Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 09 June 2012 09:39

ቻይና የኦስትሪያን መንደር አስመስላ ሰራች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የላሊበላን  ውቅር አቢያተ ክርስቲያንን ወይም  የአክሱም ሀውልትን አስመስሎ ሌላ አገር ቢሰራ ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ?

ቻይና ሰሞኑን ሰርታ ያስመረቀችው ሙሉ መንደር ተኮርጆ የተገነባ ነው - ከኦስትሪያ፡፡ በኦስትሪያ የምትገኘው የሀውልስታት መንደር በዩኔስኮ በባህል ቅርስነት የተመዘገበች የቱሪስት መንደር ስትሆን ጥንታዊቷ መንደር  ከስምንት መቶ ሰዎች በላይ የሚኖሩባት አይደለችም፡፡ ከላይ እስከታች አይተው ለመጨረስ  የአስር ደቂቃ የእግር መንገድ ብቻ የምትፈልግ በጨው ምርት የታወቀች መንደር ናት ተብሏል፡፡

በመንደሯ ያሉ የመቃብር ቦታዎች የአርኪዎሎጂስቶችን ትኩረት የሚስቡ ሲሆኑ የሞቱ ሰዎች የራስ ቅል ላይ ስማቸው፤ ይሰሩት የነበረው ስራ እና የሞቱበት ቀን ተፅፎባቸዋል፡፡ የመንደሯ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለኑሮ አመቺ ባይሆንም ተዝቆ የማያልቀው የጨው ምርቷ ሰዎች እንዳይሸሿት አድርጓታል፡፡

ከአንድ አመት በፊት አንድ ቻይናዊ ወደ መንደራቸው መጥቶ ከቱሪስቶች ጋር በመቀላቀል ፎቶግራፎችን ሲያነሳ መጠነኛ ጥርጣሬ ያደረባቸው ነዋሪዎች ባይጠፉም መንደራቸውን ሌላ ቦታ ሊገነባ ነው ብለው ግን ፈፅሞ አልገመቱም፡፡ በቻይና ጉዋንግዱግ በተባለ ግዛት የሀውልስታትን መንደር የገነባው ሚንሜታልስ ኮርፖሬሽን  የተባለ ታዋቂ የማዕድን ኩባንያ ሲሆን ግንባታው ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም ባለፈው ቅዳሜ ለመመረቅ በቅቱዋል፡፡

በምርቃቱ ላይ የተገኙ የመንደሯ ነዋሪዎች መንደራቸው ለመኮረጅ ስለበቃች መኩራታቸውን ሲገልፁ የተሰራበትን መንገድ ግን ነቅፈዋል፡፡ በመንደራቸው ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች፤ መንደራቸውን አስመስሎ ለመስራት ሲታሰብ ሊነገራቸው እንደሚገባ ገልፀው ድርጊቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

በኦስትሪያዋ ሀውልስታት የሆቴል ባለቤት የሆኑ ግለሰብ ድርጊቱ በጣም አበሳጭቷቸዋል፡፡ በመጀመሪያ መንደሯን አስመስለው ለመስራት ሲያስቡ በመንደሯ የሚኖሩ ንብረታቸው ተኮርጆ የተሰራባቸው ሰዎች ፈቃድ ያስፈልግ ነበር ሲሉ ቻይናን ነቅፈዋል፡፡

በቻይናዋ ሀውልስታት ምርቃት ላይ የተገኙት የኦስትሪያው ሀውልስታት ከንቲባ አሌክስ ሼቱዝ፤ የባህል ልውውጥ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን “በጣም ኮርተናል” የሚል አጭር ዲፕሎማሲያዊ አስተያየት እንደሰጡ ተገልጿል፡፡

በሁኔታው ያልተደሰቱ አንድ ቻይናዊ በሰጡት አስተያየት፤ “የቻይናው ሀውልስታት መንደር ዋናውን ለመምሰል ብዙ ነገሮች ይቀሩታል፤ ተፈጥሮአዊ የሆኑ የመንደሯን ገፅታዎች ቻይና ውስጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ የቻይና የስነህንፃ ጥበብ የራሱ ዘይቤ እና መለያዎች ስላሉት በራስ ዘይቤ መስራት እያለ መኮረጅን ምን አመጣው? አበቦቹ ሳይቀር የውሸት ናቸው፤ ማንም ሰው ገና እንዳየው ውሸት መሆኑን ይናገራል” ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ሀውልስታቶች በጎብኚዎች እየተጨናነቁ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ቻይና ብዙ ነገሮችን አስመስሎ በመስራት የታወቀች አገር ነች ያሉ አስተያየት ሰጪ፤ የሀውልስቴት መንደርን ደግሞ መስራቷ፤ አስመስሎ መስራትን ወደ ሌላ ደረጃ ያሸጋገረ ነው ሲሉ አሞካሽተዋል፡፡

 

 

 

Read 4467 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 12:24