Saturday, 09 June 2012 10:18

“ስኖው ዋይት ኤንድ ሃንትስ ማን” በልጃገረዶች ተወዷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

“ስኖው ዋይ ኤንድ ሃንትስ ማን” ባለፈው ሳምንት 56.26 ሚሊዮን ዶላር በሰሜን አሜሪካ አስገብቶ በምረቃው ሰሞን የአመቱን ከፍተኛ ገቢ በአራተኛ ደረጃ በማስመዝገብ የቦክስ ኦፊስ የገቢ ደረጃን እየመራ ነው፡፡ ፊልሙ በተለይ  እድሜያቸው ከ18 እስከ 25 በሆኑ ልጃገረዶች ዘንድ መወደዱ ይገለፃል፡፡ በተቀረው የዓለም ክፍል የፊልሙ ገቢ 39.3 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የመላው ዓለም ጠቅላላ ገቢው 95.6 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በ170 ሚሊዮን ዶላር በጀት በዩኒቨርሳል ስቱዲዮ የተሰራው “ስኖው ዋይት ኤንድ ሃንትስ ማን” ላይ በ”ትዋላይት” ፊልሞች የምትሰራው ክርስትያን ስትዋርት እና ደቡብ አፍሪካዊቷ ተዋናይት ቻርልስ ቴሮን ይተውናሉ፡፡ ፊልሙ በእንግሊዝና አሜሪካ ፊልም ሰሪዎች ጥምረት በጀርመን ታዋቂ ተረት ላይ ተመስርቶ የተሰራ ፋንታሲ ፊልም ነው፡፡ ፊልሙ በሳምንታዊ ገቢው አስቀድሞ ከተገመተው 20 በመቶ ጭማሪ ያስመዘገበ ሲሆን በዚሁ ዓመት በተመሳሳይ ተረት ላይ በጁሊያ ሮበርትስ የተሰራው “ሚረር ሚረር” የተባለ ፊልም ግን ብዙ በገቢ አልቀናውም ነበር፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የኤምቲቪ ሙቪ አዋርድ “ዘ ትዋይላይት ሳጋ፡  ብሬኪንግ ዳውን ክፍል 1” የዓመቱ ምርጥ ፊልም ተብሎ ተሸለመ፡፡ በስነስርዓቱ አራት ሽልማቶችን በመሰብሰብ የተሳካለት ፊልም ደግሞ “ዘ ሃንገር ጌምስ” ነው፡፡ ዘ ሃንገር ጌምስ በምርጥ ተዋናይነት በሁለቱም ፆታዎች የቀረቡ ሽልማቶችን ሲወስድ ቀሪዎቹ ሽልማቶች ምርጥ ለውጥ ያሳየች ተዋናይና ምርጥ ድብድብ የታየበት ፊልም ተብሎ ያገኛቸው ናቸው፡፡ በላዮን ጌትስ በ78 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው “ዘ ሃንገር ጌምስ” ለእይታ ከበቃ በኋላ ባለፉት 73 ቀናት ጠቅላላ የዓለም ገቢው 600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል፡፡

 

 

Read 858 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 10:22