Tuesday, 16 July 2019 10:09

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

    “ራስህን ስትረዳ ስሜትህን መግራት አያዳግትም”
                             

           ሰውየው በረዥምና በማይታየው እጁ ብዙዎችን አድቅቋል፡፡ አሁን ግን ጊዜውን ጨርሶ መሰናበቻው ደረሰ፡፡ በከባድ ህመም እየተሰቃየ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር አንዳንድ ጊዜ “ሞተ”፣ “አለቀለት” ብለው ቤተሰቦቹ ሲዘጋጁ አጅሬ ነፍስ ይዘራል፡፡ ሲታመምና ሲሻለው ብዙ ዓመታት አለፉ፡፡ እሱ እንደሚያስበው፣ እየሞተ የሚድንበት ምክንያት ወደ ውጭ ሀገራት እየተመላለሰ በሚደረግለት የህክምና እርዳታና በሚወስዳቸው መድሃኒቶች ፍቱንነት ይመስለዋል:: ረዥም ጊዜ በ “መኖር” እንዲቀጣ የተፈረደበት መሆኑን አላወቀም፡፡ ከስቃይ ለመገላገል ማረፍ ቢፈልግ እንኳ አይችልም፡፡ ለምን?
***
ወዳጄ፡- ጨርሶ በማታውቀው ምክንያት መኖርህን የሚፈታተኑ አበሳዎች ብዙ ናቸው፡፡ በየጊዜው ፊታቸውን እየለዋወጡ ይፋለሙሃል:: ዘመንህን ሁሉ መከራን እያስተናገድክ “እንድትኖር” የተፈጠርክ ይመስል… ትበሳጫለህ፣ ተስፋ ትቆርጣለህ፡፡ ነገር ግን ካንተ በላይ ፍዳቸውን የሚያዩ ሌሎች ሰዎች አሉ፡፡ ልዩነታችሁ እነሱ ዛሬ ላይ ሆነው ነገን መመልከት የቻሉ፣ የበደላቸውን ምንጭ አውቀው፣ ችግሩን ተላማምደው ትግላቸውን ከችግሩ ጋር ሳይሆን ችግሩን ከፈጠሩት ጋር ማድረጋቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው የማይሰበሩት፡፡
ወዳጄ፡- ዕድሜ ተሰፍሮ የታደለው ማንም የለም::
ማንም የነገን አያውቅም፡፡ የበቁ ጠቢባን ካልሆኑ በቀር ለሌሎቻችን እያንዳንዷ ቀን የሙከራ ጊዜያችን ናት፡፡ አለመኖርን ላለማሰብ እንሞክራለን፡፡ በእጃችን በጨበጥናት በዚች ተዓምራዊ ቅጽበት ውስጥ ነገን ተስፋ እናደርጋለን፣ ዘለዓለማዊነትን እናስባለን፡፡
ወዳጄ፡- መኖር ለብዙዎች ፈተና ነው:: ባላሰብክበት ሰዓት ድንገት ተንደርድረው በመምጣት ወደ ሞትህ የሚገፈትሩ ንዴትና ብስጭቶች ስሜትህ ውስጥ ብቅ፣ ጥልቅ ማለት ሲጀምሩ አትኩሮትህን ሁሉ ትዕግስት ላይ በመሰብሰብ፣ በውስጥህ የሚንፈራገጠውን አውሬ “እረፍ” ማለት መቻል አለብህ፡፡ ትዕግስት ራስን ከመረዳት ይወለዳል:: ራስህን ስትረዳ ስሜትህን መግራት አያዳግትም:: ያኔ ንዴትና ብስጭት በለኮሱት የእሳት ነበልባል በሚፈጠር ብርሃን አካባቢህን ለማየት ትችላለህ:: መቻል ከሙከራ፣ ሙከራም ተስፋ ካለመቁረጥ የሚገኝ በረከት ነው፡፡
