Print this page
Saturday, 20 July 2019 12:24

የአንዳርጋቸው የታሪክ ተራሮች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)


     “--ይህ አለመደማመጥ ከዚህም በፊት የኢትዮጵያውያን የኪሳራ ልማድ ነው፡፡ አፄ ኃይለ ስላሴ፣ የተክለ ሃዋርያት ተክለማርያምን ምክር ሰምተው ቢዘጋጁ፣ የማይጨው ጦርነት በሽንፈት አይደመደምም ነበር፡፡ የሌተናል ጀኔራል ከበደን ገብሬን ማሳሰቢያ በጊዜ ውል ቢያስይዙ፣ በኤርትራ ያ ሁሉ ሰው አያልቅም ነበር፡።--”
       
     ባለፈው ሳምንት በወፍ በረር የቃኘሁት የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ፣ ባለ ብዙ ረድፎች ሀሳብ የያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የታላቅ የታሪክ ሁነቶች የሳለ፣ የፈተሸና የመዘነ፣ የፊውዳሉን ሥርዓት ግስንግስ፣ የውጭ ወራሪዎችን ጡጫና የአገር ውስጥ መናጨትን ሁሉ፣ ከቤተሰቡና ከራሱ ሕይወት ጋር አዛምዶ አሳይቶናል፡፡ እኛ ‹‹አብዮት›› ስንል የኖርነውን፣ ‹‹አብዮት›› አይደለም ብሎ ከማሳመኛ ሀሳቡ ጋር ከመቋጨቱ በፊት፣ የግብታዊውን ለውጥ እንቅስቃሴ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ምን መልክ እንዳለው ከታሪክ ድርሳናት ጋር እያስተያየ አስነብቧል፡። የፊውዳሉን ሥርዓት ለመገርሰስ የተፋለሙ፣ የታገሉና የወደቁ፣ ከዚያም በኋላ፣ የወታደሩ ቡድን የነጠቀውን ለውጥ ላለማጣት፣ በፈተና ሲያልፉ አሳይቶን ተደምመናል፡፡
የመኢሶን፣ የኢሕአፓና የደርግ መፋጠጥ፣ በተለይ ደርጉ ቃሉን እንኳን የማያውቀውን አብዮት እራሱ እንዳመጣው፣ የማርክስና የሌኒንን ጡጦ ለራሱ ሳይጠባ፣ ለህዝቡ እንዳጎረሰ፣ መኢሶን የነቃ፣ የተደራጀና የታጠቀ ሕዝብ ስለሚያስፈልግ ከደርግ ጋር እግር ሳይለካኩ አብዮቱን ኮምጠጥ እስከሚሉ ‹‹ወፌ ቆመች›› ማለት ሲመኝ፣ ኢሕአፓ “ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም!›› ሲል ባለመደማመጣቸው፣ ምክንያት አንድ ሙሉ ትውልድ መባኩን አይተናል፡፡ ይህ አለመደማመጥ ከዚህም በፊት የኢትዮጵያውያን የኪሳራ ልማድ ነው፡፡ አፄ ሀይለ ስላሴ፣ የተክለ ሃዋርያት ተክለማርያምን ምክር ሰምተው ቢዘጋጁ፣ የማይጨው ጦርነት በሽንፈት አይደመደምም፡፡ የሌተናል ጀኔራል ከበደን ገብሬን ማሳሰቢያ በጊዜ ውል ቢያስይዙ በኤርትራ ያ ሁሉ ሰው አያልቅም ነበር። ምናልባት አፄ ምኒልክ የተሻለ ሰክነት ስለነበራቸው ራስ መኮንንን አዳምጠውና ተግብረው፣ የአድዋ ድል፣ የሥልጣኔም ብርሃን ይደምቅ ዘንድ አግዟል፡፡ ወያኔም ሁለት ጆሮዎቹን በጠጠር ደፍኖ፣ ይኸው ዛሬ ለኛም ለእርሱም መከራ ወዝፏል።
