Saturday, 27 July 2019 12:30

የደቡብ ክልል የፖለቲካ ትኩሳትና የክልሉ ቀጣይ እጣ ፋንታ 3 አማራጮች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬና አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)


        - በክልሉ ጉዳይ ላይ 17 ሺ የክልሉ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ጥናት ውጤት ተገለጸ፡፡
       - አብዛኛዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች ችግሮቹ ተስተካክለው ክልሉ አሁን ባለው አደረጃጀት ቢቆይ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
       - የክልል ምስረታ ጥያቄዎች እንዲዘገዩና በሰከነ መንፈስ እንዲታዩ ተጠይቋል፡፡
                    
         ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ሁከትና ግርግር፣ ሳቢያ በደቡብ ክልል የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች ውጥረት ነግሶ ሰንብቷል፡፡ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር የሰዎች ሕይወት ማለፉና እስከአሁን ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙ እንዲሁም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወገኖች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ታውቋል፡፡ ይህንኑ ሁከትና ግርግር ተከትሎ ክልሉ ከሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የፀጥታ ሥራው በፌደራልና በፀጥታ ኃይል ቁጥጥር ስር ሆኖ በጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት እየተመራ ይገኛል::
በክልሉ የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ ለመወሰን የሚያግዝ ምከረ ሀሳብ ለማቅረብ የተቋቋመውና -13 አባላት ያሉት የምሁራን አጥኚ ቡድን፣ ከ17ሺ በላይ የክልሉ ሕዝብ ተሳታፊ የሆነበትን ጥናት አካሂዶ የጥናቱን ውጤት ይፋ አድርጓል:: የክልሉ ተወላጅ ምሁራንና በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተሳታፊ በሆኑበት በዚህ ውይይት ላይ ይፋ የተደረገውና የክልሉን ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመወሰን ያግዛል ከተባሉት 3 አማራጮች መካከል በበርካታ የጥናቱ ተሳታፊ በሆኑ የክልሉ ሕዝቦች ድጋፍ ያገኘው አማራጭ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የስልጣን ክፍፍሉና፣ የሀብት ስርጭት ኢ-ፍትሐዊነት እንዲሁም ሌሎች የችግር ምንጭ የሆኑ አሰራሮች ተስተካክለው፣ አሁን ያለው የደቡብ ክልል አደረጃጀት ቢቀጥል የተሻለ ነው የሚል አማራጭ ሀሳብ አቀርበዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ከቀረና ክልሉ አሁን ባለበት አደረጃጀት መቀጠል ባይችል፣ ሁለተኛ አማራጭ ሆኖ በጥናቱ ተሳታፊዎች የቀረበው፤ ክልሉ ለሁለት እና ከዚያ በላይ ተከፍሎ እንዲደራጅ የሚለውን ሀሳብ ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ አዲስ የሚመሰረቱት ክልሎች ቁጥር ግን ከአምስት መብጥ የለበትም ብለዋል፡፡
በጥናቱ ላይ 3ኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበው ሀሳብ ደግሞ የቀረቡት የክልል ምስረታ ጥያቄዎች እንዲዘገዩ በማድረግ፣ ክልሉንም ሆነ አገሪቱን ከክልል እንሁን ጥያቄ ወለድ ግጭት መጠበቅ ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ ጥናቱን ያደረጉት ምሁራን፤ የክልል ምስረታ ጥያቄዎች በሰከነ መንፈስ እንዲታዩ ማድረግ ይገባል የሚል ሀሳብም ሰጥተዋል፡፡ የጥናት ውጤቱ ለውሳኔ የሚያግዝ ምክረ ሀሳብ የማቅረብ እንጂ የመጨረሻ ውሳኔም እንዳልሆነ የጥናት ቡድኑ አስታውቋል፡። በጥናት ውጤቱ ላይም የክልሉ ሕዝብ በየደረጃው እንዲወያይበት ይደረጋል ተብሏል፡፡
ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በሃይል የሲዳማን ክልልነት ለማወጅ የተንቀሳቀሱ አካላት የፈጠሩትን ሁከት ተከትሎ፣ በሲዳማ ዞን ስለደረሰው ውድመትና ሰብአዊ ጥፋት መንግስት ግልጽ መረጃ ከመስጠት ቢቆጠብም የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከ30 ሰው በላይ ህይወት ማለፉን ዘግበዋል፡፡
