Saturday, 09 June 2012 10:20

ሞርጋን ፍሪማን ሥራና ፖለቲካን እያቀላቀለ ነው ፖለቲከኞችን አበሳጨ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከሳምንት በፊት 75ኛ ዓመት ልደቱን ያከበረው ሞርጋን ፍሪማን በዘንድሮ የፊልም ስራዎቹ ማስተዋወቂያ መድረኮች ላይ የግሉን የፖለቲካ አጀንዳ ማራመዱ አንዳንድ ፖለቲከኞችንና የፊልም ኩባንያውን ዋርነር ብሮስ ሃላፊዎች እንዳስከፋ ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር ዘገበ፡፡ ሞርጋን ፍሪማን ከወራት በፊት በሲኤንኤን የፒርስ ሞርጋን ሾው በቀረበበት ወቅት፤ ዘንድሮ ስለሰራው “ዶልፊን ቴል” የተባለ ፊልሙ ሲናገር፤ ለባራክ ኦባማ ድጋፉን ለመግለፅ ዋና ተቃዋሚዎቹን የቲ ፓርቲ ፖለቲከኞች ዘረኞች ናቸው ሲል ነቅፎ ነበር፡፡ በዚህ አሉታዊ አስተያየቱም  ታዋቂውን የቲ ፓርቲ እንቅስቃሴ በሚደግፉ እና የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞች ዘንድ ቅሬታና ብስጭት ተፈጥሯል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በመጪው ክረምት ለዕይታ እንደሚበቃ በሚጠበቀው “ዘ ዳርክ ናይት ራይዝስ” ፊልም የፕሮሞሽን ስራ ላይ በፊልሙ የሚተውነው ሞርጋን ፍሪማን ተመሳሳይ ስህተት ከመፈፀም እንዲቆጠብ ፊልሙን የሰራው ኩባንያ “ታይምዋርነር” አንድ ባለድርሻ ሰሞኑን አሳስበዋል፡፡ ሞርጋን ለ30 ዓመታት ባሳለፈው የትወና ዘመኑ 45 ፊልሞች ላይ የሰራ ሲሆን በመላው ዓለም  4.12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል፡፡ በቀጣይ ክረምት ለእይታ በሚበቃው “ዘ ዳርክ ናይት ራይዝስ” ፊልም ተጋባዥ ተዋናይ ሆኖ የሚሰራው ሞርጋን ፍሪማን፤ ከቶም ክሩዝ ጋር “ኦብሊቪዮን” በተባለ ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም በመስራት ላይ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ “ናው ዩ ሲ ሚ” በሚል ፊልም ላይ እንደሚተውንም ይጠበቃል፡፡

 

 

 

Read 1084 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 10:27