የመሳፍንቱ ሰፈርና ደርጉ
መጽሐፉ በተለይ ህሊናዊ ሁኔታ (Subjective Conditions) ባልጎመራበት፣ ደርግ ተምታቶበት ሳለ፣ የቀደመው የመሳፍንቱና የሲቪል ቢሮክራሲው ሰንሰለት ለመበጠስ፣ ሁለቱም መዳኛ ተስኗቸው እንደነበር ያሳየናል፡፡ የመሳፍንቱና የእነ አክኪሉ ሀብተወልድ ጉዳይ እንደጠበቁት አልሆነም ነበር:: የመሳፍንቱ ጉዳይ ከእነ አክሊሉ የባሰ ነበር፡፡ በሲቪል ቢሮክራሲውም ሆነ በወታደራዊው እዝ ውስጥ የሚያግዛቸው የለም፡፡ ወታደሩ ማመጽ ሲጀምር ንጉሱ መሄጃ አልነበራቸውም፡፡ አመፁ የተራው ወታደርና የዝቅተኛው መኮንኖች በመሆኑ ለአክሊሉ ሀብተወልድ መንግስት ትልቅ ችግር ፈጠረ፡፡ እነዚህን አመፀኞች እንደ ጄኔራሎቹ በቀላሉ ሊያገኟቸው፣ ሊያናግሯቸውና ሊያሳምኗቸው፣ ‹‹ለጋራ ጥቅም በጋራ አብረን እንስራ›› ሊሏቸው አይችሉም፡፡ የመሳፍንቱ ልጆች፣ ወታደሩ መብላት የፈለገው እነ አክሊሉን እንጂ ንጉሱን እንዳልሆነ ሰምተው ተደሰቱ:: መጽሐፉ እንደሚነግረን፤ የ1966ቱ አብዮት ሊፈነዳ ሲል፣ ሕዝቡ በድህነትና በኑሮ ውድነት ተጠፍንጎ  ሳለ፣ ልዑላኑ ከፈረንሳይ አሰርተው ያመጡት ኬክ ተሰንጥቆ፣ ለጥገና ብቻ በጊዜው 10 ሺ ብር አውጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ደርግ ሁለቱንም ወገን በልቶ ካገሳ በኋላ ለሌላ ተረኛ ሆዱን አስፍቶ ታሪክ የማይረሳው ስህተት ፈጸመ፡፡ ምናልባትም የአገሪቱ ብስል ፍሬዎችን በማርገፍ፣ የአገሪቱን የስልጣኔ ጉዞ አጨናገፈ፡፡ ‹‹ትውልድ አይደናገር እኛው እንናገር›› እና ሌሎችም በኢህአፓ፣ በመኢሶንና በደርግ ጀኔራሎች መጽሐፍት ላይ የተጠቀሱ ታላላቅ ሰዎችን መቀጨትንም አስከተለ፡፡
ደርጉ፣ ኢሕአፓና መኢሶን
አንዳርጋቸው እንደሚለን፤ደርግ ያኔ የነበረውን የለውጥ እሳት እንደ ብርሃን ወጋገን ተጠቅሞበት ቢሆን ኖሮ፣ የዘመናት ጨለማ ተወግዶ፣ ትውልድ ለዕድገትና ብልጽግና የነበረን ዕድል የትየለሌ ነበር፡፡ ይሁንና እሳቱን ሌሎችን ለማንደድና ታሪክን ዓመድ ሥር ለማርመጥመጥ በመትጋቱ፣ አገሪቱ ቁልቁል ተሽንቀጥራ ዛሬ ላለንበት የዘረኝነት መዘዝ በቅታለች:: ገጽ 494 እንዲህ ይላል፡-
ትልልቆቹ ህብረብሄራዊ ድርጅቶች በደርግ ባይመቱ፣ እነሱ መንቀሳቀስ የሚችሉበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ በአገር ውስጥ ቢኖር፣ ደርግ ስልጣን ይዞ ወደ አፈና ሲንደርደር፣ ወደ በረሃ መግባት የጀመሩት የህወኃት መሪዎች ሃሳባቸውን በቀየሩ ነበር፡፡ በትግራይ ውስጥም አድማጭ  ባላገኙም ነበር፡፡ የብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል የሚለውን መርህ፣ የኢትዮጵያ ምሁራንና ተማሪዎች በተቀበሉበት ወቅት፣ የብሔረሰቦች ቅራኔ ዋናው የማህበረሰባችን ቅራኔ ነው በማለት አልነበረም፡፡ የሃገሪቱ ጭቁን ህዝቦች በጋራ ታግለው  በሚፈጥሩት አገር ውስጥ ይህ መርህ ይከበራል አሉ እንጂ፡፡
