Saturday, 20 July 2019 12:17

“ጭራቅ”

Written by  ደራሲ ፦ ማርጋሬት አትዉድ ውርስ ትርጉም ፦ ሃዊ
Rate this item
(1 Vote)

 ምን ማድረግ ይቻላል? ምንስ ሊደረግልኝ ይችላል? እነዚህ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ናቸው:: መደረግ የሚችሉት አማራጮች ውስን ናቸው፡፡ አማራጮቹን ቤተሰቡ አንድ በአንድ ተወያየባቸው:: ማለቂያ በሌለው ድግግሞሽ፣ በሀዘን ተጨብጠው፣ በማድ ቤት ጠረጴዛው ዙሪያ ተሰብስበው፣ መጋረጃው ተዘግቶ፣ በምሽት ደረቅ ሶሴጃቸውን በድንች ሾርባ እየተመገቡ ተወያዩባቸው፡፡
‹ፈካ› ባለው የለውጥ ሂደቴ ወቅት በምሆንበት ጊዜ እኔም አብሬያቸው በውይይታቸው ውስጥ እካፈላለሁኝ፡፡ አብሬያቸው እቀመጣለሁ፡፡ በውይይቱ መሃል የተቻለኝን ያህል ጣልቃ እየገባሁ ንግግር ለማድረግ እሞክራለሁ፤ በጎድጓዳ ሳህን በተሰጠኝ ሾርባ ውስጥ ያለውን ድንች ለማግኘት እያማሰልኩ፡፡
ጸለምተኛ በሆነው ሂደቴ ላይ ከሆንኩ ደሞ፣ በጣም ጨለማ በሚባለው የቤቱ ጥግ ተወሽቄ፣ በራሴ ለውጥ ውስጥ እዋጣለሁ፡፡ የቤተሰቡ አባላት ማንም በማይሰማው ድምጽ የሚያንሾካሽኩትን እኔ ባለሁበት ሆኜ እሰማለሁ፡፡
“እንዴት የምታምር ልጅ እኮ ነበረች” ትላለች እናቴ፡፡ “ምንም ችግር ያልነበረባት ህጻን ነበረች” … እንደ’ኔ አይነት ፍጥረት በመውለዷ ሀዘን ገብቷታል:: እንደ ጸጸት አይነት ራስን የመውቀስ ስሜት ያዘለ ንግግር ነው፡፡ ግን እሷ ምን ያጠፋችው ጥፋት አለ?
“ምናልባት እርግማን ይሆናል” አለች ሴት አያቴ፡፡ እንደምትመገበው ሶሴጅ ደረቅና የምትኮሰኩስ ናት፡፡ በእሷ እድሜ እንደዛ መሆኗ የሚጠበቅ ነው፡፡
“ለብዙ አመታት እኮ ደህና ነበረች” አለ አባቴ፡፡ “በሰባት አመቷ ያ ኩፍኝ ከያዛት በኋላ ነው… እንጂ”
“ማን እሷን የመርገም ፍላጎት አለው?” አለች እናቴ፡፡
ሴት አያቴ ተኮሳተረች፡፡ እኔን ለመርገም ብቃት አላቸው የምትላቸው ረዘም ያለ የተጠርጣሪዎች ዝርዘር አላት፡፡ ግን ቢሆንም ከዝርዝሩ ውስጥ አንድ ነጥላ ማውጣት አልቻለችም፡፡ አነሰም በዛ፣ የእኛ ቤተሰብ የተወደደ ብቻ ሳይሆን የተከበረም ጭምር ነበረ፡፡ አሁንም ድረስ ነው፡፡ በተለይ በእኔ ጉዳይ አንዳች መፍትሄ ማዋለድ ከቻለ፣ ወደፊትም የተከበረ ሆኖ ይቀጥላል፤ ግን ወሬ ከመዛመቱ በፊት መሆን አለበት፡፡
“ዶክተሩ በሽታ ነው እያለ ነው” አለ አባቴ፡፡ ‘ምክኒያታዊ ነኝ’ ብሎ ስለ ራሱ ማሰብ ይቀናዋል:: ጋዜጣውን አነሳ፡፡ እሱ ነው ማንበብ እንድማር የገፋፋኝ፡፡ በሁሉም ችግር ወስጥ--- አሁንም ድረስ--- ማበረታታቱን አላቆመም፡፡ ሆኖም፣ አሁን እንደ ድሮው ግዜ በእሱ እቅፍ ውስጥ አልጋደምም፡፡ አባቴ አሁን ከጠረጴዛው ባሻገር ነው የሚቀመጠው:: በአስገዳጅ ሁኔታ ምክኒያት በመሃላችን የመጣው ርቀት ቢያመኝም እውነታው ግን ይታየኛል፡፡
