Saturday, 27 July 2019 14:11

የታክሲው ሙሽራ

Written by  (ደ.በ)
Rate this item
(0 votes)

 ወያላው ቀልድና ፌዝ ያበዛል፡፡ በዚያ ላይ ዐይኑ አያርፍም;፤ እዚህም - እዚያም ይቃብዛል፡፡ ደግነቱ ተሣፋሪው ቀልዱን እየሰማ ዝም አይልም፤ በሣቅ ወይም በቃላት መልስ ይሰጠዋል፡፡ አንዳንዱም “አንተ ቴአትረኛ መሆን ነበረብህ!” ይለዋል፡፡
“ቴአትር ቤቱ አነሰ!...ብሔራዊ - ሀገር ፍቅር - ሌላ ምን አለ?”
“ማዘጋጃ ቤት!”
“ማዘጋጃ ቤት እንኳ - ይርቀኛል!” ይላል፡፡
ሂሣብ ሲቀበልም፤ “ቆንጂት-- ማሥረሻ-- ነፃነት-- መተኪያ--” እያለ ባልተለመደ ስም ይጣራል፡፡
“አትጨማለቅ!” ያለቺው አንድ መነጽር ያደረገች ቆንጆ ልጅ ብቻ ናት፡፡ ትልልቅ ዐይኖችዋን ስታንቦገቡግበት፤
“መነጽር ባይኖርሽ እንደ ሶሪያ ከተሞች ነድጄ ነበር!” ሲላት ሳቅዋ መጣ፡፡
ከዚያ ቀጥሎ ከሹፌሩ ወንበር ጀርባ ወደተቀመጠችው ጠይም ቆንጆ መለስ አለና፤ “ተሸላሚ ነሽ!” አላት፡፡ ዝም ብላው በመስታወት ወደ ውጭ ማየት ጀመረች፡፡ ፈገግ ትበል፣ ትቆጣ ያየ የለም፡፡
“እዚህ ታክሲ ውስጥ ካሉት አንደኛ ተሸላሚ ነሽ!...ሾፌር፤ የአበባ ጉንጉን አዘጋጅ አላልኩህም!”
ጨበሬያሙ የታክሲ ሹፌር ፀጉሩን ባንድ እጁ እየፈተለ፤ “ይዘጋጃል!” አለው፡፡
ልጅቷ ለማናቸውም መልስ አልሰጠችም፡፡ ከዚያ ይልቅ አጠገቧ የተቀመጠው ሰውዬ ሁኔታ፣ አልገባ ብሏት ሁለት ጊዜ በግልምጫ አነሳችው፡፡
“አንቺ እንደ ኢትዮጵያ ነሽ!” ወያላው አሁንም ጣልቃ ገባባት፡፡
“ዳር ድንበርሽን አታስደፍሪም! ይመችሽ አቦ!”
ቁጣዋ - አልበረደም፡፡
“ሰውዬ ምን ፈለክ?” አለችው፤ ድምጽዋን ቀንሳ::
ወያላው አንገቱን አውጥቶ ከሌሎች የታክሲ ሰዎች ጋር በምልክትና በቃላት እየተነጋገረ ነው፡፡ በየመሀሉም ይዘፍናል፡-
“ተስለሻል እንዴ ካይኔ ከመሀሉ፣
አንቺ ብቻኮ ነሽ የሚታየኝ ሁሉ!”
የተሳፋሪውን ቀልብ ስቧል፡፡
ጠይሟ ልጅ፤ አጠገቧ ያለው ሰውዬ አልተላቀቃትም፡፡ የሚያምር ሱፍ ልብስ ለብሶ ክራቫት አሥሯል፡፡ በታክሲ የሚሳፈር አይመስልም:: አለባበሱና ሁኔታው ከፍ ያለ ነው፡፡ የጠገበ ሀብታም ወይም ሚኒስትር ነገር ይመስላል፤ ግን ልጅቷ ንቃዋለች፡፡
“አርፈህ ተቀመጥ!” ትለዋለች፤ እንደ ህፃን፡፡
“ልጁ ያለሽ እውነት ነው፤ አንደኛ ነሽ!”
“አመሰግናለሁ!”
“ለአድናቆት የሚሆን ግብዣ ብጋብዝሽ ደስ ይለኛል!”
“ሰውዬ በፈጠረህ፤ ታክሲ ውስጥ ያገኘኸውን ሁሉ መጋበዝ ትክክል ነው ብለህ ታምናለህ!”