 የታሪኩ ደማቅ ሥዕሎች
መጽሐፉ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ፈጣን የታሪክ ፍሰት ያላቸው፣ ገላጭና ምስል ከሳች ትዕይንቶች ካየሁባቸው ቦታዎች አንዱ ለንደን ‹‹የወሊች›› አካባቢ፣ ኮሌጅና የክለቡ ውስጥ አዛውንቶች የቢራና የሙዚቃ፣ ደግሞም የሕይወት ትርምስ፣ በኋላ ደግሞ የኢሕአፓ የትግል ሕይወትና የፍልሚያ ቀለሞች!... ጥልፍልፍ ትልም ያስታውሰኛል፡፡ ሻምበል አምሃ፣ ሻለቃ ባሻ ወልደመድህን የተሳተፉበት ፍልሚያ፤ ፊልምም ህልምም ይመስላል፡፡ አንዳርጋቸው፤ እንደ ዕጣን ጢስ እሳቱ ላይ ተጥዶ እየተነነ የሚያወጣው አንዳች ተዓርም ይገርማል፡፡
አዲሱ ፖስታ ቤት ጀርባ ‹‹ዳሽን›› የሚባል ምግብ ቤት፣ መኪና ውስጥ ተቀምጠው ቢራ ሲጠጡ፣ የተፈጠረው ግጭት፣ የወረደው መዓት ጉድ ነው:: ሾፌሩ አንዳርጋቸው፤ ያላመላለሰው የኢሕአፓ ባለሥልጣን፣ ያልጫነው መሳሪያ የለም፡፡ የቁጭራ ባንኩን ረብጣ ብር ጨምሮ፡፡ ገጽ 537 ላይ አንዳርጋቸው ይተርከዋል፡-
እግሬ ከመኪና ውስጥ ገና መሬት አልነካም:: ምድርና ሰማይ በተኩስ ተናወጠ፡፡ መኪና ውስጥ ሲገባ ባዶ እጁን የመሰለኝ ከኋላ ተቀምጦ የነበረው ወጣት፣ እንደ አስማተኛ ከየት እንደመዘዘው የማላውቀውን ታጣፊ ክላሽ፣ መኪናዋ ጣራ ላይ አስደግፎ ይተኩሳል፡፡ --
እዚህ ጋ ምግብ ያልቀመሰው የአንዳርጋቸው ምጥ፣ የልብ ሰቃይ ልቦለዶችን ያህል ያስምጠናል። እያንዳንዱ ትዕይንት፣ እያንዳንዱ ዕርምጃ፣ እንባና ደም ቀይጦ እንደ መረብ ኳስ ይሰርበናል፡፡ ይጠልዘናል!
መጽሐፉ ከገጽ 534-569 ድረስ ያለውን ታሪክ ‹‹የሱፍ አበባ›› በሚለው በኢህአፓ ትግል ዙሪያ ከሚያጠነጥነው መጽሐፍ ጋር በትረካ ፍጥነታቸውና ስዕላቸው ይመሳሰላሉ፡፡ ቢታንያ፣ ኢሳይያስ፣ ሸዋዬና ሌሎቹም ፍቅራቸውና ጽናታቸው ትዝ ይለናል:: ‹‹ለካ መሲሁ ነበር›› በሚለው ንዑስ ርእስ ሥር፣ ስለ ዶክተር ተስፋዬ ደበሳይ የቀረበው ታሪክ በእጅጉ ይመስጣል፡፡ ይታያል፣ ይዳሰሳል፤ ልብ ይነጥቃል፤ ይሰቅቃል!... የተስፋዬን ህይወት በየትኞቹም መጻሕፍት ካነበብኩት ይልቅ አንዳርጋቸው ሙሉ ሥዕሉን አሳይቶኛል፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው፡። የእግር እሳት ሆኖ ይብስ አንገበገበኝ!  ዕድላችን ሆኖ ታሪካችንን ባነበብን ቁጥር የሚተርፈን መንደድ ነው፤ መቃጠል ብቻ!!