“ታዲያ መድኃኒት ለምን አልሰጠንም?” አለች እናቴ፡፡ ሴት አያቴ በአፍንጫዋ ተንፍሳ አላገጠች፡፡ እሷ የራሷ መፍትሄ የምትላቸው እምነቶች አሏት፣ የራሷ ጠበሎችና የመጋኛ መድኃኒቶች፡፡
ልብስ የታጠበበት ቆሻሻ ውኃ ስር ጭንቅላቴን ደፍቃ ይዛኝ ታውቃለች፡፡ ደፍቃ እንደያዘችኝ ትጸልይ ነበር፡፡ እጣቢ ውኃው በአፌ ገብቶ ወደ ደረት አጥንቴ አካባቢ የተቀመጠውን ሰይጣን አባሮ እንዲያስወጣላት ነው እቅዷ፡፡ “በጎ አስባ ነው” ትላለች፤ እናቴ ስለ አያቴ፡፡
“ዳቦ መግቧት” አለ ዶክተሩ፡፡  “ብዙ ዳቦ መጠየቋ አይቀርም፡፡ ዳቦና ድንች፡፡ ደም መጠጣትም ትፈልጋለች፡፡ የዶሮ ደም ወይም የከብት ደም ስጧት:: ግን ከመጠን በላይ እንድትጠጣ አትፍቀዱላት፡፡”
የበሽታውን ስም ነገረን፡፡ “P” እና “R” ፊደል ያለበት ቃል ነው፡፡ ለእኛ ምንም ትርጉም አልሰጠንም፡፡ ዶክተሩ እንደዚህ አይነት በሽታ ከእኔ በፊት ገጥሞት የሚያቀው አንዴ ብቻ ነው፡፡
ቢጫ አይኖቼን፣ ሮዝ ጥርሶቼንና ቀያይ ጥፍሮቼን አገላብጦ  እያስተዋለ … እንዲሁም ደረቴና እጆቼ ላይ እየበቀሉ ያሉትን ፀጉሮች እየመረመረ ሳለ ነው፦ እንደኔ አይነት በሽታ ከዚህ ቀደም አንዴ ብቻ ስለማየቱ የተናገረው፡፡ ወደ ከተማ አብሬው እንድመጣና ሌሎቹ ዶክተሮች እንዲመለከቱኝ ፈልጎ ነበረ፤ግን ቤተሰቦቼ አልተስማሙም፡፡
“Lusus Naturae ናት” አላቸው፡፡
«ምን ማለት ነው?» ብላ ጠየቀችው ሴት አያቴ፡፡
“Freak of Nature” አላት ዶክተሩ፡፡
ከሩቅ ቦታ የመጣ ዶክተር ነው፡፡ አስጠርተን ነው ያመጣነው፡፡ የእኛን ቤተሰብ ከዚህ ቀደም ያክም የነበረው ዶክተር፤ ሃሜት ያሰራጭብናል በሚል አላማከርነውም፡፡
“የላቲን ቃል ነው፤ ‘ጭራቅ’ እንደማለት ነው” አለ ዶክተሩ፡፡ የምሰማው አልመሰለውም፡፡ ምክኒያቱም… እነሱ ከሚወያዩበት ርቄ ስርቻ ውስጥ ስለተወሸቅሁ::
“የማንም ጥፋት አይደለም” አለ ዶክተሩ፡፡
“የሰው ልጅ ናት” አለ አባቴ፡፡ ለዶክተሩ ብዙ ገንዘብ ከፍሎ እንዲሄድ አደረገው፡፡ ወደመጣበት ሀገር ተመልሶ እንዲሄድና በድጋሚ እንዳይመጣ፡፡
“እግዚአብሔር ለምን በእኛ ላይ ይሄንን አደረገ ?” አለች እናቴ፡፡
“እርግማንም ሆነ በሽታ ምንም ዋጋ የለውም ” አለች ታላቅ እህቴ፡፡ “ እርግማንም ሆነ በሽታ፣ ሰው ስለሷ ከሰማ ማንም እኔን ማግባት አይፈልግም ”
እኔ ‘ትክክል’ ብዬ ጭንቅላቴን በመስማማት ነቀነቅሁኝ፡፡ እህቴ በጣም የምታምር ልጃገረድ ናት:: ደግሞ ቤተሰባችን ደሃ የሚባል አይነት አይደለም:: እንዲያውም ሞጃ ነን፡፡ እኔ ጋሬጣ ባልሆንባት የህይወቷ መንገድ የተስተካከለ ይሆን ነበር፡፡
ቀን-ቀን ጨለማ በሆነው ክፍሌ ውስጥ ተዘግቼ እውላለሁኝ፡፡ ይሄ በእኔ በኩል ችግር የለውም፡፡ ምክኒያቱም፣ የፀሀይ ብርሃንን መቋቋም አልችልም:: ማታ ደግሞ እንቅልፍ የለኝም፡፡ ቤቱ ውስጥ ስንጎራደድ አድራለሁኝ፤ የሌሎቹን የቅዠት ድምፅና ኩርፊያ እያደመጥኩኝ፡፡ ድመቱ አብሮኝ ይሆናል፡፡ ከእኔ ጋር መሆን የሚፈልግ ፍጥረት እሱ ብቻ ነው:: ሁለመናዬ ደም-ደም ነው የሚሸተው፡፡ የከረመ ደረቅ ደም፡፡ ምናልባት ድመቱ እንደ ጥላ የሚከተለኝ በደሙ ሽታ ምክኒያት ሊሆን ይችላል፡፡ እላዬ ላይ ይወጣና መላስ ይጀምራል፡፡
