Tuesday, 16 July 2019 10:16

አያዎ…

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ‹‹ካላታገለኝና ካልፈተነኝ፣ ልኬ አይደለም!...››


       በሌሎች አይን ሲታይ ባለሁለት መልክ ነው፤ ሰውዬው… በተለያዩ ሰዎች ልቦና ውስጥ ፍጹም ለየቅል ምስል አለው፤ ‹‹ኤርሚያስ አመልጋ›› የሚለው ስም፡፡
እንዲህ ነው ሰውዬው…
በዚህ ውዳሴና አድናቆት ሲጎርፍለት፣ በዚያ ወቀሳና ትችት ይዘንብበታል፡፡ ለአንዱ ፈር ቀዳጅ ባለ ሃብት፣ ስኬታማ የቢዝነስ ሰው፣ የአዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦች አፍላቂና እሳት የላሰ ኢኮኖሚስት የሆነው ኤርሚያስ አመልጋ፤ ለሌላው ደግሞ ብዙዎችን ለኪሳራ ዳርጓል (በተለይ ከአክሰስ ሪል እስቴት ጋር በተያያዘ) በሚል የወቀሳ መዓት የሚዘንብበትና የሚወገዝ ሰው ነው፡፡
የኢኮኖሚክስ እውቀቱንና አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦችን የማፍለቅ ክህሎቱን በማድነቅ ምስክርነታቸውን የሚሰጡለት በርካቶች የመሆናቸውን ያህል፣ ከአቅሙና ከሚችለው በላይ ለመስራት የሚታትር እጅግ ሩቅ አላሚ ‹‹ኦቨር አምቢሽየስ›› በመሆኑ ስራዎቹን ከግብ ለማድረስ ሲቸገር አይተናል በሚል የሚተቹትም አሉ፡፡ ስራዎቹን ከግብ ለማድረስ ሲቸገር ማየታቸውን የማይክዱ ሌሎች በበኩላቸው፣ በምክንያትነት የሚጠቅሱት ‹‹ኦቨር አምቢሽየስ›› ሳይሆን ‹‹ኦቨር ኳሊፋይድ›› መሆኑን ነው፡፡ እነሱ እንደሚሉት፤ ሰውዬው ደጋግሞ ተደናቅፎ ደጋግሞ የወደቀው ከአገሪቱ ቢዝነስና ኢኮኖሚ ቀድሞ የተራመደና ከሚገባው በላይ ብቃት የተላበሰ በመሆኑ ነው፡፡
ኤርሚያስ ማንም አስቦት ከማያውቀው ተራ የሚመስል ነገር ውስጥ ትልቅ ሃብት ፈልቅቆ የማውጣት ብቃት፣ ብዙዎች ልብ ከማይሉት ጥግ አጀብ የሚያሰኝ የቢዝነስ ሃሳብ የማፍለቅ ወደር የለሽ ብቃት እንደተላበሰ የሚናገሩ በርካቶች ቢሆኑም፤ አንዳንዶች ግን እሱ ጎበዝ የቢዝነስ ሃሳብ አፍላቂ እንጂ ጎበዝ የቢዝነስ መሪ አይደለም በማለት በአስተዳደር ላይ ክፍተት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
አዳዲስ ቢዝነሶችን በመፍጠር ባልተሄደበት መንገድ ለመሄድ የማያመነታ ደፋር መሆኑን የሚናገሩለት ብዙ አድናቂዎች ያሉት ሰውዬው፤ ከመጠን ያለፈ አደጋን የማስተናገድ ፈቃደኝነቱና ፈተና አነፋናፊነቱ አሳሩን የሚያሳየው ‹‹መከራ ወዳድ›› ነው ብለው የሚተቹትም በርካቶች ናቸው:: እነዚህኞቹ በአብነት ከሚጠቅሱት ጉዳይ መካከል አንዱ፣ የአክሰስ ሪል እስቴት ቀውስ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በአገሪቱ ተሞክሮ በማያውቀው የስቲል ስትራክቸር ቴክኖሎጂ ቤቶችን ለመገንባት መወሰኑ፣ አስተማማኝ የግንባታ  ግብዓቶች አቅርቦትና የተመቻቸ የግንባታ ምህዳር በሌለበት ሁኔታ ቤቶቹን ቃል በገባው መሰረት በጊዜው ሰርቶ ካላጠናቀቀ ለቤት ሰሪዎች በየወሩ ቅጣት ለመክፈል መስማማቱ ኩባንያውን ለቀውስ ከዳረጉት የኤርሚያስ ድፍረቶች መካከል ይገኙበታል ባይ ናቸው- እነዚህኞቹ፡፡
የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ ባልተገባ ድፍረት ራሱን ወደ አደጋ መጎተቱን፤ ከመደበኛው አሰራርና አካሄድ አፈንግጦ ባልተሞከረ መንገድ እየተጓዘ በራሱ ላይ ችግር መጥራቱን፤ እንደ ጀብደኛ ገጸ - ባህሪ ዝም ካለና በእርጋታ ከሚፈስስ ጉዞ ይልቅ ትግል ወዳጅነቱን፣ ፈተና አነፍናፊነቱን እንደማይወዱለት ነው - እነዚህኞቹ የሚናገሩት፡፡
ችግሩ ግን፣ እነሱ የማይወዱለትን ፈተና እሱ ይወደዋል…
‹‹ዝም ያለ ነገር አልወድም!... እንኳንስ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት፣ ቀለም ራሱ ፈዘዝ ወይም ለስለስ ሲል አልወድም፡፡ ደማቅ ቀለም ነው ምርጫዬ፤ ከደማቅም የመጨረሻው ደማቅ!... በተለየ ሁኔታ የምወዳቸው ቀለማት ደማቅ ቀይና ደማቅ ጥቁር ናቸው፡፡ የአክሰስ ካፒታል፣ የአክሰስ ሪል እስቴትና የዘመን ባንክ መለያ ቀለም ቀይ ነው፡፡ ቢዝነስና ኢንቨስትመንትም ለስላሳ ወይም የተለመደ አይነት ሲሆንብኝ ደስ አይለኝም፡፡ ስራው ካላታገለኝና ካልፈተነኝ ልኬ አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡›› ይላል ሰውዬው፡፡    
(“የማይሰበረው ኤርሚያስ አመልጋ”፤ አንተነህ
ይግዛው እንደጻፈው፤ ሰኔ 2011 ዓ.ም)

Read 1939 times Last modified on Thursday, 18 July 2019 11:02