Saturday, 20 July 2019 11:50

በሃዋሣና በሲዳማ ዞን ከተሞች በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

 “ትግላችን ሠላማዊ ነው፤ ወጣቱ ምንም አይነት ሃይል ከመጠቀም መቆጠብ አለበት” ሲአን የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች በስጋትና ጭንቀት ተወጥረዋል

   ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ርዕሰ መዲና የሆነችው ሃዋሣ እና የዞኑ ከተሞች በውጥረት ሁከትና ግርግር የሰነበቱ ሲሆን፤ ወጣቶች ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በፈጠሩት ግጭት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን ምንጮች ጠቆሙ፡፡
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ከረፋዱ ጀምሮ ሃዋሣ በግርግር ማሳለፏን የሚያስታውሱት ምንጮች፤ በተለይ ከተለያዩ የአካባቢው የሲዳማ ዞን ተሰባስበው የመጡ ወጣቶች “ወደ ከተማዋ እንገባለን” በሚል ከፖሊስ ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸውን ይገልፃሉ፡፡
የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት የመበተን እርምጃም፣ ከሰአት በኋላ በርካቶቹ ወደየመጡበት መመለሳቸውን የገለፁት ምንጮች፤ ነገር ግን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በቡድን የተደራጁ ወጣቶች በድንጋይ መንገድ በመዘጋጋት፣ ጐማ በማቃጠል፣  ድንጋይ በመወርወርና ጩኸት በማሰማት ግርግር ሲፈጥሩ መዋላቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በሃዋሣ ከተማ በተለይ በአሞራ ገደል፣ ሎቄ፣ ታቦር አካባቢዎች ውጥረቱ አይሎ መዋሉን ምንጮች ጠቁመው፤ ይርጋለምን ጨምሮ በተለያዩ የሲዳማ ዞን ከተሞችም ሁከትና ግርግሮች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ግርግር በሐዋሳ አንድ ሰው በጥይት ጭንቅላቱን ተመትቶ መሞቱንና ሁለት  መቁሰላቸውን የጀርመን ድምጽ የሆስፒታል ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
በከተማዋና አካባቢው የፌደራልና የክልሉ ልዩ ፖሊሶችን ጨምሮ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተሽከርካሪ በመጠቀም ጭምር ቅኝት ሲያደርጉ መዋላቸውንም የገለፁት፤ የሃዋሣ ከተማ ከፍተኛ ጥበቃ ቢካሄድበትም በተለያዩ የሲዳማ ዞን ከተሞች ቅድመ ጥንቃቄ ባለመደረጉ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ከሃዋሣ በ25 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ለኩ ከተማ ተወልደው ማደጋቸውን የሚገልፁጽ አንድ ግለሰብ፤ ከተማዋ ከሐሙስ ጀምሮ በውጥረት ላይ እንደነበረች ጠቁመው፤ በርካታ የመንግስት ድርጅቶችና የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችም ተቃጥለዋል ብለዋል፡፡
ሐሙስ እለት በለኩ ከተማ የሆነውን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት እኚሁ ግለሰብ፤ ጠዋት ከ1ሰዓት ጀምሮ በሲኖትራክ መኪና ድንጋይና አፈር በአስፓልት መንገዶች ላይ በመድፋት መንገዶች እንዲዘጋጉ የተደረገ ሲሆን፣ መንገዶች በዚህ አኳኋን ከተዘጋጉ በኋላም ከተለያዩ የገጠር አካባቢዎች የተሰባሰቡ ወጣቶች፣ በየመንግስት መስሪያ ቤቶች እየገቡ በአማርኛ የተፃፉ ታፔላዎችን መነቃቀል መጀመራቸውን፣ ቀጥሎም በተቋማቱ ላይ ዘረፋ መፈፀማቸውን፣ ሰነዶችን መበተናቸውንና ተቋማቱን በእሣት ማቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
መንገዶችን የመዘጋጋት ሂደቱ በሲኖትራክ የታገዘ መሆኑን የገለፁልን ሌሎች ምንጮችም፤  እስከ ይርጋለም ያለው አውራ ጐዳና ሙሉ ለሙሉ መዘጋጋቱንም ጠቁመዋል፡፡
በለኩ ከተማ የከተማ አስተዳደር ም/ቤት ህንፃ፣ የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ፣ የገቢዎች ቢሮና የተለያዩ የመንግስት ተሽከርካሪዎች በወጣቶቹ መቃጠላቸውን ምንጮች ገልፀዋል፡፡
የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በዚህ መልኩ ካወደሙ በኋላ ወደ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ፊታቸውን ማዞራቸውን የሚናገሩት ምንጮቹ፤ የበርካታ ግለሰብ ቤቶች በድንጋይ መሰባበራቸውንም አመልክተዋል፡፡
“ይህ ሁሉ ሲፈፀም አንድም የፌደራል የፀጥታ ሃይል አልነበረም” ያሉት ምንጮች፤ የፌደራል የፀጥታ ሃይሎች ወደ ከተማዋ መግባት የጀመሩት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ነው፤ የገቡትም በተሽከርካሪ ሳይሆን በእግራቸው ነው” ይላሉ፡፡
ወጣቶቹ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በድንጋይ ፍልሚያ ውስጥ መግባታቸውንና የፀጥታ ሃይሎችም ተኩስ መክፈታቸውን፣ በዚህም አራት ሰዎች መገደላቸውንና እና 10 ያህል ወጣቶችም መቁሰላቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ከተማው  ከገጠር አካባቢ በመጡ ወጣቶች መሞላቱን፣ በዚህም የከተማው ነዋሪዎች እስከ ትናንት ከቤታቸው ሳይወጡ መዋላቸውንና ሁኔታው እጅግ አስጨናቂ እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡
መንገዶች በከፍተኛ ሁኔታ በመዘጋጋታቸው የታመሙ ሰዎችን እንኳ  በአምቡላንስ ሆስፒታል ማድረስ አስቸጋሪ እንደሆነ የገለፁት ምንጮች፤ ‹‹አመፁ እስከ አስር ቀን ይቀጥላል›› የሚል መልዕክት መሠራጨቱን ተከትሎ የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ ስጋት ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ከሌላ ብሔር የተወለዱ ቢሆንም ውልደትና እድገታቸው እዚያው ለኩ ከተማ  እንደሆነ የገለፁልን ምንጫችን፤ ተወልደን ባደግንበት ሀገር፣ በባይተዋርነትና በጭንቀት ግራ እንድንጋባ ሆነናል ብለዋል፡፡
ሌላው በይርጋለም ከተማ የሚገኙ ምንጫችን በበኩላቸው፤ በከተማዋ በለኩ ከተማ ከተፈፀመው ድርጊት ጋር ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙንና እስከ ትናንት ድረስ ከተማዋ ባለመረጋጋት ውስጥ መሰንበቷን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችም በተለያዩ አካባቢዎች መቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
“እኔ ልጆቼንና ባለቤቴን አስቀድሜ ወደ ሌላ ከተማ አሽሽቼ ነው ግራ ተጋብቼ የተቀመጥኩት” ያሉን ምንጫችን፤ የፀጥታ ሃይሎች በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸው ወደ ከተማዋ እስኪገቡ ድረስ የወደመው ንብረት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ሐዋሣ ከተማን ጨምሮ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት እስከ ትናንት መቋረጡን፤ በሃዋሣም ሆነ በሌሎች ከተሞች የንግድ እንቅስቃሴ እስከ ትናንት ሙሉ ለሙሉ ተስተጓጉሎ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፤ በሃዋሣና በተለያዩ አካባቢዎች ከትላንት በስቲያ ግጭቶች ተፈጥረው እንደነበር ጠቁሞ፤ በግጭቱም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡ በትናንትናው እለት አንፃራዊ ሠላም ሠፍኖ መዋሉንም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡    
ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የህዝበ ውሣኔ ለማደራጀት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤  የደቡብ ክልል ም/ቤት አስፈላጊ የውሣኔ ሰነዶችን እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲያቀርብለት የጠየቀ ሲሆን፤ ህዝበ ውሣኔው በቀጣይ 5 ወራት ውስጥ ይካሄዳል ብሏል፡፡
የክልሉ ም/ቤት የውሣኔ ሃሳብና የህዝበ ውሣኔ ጥያቄ ህዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም እንደቀረበለት የገለፀው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ እስካሁን ቦርዱን የማጠናከርና የቦርድ አባላትን የማሟላት ተግባር ሲያከናውን በመቆየቱ ፈጣን ምላሽ ሳይሰጥ መቅረቱን በመግለጽ፣ በቀጣይ 5 ወራት ውስጥ በሚደረግ ዝግጅት ህዝበ ውሣኔ ይካሄዳል ብሏል፡፡
