Tuesday, 16 July 2019 10:48

ቴለር ስዊፍት በ185 ሚ. ዶላር ገቢ የአለማችን ቀዳሚ ዝነኛ ሆናለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ሪሃና በ600 ሚ. ዶላር ሃብት ከሴት ድምጻውያን 1ኛ ናት


        ታዋቂዋ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቴለር ስዊፍት በፎርብስ መጽሄት የ2019 የአለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ የአንደኛ ደረጃን መያዟን ባለፈው ረቡዕ የወጣው አመታዊ መረጃ የጠቆመ ሲሆን ሪሃና ከአለማችን ሴት ድምጻውያን መካከል በሃብት ቀዳሚነትን መያዟ ተነግሯል፡፡
የ29 አመቷ ድምጻዊት በአመቱ ከግብር በፊት በድምሩ 185 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የጠቆመው ፎርብስ መጽሄት፣ የገቢዋ መጠን ከአንድ አመት በፊት ከነበረው የ131 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና አብዛኛውን ገቢዋን ያገኘችውም ከሙዚቃ ኮንሰርቶች መሆኑን አመልክቷል፡፡ ቴለር ስዊፍት እ.ኤ.አ በ2016 በተመሳሳይ ሁኔታ የአለማችን ቁጥር አንድ ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኛ እንደነበረችና በወቅቱ 170 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
በአመቱ በድምሩ 170 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘችዋ የሪያሊቲ ቲቪ ሾው አቅራቢዋና የመዋቢያ ቁሳቁስ አምራች ኩባንያ ባለቤት የሆነችው ካይሌ ጄነር የሁለተኛነት ደረጃን ስትይዝ፣ አሜሪካዊ ራፐር ካይኔ ዌስት በ150 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በ127 ሚሊዮን ዶላር፣ የሙዚቃ ደራሲው ኤድ ሼራን በ110 ሚሊዮን ዶላር፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ109 ሚሊዮን ዶላር፣ ኔይማር በ105 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውም ተነግሯል፡፡ በአመቱ የፎርብስ መጽሄት ከፍተኛ ተከፋዮች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች የአለማችን ዝነኞች መካከልም፣ በ93 ሚሊዮን ዶላር 12ኛ ደረጃን የያዘው የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቹ ሮጀር ፌደረር፣ በ84 ሚሊዮን ዶላር 19ኛ ደረጃን የያዘው ኤልተን ጆን፣ በ62 ሚሊዮን ዶላር 36ኛ ደረጃን የያዘችው ሪሃና ይገኙበታል፡፡ በ2019 የፎርብስ መጽሄት የአለማችን ከፍተኛ ተከፋዮች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት 100 ዝነኞች ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ ከግብር በፊት 6.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ ታዋቂዋ ድምጻዊት ሪሃና ከአለማችን ሴት ድምጻውያን መካከል በሃብት የአንደኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆመው ፎርብስ መጽሄት፣ የድምጻዊቷ አጠቃላይ ሃብት 600 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ከሰሞኑ አስነብቧል፡፡ ሌላኛዋ ተወዳጅ ድምጻዊት ማዶና በ570 ሚሊዮን ዶላር የአመቱ ሁለተኛ ባለጸጋ ሴት ድምጻዊት ስትባል፣ ሴሌን ዲዮን በ450 ሚሊዮን ዶላር፣ ቢዮንሴ በ400 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

Read 3705 times