Print this page
Saturday, 27 July 2019 14:04

“ሂጅራ” ከወለድ ነፃ አገልግሎት ባንክ በአንድ አመት ውስጥ ሥራ ይጀምራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ሁለተኛው የእስላም ባንክ በምስረታ ላይ ነው
             
            የሸሪአን ሕግ መሰረት አድርጎ የሚሰራውና ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጠው ሂጅራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ተመስርቶ አክሲዮን መሸጥ ጀመረ፡፡ ከውጭና ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ 38 አደራጆች ያሉት ባንኩ ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በንግድ ባንክ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል፣ በንብ፣ በኦሮሚያ ህብረት ባንክ፣ በአባይ፣ በአቢሲኒያ፣ በአዋሽ፣ በዳሽንና ወጋገን ባንኮች አክስዮን መሸጥ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ባንኩ ሙሉ ለሙሉ የሸሪአ ሕግን መሰረት ያደረገ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል፡፡
ባንኩ 1ሚ አክሲዮኖችን ለሽያጭ ማቅረቡን አስታወቆ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 1 ሺሕ ብር መሆኑንና ከአክሲዮን ሽያጩ 1ቢ ብር በመሰብሰብ ባንኩን ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት ባለጊዜ ውስጥ ሥራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አደራጆቹ ገልጸዋል፡፡ አክሲዮኖቹን በ3 ወራት ውስጥ ሸጦ ለመጨረስ እቅድ መያዙንም ጨምረው አብራርተዋል፡፡
ንግድ ባንክን ጨምሮ በ11 ባንኮች በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ሲሰጥ ቢቆይም እስካሁን ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ባለመኖሩ ብዙዎች ከሀይማኖታቸው ጋር በተያያዘ አገልግሎት ሳያገኙ ለቆዩት ትልቅ መፍትሄ ይሆናል ብለዋል አደራጆቹ፡፡
አንድ ሰው ሊገዛ የሚችለው ትንሹ 30 አክሲዮን ወይም 30 ሺህ ብር ሲሆን ትልቁ 20 ሺህ አክሲዮኖች 20 ሚ ብር እንደሆነም ታውቋል፡፡ ሂጅራ ባንክ አክሲዮን ማህበር በ8 ሰዎች ሀሳብ ጠንሳሽነት ተጀምሮ አሁን ላይ 38 አደራጆች ያሉት ሲሆን አደራጆቹ በዓለም አቀፍ ደረጃና በአገር ውስጥ  የትልልቅ የቢዝነስ ኩባንያ አማካሪዎች፤ አለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ  ባለሀብቶችና ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ፒኤችዲ የደረሱና የዳበረ እውቀትና ልምድ ያላቸው ስለመሆኑም በዕለቱ ተገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ “ዛድ ኢስላሚክ ባንክ” የተሰኘ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክም ሊመሠረት መሆኑ ታውቋል፡፡
ዛድ ኢስላሚክ ባንክ አ.ማ የአክሲዮን ሽያጭና የባንክ ሂሳብ የመክፈት ፍቃድ ከብሔራዊ ባንክ ማግኘቱንና በቅርቡ የአክሲዮን ሽያጭ እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3561 times