ህዝበ ውሣኔውን ለማደራጀት ይረዳ ዘንድም የደቡብ ክልል ም/ቤት ከክልሉ መንግስትና ከዞኑ መስተዳድር ጋር በመመካከር በአሁኑ ወቅት የሲዳማ ዞንም የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሆና በማገልገል ላይ የምትገኘው የሃዋሣ ከተማ ላይ የሚነሱ የመብትና የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች የሚስተናገዱበትን አሠራር አዘጋጅተው እንዲያቀርቡለት፣ ህዝበ ውሣኔውን ለማከናወን የሚያስችል ጥበቃ ማለትም የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ፖሊስና የዞኑ ፖሊስ በትብብር የሚሰሩበትን እቅድ አውጥተው እንዲያሳውቁት እንዲሁም በሲዳማ ዞን ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች አባላት ከህዝበ ውሣኔው በኋላ የሚኖራቸውን ህጋዊ የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ግልጽ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማዕቀፍ የክልሉ ም/ቤት አዘጋጅቶ እስከ ቀጣይ ሐሙስ ሐምሌ 19 ቀን 2011 እንዲያቀርብ ቦርዱ አመልክቷል፡፡
በጽሑፍ የሚቀርብለትን የክልሉንና የዞኑን የዝግጁነት ማረጋገጫ መሠረት በማድረግም፣ ቦርዱ ህዝብ ውሣኔውን ማደራጀት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ በሲዳማ “ክልል ልሁን” ጥያቄ ጉዳይና በክልሉ በሚነሱ ተያያዥ ጥያቄዎች ላይ አተኩሮ ለ11 ቀናት ሲመክር የሰነበተው የደኢህአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በበኩሉ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ መወሰኑን በስብሰባው የተሳተፉ አካላት አስረድተዋል፡፡
ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የምርጫ ቦርድን ስራ በትዕግስት መጠባበቅ እንደሚገባ ያስገነዘቡት የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ጫዌቻ፤ የሲዳማ  ዞን አስተዳደር ከክልሉ መንግስትና ከደኢህዴን ጋር በመሆን በምርጫ ቦርድ እንዲሟሉ በተጠየቁ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ እየተወያየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ጥያቄውን በሠላማዊ መንገድ ሲያቀርብ የቆየው የሲዳማ ህዝብም፤ ቦርዱ በ5 ወራት ውስጥ ህዝበ ውሣኔ ለማደራጀት መወሰኑን ከግምት በማስገባት፣ በትዕግስት እንዲጠባበቅ ጠይቀዋል - አስተዳዳሪው::
የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን ዋነኛ መታገያው አድርጐ ላለፉት 30 አመታት ገደማ የቆየው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) በበኩሉ፤ የሲዳማ ወጣቶች ለምርጫ ቦርድ ቀጣይ ተግባራት ተባባሪ እንዲሆኑና የቦርዱን ክንውን በትዕግስት እንዲጠባበቁ አሳስቧል::
ከሰሞኑ በምርጫ ቦርድና በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለህዝቡ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ፤ የዘገየ ቢሆንም ተገቢ ነው ያሉት የሲአን ሊቀመንበር ዶ/ር ሚሊዮን ቱማቶ፣ የሲዳማ ህዝብም ያቀረበው ጥያቄ ፍትሃዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን በመገንዘብ፣ ፍትሃዊና፣ ህጋዊ ምላሽ እስኪሰጥ፣ በከፍተኛ ትዕግስትና ሠላማዊነት መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል::  የውሣኔው አፈፃፀም ከቀውስ የፀዳ ስርአት ያለውና በመግባባት የተሞላ መሆን አለበት - ብለዋል ዶ/ር ሚሊዮን፡፡ “ምንም አይነት ሃይል መጠቀም አይገባም ትግላችን ሠላማዊ ነው” ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ የዞኑ አስተዳደር፣ የክልሉ ም/ቤትና ደኢህአዴንም በምርጫ ቦርድ የተሰጣቸውን የቤት ስራ በአፋጣኝ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

Read 9799 times