Saturday, 20 July 2019 11:46

የአድዋ ማዕከል ዋነኛው የቱሪዝም መስህብ ይሆናል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በአዲስ አበባ ፒያሣ አፄ ሚኒልክ አደባባይ አጠገብ የሚገነባው “የአድዋ ማዕከል” ከሁለት አመታት በኋላ ሲጠናቀቅ የመዲናዋ ዋነኛው የቱሪዝም መስህብ እንደሚሆን ተገለጸ፡፡
የአድዋ ድልን የሚዘክር ሙዚየምን ጨምሮ ቤተ መጻሕፍትና የተለያዩ መዝናኛዎችን የሚያካትተውን ይሄን ማዕከል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ በራሱ ወጪ ያሠራዋል ተብሏል፡፡
የአድዋ ማዕከል ግንባታ ከሁለት አመት በኋላ ሲጠናቀቅ ማዕከሉ ከሚኖሩት አገልግሎቶች መካከል የአድዋ ሙዚየም (በውስጡ የጦርነቱን ሙሉ ታሪክ የሚዘክሩ ቅርሶች የያዘ)፣ ከ2ሺህ ሰው በላይ የሚያስተናግድ የአድዋ አዳራሽ (ለስብሰባና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል)፣ እያንዳንዳቸው 4መቶ ሰው የሚይዙ ሶስት ተጨማሪ አዳራሾች፣ ሲኒማ ቤት፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ጂምናዚየም፣ የህፃናት ማጫወቻና ማቆያ፣ የጌጣጌጥ መደብሮች፣ የቤተ ስዕል ማዕከላት፣ ዘመናዊ የአውቶቡስና ታክሲ ማቆሚያ፣ ከ6 መቶ በላይ መኪና ማስተናገድ የሚችል የመኪና ማቆሚያ ተርሚናል፣ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች እንዲሁም ለንባብ አገልግሎት የሚሆኑ የአረንጓዴ ስፍራዎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡
የዚህ ማዕከል ግንባታ በቻይናው “ቻይና ጂንግሱ ኢንተርናሽናል” ኩባንያ የሚከናወን ሲሆን፤ ማዕከሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ “ሁሉም ከዚህ ይጀምራል” “0.00” ኪሎ ሜትር” የሚል ጽሑፍ በጉልህ ይቀረጽበታል ተብሏል፡፡
 ማዕከሉ በዲዛይን አሠራሩ፣ የከተማዋ መለያ ምልክት እንዲሆን ተደርጐ የተዘጋጀ መሆኑንም ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የአድዋ ማዕከል በብድር በተገኘ 4.6 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚገነባም ታውቋል፡፡

Read 1183 times