Saturday, 09 June 2012 10:03

የአሸር “ሉኪንግ 4 ማይሰልፍ” ለገበያ ሊቀርብ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የመጀመርያ አልበሙን ካወጣ 20 ዓመታት ያስቆጠረው አሸር “ሉኪንግ 4 ማይሰልፍ” የተሰኘ አዲስ አልበሙን የፊታችን ማክሰኞ ለገበያ ያበቃል፡፡ የአሸር አዲስ አልበም በአር ኤንድ ቢ እና በኤሌክትሮኒክ የሙዚቃ ስልቶች የተሰሩ 14 ዘፈኖችን ይዟል፡፡ ከሮይተርስ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ አዲሱን አልበም በተዋበ ጥበብ መስራቱን የገለፀው አሸር፤ ዳግም የተወለድኩበት ስራ ነው ብሏል፡፡ ማይክል ጃክሰን በዳንስ ተምሳሌቴ እንደሆነው ሁሉ በፈጠራ የታዋቂው ሰዓሊ ፒካሶ የጥበብ ስራዎች አነቃቅተውኛል ሲልም ተናግሯል፡፡ አሸር አዲስ አልበሙን ለገበያ በሚያበቃበት እለት በለንደን ከተማ በሚገኘው የሃመርስሚዝ አፖሎ ቲያትር የሚያቀርበውን ኮንሰርት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሰሩ የሆሎግራም ዳንሰኞችን በመጠቀም፣ በዩቲውብ ድረገፅ የቀጥታ ስርጭት እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡ በአልበም ምረቃ አዲስ አቅጣጫ ያሳያል የተባለው የአሸር አልበም በ youtube.com/UsherVEVO ላይ አድናቂዎቹ የራሳቸውን ምስል እንደአቫታር በመፍጠር አብረው እየደነሱ የሙዚቃ ድግሱን እንዲሳተፉበት ያስችላል እየተባለ ነው፡፡

ከቀድሞ ሚስቱ ጋር በልጆቹ ሞግዚትነት የይገባኛል ጥያቄ በክርክር ላይ ያለው አሸር፤ “ሴቶች በራሱ የሚተማመንና ስኬታማ ወንድ እንደሚወዱ አውቃለሁ፡፡ የላቀ ችሎታ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡  ዝነኛነትም ሴቶችን ለመሳብ ይጠቅማል” የሚል አስተሳሰብ እንዳለው ሰሞኑን “ኪው” ለተባለ መፅሄት ተናግሯል፡፡አርቲስቱ አምስት የግራሚ፤ ሦስት የቢልቦርድ፤ አራት የዎርልድ ሚውዚክ፤ አራት የአሜሪካን ሚዩዚክ አዋርድ ሽልማቶችን የሰበሰበ ሲሆን ማክሰኞ የሚያወጣው “ሉኪንግ 4 ማይሰልፍ”  ሰባተኛው አልበሙ ሲሆን ባለፉት አስር ዓመታት ለገበያ ያበቃቸው ስድስት አልበሞቹ በመላው ዓለም 60 ሚሊዮን ቅጂዎች ተሸጠውለታል፡፡

 

Read 829 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 10:18