Saturday, 20 July 2019 11:45

ሜሪጆይ 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን ያከብራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 በቀጣዮቹ 5 ዓመታት 349 ሚ. ብር ለማሰባሰብና አገልግሎቱን ወደ አምስት ክልል ለማስፋት አቅዷል
        

    በ1986 ዓ.ም ለ100 ያህል ችግረኛ ህፃናት ድጋፍ በማድረግ ሥራ የጀመረው ሜሪጆይ የልማት ማህበር የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዮ በዓል “25 የበጐ ስራ አመታትና የነገ ብሩህ ተስፋ” በሚል መሪ ቃል፣ ከነሐሴ 1 ቀን 2011 እስከ ጥር 30 ቀን 2012 ዓ.ም፣ ለተከታታይ ስድስት ወራት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር ተገለጸ፡፡
የልማት ማህበሩ ሐሙስ ረፋድ ላይ ፒያሳ በሚገኘው ኤልያና ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቅርቡ የሻሻለውን የበጐ አድራጐትና ማህበራት ኤጀንሲ አዋጅ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከግለሰቦች፣ ከበጐ ፈቃደኞችና ለጋሽ ድርጅቶች ከ349 ሚ.ብር በላይ ገቢ በማሰባሰብ አገልግሎቱን አሁን ተደራሽ ከሚያደርግበት ሶስት ክልሎች ወደ አምስት  ለማስፋትና ከፍተኛ እንቅስቃሴ ለማድረግ ማቀዱን፣ የልማት ማህበሩ መስራች ሲስተር ዘቢደር ዘውዴና የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ይሰማ ሸዋ ስዩም አስታውቀዋል፡፡
የልማት ማህበሩ በ1986 ዓ.ም ከአሜሪካ ኤምባሲ በተገኘ 41ሺህ 625 ብር የጀመረውን ስራ በማስፋት፣ በ25 ዓመታት ውስጥ 322 ሚ. ብር በማሰባሰብና በ190 ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎችና በበጐ ፈቃደኞች በመታገዝ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና በደቡብ ክልል ባደረጋቸው የኢኮኖሚ አቅም ግንባታና ኑሮ ማሻሻያ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በንፁህ የመጠጥ አቅርቦትና የአቅም ግንባታ ሥልጠና የተቀናጁ ፕሮግራሞች፤ 1.6 ሚሊዮን ዜጐችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረጉም ተገልጿል፡፡
ሜሪጆይ በቀጣዮቹ 5 ዓመታት የገቢ ምንጩን 58 በመቶ ለማሳደግ ማቀዱን ጠቁሞ፤ 52 በመቶውን ከአገር ውስጥ 48 በመቶውን ደግሞ ከውጭ በመሰብሰብ በሚያገኘው 349 ሚ 386 ሺህ 463 ብር፤ 25ሺህ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ህይወት የመቀየር፣ 3ሺህ 800 ህፃናትና አረጋዊያንን በማህበራዊ ስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ተጠቃሚ የማድረግ፣ 45ሺህ ህፃናትን የማስተማርና የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ስራዎችን የማከናወን እንዲሁም በተቀናጀ የመከላከልና የህክምና አገልግሎት ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ መያዙንም በጋዜጣዊ መግለጫው ተብራርቷል፡፡
ከነሐሴ 1 እስከ ጥር 30 ቀን 2012 በሚቆየው የስድስት ወር የብር ኢዮቤልዮ በዓል አከባበር ላይ የፎቶግራፍ አውደርዕይ፣ የእግር ጉዞ፣ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድሮች፣ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ መሰናዶዎች፣ ዘጋቢ ፊልም፣ የመጽሔት ዝግጅትና በሜሪጆይ የ25 ዓመት ጉዞው ድጋፍ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር፣ የገቢ ማስገኛ ሁነቶችና የልገሳ መርሃ ግብሮች በአዲስ አበባና በሐዋሳ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

Read 885 times Last modified on Saturday, 20 July 2019 12:11