Print this page
Saturday, 20 July 2019 12:34

የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግር ይፈታል የተባለ ፕሮጀክት ቀረበ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ቤዝ ሶሉሽን ፕሮጀክት የተባለ ድርጅት፤ የአዲስ አበባ ከተማን የመኖሪያ ቤት ችግር ይፈታል የተባለ ዘዴን ለአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ኤጀንሲ አቅርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የቤዝ ሶሉሽን ዋና ጠንሳሽ አቶ ናደው ጌታሁን ባለፈው ሐሙስ በስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫ፤ በከተማው ውስጥ 500 ካሬ ሜትርና ከዚያም በላይ ነባር ይዞታ ያላቸው ሰዎች፣ ከይዞታቸው ሳይነሱ የመኖሪያ ቤትና ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያገኙበት ዘዴ አቅርቤያለሁ ብለዋል፡፡
በከተማ ውስጥ ነባር 500 ካሬ ሜትርና ከዚያ በላይ ይዞታ ያላቸው ሰዎች “ይዞታዬን አጋራለሁ፤ ከተማዬንም አለማለሁ” በሚል መርህ፣ ይዞታቸውን ለሌሎች በማጋራት፣ ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙበት አሰራር መዘየዳቸውን አቶ ናደው ገልጸዋል፡፡ 500 ካ.ሜ መሬት ያለው አንድ ሰው፤ በተለመደው አሠራር፣ በ5 ሚሊዮን ብር ቦታውን ሸጦ ከዚያ ለቅቆ ይወጣል፡፡ “ይዞታዬን አጋራለሁ” በሚለው በእኛ አሠራር ግን 40 እግ 60 ዓመት ከኖረበት ከይዞታው ሳይለቅ፣ እዚያው ሆኖ፣ አምስት ባለ 3 መኝታ ክፍል ቤቶች ያገኛል፣ በተጨማሪም 12 ሚሊዮን ብር ይከፈለዋል፡፡ ከአምስቱ ቤቶች በአንዱ ቢኖርበት፣ አራቱን በማከራየት ይጠቀማል ብለዋል - አቶ ናደው፡፡
ለምሳሌ በቤዝ ሶሉሽን፣ የቤቶች ኤጀንሲ የሚያደራጃቸው መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ይኖራሉ፡፡ ለአንድ የመኖሪያ ሕንፃ የተደራጁት ሰዎች 60 ቢሆኑ፣ መሬቱን ላጋራቸው ሰው እያንዳንዳቸው  ሁለት መቶ ሺህ ብር ይሰጡታል፡፡ 60 ሰዎች ለባለመሬቱ በአጠቃላይ 12 ሚሊዮን ብር ይሰጡታል ማለት ነው፡፡ ባለመሬቱ የመኖሪያ ህንፃው ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ 5 ባለ 3 መኝታ ክፍል ቤቶች ያገኛል፡፡ 500 ካ.ሜ መሬት አጋርቶ፣ 12 ሚሊዮን ብርና 5 ቤቶች ያገኛል ማለት ነው፡፡
በማኅበር የተደራጁት ደግሞ መሠረተ ልማት በተሟላለት ከተማ መሀል መኖሪያ ቤት በማግኘታቸው እፎይታቸው ከፍተኛ ይሆናል ያሉት አቶ ናደው፤ የሚከፍሉት ገንዘብ መመዝገቢያውን ጨምሮ የሕንፃው ግንባታ እስኪያልቅ 1.5 ሚሊዮን ብር ይሆናል በማለት አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት ቤዝ ሶሉሽን በከተማው ውስጥ 500 ካ.ሜና ከዚያ በላይ የሆኑ 1,700 ባለግል ይዞታዎች ካርታ ከእነ ፕላኑ፣ ስምምነታቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት ኤጀንሲ ሰብስቦ አቅርቧል፡፡ በእያንዳንዱ ይዞታ ላይ ምን ያህል ሰዎች ማስፈር እንደሚችል ባዘጋጀው የናሙና ዲዛይን ሰርቷል፣ በአጠቃላይ ጎጆ ማርኬቲንግ ሰርቪስ፤ ከ1,700 የግል ይዞታዎች ሁለት ሚሊዮን ካ.ሜ ቦታ የሰበሰበ ሲሆን በእነዚህ ቦታዎች ላይ እንደየ ሕንጻው ከፍታ ከ2 ሚሊዮን - 3 ሚሊዮን ነዋሪዎች ማስፈር እንደሚቻል አመልክቷል፡፡
የሚሠሩት ቤቶች ከእነ መኪና ማቆሚያው 92 ካ.ሜ ስፋት ይኖራቸዋል ያሉት አቶ ናደው ጌታሁን፤ በዚህ አሠራር ሦስቱም ወገኖች፤ ባለይዞታው በማኅበር የሚደራጀውና መንግሥት ተጠቃሚ ይሆናሉ፤ መንግሥት ያለበትን የቦታ እጥረት ይፈታል፤ግንባታውን  የሚያከናውኑ መልካም የሥራ አፈጻጸም ያላቸውን የሕንፃ ተቋራጮች መርጦ ያቀርባል፤ ግንባታውን በቅርብ ሆኖ አፈጻጸሙን ይቆጣጠራል፤ ይገመግማል፤ ግንባታው ሲያልቅ ለተመዘገቡ ነዋሪዎች ቤቱን በዕጣ ያከፋፍላል፤ ለቤቱ ማረጋገጫም ይሰጣል በማለት አስረድተዋል፡፡

Read 2959 times