ለጎረቤቶቻችን አንዳች ገዳይ በሽታ እንደያዘኝ ነግረዋቸዋል፤ ትኩሳትና ቅዠት ውስጥ መውደቄን:: ጎረቤቶቻችን ሊጠይቁኝ አልፎ አልፎ ይከሰታሉ፡፡ እንቁላልና ጥቅል ጎመን ይዘው ይመጣሉ፡፡ በእውነቱ ግን፣ ወሬ ሊቃርሙ ነው የሚመጡት፡፡ ቢመጡም እኔን ለማየት ያን ያህል ፍላጎት የላቸውም፡፡ የያዘኝ በሽታ ምን እንደሆነ ባያውቁም እንዲጋባባቸው ግን አይፈልጉም፡፡
በኋላ ላይ፣ መሞት እንዳለብኝ ቤተሰቡ ተስማማ:: እንደሞትኩ ከተነገረ፣ እህቴና የወደፊት የትዳር ህይወቷ ላይ ጣልቃ አልገባም፡፡ እንደ መጥፎ እጣ ፈንታ በእሷ መፃዒ ህይወት ላይ አላንዣብብባትም፡፡
“አንዳቸው ደስተኛ ቢሆኑ ይሻላል፤ ሁለቱም ኃዘንተኛ ሆነው ከሚቀሩ” አለች ሴት አያቴ፡፡ ሴት አያቴ የተጎነጎነ የነጭ ሽንኩርት አንኳሮች በክፍሌ በር ላይ የማንጠልጠል ባህሪ አምጥታለች፡፡ እኔም ቤተሰቡ ባዋለደው በዚህ እቅድ ተስማምቻለሁ:: ለተፈጠረው የቤተሰባችን ጭንቀት መፍትሄ ማዋጣት እፈልጋለሁኝ፡፡
ቄሱ ጉቦ ተሰጠው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቄሱ ለሚያራምደው እርስ በእርስ የመተዛዘን ቀኖና፣ የእኛ ቤተሰብ የተመቸ ነበር፡፡ በመሰረቱ ሁሉም ሰው ስለ ራሱ መልካም ተግባር በማከናወን ላይ እንደተጠመደ ያስባል፡፡ እያሰበም  በዛውም ወደ ኪሱ ገንዘብ ይጨምራል፡፡ ቄሱም ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡
ቄሱ ልዩና ብርቅ የሆንኩ ሴት መሆኔን ነገረኝ፤ ልክ እንደ ሙሽራ ማለት ይቻላል፡፡ ፈጣሪ እኔን የጠራኝ ለመስዋዕትነት እንደሆነ ነገረኝ፡፡ የማሳልፈው ስቃይ ነፍሴን ለማጥራት እንደሆነ ገለፀልኝ፡፡ እድለኛ መሆኔንም አክሎ ነገረኝ፡፡ ምክኒያቱም፣ እድሜ ልኬን የዋህ እንደሆንኩ ስለምዘልቅና ማንም ወንድ ንፅህናዬን ለመበከል ስለማይጠጋኝ ነው፡፡ በመሆኑም… መንግስተ ሰማይ በቀጥታ እንደምገባ አስረዳኝ፡፡
ቄሱ ለጎረቤቶቻችን በፃድቅነት ስለ መሞቴ መርዶ ነገራቸው፡፡ በጣም ጨለማ በሆነ ክፍል ውስጥ፣ ጠለቅ ባለ የሬሳ ሳጥን፣ ነጭ ቀሚስ ለብሼ እንድጋደምና ጎረቤቶች መጥተው እንዲሰናበቱኝ ተደረገ፡፡ ነጩ ቀሚስ፣ ቬሎ ያለውና ፊቴ ላይ የበቀለውን ፀጉር እንዲደብቅ ሆኖ የተዘጋጀ ነበር:: ለሁለት ቀናት በዛ ሬሳ ሳጥን ውስጥ አሳለፍኩኝ:: እርግጥ ማታ-ማታ እየተነሳሁኝ፣ በቤቱ ውስጥ እዘዋወራለሁኝ፡፡ ሰው ሊጎበኘኝ ሲመጣ ትንፋሼን አምቄ እይዛለሁኝ፡፡ ሊሰናበቱኝ የመጡ ጎብኚዎቼ፣ በጥፍራቸው እየጠቀሱ በሬሳ ሣጥኑ ዙሪያ ሲራመዱና በሹክሹክታ ሲያወሩ እሰማቸዋለሁኝ፡፡ ወደ ሬሳ ሳጥኑ ፈፅሞ አይጠጉም፡፡ ለእናቴ ‘ መልዐክ እንደምመስል ’ ይነግሯታል፡፡
