Saturday, 27 July 2019 13:45

“ልጃችሁን ለልጃችን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
(የምርም… ረዘም አድርጎ “አንዴት ሰነበታችሁ?” ብቻ ሳይሆን “እንዴት አደራችሁ?” ብቻ ሳይሆን “እንዴት አረፈዳችሁ?” “እንዴት ዋላችሁ?” “እንዴት አመሻችሁ?” መባባል የሚያስፈልግበት፣ “አይመጣምን ትተሽ፣ ይመጣልን ለመያዝ እንኳን ግራ የተጋባንበት ጊዜ ነው፡፡ ብቻ… ሁሉንም ለበጎ ያደርገውማ!)
ስሙኝማ…የትኛው ስፍራ ምን መባል እንዳለበት፣ ምን መባል እንደሌለበት የጠፋብን ሰዎች በርከት ያልን አንመስልም! (ሆነ ብለን በማወቅና በእቅድ አንድ የሆነን ነገር መነሳት በሌለበት ስፍራና ጊዜ የምናስጮህ እንዳለን ሆነን ማለት ነው፡፡)
እናላችሁ…ለምሳሌ ሠርግ ላይ “የመቃብር እጮኛዬ ጠብቂኝ እመጣለሁ” ብሎ ቢዘፍንስ! እሱ ለ‘ክፋት ሳይሆን’ ዘፈኑ ደስ ስለሚለው ብቻ ዘፍኖ ሊሆን ይችላል፡፡ (ሙሽራ ግን “ካላጣው ዘፈን ይሄን ዘፈን የዘፈነው የሚያውቀው ምስጢር ቢኖር ነው!” ማለቱ አይቀርም፡፡ ያለ ግብዣ ወረቀት እንደሚገባበት ትያትር ቤት፣ በሮቹ ወለል ብለው ስለተከፈቱት ‘ቦተሊካችን’ እንደምንለው ማለት ነው፡፡)
ታዲያላችሁ… “ሙሽሪት ለምዳለች…” ብሎ እንዳበቃ “አትድረሽብኝ አልደርስብሽም…” የሚል ዘፈን ቢያስከትል.፤ ሙሽሪት “ይሄ ነገር ቅኔ ነው እንዴ!” ምናምን ብትል አይፈረድባትም…የባሏ ቃልና የአዝማሪው ቃል አልገጠሙላትማ! (ይቺን ስሙኝማ…አንድ ጊዜ ለመልስ ወላጆቿ ቤት የሄዱ ሙሽሮች፣ በምን ይጋጩ በምን ማንም ሳያወቅ፣ ሙሽሪት ‘የውሀ አጣጪዋን’ እዛው መድረኩ ላይ በጥፊ አጠናግረዋለች፡፡ የሆነ በ“ናፍቆት ሲጠበቅ” የነበረ አዲስ ዘፋኝ፣ እስከ ዛሬ በሲንግል ያልለቀቀው፣ በቴሌግራም ስላልተበተነ፣ ኢንስታግራም ላይ ስላልተለጠፈ ይሆን እንዴ! የምር፣ ፖለቲካው እንኳን ባያምርብን፣ በሌላው ነገር ‘ደስ ስንል!’ ልክ ነዋ… ከአምስቱ አክስቶቹ አራቱ የማያውቁትን ሰው እኮ አስር፣ ሀያ ሚሊዮናችን ያህል በናፍቆት የምንጠብቅባት ሀገር ናት!)
እናማ…ሀሳብ አለን፣ ሽማግሌዎች “ልጃችሁን ለልጃችሁ፣” ለማለት ሲሄዱ፣ የእሷ ወገኖች የሚጠይቋቸው ወገኖች፣ ከጊዜ ጋር መስተካከል አለባቸው፡፡ ሽማግሌዎች ሶስትም አራትም ሆነው ይመጣሉ፡፡ የሙሽሪት ወገኖችም ይቀበላሉ፡፡
“እሺ ጉዳያችሁ ምን ነበር?”
