Saturday, 27 July 2019 12:02

ዎልማርት፤ የአለማችን እጅግ ግዙፍ ኩባንያ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ታዋቂው ፎርቹን መጽሄት የ2019 የአለማችን 500 ባለ ብዙ ገቢ ግዙፍ ኩባንያዎች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን የአሜሪካው ዎልማርት 514.4 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በማስመዝገብ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በ2018 የፈረንጆች አመት ግሩፕ 414.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስመዘገበው የቻይናው ሲኖፔክ ሮያል የሁለተኛነትን ደረጃ ሲይዝ፣ ደች ሼል በ396.5 ቢሊዮን ዶላር የአለማችን የአመቱ ሶስተኛው ግዙፍ ኩባንያ ተብሎ መመዝገቡን ዘገባዎች አመልክተዋል::
ቻይና ናሽናል ፔትሮሊየም በ392.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ስቴት ግሪድ በ387 ቢሊዮን ዶላር፣ ሳኡዲ አርማኮ በ335.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ቢፒ በ303.7 ቢሊዮን ዶላር፣ ኤክሰን ሞቢል በ290.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ቮልስዋገን በ278.3 ቢሊዮን ዶላር፣ ቶዮታ ሞተር በ272.6 ቢሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአመቱ የአለማችን ኩባንያዎች ናቸው፡፡
ከ34 የአለማችን አገራት የተውጣጡት የአመቱ 500 ግዙፍ ኩባንያዎች ባለፈው የፈረንጆች አመት (2018) በድምሩ 2.15 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የጠቆመው ፎርቹን መጽሔት፤ ኩባንያዎቹ በመላው አለም ለ69.3 ሚሊዮን ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በዘንድሮው የፎርቹን ዝርዝር ውስጥ 13 አዳዲስ ኩባንያዎቿን በማካተት የምርጥ ኩባንያዎቿን ቁጥር 129 ያደረሰችው ቻይና፤ በዝርዝሩ ውስጥ ብዛት ያላቸውን ኩባንያዎች በማስመዝገብ፣ ከአሜሪካ በመቅደም የአንደኛነት ደረጃን መያዟ የተነገረ ሲሆን፣ አሜሪካ 121 ኩባንያዎቿን በዝርዝሩ ውስጥ በማካተት እንደምትከተል ተዘግቧል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ የ11ኛ ደረጃን የያዘው አፕል በሞባይል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ዘንድሮም መሪነቱን የያዘ ሲሆን፣ በ15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሳምሰንግ ይከተለዋል፡፡


Read 1298 times