Saturday, 27 July 2019 12:26

ከህገመንግስታዊ ጥያቄዎች ይልቅ ለሠላምና መረጋጋት ቅድሚያ እንዲሰጥ ኢዜማ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


          የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ዲሞክራሲን እንዲያመጣ በቅድሚያ ለሀገር መረጋጋትና ሰላም መስፈን ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ያስገነዘበው ኢዜማ፤ የዜጐች የመብት ጥያቄ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው በሠላማዊ መንገድ ብቻ ነው ብሏል፡፡
ፓርቲው በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫው፤ አሁን እየታዩ ያሉት ማንኛውንም ግላማዊና ቡድናዊ የፖለቲካ ፍላጐት በሃይል ለማስፈፀም የሚደረጉ ጥረቶች ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም ብሏል፡፡
መብትን በሃይል ለማስፈፀም መሞከር የሀገሪቱን ሠላምና ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ነው ያለው አዜማ፤ ህገመንግስቱ ላይ ባለው ህፀፅ ላይ ዝርዝር ውይይት ተደርጐ መግባባት ላይ ሳይደርስ በሽግግር ሂደት ውስጥ ህገመንግስቱን መሠረት አደረገው የሚነሱ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሔ ያገኛሉ ብዬ አላምንም ብሏል፡፡
አሁን በሀገሪቱ ላሉ ውስብስብ ችግሮች ህገመንግስቱ አስተዋጽኦ እንዳለው አበክሮ የገለፀው፤ ፓርቲ ነገር ግን ይህን ህገመንግስት አሁን ማሻሻል የሚቻልበት ሁኔታ የለም ብሏል::
መንግስትም ሆነ ባለድርሻ አካላት ከምንም በፊት ለሀገር ሠላምና መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ የጠየቀው ድርጅቱ፤ ሠላምና መረጋጋት ተፈጥሮም በቀጣይ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት ብሏል፡፡
ህገመንግስትን የማሻሻልና ሌሎች ጥያቄዎችን የመመለስ ጉዳይ ትክክለኛ የህዝብ እንደራሴዎች ሲመረጡ መከናወን ያለበት ተግባር መሆኑንም ኢዜማ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ ንቅናቄ (ኢዜማ) በዚህ መግለጫው፤ ከሲዳማ ክልል ልሁን ጥያቄ ጋር ተያይዞ በዞኑ የተፈፀሙ ድርጊቶችን በጥብቅ አውግዞ፣ ጉዳዩ በአግባቡ ተጣርቶ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡና በንፁሃን ላይ በደል የፈፀሙ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍሉ ይደረግ ዘንድም ጠይቋል፡፡
ህግን ለማስከበር በህግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ካሉ ሰዎች መካከል የኢዜማ አባላቱ እንደሚገኙበት የጠቆመው ኢዜማ፤ መንግስት ከማሠሩ በፊት በተገቢው ማጣራቱንና በቂ ማስረጃ ያለው መሆኑን እንዲያረጋግጥ ጠይቋል::   

Read 7285 times