
መጽሐፉ ውስጥ “‹‹እሰይ››፣ ረድ ሠርዌ፣ በነባሩ የአባቶቻችን ስልት እየተራመደ መጥቶ ፊቴ ተገተረ::” ይላል፡፡ ይህ አረማመድ የትውልድን አሮጌና ከሳይንስና አመከንዮ የተፋታ እርምጃ ይጠቁማል:: ሮማዊው ቸቺሮ እንደሚለው፤ የግሪክን ትሩፋት፣ ከሮማው ጋር አስታርቆ፣ ለተሻለ ነገር ለመነሳሳት አይጋብዝም፡፡ ይህ የረድ ሠርዌ በሽታ፣ የእኛ ቁስል ነው፡፡
ለጋነት ከቂቅ ጀርባ የመጣች፣ የታለ የነፍስ ሀኪም፣ የትዝታው ማስወገጃ ላጲስ ናት፡፡ ሁለት ዓመት ከሻገተበት ጓዳ፣ አደባባይ ላይ ይዟት የሚወጣ፣ በእህቱ የተዘጋጀች ጌጥ ወይም አበባ ናት፡፡
ረቂቅ  ያዘጋጀችለት የውጭ መውጫ ልብስ ምርጫም፣ የጠና ጋሻው ትዝታዋን ተከትሎ፣ ታለን አሻንጉሊት ያደረገው ያህል ቢሰማውም፣ አዲስ ፀሐይ፣ አዳዲስ ሆቴሎችና ፊቶች እያየ፣ አዲስ ቀን መጠንሰሱ አልቀረም፡። ይሁን እንጂ ነፍሱ በዚህ ነጻ አልወጣችም፤ የነፍሱ ክር በህሊና ክስ ታንቃለች:: የሚያሳድደውን የውስጥ ጩኸትና ማዕበል ፀጥ የሚያሰኝ፣ መሲህ በታንኳው አልነበረም:: በአጠቃላይ ታለ አልተረጋጋም፤ ውስጡ ብዙ ፍልስፍና፣ ብዙ ረቂቅ ሀሳብ አለ፡፡ የረድ ሠርዌ ድግምትና አስማት፣ የተንጠለጠሉ የሕይወት ጥያቄዎች፣ የመለኮት ጣልቃ ገብነት፣ አመራማሪ ፈተናዎች- ፍልሚያ ውስጥ ነው፡፡ ሁሉም ነገር መሬት አልረገጠም፤ እንደ ደመና እየሰፈፈ፣ እንደ ጅራፍ እየገረፈ የሚጮህ ነው፡፡ ሙዚቃው ሁሉ ይህ ነው፡፡ ኢ-ተጨባጭነት!
በህሊናው ሽሽት ወታደር ቤት መግባቱ፣ ኤርትራ በመወረሯ፣ ጠና ጋሻውም የጦር ትምህርት ቤት አሰልጣኝ መሆኑ፣ ሁሉም የሽሽትና የህሊና ግርፊያ ልቦና ናቸው፡፡
የታለ አባት፤ ‹‹አሮጌ ጥይት ከግንባራቸው ወጥታ ብትጠፋ፣ አገር ይያዝ ማለታቸው፣ ከዛሬ ይልቅ ትናንትን በመዘመር የኖረውን ትውልድ ለመውቀስ ፊት ለፊት የሚያጋፍጥ ነው፡፡ ዛሬን ከመሥራት፣ የነገን ተስፋ ከማጉላት ይልቅ ትናንትን እያገላበጡ መሳም፤ የትውልዶቻችን ቅርስ ነው፡። ደራሲው አሮጌዋን አገር ጀርባዋን እየገለጠ ነው፡፡ የትንሹ ነቢይ ሳሙኤል ተስፋ፣ ከሽማግሌው ዓሊ ታሪክ ያልፋልና!
መጽሐፉ ውስጥ እነ ሶቅራጥስ አሉ፤ ፓስካል ይወራል፤ ክርስቶስ ይሰብካል፣ ሳጥናኤል ያፏጫል:: ሁሉም በየራሳቸው ጫማ ቆመዋል፡፡ ረድ ሠርዌ ባንድ በኩል ባዮሎጂ ያጠናል፡፡ በሌላ በኩል መልኮቹን ይደግማል፡፡ ምስራቅና ምዕራብ የሆኑ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡
ከተማው ውስጥ ‹‹ወያኔ ሌባ›› የሚል የወጣቶች የትግል ድምጽ አለ፡፡ “ኤርትራውያን ይውጡ” የሚል የታሪክ ገጠመኝ ጣልቃ ገብቷል፡፡
ነፀብራቅ ሌላዋ የሕይወትና የዘመን ማሳያ ናት፡፡ ብዙ ስድብ አዘጋጅታ፣ ልብዋን አንጠራርታ መጥታ በፈጠጠ እውነት፣ ርቃን በቆመ ሀቅ የምትሸነፍ!
 አለማየሁ፤ እዚህም መጽሐፍ ላይ የሴቶችን ጉዳይ ረቂቅ አድርጎታል፤ ምናልባትም ወንድ ገራገር ነው ብሎ አስቧል፡፡ ስለዚህም “ከሴት ጋር አውርቶ ለመግባባት የጦርነት ዕቅድ ያስፈልጋል፤ ሊያጠቁ ሲወጡ መጥፋት ካልሆነም ድልድይ አፍርሶ ማዶ ለማዶ መተያየት፡፡ ስታጠቃ ደግሞ ሽምቅ እንጂ ሴትን በአጠቃላይ ጦርነት ገጥሞ ያሸነፈ ወንድ የለም›› ይለናል፡፡
በስተመጨረሻ፣ የረቂቅ ነገር በኤልካና በኤልያስ መካከል እንደገባው የእሳት ሰረገላ ይዟት ሳይነጠቅ አይቀርም ማለቱ፣ በብርሃን- ውም መሰወሩ… ሁሉም ነገር ህልም ይመስላል፣ ሁሉም ነገር ተዐምር ነው። ሃጂ ለማድረግ የሚሄደውና ስሩዲን፣ የራሱን ህልም መጠራጠሩ፣ ምልክት አግኝቶ መተኛቱ፣ ከዚያም ምልክቱ/አሻንጉሊቱን ሲያጣ መባተቱ፣ ራስን ፍለጋ፣ ጥርጥር፣ እርግጠኛ ያለመሆን ሁሉ--- የአለማየሁ ገላጋይ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን፣ የሕይወት ዝብርቅርቅ፣ የዚህች ዐለም ወለፈንዴነት ነው፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ አርታኢ ገፀ ባህሪ ሆኖ የተሳለው አለማየሁ፤ ለኛ የመጽሐፉ ደራሲ ቢሆንም፣ ስናነበው ግን አለማየሁ የለም፡፡ አለማየሁ ሞቷል:: ያለነው እኛ ነን፡፡ አንብበነዋል፤ አይተነውማል - ፈክረነዋልም!
ስለ ንባብ ዕውቀቱ፣ ስለ አተያዩ፣ ስለ ፍተሻውና ፍተናው፤ ማማው ከፍ ብሏል ማለታችን ግን አይቀርም! የአለማየሁ ገላጋይ ቀንዶች ከፍ ከፍ ብለዋል፡፡ በዚህ ብረት፣ ሸክላ፣ ብርና ነሀስ በቀላቀለው፤ የባቢሎን ንጉሥ ህልም አይነት- የተከወነውን፤ መጽሐፉ ተዐምራት ነው፡፡…

Read 785 times