አንዳርጋቸው፤ ደርግ ‹‹አብዮት›› ብሎ ሰውን እንደ ጧፍ ያቃጠለበትን ችቦ በመውቀስ ብቻ አያበቃም፡፡ ይልቅስ ነገሩ ካለፈ በኋላ፣ ወደ ሌላ የታሪኩ ምዕራፍ ተሻግረን ሁላችንም ሜዳውን ከለቀቅን በኋላ ‹‹ተሳስቻለሁ›› ማለት ማንን ገደለ? የሚል ቁጭት የሚያንጸባርቅ  ይመስላል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
ወታደሩንና ሁሉንም አብዮታዊ ሀይሎች ያካተተ የብሄራዊ አንድነት አብዮታዊ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት የማቆሙን የኢህአፓን አማራጭ ወደ ጎን ገፍተው፣ ስልጣን ለብቻቸው በሞኖፖል ለመያዝ የወሰኑት ኮሎኔል መንግስቱና ተባባሪዎቻቸው፣ ማህበረሰቡን አስከፊ ግፍጫ ውስጥ መክተታቸውን ማመን አለባቸው፡። ከዚህ ውጭ የጭካኔያቸው ሰለባ ብቻ ስለሆንኩ፣ ‹ከነሱ የተሻለ የሞራል ሰብዕና ነበረኝ›› ብዬ አልመጻደቅም፡፡ የሁላችንም የአብዮት ጡጦ የተሞላው ‹‹በሰው ልጆች ሕይወት ክቡርነት›› ወተት አልነበረም፡፡ ‹‹አብዮት የራት ግብዣ አይደለም›› በሚለው የሬት ጠጅ ነበር::›› ይልና ‹‹ሰዎች ታሪክን ይሰራሉ ግን እንዳሻቸው አይሰሩትም፡፡›› በሚለው የማርክስ አባባል ደርዝ ያስይዘዋል፡፡
አንዳርጋቸው ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡- ‹‹መንግስቱ ሀይለማርያም፣ ሃይሌ ፊዳ፣ መኢሶን፣ ሰደድ፣ የውድቀታችን ሰበቦች እንጂ ምክንያቶች አልነበሩም።”
የአንዳርጋቸው ሥነ ልቡናና ሚዛናዊነት
እንደ አንባቢ፣ የደራሲውን የሕይወት ውጣ ውረድ የሚያውቅ ሰው፣ የዚህ ዓይነት ለስላሳ፣ ድምፀት፣ የሰከነ አተያይና ምዘና ይኖረዋል ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡ እንደ መብረቅ ብልጭ የሚል ስሜት፣ ደም የተነከረ ዘንባባ፣ ሳቅ የሸሸው ቋንጣ አረፍተ ነገርና አንቀጽ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ እንደተረጋጋ ወንዝ፣ ብዙ ገጠመኝ አዝሎ፣ ከንባብ የተገኙ አዳዲስ ጉዳዮች መንዝሮ፣ በአርምሞ ያወራናል፡፡ ታሪኩን ከዳር እስከ ዳር ስናነበው፣ ጥላቻና ቂም፣ ምሬትና ዋይታ አይታይበትም፡። ይልቅስ የሰከነ መዝሙር ይመስል ልብን የሚሰረስሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ምናልባት ለክስ የማይበቁ እጅግ ጥቂት ቦታዎች ላይ የሌላ ወገን ጸሐፍት ዋሾነት ሲያስመርረው እናያለን፡፡ ይህ ደግሞ ከሚያቀርባቸው መረጃዎች ጋር ሲተያይ፣ የሳቅና የቀልድ ያህል የምናስበው ነው፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይ በግርጌ ማስታወሻዎቹ ላይ የላቀ ብቃት የታየበት፣ የሻምበል ፍቅረ ስላሴን ‹‹እኛና አብዮቱ›› የተሰኘ መጽሐፍ በተመለከተ ያቀረበው ነው፡፡ የሻምበሉ መጽሐፍ ደግሞ እርሱን ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻችን ወሽመጥ የበጠሰና ያዘንበት ነው፡፡ ከደርጉ ባለሥልጣናት መካከል የተሻለ ግምት የሰጠናቸውን ያህል ሆነው ባለመገኘታቸው አዝነናል፡፡
ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ‹‹እኛና አብዮቱ›› በሚል መጽሐፋቸው፣ የኤርትራን ጉዳይ በሚመለከት፣ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት መቋቋምን አስመልክቶ፣ ተማሪው መካተቱን በመንቀፍ፣ ወታደሩ ከህዝቡ ጎን ባይቆም፣ የለውጡ መጨንገፍና ሌሎች ብዙ ጉዳዮች ላይ ጽፈዋል፡፡ አንዳርጋቸውም ያንገሸገሸው ባብዛኛው የደርግን ሀጢአት መሸፈኛ ሙግት እንጂ ለትውልድ ሊተላለፍ የሚገባ ንጹህ እውነት አይደለም የሚለው ነው፡። ‹‹ሻምበል ፍቅረ ስላሴ መጽሐፉን የጻፈው የደርግን ታሪክ ለማስተላለፍ ነው ወይንስ ከኢሕአፓ ጋር ያላለቀ ትግል ለማድረግ? የሚል ጥርጣሬ እስኪሰማኝ ድረስ ብዙ ነገሮችን አጣምሞ ጽፏል፡፡›› በማለት ዝርዝሩን ያወጋናል፡፡ (ገጽ 377-378)  ይሁንና በሚዛናዊነት የሚስማማባቸው ነገሮችም አሉት፡፡ ለምሳሌ ገጽ 378 ላይ እንዲህ ሰፍሯል፡- ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ (ገጽ 49 ላይ) ወታደሩ ከሕዝቡ ጎን ባይቆም፣ ሕዝብ ምንም ማድረግ አይችልም በማለት የጻፈው ትክክለኛ ነጥብ ነው›› ይላል፡። የማይስማማው ግን ‹‹የተሻለ ሥርዓት ተክቶ የሕዝብን መብት ማስጠበቅ›› በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ደርግ የሕዝብን መብት መጠበቅ ያልቻለ፣ የሕዝቡን ጥያቄዎች ሁሉ በጠመንጃ ለመመለስ የሞከረ አምባገነን  ነው ባይ ነው፡፡ ሌላው የጸሐፊው ሙግት ‹‹እኛና  አብዮቱ›› የሚለው መጽሐፍ፤ በተደጋጋሚ የደርጉን አብዮተኛነት ለመግለጽ፤ ‹‹ወታደሩ ከአርሶ አደሩና ከጭቁኑ ማህበረሰብ የወጣ በመሆኑ›› በማለት ራሱን ለመለጠፍ የሞከረበትን መንገድ መቃወም ነው፡፡ ይልቅስ በኢህአፓ ውስጥ የነበሩ ተማሪዎችን “ለሥልጣን አይበቁም” በሚል ፍቅረስላሴ ላቀረቡት  ሽሙጥ ተመጣጣኝ ምናልባትም የመረረ መልስ ሰጥቷል፡-
‹‹በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበሩትን የቀድሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር ተመራጮች እነ ጌታቸው ማሩ፣ እነ ግርማቸው ለማ፣ እነ መለስ ተክሌ፣ እኔ ጌታቸው በጋሻው---የአንዳንዶቹ ጭንቅላት ብቻ በትንሹ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የደርግ አባላትን  ጭንቅላቶች አንድ ላይ ቢጨመቁ ማቅረብ የማይችሉት የፖለቲካና የህግ፣ የአስተዳደር ሀሳብ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ደርግ ውስጥ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ተራ ወታደሮችና የእስር አለቃዎች መኖራቸውንም ይነግረናል፡፡ በኢሕአፓ ታሪክ ውስጥ የቦታ፣ የጊዜና የሁነቶች መዛነፍን በተመለከተ የ‹‹ያ ትውልድ›› ደራሲ ክፍሉ ታደሰ፣ ማስተካከልና ማረም ያለበትን ችግሮች በጥንቃቄ ጠቁሞታል፡፡ በተረፈ መኢሶን ያግበሰበሳቸውን የአብዮት ጥበቃና መሰል ሰነፍ ሰዎች አካሄድ፣ “የማይመጥነው ቦታ ተገኝቷል” ሲል ነው የገለጸው፡፡  