ወዳጄ፡- በያንዳንዱ ሰው ልቡና ውስጥ መኖርና አለመኖር ባልተናነሰ ዐቅም ይታገላሉ:: ተወልደህ አንድ ዓመት ሲሞላህ፣ አንድ ዓመት ወደ ሞትህ እየቀረብክ ነው፡፡ ሃምሳ፣ ስልሳ፣ ሰባ… እያልክ ስትገሰግስ በፍጥነት እየተጠጋኸው፣ እሱም ወዳንተ እያቀና መሆኑን እንዳትረሳ፡፡ አንድ ቀን ትገናኛላችሁ:: ያኔ መኖርና አለመኖር አንድ ይሆናሉ:: “አቤት” ያልከው ተፈጥሮ ስለፈለገችህ ስለሆነ ሞት አላተረፈብህም፡፡
ወዳጄ ፡- እኔ እንደሚገባኝ፤ በገነት መኖር ማለት ራስን ለመልካም ሃሳብ ማስገዛት ማለት ነው:: ቅናት፣ ተንኮልና የመሳሰሉት ስሜቶች፤ የህሊና ገነታችንን የሚያቆሽሹ የአስተሳሰብ ጥቀርሻዎች ናቸው፡፡ መልካምነትና ምክንያታዊነት አንድም ሁለትም ይሆናሉ፡፡ መልካም ሰዎች ለመውደድም ሆነ ለመጥላት ሰበብ አይፈልጉም፡፡ የሰውየው ወይም የእንስሳው መንፈስ ራሱ ይስባቸዋል ወይም ይገፈትራቸዋል:: እንደ ምክንያታዊ ሰው “ለምን”፣ “እንዴት” የሚሉ ከጥቅም ጋር የተዛመዱ ጥያቄዎች አያስጨንቋቸውም፡፡ ጽድቅና ኩነኔያቸው የተቀበረው ደመነፍሳቸው ውስጥ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ወደ ራሳችን ጉዳይ ስንመጣ፤ ዋነኛው ማህበራዊ ችግራችን ስራ አጥነት ነው:: አድሏዊ ስርዓት ባለበት፣ ማህበራዊ ዋስትና በሌለበት አገር፤ ዜጐች ስራ አጥ የሚሆኑት ስራው ስለሌለ ብቻ አይደለም:: የስርዓቱ አድሏዊነት “አልመረጣችሁኝም”፡፡ በሚል ሰበብ ከስራ ገበታቸው ስለሚያፈናቅልም ጭምር ነው::
የተጫነባቸውን የጐሳ ፖለቲካ ተቋቁመው፣ ለወገኖቻቸው የስራ ዕድል የከፈቱ ግዙፍ የንግድ ኩባንያዎችን፣ ባንኮችንና አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችን በጥረታቸው ያቋቋሙ ታላላቅ ኢትዮጵያውያንም የተበላሸው ስርዓት ውስጣቸውን አምክኗል፡፡ ገንዘባቸው እንዲዘረፍ፤ ንብረታቸው እንዲባክን በማድረግ ሊሰብራቸው ሞክሯል፡፡
ወዳጄ፡- “ስራ አጥነት ጊዜ ቆጥሮ የሚፈነዳ ቦንብ ነው” ይባላል” ራስንም ሌላውንም የማይምር፡፡ ታላቁ ቮልቴር፤ “አለመስራትና አለመኖር አንድ ናቸው” በማለት ጽፏል፡፡ ጥያቄው፤ “ዜጐች በችሎታቸው ሰርተው መኖር የማይችሉበት ሥር የሰደደው አግላይ ስርዓት፣ ሪፎርም የሚደረገው መቼ ነው?” የሚል ነው፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፤ ባለ ረዥሙ እጅ ሰውዬ፣ የመሞቻቸው ቀን ቢደርስም አልሞቱም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምድር ላይ በነበሩበት ጊዜ ከስራቸው አፈናቅሎ ያሰራባቸው ነፍሳት የመልዓከ ሞትን ዓይን እየጋረዱ፣ ሰውየውን እንዳያይ ስለሚያደርጉት ነበር:: ነፍሳቱ ጣዕረ ሞትን (Ghost) በየተራ ወደ ምድር እየላኩ፣ ሰውየው መብላት ሲፈልግ እንዳይበላ፣ መጠጣት ሲያምረው እንዳይጠጣ፣ መተኛት እየፈለገ ዕንቅልፍ እንዳይወስደው በማድረግ እየተበቀሉት ስለሆነ ነው፡፡
ሠላም!!

Read 706 times