Print this page
Saturday, 20 July 2019 11:58

ስራ አጥነት - የመንግስት ትልቁ ፈተና

Written by  (አሸናፊ በሪሁን ከSeefar)
Rate this item
(2 votes)

ወጣትነት ለሥራ፣ ለትግል፣ ለለውጥ፣ ለአዲስ ነገር ተነሳሽነት ጎልቶ የሚታይበት ዕድሜ እንደመሆኑ፣ የአንዲት አገር ዕድገትም ሆነ ውድቀት በየዘመኑ ባለው ወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡  ሥራ ፍለጋ ከገጠር ወደ ትናንሽ ከተሞች የሚፈልሱ እንዲሁም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በተለያያ ደረጃ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ማስተናገድ የሚችል የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩ፣ ከተሞች የሥራ አጥ ወጣቶች መናኸሪያዎች ሆነዋል። የአገሪቱን ከተሞች ያጨናነቁ፣ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮባቸዋል። በአገራቸው ሥራ አግኝተው የተሻለ ህይወት የመኖር ተስፋ የራቃቸው ወጣቶች፣ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት እየተጋለጡም ነው።
በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት፤ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ዜጎች ቁጥር 71 ከመቶ ነው። ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። በኦፊሴላዊ ግምት ብቻ በ16.5 በመቶ የሚያድግ የሥራ አጥነት እንዳለ ይነገራል። ምንም እንኳን ኢኮኖሚው በዕድገት ላይ ነው ቢባልም፣ በየዓመቱ በእጅጉ እየጨመረ ለሚመጣው ለዚህ አምራች ኀይል አቻ የሚሆን በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ግን አልቻለም። በ2011 የወጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ 77.8 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት ኑሮውን የሚገፋው በቀን ከሁለት ዶላር ባነሰ የገንዘብ መጠን ነው።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወጣቱን ጥም ማርካት እንዳልቻለ ይተቻል። በየአመቱም ሁለት ሚሊዮን አዲስ ስራ ፈላጊዎች ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡ ከአርባ በላይ ከሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችም በየአመቱ ከ150 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይመረቃሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ አገሪቷ ተጨማሪ የስራ ዕድሎችን መፍጠር እንዳለባት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የስራ ዕድሎችን መፍጠር ነው፡፡  ከባለፈው አመት ጀምሮም መንግስት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የስራ ፈጠራ መነሻ የሚሆን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ በጀት መድቧል። ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮችም ከበጀታቸው በመቀነስ በተመሳሳይ ሁኔታ በጀት በመመደብ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡
በቅርቡ ለፓርላማ አመታዊ ሪፖርት ያቀረቡት ጠ/ሚኒስትር  ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 11 ሚሊዮን በላይ ስራ አጥ ወጣቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለ3 ሚሊዮን ያህሉ በመጪው አመት ስራ ለመፍጠር መታቀዱን ይፋ አድርገዋል፡፡ የዕቅዳቸው አንዱ አካል ደግሞ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ ወደ አረብ አገራት መላክ ነው፡፡ ለዚህም 50ሺ የሚሆኑ ወጣቶችን በዚሁ ዓመት ወደ አረብ ሀገራት ለመላክ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ደግሞ 250 ሺ ወጣቶችን ወደ አረብ ሃገራት ለመላክ ዕቅድ ተይዟል፡፡ እነዚህን ወጣቶች በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ አገራት መላክ ከወጣቶቹም አልፎ ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ ወጣቶቹ የራሳቸውን ዕውቀት ከማሳደግ ባለፈ  በሚልኩት ገንዘብ፣ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሥራ ልምድ የአገራቸውን ኢኮኖሚ በመደገፍ፣ የድህነት ምጣኔን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። የአገራቸውን ባህልና ልዩ ምርቶች ለውጭው ዓለም ከማስተዋወቅም አንጻር ሚናቸው ቀላል አይሆንም፡፡
3 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው የሚልኩት ገንዘብ (Remittance) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2010 ከሪሚታንስ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን በ2017 ወደ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሪሚታንስ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከውጪ የሚላከው ገንዘብ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 5% የሚሆነውን የሚሸፍን ነው፡፡ በርግጥ ይህ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ላይቤሪያ በስደት በውጭ ከሚገኙ ተወላጆቿ የምታገኘው ገንዘብ ከአገሪቱ ጠቅላላ ምርት 26 ነጥብ 7 በመቶውን ሲይዝ፣ ሌሴቶም 18 ነጥብ 2 በመቶውን  የሚሸፍን ነው፡፡ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ የሚላክላቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከሪሚታንስ የሚጠበቀውን ያህል እንዳታገኝ አድርጎል፡፡ ኢትዮጵያውያን በብዛት  ከሚኖሩባቸው ሀገራት መካከል  አሜሪካ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣልያን ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ ከፍተኛ ገንዘብ የሚላከውም ከእነዚሁ አገራት ነው።
በ2017 ናይጄሪያ 21 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ግብፅ 20 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚ አገራት መሆናቸውን የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል። ሕንድ 69 ቢሊዮን ዶላር፣ ቻይና 64 ቢሊዮን ዶላር፣ ፊሊፒንስ 29 ነጥብ 7 ቢሊዮን  ዶላር ከሪሚታንስ ገቢ በማግኘት፣ ከዓለም ከአንድ እስክ አራተኛ ደረጃን ይዘዋል። ይህም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ከተሰማሩ፣ ሀገራቸው ከሪሚታንስ  ከፍተኛ ገቢ እንደምታገኝ ማሳያ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለመንግስት ከፍተኛ ራስ ምታት የሆነው  የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም ዘርፈ ብዙና መጠነ ሰፊ የሆኑ አማራጮችን መዘርጋትና መጠቀም ግድ ይላል፡፡  በዋናነት በአገር ውስጥ ከሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች በተጨማሪ ሥራ ፈላጊ ዜጎችን ወደ ውጭ አገራት መላክ ለጊዜውም ቢሆን ችግሩን የሚያቃልል ከመሆኑም ባሻገር የአገርንም ኢኮኖሚ ይደግፋል፡፡ 

Read 4201 times