ሌላው ገራሚ ነገር አንዳርጋቸው፤ ስለ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያቀረበበት መንገድ ነው፡፡ ጸሃፊው ስለ መለስ ዜናዊ ሲያቀርብ አዳልጦት እንኳ ያለ መዝለፉ፣ በተረጋጋ መንፈስና ስሜት መጻፉ ስክነቱንና ብስለቱን ይመሰክራል፡። ለምሳሌ ገጽ 347 ላይ እንዴት እንደተዋወቁ ሲነግረን፡-
እኔና መለስ አብዮቱ ፈንድቶ እስከምንለያይ ድረስ ተማሪውን ገንዘብ እየበላን ያስመረርንበት የቁማር ሽርክና የተጀመረው በ1965ቱ የገና እረፍት ነበር:: ከቁማርም ያለፈ መቀራረብ የቻልነው ከቁማር በጀመርነው ግንኙነታችን ነው›› ይላል፡፡ አንዳርጋቸው ይህን ብቻ ብሎ ቢያበቃ ግድ የለም፤ መለስ ዜናዊ ጎበዝ ተማሪ እንደነበር ሳይደብቅ ይመሰክራል፡። የዚህ ዓይነቱ ቀናዒነት፣ ለኢትዮጵያውያን ስነ ልቡና ሩቅና ተራራ የመውጣት ያህል ነው፡፡ እንዲህ አስፍቶታል፡-
‹‹መለስ ቁማር የሚጫወተው አፄ ሀይለ ስላሴ በየወሩ በሚከፍሉት መቶ ብር ነው፡፡ ክፍያው ለእሱና ለሌሎች ዘጠኝ የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት መልቀቂያ ፈተናን በከፍተኛ ውጤት ላለፉት ተማሪዎች የሚሰጥ የአፄ ኃይለስላሴ ‹‹የግላቸው” ሽልማት ነበር፡፡”
እዚህ የኃይለ ስላሴ ሽልማት ውስጥ አንዳርጋቸው ቢኖር የራሱንም ጉብዝና ሊነግረን ነው ብለን በተለመደ ጠማማነትና ጠርጣራነታችን ምስጋና እንነሳው ነበር፡፡ እርሱ ግን ይባስ ብሎ “እኔ የማገኘው አባዬ ጥሩነሽ ካወረሱኝ የምንጃር መሬት ነው›› ይለናል፡። አንዳርጋቸው ሲበዛ ቀና ነው፡።
መደምደሚያ
መጽሐፉ ዳጎስ ያለ ከመሆኑ አንጻር በወፍ በረር ከመቃኘት በቀር ሁሉንም ዘልዝሎ ማንጠልጠል አይቻልም፡፡ በዚያ ላይ ውስን በሆኑት የጋዜጣ ገጾች፣ በአጣዳፊው የሕይወትና የኑሮ ሁኔታ ዘልቆ ውቅያኖስ ውስጥ ያሉትን አሳና እንቁራሪቶች፣ ጉማሬና አልቅቶች መፈተን አዳጋች ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ የዘለቀውን ዝንጉርጉር የታሪክ ገጽታና ጥምልምል ርምጃ በቀላሉ መፈክርና መተንተን አይቻልም፡፡ እንደ መደምደሚያ መጽሐፉ ውስጥ ባይኖሩ፣ ቢስተካከሉ ያልኳቸውን ነገሮች አለፍ አለፍ ብዬ እጠቁማለሁ፡፡
በዋነኛነት በብዙዎቻችን ዘንድ የተለመደው (Common mistake) የስም አረባብ ችግሮች  አስተውያለሁ፡፡ ለምሳሌ መኳንንት /መኳንንቶችች፣ መሳፍንት/ መሳፍንቶች፣ ቀደምት/ ቀደምቶች፣ ወራት/ ወራቶች፣ ጠበብት/ ጠበብቶች፣ መጻሕፍት/መጻሕፍቶች ወዘተ-- በሚል ተጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ “መሳፍንት” በራሱ የብዙ ቁጥር በመሆኑ “መሳፍንቶች” አይባልም፡፡ የዚህ ዓይነት ችግሮች የብዙ የአገራችን ጸሐፍትና ደራስያን ችግር ቢሆንም በተለይ አንዳርጋቸውን አይመጥነውም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆነው ግድፈት