Monday, 15 July 2019 10:06

እንደማመጥ

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

  !“--በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በብዙዎቹ አካባቢዎች ፈጣሪን መፍራት ቀርቷል፡፡ ትልቅ ሰው ማክበር ብርቅ ሆኗል፡፡ ፍቅርና መተሳሰብ ርቋል:: ይሉኝታ የሚባል ነገር ተረት ተረት ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው በአጭሩ መደማመጥ መጥፋቱን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ “ገሀነም” የሚወስዱ መንገዶች ወለል ብለው ተከፍተዋል፡፡ ከተደማመጥን በብልሃት እንሻገራቸዋለን፡፡--”
                  

            በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ መጣጥፎችን በተከታታይ ማቅረብ ከጀመርኩ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ይሆነኛል፡፡ የምጽፈው የላቀ እውቀት ስላለኝ አይደለም፡፡ የምጽፈው የተሻለ ሃሳብ ኖሮኝም አይደለም፡፡ የምጽፈው የመጻፍ ችሎታዬን ለማሳየትና ከንቱ ውዳሴን በመሻት አይደለም፡፡ ጽሁፎቼ ጭንቀት የወለዳቸው ሃሳቦች ጭማቂዎች ናቸው፡፡ ከእነ ተረቱ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” አይደል የሚባለው? አዎ! እንዲያ ነው ነገሩ! … እንደ ዜጋ የሀገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ ፊደል እንደቆጠረ ሰው የሀገሬ መጻዒ ሁኔታ ያስጨንቀኛል፡፡ እናም “እንዲህ ቢሆን፣ እንዲያ ቢደረግ፣ በዚህ መልኩ ቢታይ…” እያልኩ እጽፋለሁ:: ከአንባቢያን አሉታዊም አዎንታዊም አስተያየቶች ይደርሱኛል፡፡ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ፡፡ ጥረቴም ይቀጥላል… የዛሬውም መልዕክቴ  እነሆ!
የሀገራችንን የፖለቲካ ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ፣ ኢትዮጵያ ሀገራችን (እንደ ሀገር፣ እንደ ህዝብ) በርካታ ፈታኝ ወቅቶች ገጥመዋት እንደነበር ለመገንዘብ እንችላለን፡፡ እነዚያን የፈተና ምዕራፎች በየዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰቦችና የፖለቲካ መሪዎች ተጨባጭ ሁኔታውን በመጋፈጥ አልፈውታል፡፡
ታሪክ እንደሚነግረን የፈተና ምዕራፎቹ እንዲሁ እንደ ዋዛ፣ እንደ ዘበት የታለፉ አልነበሩም፡፡ በእነዚያ ፈታኝ ወቅቶች በርካታ ዜጎች የህይወት መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ ቤት ተቃጥሏል፡፡ ንብረት ወድሟል:: ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ሴቶች ተደፍረዋል:: ህፃናት ተርበዋል፣ ተጠምተዋል፡፡ አረጋውያን ተንገላተዋል … ይሁን እንጂ፤ ይሄ ሁሉ የህይወት መስዋእትነትና የንብረት ውድመት ቢደርስም፣ አካል ቢቆረጥም፣ ቤተ ክርስቲያንና መስጂዶች ቢቃጠሉም የሀገሪቱ ሉዓላዊነት አልተደፈረም፡፡ አስተዳደሩ ቢናጋም የፖለቲካ ስርዓቱ አልፈረሰም፡፡ ሀገሪቱ አልተበተነችም፡፡
