Tuesday, 16 July 2019 10:00

ፈጣጣው

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(0 votes)


                        የጋዜጣው ዜና እንደ አጭር ልብወለድ
                            ምንጭ- ‹‹ዘ ወርልድስ ዊርደስት ኒውስፔፐር ስቶሪስ›› ትርጉም፡- ኢዮብ ካሣ


          ይህ አስገራሚ ታሪክ የተፈፀመው በበኪንግሃም ቤተ መንግስት እንግሊዝ አገር ውስጥ ነወ፡፡ ሐምሌ 1982 ማለዳ ላይ ነበር:: ህይወት የተለመደ ዑደቷን ቀጥላለች:: ንግሥት ኤልሳቤጥን ከእንቅልፏ ድንገት አንድ የማታውቀው ሰው ቀሰቀሳት፡፡ ሰውየው ባዶ እግሩን ነበር፡፡ ጂንስ ሱሪና የአደፈ ሸሚዝ ለብሷል፡፡ የተሰበረ የሲጋራ መተርኮሻ በእጁ ይዞ፣ ንግሥቲቱ አልጋ ጫፍ ላይ ተቀምጧል:: የንግሥቲቱ አልጋ ልብስ ላይ ደም ተንጠባጥቧል::
አስፈሪ ለሆኑ አሥር ደቂቃዎች ያህል ሰውየው ንግሥቲቱን አነጋግሯታል፡፡ አንዳችም የማስፈራራት እንቅስቃሴ ለማድረግ አልሞከረም፡፡ ንግሥቲቱ ከድንገተኛ ውጥረቷ እፎይ ያለችው የግል አገልጋይዋ ወደ መኝታ ክፍሏ በገባች ጊዜ ነበር፡፡ አገልጋይዋ ወደ ንግሥቲቱ ክፍል እንዴት ተሽሎክሉኮ እንደገባ ያልታወቀውን እንግዳውን ሰውዬ ተመለከተችውና “ወላዲተ ቅድስት! ይህን የመሰለ ሰይጣን እዚህ ምን ይሰራል!” አለች፡፡
እውነቷን ነው፡፡ የተከበረችው የእንግሊዝ ንግሥት መኝታ ክፍል ውስጥ ይሄ ሰውዬ ምን ይሰራል? ወደ መኝታ ክፍሏስ እንዴት ገባ? ጥበቃዎቹስ የት ነበሩ? ኧረ ለመሆኑ ልሁል ፊሊፕስ የት ነበር? የዚህ ልብ አንጠልጣይና ስሜት ቀስቃሽ ሙሉ ታሪክ አደባባይ የወጣው ከብዙ ሳምንት በኋላ ነበር፡፡
ወደ ንግሥቲቱ የመኝታ ክፍል የገባው እንግዳ ሰው ሚካኤል ፉጋን ይባላል፡፡ ዕድሜው 33 ነው፡፡ የምዕራብ ለንደን ነዋሪ ሲሆን፤ በጌጣጌጥ ሥራዎች ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ፉጋን ፍርድ ቤት የተጠራው ንግሥቲቱ መኝታ ክፍል ውስጥ በመግባቱ አይደም፡፡ ቀደም ሲል በፈፀመው ሌላ ወንጀል ነው፡፡ ቀደም ብሎም ሚካኤል ፉጋን ቤተ መንግስቱ ውስጥ ገብቶ ነበር ቢባል የማይታመን ጉዳይ ሊመስል ይችላል፡፡ ግን እውነት ነው፡፡ ሰኔ 7 ምሽት ላይ ቤተ መንግስቱ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የተከሰሰው ግን ግማሽ ጠርሙስ ቪኖ በመስረቁ ነበር፡፡