“ማን ያውቃል? ታክሲ ውስጥ ትዳር ቢገጥመኝ!”
“እኔ በታክሲ ጨዋታ ወደ ትዳር የምመጣ ዘልዛላ አይደለሁም፡፡ ደግሞስ ትዳር ይኑረኝ አይኑረኝ በምን አውቀህ ነው!”
“ታስታውቂያለሽ! ትኩስ ነሽ!”
“ይቅርታ ነፃነቴን ስጠኝ” ዞር ብላ ግራና ቀኝ አየች፡፡ ቦታ መለወጥ ፈልጋ ነበር፡፡ ታክሲው ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡ ሰዐቷ ተመለከተች፡፡
“ቀጠሮ አለሽ እንዴ?”
“አዎ!”
“ከማን ጋር?”
“ያ- የራሴ ጉዳይ ነው!”
ወያላው ጀመረ፤ “ታክሲያችን የፍቅር ታክሲ ናት:: ልብ ለልብ ለተገናኙ ሰርቃ ትደግሳለች፡፡ ሹፌሩንም በነገር መጥበስ እንጂ በፍቅር መጥበስ ይቻላል!..እኛ የማንወድደው ኩርፊያና ግልምጫ ነው፡፡ የተደመረ ሰው ደግሞ ጥላቻ አያሳይም፡፡” አለና፤ ወደ ጠይሟ ልጅ አየ፡፡ አንዴ በዐይኗ ገላመጠችው፡፡
“ዘመኑ የይቅርታና የፍቅር ነው! ...ያራዳ ልጅ ቁርስ ምሣው ፈገግታ ነው! እናንተን አያሳጣኝ!...ቁርሱን ያልበላ ካለ፣ ቁርስ እንጋብዛለን! ብቻ ጠጋ ጠጋ በሉና ክረምቱን በሙቀት፣ እኛን በፍቅር እርዱን!”
አሁንም አንገቱን ብቅ አድርጐ ትራፊኩን “ጌታዬ!” አለና ቀለደ፡፡
“አንተ ምላሰኛ ደ‘ሞ መጣህ?”
“እናንተን ያኑርልን!” ካለ በኋላ ወደ ተሳፋሪው ዞር ብሎ፤ “ቄሶቻችን እነርሱ ናቸው፤ የኛ የነፍስ አባታችን! ሃጢአታችንን አናዝዘው ወይ ጡርሻ አሊያም በቅጣት ነፃ ያወጡናል!”
ሰውየው እጁን ወደ ጭንዋ ሲሰድ፤ “ምን አይነት ባለጌ ነህ!” እንደ መብረቅ ስትጮህ፣ ሰውየው ድንግጥ አለ፡፡ ዞር ብሎ ቢያይ፣ ሰው ሁሉ በወያላው ወሬ ተመስጧል፡፡
“ሾፌር ወራጅ አለ! ወራጅ!”
ጨበሬያሙ ሾፌር ዞር ብሎ “ሳይሻገር ነው?” አለው፡፡
“እዚሁ ፍሬን ያዝ! እኔ እወርዳለሁ!”
ሳቀ፤ ሹፌሩ የፊት ጥርሶቹ ላይ ብልዘት ይታያል፡፡ ከንፈሮቹም በሲጋራ የነደዱ ናቸው፡፡
“አንተማ ከምትወርድ እኔ እወርዳለሁ!”
“ህዝብህን ጥለህ እንዳትወርድ! እኔ ግን አልቻልኩም!”
“ምኑን ነው ያልቻለከው?”
“ውበት አነደደኝ፣ ውበት አሰከረኝ! አዙሮኝ ከምወድቅ ብዬ ነው፡፡”
“አይዞህ በለስላሳ ጣቶችዋ እሹሩሩ የምትልህን ሞግዚት እንቀጥራለን! የምትቧጭርህን እናስቀጣለን::”
“አልቻልኩም!”
“በለውና ይውጣልህ!”
“የሙሉ ቀን መለስን”
“የቱን?”
“ቁመትሽ ሎጋ ነው ሰንደቅ ያሰቅላል - ሆድዬ!”
“ኧረ ሰንደቅ መስቀያ እንኳ አልፈልግም! ከህዝብ አታጣላኝ” ብሎ ወደ ተሣፋሪዎቹ ተመለከተ፡፡
“ዑራኤል ወራጅ ይኖራል፣ በድልድዩ ሥር ልንሄድ ነው!”