እናቴ ኩሽና ቁጭ ብላ ልክ የእውነት እንደሞትኩ ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች፡፡ እህቴ ራሷ በጣም እንዳዘነች መተወኑ ተዋጥቶላታል፡፡ አባቴ ጥቁሩን ሱፉን ለብሷል፡፡ ሴት አያቴ ብስኩት እየጋገረች ነበር:: ሁሉም ሰው የተጋገረውን ወደ አፉ ሲሞላ ቆየ፡፡
በሶስተኛው ቀን፣ የሬሳ ሳጥኑን በቆሻሻ ሳር ሞልተው ወደ መቃብር ቤት ወስደው ቀበሩት:: ቀብሩ ላይ ፀሎት ተደረገ፣ ማለፊያ የሚባል የእምነበረድ ድንጋይ በመቃብሩ ራስጌ ተቀመጠ:: ከሦስት ወር በኋላ እህቴ አገባች፡፡ ስታገባ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሄደችው በሰረገላ ነው፣ የቤታችን የመጀመሪያ ሙሽራ ናትና፡፡ የእኔ ሬሳ ሳጥን ለእህቴ መሰላል አንድ መርገጫ ነው፡፡ አሁን ከሞትኩኝ በኋላ የበለጠ ነፃ ሆንኩኝ፡፡ ከእናቴ በስተቀር ማንም እኔ ክፍል እንዲገባ አይፈቀድለትም፡፡ ለጎረቤቶቻችን ክፍሉን እንደ ‘ሽራይን’ የእኔ ማስታወሻ ሆኖ እንዲቆይ ማዋላቸውን ገለፁላቸው፡፡ የእኔን ስዕል በበሩ ላይ ሰቀሉት፡፡ ስዕሉ የተሳለው እኔ ድሮ ሰው እመስል በነበረ ጊዜ ነው፡፡ አሁን ምን እንደምመስል ፈፅሞ አላውቅም፡፡ መስታወቶችን እፀየፋለሁኝ፡፡
በደበዘዘው የክፍሌ ጨለማ ውስጥ ፑሽኪንን አነበብኩኝ፡፡ እንዲሁም የሎርድ ባይረንንና የጆን ኬትዝን ግጥሞች፡፡ በፍቅር ስለ መጎዳት፣ ስለ እንቢ ባይነትና ስለ ሞት ጣፋጭነት ተማርኩባቸው፤ እነዚህን ሃሳቦች የሚያፀኑ ሆነው አገኘኋቸው፡፡
እናቴ ድንችና ዳቦዬን፣ በጎድጓዳ ሳህን ደግሞ ደም ይዛልኝ ትመጣለች፡፡ የመፀዳጃ እቃውን ደግሞ አንስታ ትወጣለች፡፡ አንድ ጊዜ፣ ፀጉሬን ለማበጠር ሞክራ እፍኝ ሙሉ ፀጉር ተነቅሎ ወጣ፡፡ ቀደም ሲል ታቅፈኝና ታለቅስ ነበር፡፡ አሁን ይሄ አባዜ ሙሉ ለሙሉ ለቋታል፡፡ በተቻለ ፍጥነት ቶሎ ወደ ክፍሌ ገብታ ትወጣለች፡፡ ምንም ያህል ልትሸሽገው ብትጥርም፣ እኔን መቀበል ማቆሟ ግልፅ ነበረ፡፡ ሰው ለሰው ማዘን የሚችለው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከቆይታ በኋላ፣ የተከሰተው እኩይ እጣ ፈንታ እሱን ሆን ብሎ ለማሰቃየት የታቀደ ይመስል ሰለባውን ማኩረፍ ይጀምራል፡፡
ማታ ማታ የቤቱ ጌታ እኔ ነኝ፡፡ በቆይታ ደግሞ የጊቢው ጌታም መሆን ጀምርኩኝ፡፡ ሲከራርም ደግሞ የጫካው ጌታም ወደ መሆን ተሸጋገርኩኝ፡፡
አሁን በሰዎች መንገድ እና ህይወት ውስጥ ጣልቃ እገባለሁኝ ብዬ አልፈራም፡፡ እኔን በተመለከተ ግን ምንም የወደፊት ተስፋም ሆነ ህይወት የለኝም፡፡ እኔ ያለኝ አሁን ብቻ ነው፡፡ አሁኑም የሚለወጥ አሁን ነው፡፡ ወይም ለእኔ እንደዛ ይመስለኛል፣ ጨረቃም አብራ ትለወጣለች፡፡