የዛሬው “የለመደች ጦጣ…” መሆኑ ነው:: ሚካኤል ፉጋን በብረቶቹ ላይ ዘሎ ከወጣ በኋላ በፍሳሽ ቱቦዎቹ ላይ ተንጠልጥሎ በአልጋ አንጣፊዋ መኝታ ክፍል መስኮት በኩል ብቅ አለ፡፡ ሠራተኛዋ ከፀሎት ቤት ወደ ክፍሏ ገና መመለሷ ነበር፡፡ በመስኮቱ በኩል የአንድ እንግዳ ሰው ከሲታ ፊት ብቅ ሲል ድንገት ተፋጠጡ፡፡ በአለችበት በድን ሆና ቀረች፡፡ ከአፍታዎች በኋላ እየሮጠች ሄዳ የገጠማትን ድንገተኛ ጉዳይ ለቤተ መንግስቱ የሥራ ባልደረቦቿ ብትነግራቸውም የተቀበላት አልነበረም፡፡ ጭራሽ “ፃዕረ ሞት ነው ያየሽው” እያሉ አፌዙባት፡፡
ፉጋን ወዲህ ወዲያ እያለና በቤተመንግስቱ ውስጥ ያሉትን ስዕሎች እየተመለከተ ወደ ክፍሎቹ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡ ጥቂት ክፍሎችን እንዳለፈ በአንዱ በር ላይ “ልዕልት እና” በሌላኛው ደግሞ “ማርክ ፊሊፕ” የሚል አነበበ፡፡ እንቅልፍ ላይ ስለሚሆኑ ሊረብሻቸው አልፈለገም፡፡ ቀጥሎ “ልዑል ፊሊፕ” ተብሎ የተፃፈበት በር አገኘ፡፡ ከዚያም የልዑል ቻርለስ የግል ፀሐፊ ክፍል ውስጥ ገባ፡፡ በክፍሉ ውስጥ ለግማሽ ሰዓት ያህል ቆየ፡፡ ቢፈልጉ ይያዙኝ ብሎ ነው፡፡ ማንም ግን ዝር አላለም፡፡
በክፍሉ ውስጥ አዲስ ለተወለደው ለልዑል ቻርለስና ለልዕልት ዲያና ልጅ በርካታ ስጦታዎች ተቀምጠዋል፡፡ ከህፃኑ ልጅ ቆዳ ቦት ጫማ አጠገብ አንድ የወይን ጠጅ ጠርሙስ አለ፡፡ ፉጋን ሆዬ! ያንን የወይን ጠጅ ጠርሙስ ከፈተና ሁለት ብርጭቆ ተጐነጨለት፡፡ “እፎይ፤ ጠምቶኝ ነበር፡፡ ለንግሥቲቱ ትልቅ ሥራ ስሰራ ነው የዋልኩት” አለ ፉጋን - ለራሱ፡፡ ወቸ ጉድ! በዚህ ሁሉ ሰዓት ውስጥ‘ኮ አንድ ሰው መጥቶ እንዲይዘው ፈልጐ ነበር፡፡ “እናታቸውን! ማንም የለም” አለ በመጨረሻ፡፡
ፉጋን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ቤተመንግስቱ የገባው አምባሳደሮች መግቢያ በር አጠገብ ባለው ብረት ላይ ተንጠላጥሎ ነበር፡፡ ከጠዋቱ 12፡45 ሲሆን የግቢው ፖሊሶች አንድ እንግዳ ሰው እንደገባ ምልክት ያገኙ ቢሆንም፣ የፖሊስ ቁጥጥር ክፍሉ ማስጠንቀቂያውን ችላ ብሎ አለፈው፡፡