መልስ የለም፡፡
“ከህዝቡ ጋር ምን ያባልሃል!” አለው፤ አንድ ተሣፋሪ፡፡
“ሰንደቅ ጥሩ አይደለም፤ እዚህ ታክሲ ውስጥ የትኛው ሰንደቅ ዓላማ ይሰቀል ቢባል አሥር ዓይነት ይሆናል! እኛ ደግሞ አንድ ባንዲራ፣ አንዲት ሚስት፣ አንድ ሃይማኖት ይበቃናል ብለን ቆርበናል! አይደል እንዴ ግርምሽ?”
ሾፌሩ እየሳቀ፤ “አሁን በቃህ፤ የዜና ሰዓት ይድረስ! ኮረንቲና ፖለቲካ አትድፈር!” አለው፡፡
“የሰው ጭን ከመድፈር አይሻልም!”
ገና ወደ ፕላዛ ሲጠጋ፤ “ወራጅ” አለ ሰውየው፡፡ የሰው ጭን ያለው ነገር፣ ያስደነገጠው ይመስላል፡፡
“እውይ!” አለች፤ ጠይሟ ቆንጆ፡፡
“እኛ እንኳ እፎይ የምንለው ዛሬ አይደለም፤”
“ምን ሲሆን ነው?!”
“ትራፊክ ሲጠፋ! ነዳጅ ሲቀንስ!”
መገናኛ ደርሰው ሲወርዱ ጠይሟ ልጅ ቁጣዋ አልበረደም፡፡ “ብሽቅ?” እያለች ወደ ምትሄድበት አቀናች፡፡ አስፋልቱን በእግሯ ተሻግራ ጓደኞችዋ ወደ ጠቆሟት የእምነት ሥፍራ ሄዳ ስሜትዋን ለመቀየር ተጣደፈች፡፡
ቀኝዋን ይዛ ስትሄድ የነገሯትንም ምልክት አገኘች:: ስልኳን አውጥታ ስትደውል ትክክል ናት:: ጓደኛዋ ወጥታ ተቀበለቻት፡፡ ተሳስመው ገቡ:: ቀጥሎ የነበረው ፕሮግራም ልቧን እየዳሰሰ----እየዳሰሰ---ውስጧን አረሰረሰው፡፡ ዝላይ ሳይሆን የተረጋጋ መዝሙር፣ ነፍሷን የሚሰቀስቅ ዜማ ፈልጋለች፡፡
“በህይወቴ ዘመን--- በህይወቴ---ዘመን በህይወቴ---ዘመን ጌታ…”
ደስስስ አላት፡፡ ቀዝቃዛ ናት፤ ቶሎ አትሞቅም፤ እንደ እንጀራ ምጣድ፣ ማገዶ ትፈጃለች ይሏታል፤ ጠንቃቃት ናት፡፡ የተወሰኑ ደቂቃዎች መዝሙር ተዘመረ፡፡ ከዚያ ፕሮግራም መሪው ፀለየ፤ ፀሎቱም ጥሩ ነው፡፡ ለሀገር ሰላም፣ ለትውልድ መፀለይ ደስ ይላል፡፡ በዚያ መሀል ሌላ ወፍራም ድምጽ አዳራሹን ነቀነቀው፡፡ ለሬዲዮ የሚያምር ድምጽ ነው፡፡
ዐይኗን ገለጠች፤ ፀሎቱ ቀጠለ፡፡ ጠይሟ ልጅ ተዘረረች፡፡ አጠገቧ ያሉት ሰዎች የጌታን ስም ጠሩ፡፡
“በኔ ፊት ሰይጣን መቆም አይችልም!” አለ፡፡
ከዚያም ከመድረክ ወርዶ “ጩህ!” እያለ የጌታን ስም ሲጠራ
“አንተ ሳትወድቅ ሰይጣን ይወድቃል!...ሰይጣን ለሰይጣን!” አለችው፡፡
“ውሻ!”
ሰው ተንጫጫ፡፡
“ባለጌ!...አንተ ነህ ሰባኪው?...አንተ ነህ አማኙ!”
ድንጋጤ ሆነ፡፡
የታክሲው ሰይጣን! የእምነት ሠፈሩ መልዐክ!
ተነስታ ወጣች፡፡

Read 526 times