በአንድ ሀገር ላይ እንደዚህ ያሉ ውጣ ውረዶችና ጠመዝማዛ መንገዶች መከሰታቸው ተፈጥሯዊ በመሆኑ “ይህ ለምን ሆነ?” ልንል አንችልም፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ግን በየዘመኑ (ማለትም፤ በዮዲት ጉዲት ዘመንም፣ በግራኝ አህመድ ዘመንም፣ በዘመነ መሳፍንትም፣ በኦሮሞ ፍልሰትም፣ በምኒልክም፣ በደርግም፣…) የሚከሰትና በየትውልዱ ደም እየፈሰሰ፣ ህይወት እየተገበረ መቀጠል የለበትም:: በታሪክ ሂደት የሆነ ጊዜ ላይ ሊቆምና በምትኩ ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት ሊመሰረት  ይገባል፡፡
ይህ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀደም ሲል መንታ መንገድ ላይ ከቆመችባቸው ጊዜያት ጋር ተመሳሳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ዘመን ለመንግስትም ለህዝብም ከባድ የፈተና ወቅት ነው፡፡ ለሀገር ሽማግሌዎች የፈተና ጊዜ  ነው፡፡ ለሃይማኖት አባቶች አጣብቂኝ ጊዜ ነው፡፡ ለምሁራን የውጥረት ወቅት ነው፡፡ ለህፃናት፣ ለአረጋውያንና ለሴቶች የዋይታና የሰቆቃ ጊዜ  ነው፡፡ ለአርሶ አደሩ፣ ለአርብቶ አደሩ፣ ለወዛደሩ፣ እንዲሁም ለባለሀብቱ ጭምር የጭንቅ ወቅት ነው፡፡
ታዲያ ይህ ወቅት ፈተና፣ ውጥረትና ጭንቀት የማይሆነው ለማን ነው? የሚለውን ጥያቄ እዚሁ ላይ አብሮ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ አዎ! ይህ ወቅት፤ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚል ባልቴት ብሂል ላነገቡ፣ ልበ-ደንዳና፣ የስልጣን ጥመኛ ፖለቲከኞች ሰርግና ምላሽ እንደሚሆንላቸው አስባለሁ፡፡ ስለ ነገ ለማይጨነቁ፣ የሀገር አንድነት ለማያሳስባቸው፣ ካፍንጫቸው አርቀው ለማያስቡ፣ ለመግደልም ለመሞትም ለማይራሩ፣ ልባቸውም አእምሯቸውም ለተደፈነ ከንቱዎች፤ ይህ ወቅት አያሳስባቸውም፤ ጭንቀትና ውጥረት አይፈጥርባቸውም፡፡ ፈተና አይሆንባቸውም፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት የሀገሪቱን የፖለቲካ ስልጣን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ ሲያስተዳድር የነበረውን “ህወሓት መራሹን ኢህአዴግ” ያላማረረው ዜጋ፣ ያልወቀሰውና ያልከሰሰው ግፉዓን፣ ያልመከረው ወገን፣ ያልተቸውና አቃቂር ያላወጣለት ፖለቲከኛ፣ ያልዘለፈውና ያላዋረደው አክቲቪስት፣ ክፍተቱን ያላመላከተና ስህተቱን ያላጋለጠ ጋዜጠኛ፣… አልነበረም፡፡
ኢህአዴግ ግን ጆሮውን በጥጥ ደፍኖ፣ አልሰማም አልለማም አለ፡፡ የሚነገረውን አለመስማት ብቻ ሳይሆን፤ ይባስ ብሎ ወፈ ሰማይ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ እስር ቤት አጉሮ፣ ደርዘን ጋዜጠኛ ጠፍሮ አስሮ፣ የፖለቲካውን ምህዳር አጥብቦ፣ ዜጎችን አንድ ለአምስት ጠርንፎና መፈናፈኛ አሳጥቶ፣ የሀገሪቱን ካዝና ተቆጣጥሮ፣ ያልተመጣጠነ ኢ-ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ስርዓት ዘርግቶ፣ … እንዳሻው ሲፏልል የህዝብ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ ኢህአዴግ ከውስጥም ከውጪም ተናጠ፡፡ ሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሁከት ማዕበል ተናጠች፡፡ በሂደቱ ህይወትም ንብረትም ወደመ፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ጎሳ ተኮር መፈናቀል ደረሰ፡፡