በ‹‹ጋር›› እና በ‹‹ጋ›› መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡ ይህም በምን ምክንያት እንደሆነ ባይታወቅም እየተለመደ የመጣ ትርጉም የሚያዛባ አካሄድ ነው፡፡ ‹‹አንተ ጋ እመጣለሁ” ማለት እና ‹‹ካንተ ጋር›› ማለት በጣም ይለያያል፡፡ በተመሳሳይ “ከዚያ በኋላ” እንጂ ‹‹ከዛ በኋላ›› ማለት ትክክል አይደለም፡፡ በተለይ አንዳንድ ቦታ ‹‹በዛ›› የሚለውን ስንጠቀም የትርጉም ለውጥ ያስከትላልና የዘመኑ ፀሐፍትና ደራስያን  ልንጠነቀቅ ይገባል። ይህ ደግሞ ባብዛኛው በአርትኦት የሚሳተፉትን ባለሙያዎች ይመለከታል፡።
ውበትን በተመለከተ መጽሐፉ እጅግ ውብ በሆነ ቋንቋና ገለጻ የተሽሞነሞነና አንዳንዴም እንደ ግጥም የሚጥም ቀለማዊ ነው፡፡ ይሁንና በጣት የሚቆጠሩ ገጾች ላይ በቀላሉ ሊታረሙ የሚችሉ ውበትን የሚቀንሱ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ገጽ 49 ላይ ብቻ ሁለት አንቀጾች ላይ አራት ጊዜ ያህል ‹‹ችያለሁ›› የሚሉ፣ ሁለት ቦታ ደግሞ ‹‹እድል አግኝቻለሁ››:: በሚሉ ማሰሪያዎች ተደርቷል፡፡ ገጽ 76 ላይም ተመሳሳይ ችግር ስላለ ቢያንስ በድጋሚ ሲታተም እርማት ቢደረግበት መልካም ነው፡፡  
በአጠቃላይ መጽሐፉ ውበት፣ እውነት፣ የተዋጣና መንስዔና ውጤት የያዘ፣ በተሞክሮና በንባብ የጠና ስለሆነ ለማንበብ የሚቀልልና ልብ የሚያንጠለጥል ነው፡፡ በዚያ ላይ እስካሁን ያልተነገሩ ታሪኮች ስላሉት ለአንባቢ የሚሰጠው እርካታ የትየለሌ ነው፡፡ በታሪኩ አካሄድ ላይ ትንሽ እርግበት ፈጥሯል የምለው፤ በልጅነት ጉዳይ ላይ የተጻፉት ሃሳቦችና ይበልጡኑ ደግሞ የእስር ቤት ትዝታዎቹ፣ ታሪኩን እንዳያረግቡት ትንሽ ወጠር ቢደረግ መልካም ይመስለኛል፡፡ በተለይ የእስር ቤቱ ትረካ የደራሲ ሕይወትን ‹‹ማማ በሰማይ›› የተሰኘ መጽሐፍ ሰቀላ ዝቅ እንዳደረገው ሁሉ በአንዳርጋቸው መጽሐፍም ላይ መሰላቸት እንዳይፈጥር ስጋቴ ነው፡፡ ምናልባት የአስካለች ነጋ ታሪክ፣ በታሪኩ ውስጥ በግድ ‹‹ይግባ›› የሚያሰኝ ባይሆንም፣ አንድ ቦታ የምዕራፍ መጀመሪያ መደረጉ ግን የሚያምታታ ነገር ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ በኢህአፓ ታሪክ፣ የሴቶችን ፅኑ አቋምና ዓላማ ለማሳየት ጠቃሚ መሆኑ አልስተውም፡፡  
አንዳርጋቸው፤ እንደ ሩሲያዊው ደራሲ ፌዮዶር ዶስትየቭስኪ፣ ከሞት ያመለጠና ለተሻለ ሥራ የተፈጠረ ሰው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንኳንም አልሞተ!! ፊታውራሪ ተክለሃዋርያትን ፈረንጅ እናታቸው፤ ‹‹የገዛ ወገኖችህ ያስቸግሩሀል›› እንዳለችው ቢሆንበትም፣ ዛሬ ግን ሌላ ቀን ነው:: እንኳን ዕድሜ አገኘ! የሚያሰኝ ግሩም መጽሐፍ ጽፎልናል፡፡ መቃብር ውስጥ ገብተው ታሪካቸው አመድ የለበሰን ፍም ወጣቶች፣ እንደገና ወደ ታሪክ አደባባይ አውጥቷቸዋል! አንዳርጋቸው፤ ሌሎች ብዙ ታሪኮችን እንዲጽፍልን፣ የሚጣፍጡ መጻህፍትም እንዲያበረክትልን ---- ፈጣሪ ዕድሜ ይስጠው!!     

Read 1708 times