ድንገት የሚያጣድፉኝ መወራጨቶች (fits)፣ ወይም ለሰዓታት ሰቅዞ የሚይዘኝ ህመም ወይም በጆሮዬ የሚያንሾካሹኩት ትርጉማቸው የማይገቡኝ ድምፆች ባይኖሩ… ደስተኛ ነኝ ማለትም በቻልኩ ነበር፡፡
***
ሴት አያቴ ሞተች፤ ቀጥሎ ደግሞ አባቴ፤ ድመቱ ደግሞ አረጀ፡፡ እናቴ የበለጠ በኀዘን መቀመቅ ውስጥ ወደቀች፡፡ “የእኔ ምስኪን ልጅ ” ትለኛለች፡፡ አባባሏ ልጅ መባል የምችል እንዳልሆንኩ የሚያሳብቅ ነው፡፡
“እኔ ስሞት ማን አንቺን ይንከባከብሻል?”
ለዚህ ጥያቄ መልሱ አንድ ብቻ ነው፡፡ እኔ ነኝ ልሆን የምችለው፡፡ በእኔ ውስጥ ያለውን አቅም ወይም ኃይል መመርመር ጀመርኩኝ፡፡ ሰው እያየኝ ባልሆነበት ቅፅበት የበለጠ ኃይል እንዳለኝ ተገነዘብኩ፡፡ ከሁሉም  የበለጠ ኃይል የሚኖረኝ ግን በከፊል በምታይበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለት ህፃናት ልጆችን ጫካ ውስጥ ሆነ ብዬ አስበረገግዃቸው፡፡ ሮዝ ጥርሴን፣ ፀጉር የሸፈነው ፊቴንና ቀይ ጥፍሬን አሳየዃቸው፡፡
እንደ ድመት በመሰለ ድምፀት ተቆጣኋቸው:: እነሱም እየጮሁ ሸሹ፡፡ ከግዜ በኋላ ሰዎች በእኛ ቤት አካባቢ ያለውን ጫካ ራቁት፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ፣ በሰው ቤት መስኮት ወደ ውስጥ ተመልክቼ አንዲት ወጣት ሴት በፍርኃት አቅሏን እንድትስት አድርጌያታለሁኝ፡፡
“…አንድ ነገር… አንድ የሆነ ነገር አየሁ! ” ብላ ተንሰቀሰቀች፡፡ ‘የሆነ ነገር’ የመሰለ ገፅታ ነበረ በወቅቱ የነበረኝ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ ፦ ‘የሆነ ነገር’ እንዴት እንደ ሰው ሊቆጠር አልቻለም? የሆነ ሰውዬ ደግሞ የእኛን እርሻ ለመግዛት ተመን አቀረበ፡፡ እናቴ እርሻውን ሸጣ ከእህቴና ባሏ እንደዚሁም በጤናማ ሁኔታ በማደግ ላይ ካለው ቤተሰቧ ጋር ለመዳበል ፈልጋ ነበረ፡፡ የእህቴና የቤተሰቧ ምስል በቅርቡ በሰዓሊ እንዲሰራ ተደርጓል፡፡ … ግን እኔን እንዴት ጥላኝ ትሂድ? ባለው ሁኔታ መቀጠል ባትችልም ጥላኝ ለመሄድ ግን አልሆነላትም፡፡
“ሂጂ” አልኳት እኔ፡፡ አሁን ድምጼ እንደ አውሬ ወደ ማጓራት እየተቀየረ ነው፡፡ “ የመኖሪያ ክፍሌን ለቅቄ እወጣለሁ፤ ሌላ መቀመጥ የምችልበት ቦታ አለ” አልኳት፡፡ ደስ አላት -- ምስኪን፡፡ ከእኔ ጋር አንዳች የጠበቀ ግንኙነት አላት፡፡ ልክ ልብስ ከመስቀያ ሚስማሩ ጋር ወይም ሰው ከኪንታሮቱ ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንደሚያዳብረው፡፡ የእሷ ነኝ፡፡ ግን ብትገላገለኝ ደስ ይላታል፡፡ ለእድሜዬ ልክ የሚበቃ ውለታ ውላልኛለች፡፡
ቤታችን ውስጥ ያለውን ቁሳቁስ ለቃቅመው ወደ ገበያ ለሽያጭ በሚወስዱበት ቀን… በሳር ክምሩ ውስጥ ተሸሽጌ ዋልኩኝ፡፡ የሳር ክምሩ ከፀሐይ ለመከላከል በቂ ነበረ፤ ግን ለክረምት ጊዜ አያገለግልም፡፡
                               ***
