Saturday, 27 July 2019 12:29

አብን በአመራሮቼና አባላቶቼ ላይ እስርና ወከባ እየተፈፀመ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 - የንቅናቄው የጽ/ቤት ኃላፊ ትናንት ታስረዋል
              - ከ5መቶ በላይ አመራርና አባላት ታስረውብኛል ብሏል

          በአመራሩና አባላቱ ላይ እስርና ወከባ እየተፈፀመ መሆኑን የገለፀው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ ትናንት ከሰአት በኋላ የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ በለጠ ካሳ መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡ የአብን የጽ/ቤት ኃላፊው አቶ በለጠ ካሳ ትናንት አርብ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ለጉዳይ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት “በፖሊስ ትፈለጋለህ” ተብለው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መወሰዳቸውን ነው ፓርቲው ያመለከተው፡፡
በሌላ በኩል የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ አመራሮችን የችሎት ውሎ ለመዘገብ ፍ/ቤት የተገኙ 27 የፓርቲው አባላት ታስረው፣ 24ቱ እያንዳንዳቸው በ3ሺህ ብር ዋስ ከትናንት በስቲያ ሲለቀቁ ሶስቱ ማለትም አቶ ዮናስ አሰፋ የአብን የቦሌ ክ/ከተማ ሰብሳቢ፣ አቶ ሺገዛ ሙሉጌታ የአብን የኮልፌ ክ/ከተማ ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እንዲሁም አቶ በዕውቀቱ በላቸው የአብን የቂርቆስ ክ/ከተማ ድርጅት ገዳይ ኃላፊ “ለተጨማሪ ምርመራ ትፈለጋችሁ” ተብለው ዋስትና መክልከላቸውንና ፍ/ቤት ቀርበውም የ28 ቀን ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ፓርቲው አስታውቋል፡፡ አመራሮቹ እና አባላቱ ከሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ባለስልጣናት እና የመከላከያ ኢታማዦር ግድያ ጋር በተያያዘ መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤት አስረድቷል፡፡
አብን ቀደም ብሎ ባሰራጨው የአቋም መግለጫው በየአካባቢው ያሉ አመራሮቹ እና አባላቱ ላይ ማዋከብና እስራት እየተፈፀመ መሆኑን አስረድቷል፡፡
የጅምላ እስራቶች አሳስበውኛል ሲል ባለፈው ሳምንት መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በበኩሉ 66 የአብን አባላት መታሠራቸውን የገለፀ ሲሆን፤ ፓርቲው በበኩሉ ትናንት የታሠሩትን የጽ/ቤት ኃላፊውን ጨምሮ ከ5 መቶ በላይ አባላቱ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች እንደታሠሩበት አስታውቋል፡፡

Read 7216 times