Print this page
Saturday, 27 July 2019 12:18

የኮዬ ፈጬ ኮንዶምኒየም እድለኞች መንግስት ቤቱን እንዲያስረክባቸው ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  “አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጠን ከሆነ ሠላማዊ ሠልፍ እንወጣለን”

             ከ5 ወራት በፊት በኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ የደረሳቸው ዜጐች መንግስት ቤቱን በአፋጣኝ እንዲያስረክባቸው የጠየቁ ሲሆን ጥያቄያቸው ምላሽ የማያገኝ ከሆነ መብታቸውን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚወጡ ገለፁ፡፡
“ከ15 ዓመታት በላይ በተስፋ ተጠባብቀንና ከልጆቻችን ጉሮሮ ላይ ቆጥበን ባጠራቀምነው ገንዘብ ያገኘነውን መኖሪያ ቤት ባልተገባ የፖለቲካ ጨዋታ ልንከለከል አይገባም” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ መንግስት መብታቸውን ያለ ልዩነት እንዲያከብር ጠይቀዋል፡፡
ለበርካታ አመታት የጋራ መኖሪያ ቤት ባለእድል እሆናለሁ በሚል ተስፋ ቤተሰባቸውን ይዘው በኪራይ ቤት ሲኖሩ መቆየታቸውን የተናገሩት አንድ ቅሬታ አቅራቢ፤ “ቤቱ እንደደረሰን ከተገለፀ በኋላ በውዝግብና በግርግር እስካሁን ሳይተላለፍልን መቆየቱ አግባብ አይደለም” ብለዋል፡፡
“ሁኔታው መንግስት የዜጐችን መብት የማስከበር አቅም ላይ ጥያቄ አጭሮብኛል” ያሉት ዕጣው የደረሳቸው የቤት ባለቤት፤ “የከተማ አስተዳደሩ ውዝግቡ ከተፈጠረ በኋላ እንኳ እጣው የደረሰንን 30ሺህ ያህል ዜጐችን ለማነጋገር አልሞከረም” ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
“መንግስት ጉዳያችን በቸልታ መመልከቱ እንደ ዜጋ የመገፋት ስሜት ፈጥሮብኛል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢው “መንግስት ከህጋዊ ሰዎች ይልቅ የህገወጥ ሰዎችን መብት እያስከበረ” ነው የሚል እምነት አድሮብኛል” ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ የተናገሩት አቶ ጌታቸው በላይ፣ “ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ተመዝግቤ ቁጠባ እየቆጠብኩ ቤት አገኛለሁ በሚል ተስፋ በኪራይ ቤት ሆኜ  ስጠባበቅ ከቆየሁ በኋላ ከወራት በፊት ደርሶሃል ተብዬ ደስታዬን “ሳልጨርስ በህጋዊ መንገድ ያገኘነው ቤት በሌላ ድርድር ውስጥ መግባቱ አሳዛኝ ክስተት ነው፤ እንደ ዜጋም የመገፋት ስሜት ፈጥሮብኛል” ሲሉ መከፋታቸውን ገልፀዋል ፡፡ በአሁን ወቅት ቤቱን አገኛለሁ አላገኝም በሚል ጥርጣሬ ላይ ነኝ የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ “መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ ዝምታ መምረጡ ግራ አጋቢ ሆኖብኛል” ብለዋል፡፡
መንግስት በእኩል የዜግነት መብታችን ሊያስከብር ይገባል፤ በአፋጣኝ ቤታችን ተሰጥቶን ለቀጣይ አመት ልጆቻችንም ትምህርታቸውን ሳይጉላሉ እንዲማሩ እንፈልጋለን” ብለዋል - አቶ ጌታቸው፡፡
ሌላው በኮዬ ፈጬ የባለ ሁለት መኝታ ቤት ባለእድል የሆኑት አቶ ፍፁም በበኩላቸው፤ መንግስት እስካሁን ጉዳያችንን በዝምታ መመልከቱ፣ ቤቱን ላናገኝ እንችላለን የሚል ስጋት ውስጥ ከቶኛል ይላሉ፡፡
“የቤት እድሉ የደረሰን ሰዎች ተሰባስበን መንግስትን በሠለማዊ ሠልፍ ለመጠየቅ አቅደን ነበር” ያሉት አቶ ዳዊት፤ በሀገሪቱ ባለው አለመረጋጋት ላይ ተጨማሪ ችግር ላለመፍጠር ስንል ግን  የመንግስትን ምላሽ በትዕግስት መጠባበቁን መርጠናል ብለዋል፡፡
እንዲያም ሆኖ በአፋጣኝ ምላሽ የማናገኝ ከሆነ… 30ሺህ የቤት እድለኞችን በማሰባሰብ መብታችንን በሠላማዊ ሠልፍና በተለያዩ ሠላማዊ መንገዶች ለመጠየቅ እንገደዳለን ብለዋል - አቶ ዳዊት ለአዲስ አድማስ፡፡

Read 1408 times