አዲሶቹ ሰዎች ወደ ቤቱ ሲገቡ ማባረር ቀላል ነበር፡፡ ቤቱን ከእነሱ በበለጠ  መግቢያና መውጫውን አውቀዋለሁኝ፡፡ በዚያ ላይ በጨለማ ውስጥ መንቀሳቀስ እችላለሁኝ፡፡ እንደ መንፈስ ሆንኩባቸው፡፡ ቀይ ጥፍር ያለው እጅ በጨረቃ ብርሃን ፊቱን ሲዳብስ ምን ሊመስል እንደሚችል አስቡት፡፡ ወይም ሳልፈልግ ከውስጤ የሚወጣው እንደ ዛገ ማጠፊያ ሲጥ የሚለው ድምፄ…፡፡ ከቤቱ በሩጫ ነው ወጥተው የጠፉት፡፡ ቤቱንም በሰይጣን የተለከፈ ብለው ፈረጁት፡፡ ከዛ ቤቱ የእኔ ብቻ ሆነ፡፡
ምግቤ፤ ከሰው እርሻ በሌሊት ቆፍሬ የምሰርቀው ድንችና ከዶሮ ቤት የምሰርቀው እንቁላል ነው፡፡ አልፎ አልፎ ዶሮ እመገባለሁኝ፡፡ መጀመሪያ ስጋውን ከመብላቴ በፊት ግን ደሙን እጠጣለሁ፡፡ ዶሮዎቹን የሚጠብቁ ውሾች አሉ፡፡ እኔ ላይ ያጓራሉ እንጂ ፈፅሞ ለመናከስ አይሞክሩም፡፡ ምን እንደሆንኩኝ አያውቁም፡፡
ቤተሰቦቼ ቤት ተመልሼ ፊቴን በመስታወት አስተዋልኩት፡፡ የሞቱ ሰዎች የራሳቸውን ፊት በመስታወት ማስተዋል አይችሉም ይባላል… በአባባል ደረጃ፡፡ ደግሞም ለካ አባባሉ እውነት ነው፡፡ ራሴን በመስታወቱ ውስጥ ማየት ተሳነኝ:: አንድ ‘የሆነ ነገር’ ታይቶኛል ብቻ፡፡ ግን ያ የታየኝ ነገር እኔን አይደለም፡፡ ድሮ የማውቃትን፣ ምንም የማታውቀውን የዋህ ቆንጆ ሴት ልጅ የመሰለ ነገር አይደለም፡፡ እኔ በበኩሌ ደግሞ በልቤ የማምነው ያችን የዋህ ቆንጆ ሴት ልጅ አሁንም ስለመሆኔ ነው፡፡
ነገሮች ወደ ፍፃሜ እየመጡ እንደሆነ ግልፅ እየሆነልኝ መጣ፡፡
እንዲህ ነው የሆነው ፦
ጸሐይ በማዘቅዘቅ ላይ ሳለች፣ ብላክ ቤሪ እየለቀምኩ ነበር፡፡ የሳሩ መስክ አልቆ ዛፎች ያሉበት ጫካ የሚጀምርበት ወሰን ጋ ስደርስ ሁለት ሰዎች ሲመጡ አየሁኝ፡፡ የመጡት ከተለያየ አቅጣጫ ነው:: አንደኛው ጎረምሳ ልጅ ነው፡፡ ሌላኛዋ ኮረዳ ናት፡፡ የወንድየው ልብስ ከልጅቱ የተሻለ ነበረ፡፡ ጫማም አድርጓል፡፡ ፊታቸው ላይ አንዳች የመሸሸግ ፍላጎት እንዳላቸው ያስታውቃል፡፡ ያንን አይነት የመልክ ገፅታ አውቀዋለሁኝ፡፡ ሰው እንዳልተከተላቸው ወደ ጀርባቸው እየዞሩ ያጣራሉ፡፡ ቆም ይሉና እንደገና ይቀጥላሉ፡፡ እኔ ራሴ ብዙውን ጊዜ በመሸሸግ የምኖር እንደመሆኔ ባህሪውን አውቀዋለሁኝ፡፡
ቁጥቋጦው ውስጥ ተሸሸግሁና መመልከት ቀጠልኩኝ፡፡ ግንኙነት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ተጣመዱ:: ወደ ወለሉ ወደቁ ፡፡ እንደ ማቃሰት መሰል ድምጽ ይወጣቸው ጀመር፡፡ ማቃሰትና ትንሽም ጩኸት የመሰለ ድምጽ፡፡ ምናልባት አንዳች አጣዳፊ በሽታ ቀስፎ ይዟቸው ሊሆንም ይችላል፡፡ ሁለቱንም ባንድ ጊዜ የሚይዝ በሽታ፡፡ ምናልባትም…እኔ እንደሆንኩት እየሆኑም ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ እንደተለወጥኩት እየተለወጡ፡፡ ኦ! በስተመጨረሻ አምሳያዎቼን አገኘሁኝ!