ምድር ቤት ውስጥ ባለ አንድ ያልተቆለፈ መስኮት በኩል ዘሎ ወደ አንድ የቴምብር ክፍል ውስጥ ገባ፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የንጉሣውያኑ ቴምብሮች ክፍሉ ውስጥ አሉ:: ሲገባ የድንገተኛ ጥሪ ደወል ተሰምቶ ነበር:: ማንም ከቁብ የቆጠረው አልነበረም፡፡ አጅሬ በዚያው መስኮት ተመልሶ ወጣና በቋሚው የውሃ አሸንዳ ላይ ተንጠላጥሎ ሽቅብ ወጣ፡፡
ጫማውንና ካልሲውን አወለቀና ሠራተኛዋ ባልዘጋችው ሌላ መስኮት በመዝለል ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ለሩብ ሰዓት ያህል በቤተ መንግሥቱ ኮሪደር ላይ ቢንጐራደድም፤ አንድም የጠየቀው ሰው አልነበረም፡፡
ሚካኤል ፉጋን፤ በበኪንግሃም ቤተ መንግስት ዙሪያ የተተከሉትን ልዩ ልዩ የማስጠንቀቂያ መሣሪያዎች አልፎ በግድግዳው ላይ የተሰቀሉትን ስዕሎች እየተከተለ፣ ከጋለሪው ጋር ወደ ተያያዘው የንግሥቲቷ የግል ክፍል ደረሰ፡፡
የሲጋራ መተርኮሻ በተመለከተ ጊዜ ራሱን የማጥፋት ወይም ህይወቱን የመተርኮስ ሀሳብ ብልጭ አለበት፡፡ መተርኮሻውን ሰበረና 1፡15 ሲሆን ስባሪውን እንደያዘ ወደ ንግስቲቱ መኝታ ክፍል አመራ፡፡ ንግስቲቱ ፊት የእጁን ደም ስር በመተርኮሻው ሊቆርጥ አስቦ ነበር:: እንዲያውም ወደ መኝታ ክፍሉ ሲገባ የቀኝ አውራ ጣቱ እየደማ ነበር፡፡
አገልጋይዋ የደረሰችው እንግዲህ ይሄኔ ነበር:: ሁለቱ ሴቶች እንዴት እንደሚያስወጡት መላው ጠፋቸው፤ በመጨረሻ ንግሥቲቱ፤ አገልጋዩዋ ሰውየውን ከክፍሉ ካስወጣች በኋላ ሲጋራ እንድትሰጠው አዘዘቻት፡፡ አገልጋይዋ እንደታዘዘችው አደረገች፡፡ ወደ አንደኛው ጓዳ ይዛው ሄደች፡፡ በዚህ ጊዜ የቤተመንግስቱ እንግዳ ተቀባይ ከሄደበት ተመልሶ መጣ፡፡ ምን እንደምታደርግ ግራ ገብቷት የነበረችው ንግሥት፤ ወዲያውኑ ሁኔታውን ለእንግዳ ተቀባዩ ነገረችው፡፡ እንግዳ ተቀባዩ ለፉጋን ተጨማሪ ሲጋራና ውስኪ ሰጠው፡፡ እንደ መደለያ መሆኑ ነው፡፡
ፉጋን ውስኪውን ከደጋገመ በኋላ ዳግም ወደ ንግሥቲቱ ክፍል ለመግባት ያዙኝ ልቀቁኝ ይል ጀመር፡፡ እንግዳ ተቀባዩ ግን በጄ አላለም፡፡ የንግሥቲቱ አገልጋይ ወዲያውኑ ወደ ፖሊሶቹ ሄዳ ጉዳዩን አሳወቀች፡፡ ተረኛው ፖሊስ ከተፍ አለ፡፡
