Saturday, 27 July 2019 12:24

አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግ እያከራከረ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ከዚህ ቀደም የነበሩ አሠራሮችን የሻሩ በርካታ አዳዲስ መስፈርቶች አካቶ የተዘጋጀው አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግ ላይ ፓርቲዎች መግባባት አልቻሉም፡፡
በረቂቅ ህጉ ውይይት ላይ በስብሰባ መግባባት ላይ አለመደረሱን ተከትሎ ሁሉም ፓርቲዎች በአዲሱ ህግ ላይ ያላቸውን አስተያየትና እንዲሻሻሉ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ምርጫ ቦርዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱም ታውቋል፡፡
ፓርቲዎቹን ቅሬታ ውስጥ ከከተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ፓርቲ ለመመስረት ማሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች፣ እጩ ተወዳዳሪዎች ሊያሟላቸው ይገባል ተብለው በአዋጁ የተቀመጡት መስፈርቶች ይገኙባቸዋል፡፡
የፓርቲው ደጋፊዎችን በተመለከተና የፖለቲካ ከበጐ አድራጐት ድርጅቶች ገንዘብ መቀበል እንደማይችሉ መደንገጉም ውዝግብ አስነስተዋል፡፡
የምርጫና የፓርቲዎች ህጉ ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ በፓርቲዎች የሚቀርቡ እጩዎች ለመወዳደር በቅድሚያ ከሚወዳደሩበት አካባቢ የ3ሺህ ሰዎች የድጋፍ ድምጽ ማቅረብ አለባቸው መባሉ ቅሬታ ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ ነው ያሉት የውይይቱ ተሣታፊ የመኢአድ አመራር አቶ ሙሉጌታ፤ ይህ አንቀጽ የፓርቲዎችን ህልውና የሚጋፋ፣ የምርጫ ውጤትን አመላካች በመሆኑ ፓርቲዎችን ለድህረ ምርጫ ውዝግቦች የሚጋብዙና አለመግባባት የሚፈጥር ነው የሚል ቅሬታ ድርጅታቸውን ጨምሮ ሌሎችም ማቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ሊወዳደሩ የሚችሉ እጩዎችን ለመገደብ  እንደ ማጣሪያ በማሰብ ያካተተው ድንጋጌ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
ሌላው ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ አንድ አዲስ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ሲመሰረት 10ሺህ የድጋፍ ድምጽ ክልላዊ ከሆነ 4ሺህ ማቅረብ አለበት የሚለው ሲሆን ይህ ድንጋጌ ነባር ፓርቲዎችንም የሚመለከት ነው ተብሏል፡፡
“ነባር ፓርቲዎች በዚህ ድንጋጌ ይገዙበታል ቦርዱ በፈለገ ጊዜ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል” ይላል ድንጋጌው፡፡ ይህ ድንጋጌ ህግ ወደኋላ ተመልሶ አይሰራም ከሚለው የህግ መርህ ጋር የሚጣረስ ነው የሚል ቅሬታ ያቀረቡት ፓርቲዎቹ አዋጁ አስፈላጊ ከሆነም አዲሶቹን የሚመለከት መሆን እንደሚገባው ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
10ሺህ ድምጽ አሰባሰቡ መባሉ የፓርቲዎችን ማበብ የሚያቀጭጭ እንደሆነ ቅሬታቸውን የገለፁ በርካቶች ሲሆኑ ግንባር፣ ውህደት፣ ቅንጅት ለመፍጠርም ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ መወሰን አለበት የሚለው ተገቢ አይደለም፤ ከውህደት ውጪ ያለው በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ሊወሰን የሚችል ነው ብለዋል፡፡
ሌላው በዚህ አዋጅ ቅያቄ የተነሳበት አንቀጽ ለፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ ሲሆን፤ አዋጁ “እስከ 5ሺህ ብር የሰጠ ደጋፊ ስሙ በግልጽ መታወቅ አለበት” ሲል ይደነግጋል፡፡
አንቀፁ የደጋፊዎችን ነፃነት የሚጋፋና ለተለየ ጥቃት የሚያጋልጥ ድንጋጌ ነው በሚል ተቃውሞ ቀርቦበታል - ከበርካታ ፓርቲዎች፡፡ በተመሳሳይ የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ለፓርቲዎች ምንም አይነት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አይችሉም የሚለው ድንጋጌም ጥያቄ አስነስቷል፡፡
የበጐ አድራጐት ተቋማት ለፖለቲካ አላማ ድጋፍ ማድረግ መከልከሉ ተገቢ ቢሆንም ለምርጫና እና የስነ ምግባር ሥልጠናዎች በቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ግን ሊፈቀድ ይገባል የሚል ሃሳብ ተነስቷል፡፡
በዚህ አዋጅ በበጐነት በፓርቲዎቹ ከታዩ አዳዲስ ድንጋጌዎች መካከል ለፓርቲዎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ መንግስት የገንዘብ ድጐማ ያደርጋል የሚለው አንቀፅ ነው፡፡
አንዳንድ ፓርቲዎች በህግ ማሻሻያው ላይ ያቀረብነው ሃሳብ ተቀባይነት አላገኘም በሚል ውይይቱን ረግጠው መውጣታቸው የታወቀ ሲሆን ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ ሁሉም ፓርቲዎች ያላቸውን የማሻሻያና የማዳበሪያ ሃሳብ እስከ ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 137 አዲስና ነባር ፓርቲዎች በሀገሪቱ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡  

Read 946 times