የተሻለ እንዲታየኝ ቀረብ አልኩኝ፡፡ እኔን አይመስሉም፡፡ ለምሳሌ እንደ’ኔ በጸጉር የተሸፈኑ አይደሉም፡፡ ጸጉር ያላቸው ጭንቅላታቸው ላይ ብቻ ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ በደንብ ማረጋገጥ የቻልኩት ልብሳቸውን ሙሉ ለሙሉ አውልቀው ስላየዃቸው ነው፡፡ ነገር ግን፣ እኔ አሁን እንደሆንኩት ለመሆን ረጅም ጊዜ ወስዶብኛል፡፡ እነሱ ገና በመጀመሪያው የለውጥ ደረጃ ላይ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ብዬ አሰብኩኝ፡፡ አንድ ዓይነቶቹ ተመራርጠው አብረው ለመሆን ነው ጫካ የመጡት፣ ህመማቸውን በአንድ ላይ ለመጋራት፡፡ ገላቸውን እንደ መውቃት በመሰለ አኳሁዋን በሚያደርጉት ፍትጊያ ደስታ የሚያገኙ ይመስላሉ፡፡ ይኼ እንዴት ሊከሰት እንደሚችል ከእኔ የተሻለ የሚያውቅ የለም፡፡
እንዴት መጽናናትን ባገኘሁ ነበር እኔም ብዳበላቸው!
በአመታት ውስጥ ባሳለፍኩት ቆይታ ራሴን በብቸኝነት አጠንክሬአለሁ፡፡ አሁን ድንገት ያ ጥንካሬ ሲሟሟ ተሰማኝ፡፡ ግን አይን አፋርነቴ ወደ እነርሱ እንድቀርብ ሊፈቅድልኝ አልቻለም:: ከእለታት በአንዱ ቀን፣ በአንዱ ተመሳሳይ ምሽት ወንድየው እንቅልፍ ወሰደው፡፡ ኮረዳዋ ባወለቀው ሸሚዝ እርቃኑን ገላውን አልብሳ ግንባሩን ሳመችው፤ ከዛም በጥንቃቄ በተኛበት ትታው ሄደች፡፡
ከተደበቅሁበት የቆንጥር ቁጥቋጦ ወጥቼ በቀስታ ወደተኛው ጎረምሳ ተሳብኩኝ፡፡ በተደመደመ ሳር ላይ ተኝቷል፡፡ ልክ በማቅረቢያ ሳህን ላይ ተዘጋጅቶ የተቀመጠ ነው የሚመስለው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ራሴን መቆጣጠር ተሳነኝ፡፡ ባለ ቀይ ጥፍሩን እጄን አሳረፍኩበት፡፡ አንገቱ ላይ ነከስኩት፡፡ ፍትወት ነው ወይስ ረኃብ? በሁለቱ መኃል ያለውን ልዩነት እንዴት ማወቅ እችላለሁ?