የአገሬው የወሬ እናት የሆኑት የለንደን ጋዜጦች፤ የበኪንግሃም ቤተመንግስት አብይ ርዕሰ ዜናቸው ሆነ፡፡ ከሁሉም ጋዜጦች ወሬውን ከህዝቡ ጆሮ ለማድረስ ‹‹ዘ ዴይሊ ኤክስፕሬስን›› የቀደመ ማንም የለም፡፡ ‹‹በ30 ዓመት የንግሥና ዘመኗ፣ ከባዱና አሳፋሪው የደህንነት ጥበቃ መላላት›› በሚል ርዕሰ ዝርዝር ዜናውን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ‹‹ዘ ሰን›› የተሰኘው ጋዜጣ ደግሞ ‹‹በሞል ጎዳና ስትጓዝ ውሃ ከጠማህ ለምን ወደ በኪንግሃም ቤተ መንግስት ጎራ ብለህ አንድ ሁለት ብርጭቆ የወይን ጠጅ አትጎነጭም?›› በማለት አፌዘ፡፡
በቤተ መንግሥቱ በተፈጠረው ድንገተኛና ያልተጠበቀ ሽብር፣ ብዙዎቹ የመንግስት ባለሥልጣናት ተደናገጡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሚስስ ታቸር በኪንግሃም ቤተ መንግስት መጥታ ለደረሰው ሁሉ በመንግስት ስም ይቅርታ ጠየቀች:: በአደጋ ጊዜ እንደሚሆነው ሁሉ አስቸኳይ የምክር ቤት ስብሰባም ተጠርቷል፡፡ የአገር ውስጥ ፀጥታ ኃላፊው በደህንነት ጉዳይ ላይ ንግግር ለማድረግ በወጣ ጊዜ በአድማጮቹ ገጽታ ላይ ንዴትና ብስጭት ይስተዋል ነበር፡፡ ‹‹በቅርብ ዓመታት ተጨማሪ የደህንነት እርምጃዎችን በበኪንግሃም ቤተመንግስት እንዳደረግን ቢታወቅም፣ በቅርቡ የተከሰተው ሁኔታ ገና ብዙ እንደሚቀረን ይጠቁመናል፡። ከዚህ ብዙ እንማራለን፡፡›› እያለ ኃላፊው በተናገረ ጊዜ፤ የምክር ቤቱ አባላት በማሽሟጠጥና በማፌዝ አፋቸውን አጣመሙ - የሽርደዳ ሹክሹክታ ሰፈነ፡፡
ፉጋን የመጀመሪያ ክሱን ለማድመጥ ወደ ፍርድ ቤቱ በሄደ ጊዜ አዳራሹ በሰዎች ተጨናንቆ ነበር:: እጁን ወደ ኋላ አድርጎ ወደ ተከሳሽ መቆሚያው ሥፍራ አመራ፡፡ በየጊዜው ቀና እያለ ቤተሰቦቹን ይመለከትና ፈገግ ይላል፡፡ ፉጋን ሳቅ አለና ለሚስቱ ለክሪስቲንና ለእናቱ ለኢቪ እጁን አወዛወዘ፡፡ እራሱን እያዝናና ያለ ይመስል ነበር፡፡ የንግሥቲቱ ስም በተጠራ ጊዜ ግን ተናደደ፡፡ ደሙ ፈላ፡፡ የሚናገረው ጠፋው፡፡ ‹‹የንግሥቲቱን ስም እዚህ እንዳታነሳ! ኋላ ነግሬሀለሁ!›› ብሎ ጠበቃው አፈጠጠበት:: ‹‹የንግስቲቷ ስም እዚህ ውስጥ ከሚነሳ ጥፋተኛ መሆኔን ማመን ይቀለኛል›› አለ፡፡
በእነዚህ ሁሉ አስደንጋጭና እንግዳ የሆኑ ጉዳዮች ውስጥ በእርግጥም አንድ ነገር ግልጽ እየሆነ መጣ:: ሚካኤል ፉጋን ንግሥቱቱን ከማክበርም አልፎ ያመልካታል፡፡ ለዋናው ጥያቄ ፍርድ ቤት በቀረበ ሰዓትም እንኳን እንግዳ ባህርይው‹ፈጣጣነቱ›› አልለቀቀውም፡። እንደ ተዋናይ ቅንድቡን ወዲያና ወዲህ እያነቃነቀ፣ ቴአትራዊ በሆነ እንቅስቃሴና ፈገግታ ሪፖርተሮቹን በዓይኑ ሲጠቅስ ይስተዋላል:: እንደውም ይባስ ብሎ የላይኛውን አርቴፊሻል ጥርሶቹን አውጥቶ በድዱ ከገለፈጠ በኋላ ከአስረኞቹ ላይ ጥቂት ምግብ አንስቶ በላ፡፡ በፍርድ ቤቱ ውስጥ መሀላ እንዲያደርግ በተጠየቀ ጊዜ፤ ‹‹እኔ ሀይማኖት የለኝም፣ የእርስዎ አምላኪ ነኝ!