“ልጃችሁን ለልጃችን በጋብቻ እንድትሰጡን ለመጠየቅ ነው፡፡”
ስሙኝማ…እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ አለኝ፣ ከወራት በፊት የሰማነው ነው:: የልጅቷ ቤተሰብ ሽማግሌዎች እንደሚመጡ ያውቃሉ፡፡ ያልተነገራቸው አባት ብቻ ነበሩ:: ሰዎቹም በቀጠሯቸው ሲመጡ “እንግዳ መጥቷል…” ተብለው አባት ከእንቅልፋቸው ይቀሰቀሳሉ፡፡ ሳሎን ሲገቡ የማያውቋቸው ሰዎች ተሰብስበዋል፡፡ ግራ ገብቷቸው እያለም ሽማግሌዎች ተነስተው፣ ትንሽ ከዚህኛውም፣ ከዛኛውም መጻህፍት ከዛም የሆኑ ጥቅስ ነገሮች ይጠቃቅሱና “ልጃችሁን ለልጃችን በጋብቻ ለመጠየቅ ነው የመጣነው፣” ይላሉ፡፡
ይሄኔ አባት ብሽቅ ብለው የቤተሰቡን አባላት…“ለዚህ ብላችሁ ነው ከአንቅልፌ የቀሰቀሳቀችሁኝ!” ብለው ያፈጡባቸውና ወደ ሽማግሌዎቹ ዘወር ይላሉ:: “ድሮ የወሰዳችኋትን ምን ብላችሁ ነው እንደገና የምትጠይቁኝ!” ብለው ተመናጭቀው ወደ መኝታ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ ለካስ ልጅት ቀደም ብላ በከፊል ዲሞክራሲያዊ መብቷን ነገር አስከብራ፣ በወር ሁለቴ ሦስቴም ምክንያት እየሰጠች ማደር ጀምራ ነበር፡፡ አባትም በዚህ፣ በዚህ  ሲበሽቁ ኖረዋል::
እናማ ጥያቄው ይደረደራል፡፡
“ልጃችንን ብንሰጣችሁ ልጃችሁ ሳይርባት፣ ሳይጠማት የፈለገችውን ሁሉ እያሟላላት በሚገባ ሊያስተዳድራት አቀም አለው?”
“እንዴታ! ብርጭቆ የሚባለው ቦታ ሶስት ክፍል ኮንዶሚኒየም ተከራይቶ…”
(ምን! የምን ኪራይ ቤት!) ሰዎቹ ሳይጨርሱ የሙሽሪት ሰዎች ማለዳ የጠጡት ኮሶ ገና አሁን ቃናው የመጣባቸው ይመስል ፊታቸው ይወይባል:: የኮንዶሚኒየም፣ የኮንዶሚኒየም “ልጃችሁን ካልሰጣችሁኝ፣” እያለ መከራ የሚያበላቸው ጥበቃ የሚሠራው ሰውዬ አለ አይደል! የፈለገ ‘ሲኒየር ሲቲዘን’ ይሁና! ኮንዶሚኒየም እንደሁ ሲኒየር፣ ጁኒየር ብሎ ልዩነት አያውቅ! እናማ፣ ሽማግሌዎቹ ይቀጥላሉ…
“…በገቢ በኩል ችግር የለበትም፡፡ ቋሚ የመንግስት ሠራተኛ ነው…
እየፈጩ ጥሬ! በአሁኑ ዘመን የመንግስት ሠራተኛ ሆኖ፣ ልጅቷን በቆሎ ሊቀልባት ነው! አለቀ፡፡ ደግሞ “ቋሚ ነው” ይላሉ እንዴ! ቆመም፣ ተቀመጠም የመንግሥት ሠራተኛ፣ የመንግሥት ሠራተኛ ነው፡፡ እንደውም ሴቶቹ የልጅቱ ዘመዶች በሆዳቸው… “ኸር ንሺ እቴ! የመንግስት ሠራተኛ ከመሆን እንደ አትዬ ማሚቴ አረቄ እያወጡ መሸጥ ይሻላል!” ምናምን ሳይሉ አይቀሩም፡፡
“…ቤቱም የተሟላ ነው፣ ቴሌቪዥን ብቻ ቢቀረው ነው፡፡”
ምን! ቴሌቪዥን እንኳን ሳይኖረው ነው “ልጃችሁን ስጡን፣” የሚሉን! ማታ፣ ማታ እራሱ ሊዘፍንላት ነው እንዴ! እናላችሁ…ዘንድሮ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል:: “ልጃችሁን ለልጃችን…” ምናምን ሲባል የትዳር ጥያቄ ሳይሆን የሆነ የ‘ቢዝነስ ትራንስአክሽን’ ምናምን እየመሰለ ነው::
ዘንድሮ እንበልና የልጅት ቤተሰቦች… “ለመሆኑ ምን ሥራ ላይ ነው ያለው?” ሲሉ ያጠይቃሉ:: እናላችሁ ነገርየው ሁሉ የ‘ትርፍና ኪሳራ ጉዳይ ስለመሰለ የሚጠብቁት መልስ አላቸው፡፡ የባናክ ደብተሩ የዲጂቱ ብዛት ቢሆን ነው እንጂ ‘ሀብታም’ ስለመሆኑ ጥርጣሬ የለም:: የእነሱ ልጅ ‘ከላይ’ ሁለትና ሶሰት ቡሎኖቸ ካልጠፉባት በስተቀር መቼም ‘ዓይኖቿ እያዩ “ሆዳችንን በጎመን እየደለልንም ሰው የደረሰበት እደርሳለን” የሚል ቀሺም ‘ፊክሽን’ ነገር የሚያወራ ላይ አትወድቅም!  (እኔ የምለው… ተዋናይቶቻችን… አለ አይደል… “ቅልጥ ያለ ሀብታም አገባች፡፡ “ባሏ ብር ሳይሆን ዶላርና ዩሮ የሚያስነጥስ ነው አሉ” አይነት ነገር እያስባሉ “ሌላው ቀስ ብሎ ይመጣል፣ ዋናው ፍቅር ነው” የምትለውን ‘ፓራሲታሞል’ ነገር ጉልበት አሳጡብን አንዴ!)
