Saturday, 20 July 2019 11:55

በምጥ ላይ ያለች አገር?!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 “በትግርኛ ቋንቋ የእኔን አቋምና ሀሳብ፣ ለትግራይ ህዝብ ማቅረብ እፈልጋለሁ ግን አልቻልኩም

 
  - ኢትዮጵያ ከፈረሰች ምስራቅ አፍሪካ በሙሉ ነው የሚፈራርሰው
  - በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት፣ የባህር በር ባለቤት የመሆን መብት አለን
  - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት፤ ባህር ሃይል ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው

    በኢህአዴግም ሆነ በመንግስት ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘርና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ትንተና በመስጠት የሚታወቁት የቀድሞው የአየር ሃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት፤ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት! የደህንነት ማስጠንቀቂያ ደወል›› የተሰኘ መጽሐፋቸው ዛሬ ለአንባቢያን ይቀርባል፡፡ ለመሆኑ መጽሐፉ በምን ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናል? ጀነራሉ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ አዴፓ እና ህወኃት ሰሞኑን በሰጡት መግለጫዎችም ላይ አስተያየታቸውን ጠይቀናቸዋል፡፡ በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ፣ በክልልነት ጥያቄዎች፣ በኢትዮጵያ የደህንነት ስጋቶችና ህልውና እንዲሁም በገዢው ፓርቲ
ወቅታዊ ቁመና ዙሪያ --- የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ሜጀር ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖትን አነጋግሯቸዋል፡


    ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከየት ወዴት፤ የደህንነት ማስጠንቀቂያ ደውል›› በሚል ርዕስ በነገው ዕለት ስለሚወጣው መጽሐፍዎ በጥቂቱ ያስተዋወቁን?
በዋናነት የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሁኔታ፣ ቀጥሎም የምሥራቅ አፍሪካን ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ እንዲሁም ኢትዮጵያ የቀይ ባህር አገር እንደመሆንዋ፣ በቀይ ባህር ላይ ካላት እድልና ተግዳሮት ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳዮችን የሚዳስሰ መጽሐፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሠረታዊ ድክመቶችና ጥንካሬዎች ምንድናቸው? ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካው ሲበላሽ የአገር ደህንነትም ይበላሻል፡፡ ደህንነታችን አደጋ ውስጥ የሚወድቀው ፖለቲካችን ሲበላሽ ነው:: እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ጥያቄዎችን እንዴት መመለስ ይቻላል? የሚሉ ጉዳዮችን በስፋት ያነሳል፡፡ ከደህንነትም አኳያም የበፊቱን የደህንነት ፖሊሲ ይገመግማል፡፡ ከዚህ በመነሳትም በአጠቃላይ ደህንነታችንን ለመጠበቅ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን ሰፋ አድርጎ ይተነትናል፡፡ የኛ የደህንነት ዋና አደጋችን የሚመነጨው ከውስጣችን የሰላም ሁኔታ ነው፡፡ መተማመንና ሰላም ሲኖር፣ የውጭ ጠላት ስጋት አነስተኛ ነው፡፡ እርስ በእርሳችን ስንናቆርና፣ መተማመን ሲጠፋ ለውጭ ጠላት የመጋለጥ እድላችን ሰፊ ነው፡፡ መጽሐፉ፤ በዚህ መነሻነት፣ ባለፉት 70 ዓመታት ውስጥ የተፈፀሙ አንኳር ጉዳዮችን በማሳያነትም ያነሳል፡፡
እስቲ ለምሳሌ ያህል ይጥቀሱልኝ…?
ለምሳሌ ኤርትራ ለምን ተገነጠለች? የሚል ጥያቄ አንስቶ ትንታኔ ያቀርባል፡፡ ኤርትራና ሶማሊያን ያካተተ ትልቅ አገር የመመስረት ዕድሉ በአንድ ወቅት ነበረን፡፡ ያ እድል ለምን ከሸፈ? ሌላው ከደህንነት አኳያ መጽሐፉ የሚፈትሸው፣ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ነው፡፡ ጦርነቱን በስፋት ይገመግማል፡፡ ለምን ወረሩን? እኛ ለምን አልተዘጋጀንም? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ ያብራራል፡፡ እኔ ያን ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሚታዘዘውና ጦርነቱን በሙሉ የሚመራው የዕዝ ማዕከል አባል ነበርኩና፣ በወቅቱ የነበሩትን ሁኔታዎች በስፋት ዘርዝሬ አቅርቤያለሁ:: ጦርነቱም በስፋት ተገምግሞበታል፡፡ ሌላው ርዕሰ ጉዳይ፣ ለምን የባህር በር አጣን? የሚል ነው፡፡ የባህር በር ማጣት ለድህነት ትርጉሙ ምንድን ነው? የሚለውንም ይዳስሳል፡፡ በተጨማሪም ከ2008 እስከ 2010 የነበረውን የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በስፋት ይገመግማል፡፡ ሌላው በመጽሐፉ የተነሳው የውስጥ ደህንነታችንን አስተማማኝ የሚያደርጉ ጉዳዮችን የተመለከተ ነው፡፡ እነዚህም የመሬት ጉዳይ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይና የሰብአዊ መብት ጉዳይ ናቸው:: እንዴት? የሚለውን መጽሐፉ በሰፊው ይተነትናል:: ስለ ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲሁም ስለ ብሔራዊ ማንነትም በጥልቀት ይፈትሻል፡።
የባህር በር የምናገኝበትም መንገድ በመጽሐፍዎ ተጠቁሟል… ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
በመጀመርያ ደረጃ እኛ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ስለሆንን፣ የባህር በር ያስፈልገናል ከሚል አይደለም:: በአለማቀፍ ሕግ መሠረት፣ የባህር በር ባለቤት የመሆን መብት አለን፡፡ ይሄን መብታችንን ደግሞ ማረጋገጥ አለብን፡፡ ይሄን መብታችንን እንዴት ነው የምናረጋግጠው ለሚለው፣ የራሱ ስትራቴጂዎችና አካሄዶች አሉት፡፡ ይሄን በመጽሐፌ አመላክቻለሁ:: ምሁራንም በተነሱት ጉዳዮች ላይ ተወያይተው፣ መብታችንን ለማስከበር መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡  
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ባህር ሃይል እንደሚያስፈልጋት በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ ለማቋቋምም ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይነገራል:: ባህር ሃይል መቋቋሙ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? የባህር በር ሳይኖረን፣ የባህር ሃይል ማቋቋሙ ትርጉም ይኖረዋል?
