Saturday, 27 July 2019 12:27

የዜጎች ጥያቄ ህግን መሰረት ያደረገ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የህወኃትና አዴፓ ጉዳይ በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት እንዲታይ ተጠየቀ

          በመላ አገሪቱ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝና ተገቢ ምላሽ እንዲሰጣቸው ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች ያሳሰቡ ሲሆን በቃላት ጦርነት ውስጥ የገቡት የህወኃትና የአዴፓ ጉዳይ በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ቀርቦ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡
የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ (ኦነንፓ)፣ የአፋር ህዝብ ነፃነት ፓርቲ (አህነፓ)እና የአፋር ህዝብ ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰሞኑን በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ባለሥልጣናትና የመከላከያ አዛዦች ግድያ ጋር ተያይዞ እየተፈጸመ ያለው የጅምላ እስር፣ ማሳደድና ማስፈራራት በአስቸኳይ እንዲቆምና ህግና ሥርዓትን ብቻ የተከተለ አሰራር እንዲሰፍን እንዲሁም የተፈፀመው ግድያ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቀዋል፡፡
በአማራ ክልል ውስጥ ታስረው የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ዜጎች ጉዳያቸው በአስቸኳይ ተጣርቶ ከእስር እንዲለቀቁና መንግስት ከዚህ ቀደም ‹‹አስረን አናጣራም፤ አጣርተን ነው የምናስረው›› ሲል የገባውን ቃልም እንዲያከብር ጠይቀዋል ፓርቲዎቹ፡፡
የሰኔ 15ቱን ግድያ ተከትሎ በህወኃትና በአዴፓ መካከል የሚደረጉ የተንኳሽነት እሰጣ ገባዎች በአስቸኳይ ቆመው፤ የሁለቱን ህዝብ ታሪካዊ ግንኙነትን መሰረት ያደረገ መፍትሄ እንዲሰጥበት የጠየቁት ድርጅቶቹ፤ የሁለቱ ፓርቲዎች ጉዳይም በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ቀርቦ እንዲታይ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
የሲዳማ ህዝብ የክልልነት ጥያቄ ህግን መሰረት አድርጎ ምላሽ እንዲሰጥ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በንፁሀን ዜጎች ላይ ግድያ፣ ዘረፋና ወከባ የፈፀሙ አካላትም ለህግ እንዲቀርቡ ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡


Read 7483 times