“መርካቶ አራት ትላልቅ መጋዘኖች አሉት፡፡ ደግሞ አያት ሦስት፣ ሲ.ኤም.ሲ. ሁለት ጂ ፕላስ ስሪ ቤቶች አሉት፡፡”
“ምን እንበላችሁ፡፡ ዛሬ ዱባይ፣ ነገ ሻንጋይ፣ ከነገ ወዲያ ኢስታንቡል…ያለ እረፍት ዓለምን የሚዞር አስመጪ ነው፡፡”
“አዲስ አበባ ሁለት ሆቴሎች፣ ሃዋሳ፣ ባህር ዳርና አዳማ ሪዞርቶች አሉት፡፡ ቦሌ ሠላሳ ሁለት ፎቅ ህንጻ እያሠራ ነው፡፡” እናላችሁ… እንዲህ አይነት መልሶች ናቸው የሚጠበቁት፡፡ አለ አይደል… አንድ ሰው ስላለው ሀብት አይነትና መጠን ሳይሆን የሆነ መስሪያ ያወጣቸው የንግድ ዘርፎች ዝርዝር አይነት ነገር ለማለት ያህል ነው::
እናማ…ነገርዬ እንደዛ ስላልሆነ ሽማግሌዎች ትንሽ ያመነታሉ፡፡ ለምን መሰላችሁ…ሰውየው ‘አክቲቪስት’ ነው! ቂ…ቂ…ቂ… (‘አክቲቪስትነት’ን የመሰለ መቶ ኪሎ ቃል፤እንዲህ የሽልንግ እጣንን ያህል መክበድ ያቅተው! ያው እንግዲሀ መነገር አለበት…
“ልጃችን አክቲቪስት ነው፡፡”
የሙሽሪት ዘመዶች ግራ ይገባቸዋል፡፡ ‘አክቲቪስት’ ደግሞ ምን አይነት ንግድ ነው?
“እንዲገባን ምን፣ ምን እንደሚሠራ ንገሩና!” (ቢያንስ ይሄ የተሻለ ጥያቄ ነው፡፡)
“ማክሰኞ እለት እንትና ቴሌቪዥን ላይ የነበረውን ውይይት አላያችሁም?”
«አይተዋል፣ እናስ ምን ይሁን!»
  “ያ ሰማያዊ ኮተን ሱሪ አድርጎ ነጭ ጣል፣ ጣል ያለበት ከረባት…»
አበስኩ ገበርኩ!... (ሁሉም ናቸው በሆዳቸው እንዲህ ያሉት!) እኮ ያ ቀደም ቀደም የሚለው! ያ ሀኪም ሀያ አራት ሰዓት ለፍልፍ ብሎ ያዘዘው ይመስል፣ ሌሎችን አላናግር ያለው! ሶፋው ዳር ላይ ተቀምጠው ያቀረቀሩት ሴት፤ምን ብለው እያሰቡ መሰላችሁ… “አምላኬ እንደው ምንስ ብንበድልህ፣ ምንስ ሀጢአታችን ቢበዛ እንዲህ አይነት መቅሰፍት ታወርደብናለህ!”) እያሉ:: (በነገራችን ላይ ከተፈቀደልን ሀሳብ አለን… ‘አክቲቪስትነት’ ፕሳ. ሀያ ስድስት ምናምን ነገር ተብሎ በሙያነት ይመዝገብልን፡፡)
እናላችሁ..ዘንድሮ “ልጃችሁን ለልጃችን…” የሚለው ነገር… አለ አይደል…ጠያቂና ተጠያቂ በሁለት የአውቶብስ ፌርማታዎች ልዩነት ሳይሆን በብዙ መቶና በሺዎች ኪሎ ሜትሮች መካከል ቢሆን እንዲህ የአንዳንዶች ፖለቲካ መለማመጃ፣ የጊዜ ማሳለፊያና ወጣቶቹ እንደሚሉት ‘ሙድ መያዣ’ ባልሆንን ነበር፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1956 times