›› አለ:: ፉጋን እግዚአብሔር መኖሩን የማያምኑ ሰዎች የሚሰጣቸውን መሀላ እንዲወስድ ተፈቀደለት፡፡ ከላይ ጀምሮ አነበበው፡፡
‹እባክህ ስምህን በግልጽ አንብበው!›
በካርዱ ጫፍ ላይ የሰፈረውን ትዕዛዝ ከጣራ በላይ በሆነ ድምፅ ደግሞ አነበበ፡፡ ዳኛው እንኳ ፈገግ አለ፡፡
‹‹ለምንድነው ወደ ቤተ መንግስቱ የገባኸው?›› የዳኛው የመጀመርያ ጥያቄ ነበር፡፡
‹‹አንድ የሆነ ድምፅ…›› ብሎ አልቀጠለም፡፡
ዳኛው ዐይን ዐይኑን እያዩ ትንሽ ከጠበቁት በኋላ ‹‹ጥያቄውን መልስ እንጂ?›› አሉት፡፡
ፉጋን ኤሌክትሪክ እንደያዘው ሰው ዝም ጭጭ አለ፡፡ ዳኛው ቁጣ በተቀላቀለበት ድምፅ ‹‹ለምንድን ነው ወደ ቤተመንግሥቱ የገባኸው?›› ብለው አፈጠጡ፡፡
‹‹አንድ የሆነ ድምጽ ግባ ብሎ ሹክ አለኝ›› አለ፡፡
በፉጋ መልስ ዳኛው ተገረሙ፡፡ አዳራሹን ከሞላው ህዝብ ጉምጉምታ ተሰማ፡፡
‹‹በቃ የገባህበት ምክንያት ይሄው ነው?›› ዳኛው ጠየቁ፡፡
‹‹አዎ ይኸው ነው! ደሞም ለንግስቲቷ ብዬ ነው››
ዳኛው የበለጠ ተገረሙ፡፡ በአዳራሹ የተሰበሰበው ህዝብ ልቡ ተሰቅሏል፡፡ ቀጥሎ ምን ይል ይሆን እያለ ሰው በጉጉት ይጠባበቃል፡፡
‹‹እንዴት ነው ለንግስቲቱ ብየ ነው ስትል?›› ዳኛው ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ጥያቄያቸውን አስተላለፉ፡፡
‹‹ደህንነቷ  አስተማማኝ እንዳልነበር አስብ ነበር›› አለ ፉጋን፣ በራስ በመተማመን ስሜት፡፡
‹‹እና?  ከአንተ ወደ ቤተ መንግስቱ መግባት ጋር ምን ያገናኘዋል?›› ብለው ጠየቁ ዳኛው፡፡
‹‹በቃ ግምቴ ትክክል እንደሆነ አረጋገጥኩ !››  አለ ሚካኤል ፉጋን፡፡
‹‹አንዴት?›› ዳኛው በግርምት ጠየቁ፡፡
‹‹ዘልዬ ወደ ቤተ መንግስት ስገባ ማንም የጠየቀኝ የለም፡፡ ከአንዴም ሁለት ጊዜ፡፡ እሺ ንግሥቲቷ ብትደፈርስ…? ወይ ሌላ አደጋ ቢደርስባትስ….?.›› አለና በሀዘን ስሜት አቀረቀረ፡፡ ወዲያውኑ ቀና ብሎ፤ ‹‹በበኩሌ ባለብኝ የዜግነት ኃላፊነትስ የንግስቲቱ ደህንነት አስተማማኝ እንዳልሆነ አሳየሁ›› አለ የቆመበትን ጠረጴዛ እየደበደበ፡፡    


Read 1315 times