 ከእንቅልፉ ነቃ፤ ሮዝ ጥርሶቼን፣ ቢጫ አይኖቼን ተመለከተ፡፡ ጥቁሩ ቀሚሴ ሲርገበገብና ሮጬ ስሰወር አየ፡፡ ወደ የት አቅጣጫ እንደሄድኩም አስተዋለ:: በመንደሩ ለሚኖሩ መሰሎቹ የተከሰተውን ሄዶ ነገራቸው፡፡ መላምት መሰንዘር ጀመሩ፡፡ የእኔ መቃብር ቦታ ሄደው የሬሳ ሳጥኔን ቆፍረው አወጡት:: በውስጡ አስከሬን አልነበረውም፡፡ የባሰው ነገር አስፈራቸው፡፡
አሁን ጸሐይ ስትጠልቅ ጠብቀው ወደዚህ ቤት እየመጡ ነው፡፡ ረጃጅም የሾለ እንጨትና እሳት ይዘዋል፡፡ እህቴም ከእነሱ ጋር አብራ መጥታለች፤ እናም የእህቴ ባል፡፡ ሳሩ ላይ ተኝቶ የሳምኩት ወጣትም ከመኃላቸው አለ፡፡ ለመሳም ብዬ እንጂ ለመንከስ ብዬ ያደረግሁት አልነበረም፡፡
ምን ልላቸው እችላለሁኝ? እንዴት ራሴን ለእነሱ ገልጬ ላስረዳ ይቻለኛል? ጭራቅ የግድ የሚፈለግ ከሆነ አንዳችን የሚፈለገውን መሙያ መሆን ይኖርብናል፡፡ ወደፊት ገፍተህ ወጣህም አልያም ተገፋህም በስተመጨረሻ አንድ ነው፡፡ «እኔ የሰው ልጅ ነኝ» ማለት እችላለሁኝ፡፡ ግን ምን ማረጋገጫ አለኝ?
«እኔ የተፈጥሮ ጉድፍ ነኝ! ወደ ከተማችሁ ውሰዱኝ! ጥናት እንዲካሄድብኝ ያስፈልጋል!» ግን ይሄንንም ማለት ዋጋ የለውም፡፡
ለድመቱ መጥፎ ዜና ነው፡፡ እኔ ላይ ለመፈፀም ያሰቡትን ነገር ድመቱም ላይ ማድረጋቸው አይቀርም::  እኔ የይቅርባይነት መንፈስ በውስጤ ያለኝ ነኝ፡፡  እነሱም በጎ የማድረግ ፍላጎት በልባቸው እንዳለ ይገባኛል፡፡ ነጩን የቀብር ቀሚሴን፣ ለደናግላን የተገባ የሆነውን ነጭ ቬሎም ለበስኩኝ:: የሚንጫጩት ድምጾች እየጎሉ መጡ፡፡ አሁን የመሸሻ ጊዜዬ ደርሷል:: ከሚቃጠለው ጣራ ላይ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ወደ ታች ተምዘግዝጌ እወድቃለሁኝ፡፡ ስቃጠል እንደ ደመራ ቦግ ብዬ አበራለሁኝ፡፡ በአመዴ ላይ ብዙ ድግምት መድገማቸው አይቀርም፤ በድጋሚ እንዳልነሳ፣ ሞቼ መቅረቴን ለማረጋገጥ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ተዘቅዝቆ የተሰቀለ ጻድቅ እሆናለሁኝ:: የጣቶቼ አጥንቶች እንደ ቡዳ መድኃኒት ይሸጣሉ፡፡
ምናልባት በመንግስተ ሰማይ መልዐክ ልመስል እችላለሁ፡፡ ወይም መላዐክቱ እኔን ሊመስሉ ይችሉ ይሆናል፡፡ እንዲህ ቢሆን ሰዉ ሁሉ እንዴት ግራ በተጋባ ነበረ ! … ሄጄ ለማየት የሚያጓጓኝ አይነት ነገር ነው፡፡
         ***                   
የግርጌ ማስታወሻ ፦
 ፖርፒሪያ (Porphyria) ፤ በህክምና ሊስተካከሉ ከማይችሉ የዘረ-መል ቀውሶች መኃል አንዱ ነው፡፡ ሰውነት የሚሰራውን ሂሞግሎቢን የሚያዛባ እክል ነው፡፡ እንደሚታወቀው፣ ሂሞግሎቢን ደምን ቀይ የሚያደርገው ፕሮቲን ነው፡፡ የዚህ የዘረ-መል እክል ያለባቸው ሰዎች ከሚያሳዩት ምልክቶች መሓል፦ የእንቅልፍ እጦት፣ ቅዠት፣ በብርኃን መታወክ/ ብርኃን ውስጥ መሆን አለመቻል፣ ሰውነት ላይ ከመጠን ያለፈ ጸጉር ማብቀል፣ የጥርስ መቅላት፣ የቆዳ ህመምና ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡ ከዚህም ከፍ ሲል የፊት ገፅታና ቅርፅ መዛነፍን ወይንም አስቀያሚ መሆንን ያስከትላል፡፡ ይኼ በሽታና የህመም ምልክቶቹ፣ የ«ቫንፓየር» ተረቶችና ንግርቶች የተፈጠሩበት መነሻ ነው የሚል መላምት በተደጋጋሚ ይሰነዘራል፡፡ ነገር ግን፣ መላምቱ በተደጋጋሚ ውድቅ ሆኗል፡፡

Read 642 times