እኔ የጠ/ሚኒስትሩን ሀሳብ በጣም ነው የምደግፈው፡፡ የቀይ ባህር አገር ነን ብለን፣ የባህር ሃይል የለንም፡፡ የባህር ሃይል ለኛ ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን የባህር ሃይል፣ ያለ ባህር በር ብዙ ትርጉሙ የለውም:: ጠ/ሚኒስትሩ የባህር ሃይል ማቋቋም አለብን ሲሉ፣ የባህር በር ማግኘት አለብን የሚለውንም እያሰቡበት ነው ብዬ አምናለሁ፡። ያለ ባህር በር፣ ባህር ሃይል እናቋቁም ከተባለ፣ የባህር ሃይሉ ሚና፣ የቅኝት (ፓትሮል) ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሊሆን የሚችለው  በጅቡቲ፣ በሶማሊያ፣ በኤርትራና በሱዳን ፈቃድ ነው፡፡ በፈለጉ ጊዜ የሚከፍቱት፣ በፈለጉ ጊዜ የሚዘጉት አይነት ይሆናል ማለት ነው:: ነገር ግን ባህር ሃይል ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት ለኢትዮጵያ ወሳኝ ነው፡፡ ይሄን የምለው፤ ከእንግዲህ ወዲህ የሚደረጉ ጦርነቶችን ባህሪ በማሰብ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ የሚካሄዱ ጦርነቶች፤ ኤርትራና ኢትዮጵያ እንዳደረጉት አይነት አይደለም፡፡ ቀይ ባህርን የመቀራመት አይነት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በዋነኛነት የሚከናወነው በባህርና አየር ሃይል ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ከወዲሁ አየር ሃይልን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት መስጠት አለብን፡። እነ ሳውዲ፣ እነ ኤምሬት ጦርነት ቢገጥሙ፣ በእግረኛ ሳይሆን፣ በባሕር ሃይል በአየር ሃይል ነው፡፡ አሁን እየገዙት ያለው መሣሪያ የሚያመላክተው ይሄንን ነው፡፡ ሳውዲ አረቢያ በአለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነው በአንድ ጊዜ በ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሣሪያ የገዛችው፡፡ የነዳጅ ገንዘብ አሁን ወደ ጡንቻና ወታደራዊ ሃይል እየተቀየረ ነው፡፡ የእነዚህን አገራት ጡንቻ ለመመልከት፣ ለኛ የመን ጥሩ ምሳሌ ነች፡፡ ስለዚህ እኛ አየር ሃይላችንን በሚገባና በልዩ ትኩረት ማጠናከር አለብን፡፡ ባህር ሃይልንም በተመሳሳይ፡፡ ባህር ሃይል ሲባል ሶስት አይነት ነው፡፡ አንዱ የባህር በር ሳይኖር ቅኝት ለማድረግ ብቻ የሚቋቋም አለ፡፡ እኛ ባህር ሃይል ይቋቋም ስንል፣ የቅኝት ብቻ ከሆነ ትርጉም የለውም፡፡ ነገር ግን ዶ/ር ዐቢይ፤ የባህር ሃይል እናቋቁማለን ሲሉ፣ እኔ የማስበው መጀመርያ የባህር በር ይኖረናል በሚለው ነው፡፡
እስቲ ወደ ወቅታዊ ጉዳዮች እንመለስ፡፡ ሰሞኑን ህወኃት እና አዴፓ አስገራሚ የቃላት ጦርነት የገጠሙበትን መግለጫዎችን አውጥተዋል፡፡ እነዚህን መግለጫዎች እንዴት ተመለከቷቸው?
ከሶስትና አራት አመታት በፊት ኢሕአዴግን በተመለከተ በጻፍኩት ግምገማዬ፣ ኢህአዴግ አይደዮሎጂና ፖለቲካው የከሰረ (ባንክራፕት) ሆኗል ብዬ ነበር፡። ከአቶ መለስ በኋላ ስል፣ ርዕዮተ አለም፣ የሚጻፍ የሚነገር ነገር የለም፡፡  አሁን የሁለቱ ድርጅቶች መግለጫ ያወጣው፣ በውስጣቸው የነበረውን የታመቀ ግጭት ነው፡፡ ይሄ ለኔ የሚጠበቅ ነገር ነበር፡፡
ህወኃት፤ ‹‹የጀነራሎቹ ግድያ በገለልተኛ አካል ይጣራ›› ብሏል - በመግለጫው፡፡ ይሄ መልዕክት ለማን ነው? ራሱ ህወኃት፤ የመንግስት አስፈጻሚ አይደለም እንዴ? በሁለቱ ድርጅቶች መሀከል ያለው ችግር ምን ይመስልዎታል?
ይሄ እንግዲህ የሚያሳየው በፓርቲያቸው ውስጥ በጉዳዩ ላይ ሊነጋገሩ እንዳልቻሉ ነው፡፡ የትግራይ ክልል አስተዳደርና የፌዴራል መንግስት ሊነጋገሩበት አልቻሉም ማለት ነው፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፤ የሲዳማ የክልልነት ጉዳይ በህገ መንግስቱ አግባብ መፈጸም አለበትም ብሏል - በመግለጫው:: ይሄ በድርጅቶቹ መካከል መነጋገር እንደሌለ አመላካች ነው፡፡ ሰው እያየ ያለው የአዴፓ እና የህወኃትን ምልልስ ነው እንጂ ውስጥ የነበረውን የቆየ ችግር አልተመለከተም:: ይሄ በድርጅቶቹ መካከል ተወያይቶ መፍትሔ ማግኘት እንደሌለ ነው የሚያሳየው፡፡ በሁሉም በኩል የሚታየው በውስጣቸው ያለን ችግር ወደ ሌላ ሶስተኛ አካል ወይም ወደ ውጪ ማመላከት ነው:: አንድ ጊዜ አቶ ገዱ፣ ጥሩ ነገር ተናግረው ነበር:: ‹‹በአማራ ክልል ያለው ችግር በህወኃት ሊመጣ አይችልም፤ ህወኃት የሚነቀፍበት ነገር ካለ ትግራይ ውስጥ ባለ ነገር ነው:: አማራ ውስጥ ያለ ነገር ጥሩም፣ መጥፎም በራሳችን የሚመጣ ነው›› ብለዋል፡፡ ይሄ ትክክለኛ እይታ ይመስለኛል፡፡
አዲፓ የሚገርም ድርጅት ነው የሆነው:: የገዥው ግንባር አባል ሆኖ ጦርነት የሚያውጁ ጽንፈኞች ይደግፋል፡፡ ጦርነት ማወጅ ወንጀል መሆኑን የማያውቅ ድርጅት ነው የሆነው፡፡
አይደሎጂና ፖለቲካ በሚመለከት ከሁሉም የኢህአዴግ ድርጅት በከፋ መልኩ የከሰረ ነው፡፡ ወልቃይትና የራያ ጉዳይ መብት አለን ካሉ በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ መከራከር ሲችሉ እስከ ዘሪፍ ማለት የሚያስገርም ነው፡፡ በየመንደሩ ያለ ጐበዝ አለቃ ክልሉን የሚያስተዳድር የሚመስለው   
‹‹ኢህአዴግ ወደ ሚታወቅበት የቀደመ እምነታችን እንመለስ›› ሲልም ህወኃት አሳስቧል:: ይሄን ሲል ምን ማለቱ ነው? እርስዎ እንዴት ነው የተረዱት?

Read 3094 times