የዚህ ሁከትና ግርግር ሰለባ የነበሩ ሐዋሣ፣ ይርጋለም፣ ለኩ፣ አለታ ወንዶ፣ ጩኮ፣ ሀገረ ሠላም፣ ወንዶገነትና አቦስቶ ከተሞች ለሁለት ቀናት በጭንቀትና በውጥረት ከቆዩ በኋላም ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሣዊ ውድመትን አስተናግደው፣ መንግስት አጠቃላይ የደቡብ ክልልን በፌደራል ኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን ካደረገ በኋላ በየአካቢው መረጋጋት መፈጠሩን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በሁከትና ግርግር ያሳለፈውን የሲዳማ ዞንን ጨምሮ የደቡብ ክልል በኮማንድ ፖስታ ስር ከተደረገ በኋላም የቀድሞ የሐዋሣ ከተማ ከንቲባ ቴዎድሮስ ገቢባን ጨምሮ ከ150 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
የክልሉ ገዥ ፓርቲ ዲኢህዴን በበኩሉ ችግሩን አስመልክቶ ሐሙስ እለት ባወጣው ዝርዝር መግለጫው፤ በሲዳማ ዞን ከተፈጠረው ሁከትና ግርግር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ውድመት መፈጠሩን፣ የዜጐችን ስነ ልቦና እና የመኖር ዋስትና የሚፈታተን ክስተት ተፈጥሮ እንደነበር አረጋግጦ፣ አጥፊዎችን ለህግ የማቅረቡን ሂደት አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብሏል፡፡
ለዚህ ሁከትና ግርግር አስተዋጽኦ አድርገዋል ያላቸውን የሃዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሲዳማና የሃዲያ ዞን ከፍተኛ አመራሮችንም ደኢህዴን ከስልጣን ላልተወሰነ ጊዜ ማገዱንም አስታውቋል፡፡
ህዝብን ወዳልተገባ ግርግርና ሁከት የመምራት አዝማሚያ አሳይተዋል የተባሉ የከፋ እና የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ደግሞ ከደኢህአዴን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል:: “በዞኖቹ እየተስተዋለ ያለው አካሄድ የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው” ብሏል ደኢህአዴን መግለጫው በሲዳማ ዞን የደረሰውን ሰብአዊና ቁሣዊ ጉዳት በዝርዝር ከመግለጽ የተቆጠበ ሲሆን፤ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የየአካባቢው ምንጮች፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የግል መኖሪያ ቤቶች፣ ቤተ እምነቶችና የልማት ተቋማት በእሣት መውደማቸውንና መዘረፋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
መንግስት በበኩሉ የደረሰውን ጥፋት አጣርቼ በዝርዝር እገልፃለሁ ያለ ሲሆን ሰብአዊ ጉዳዮችን በመከታተል የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) በበኩሉ በዞኑ የተፈጠረውን ጉዳትና የደረሰውን ጉዳት አጣራለሁ ብሏል፡፡
በጉዳዩ ላይ የአቋም መግለጫቸውን ያስታወቁ የፖለቲካ ድርጅቶች በበኩላቸው በሲዳማ ዞን የተፈጠረው ሁኔታ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለህዝብ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡
ከእነዚህ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) በዞኑ የተፈፀመውን ሁካታና ግርግር ያስነሱት የለውጡ ተፃራሪዎችና የለውጡን ሂደት በአግባቡ ያልተረዱ ናቸው” ብሏል፡፡ ለዚህ አባባሽ የሆነው ደግሞ መንግስት ለክልልነት ጥያቄው ተገቢና ፈጣን ምላሽ አለመስጠቱ መሆኑን ሲአን አስታውቋል፡፡
የተፈጠረው ክስተት፣ መነሻ ምክንያቱን ጨምሮ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ መቅረብ እንዳለበትና እስከዚያው መገናኛ ብዙሃን የተዛቡ መረጃዎችን ከማቅረብ እንዲቆጠቡ ሲአን ጠይቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ በክልል በዞንና በወረዳዎች የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ተወጥራ ትገኛለች” ያለው ኢዜማ በበኩሉ በሲዳማ ዞን የተፈፀመው ድርጊት አሣፋሪ ነው ብሏል፡፡ ድርጊቱም እንደ ሀገር የደረስንበት አስከፊ ሁኔታ ነፀብራቅ ነው ብሏል - አዜማ፡፡
መኢአድ እና ኢህአፓን ጨምሮ 7 ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይም የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ተገቢውን ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ፤ ከሰሞኑ ተፈጥሮ ከነበረው የንፁሀን ዜጐች ግድያ፣ ዘረፋ እና ወከባ ጋር በተያያዘም በወንጀሉ የተሳተፉ ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል::
የክልሉን ህዝብ በሙሉ አቅሙ እያስተዳደረ አይደለም ተብሎ በሠላማዊ ሠልፍ ጭምር ሲወገዝ የሰነበተው ደኢህአዴን በበኩሉ እስከ ሰኞ በሚያካሂደው ስብሰባው ያሉበትን ድክመቶች ቀርፎ ቀጣይ ህልውናው ላይ የመጨረሻ ውሣኔ ወስኖ እንደሚወጣ ሊቀመንበሯ ሙፈሪያት ከማል አስገንዝበዋል፡፡    

Read 11914 times