ከኢህአዴግ ውስጥ ፈንቅሎ የወጣው የለውጥ ኃይል የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ባልታሰበና ባልተገመተ አኳሃን ስልጣን ተቆጣጥሮ በለውጥ ጎዳና ላይ ብንገኝም፣ “ቄሮ ተከሉ ኢህአዴግ” ዛሬም ከመስማት ህመሙ ሙሉ ለሙሉ የተፈወሰ አይመስልም፡፡ ዛሬም ምሁራንን አልሰማም በማለቱ፣ ዛሬም የጋዜጠኛና የሀገር ወዳዶችን ጥቆማ አልቀበልም በማለቱ፣ ዛሬም የሃይማኖት አባቶችን ምክር ችላ በማለቱ፣ … ሀገራችን ወደ ሶሪያነት፣ እናት ኢትዮጵያ ወደ ሊቢያነት፣ እምዬ ኢትዮጵያ ወደ የመንነት፣… እየተንደረደረች ነው፡፡ እናም፤ የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ ሊሄድ ነው የሚል ስጋት ተፈጥሯል፡፡ በህዝብ ደም የተገኘው ለውጥ ሊቀለበስ ነው የሚል ቁጭት ተፈጥሯል፡፡ የሀገሪቱ ህልውና በአጭር ጊዜ ሊያገግም ወደማይችልበት አረንቋ፣ አፈር ልሰን ወደማንነሳበት አዘቅት፣ ሊገባ ነው የሚል ጭንቀት ነግሷል፡፡ ወደ እርስ በርስ መጫረስ ለመሸጋገር አፋፍ ላይ ቆሟል:: በኔ እይታ፤ የዚህ የቁልቁለት ጉዞ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የመደማመጥ መጥፋት ነው!
በዚህ ወቅት የገዢው ፓርቲና የመንግስት ህዝብን፣ ተቃዋሚዎችን፣ አክቲቪስቶችን፣ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን፣ ጸሐፊዎችንና የሃይማኖት አባቶችን አልሰማም ማለት ብቻ አይደለም የስጋታችንን መጠን ከፍ ያደረገው፡፡ “ህዝቡ”ም መንግስትን አለመስማቱ፣ “ህዝቡ”ም የምሁራንን ምክር ከቁብ አለመቁጠሩ፣ “ህዝቡ”ም የሃይማኖት አባቶች የሚገዝቱትንና የሀገር ሽማግሌዎች የሚያወግዙትን አለመስማቱ ሌላ ስጋት፣ ተጨማሪ ጭንቀት ፈጥሯል፡፡ (“ህዝብ” የሚለውን “ብዙሃኑ” ብላችሁ ውሰዱልኝ)
የመንግስትና የ“ህዝቡ” መስሚያ ብቻ አይደለም የተደፈነው፡፡ ተማሪው የመምህራኑን ምክርና ተግሳጽ አልሰማም ማለቱም በገሃድ እየተስተዋለ ነው፡፡ ዱሮ ዱሮ ተማሪ የሚጣላው ሰኔ 30 ነበር፡፡ ዓመቱን ሙሉ “በገርል ፍሬንድም” በኩረጃውም… ሲናቆሩ የከረሙ ተማሪዎች “ሰኔ 30 የለውም ካሳ” የሚል “የጅል” መፈክር እያስተጋቡ የትምህርት ውጤታቸውን ተቀብለው ከጓደኞቻቸው ጋር ተናርተው ይለያዩ ነበር፡፡ ያ ሁሉ ግብግብ ክረምቱን  ተረስቶ፣ መስከረም ላይ በመነፋፈቅ መንፈስ ተገናኝተው፣ ይቅር ተባብለው አዲስ “የትምህርት ህይወትም” ይጀምራሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ ተማሪዎች ሰኔ ሰላሳን ሳይጠብቁ (ያውም ዩኒቨርስቲ ውስጥ) መጋደል እንደ ጀብዱ የሚታይ ተግባር ሆኗል፡፡ ይህም ሌላ የውድቀት ስጋት ነው!
በዚህ ወቅት ችግር የሆነው የተማሪዎችና የመምህራን አለመደማመጥና የተማሪዎች እርስ በርስ መገዳደል ብቻ አይደለም፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን አለመስማታቸውም የዚህ ወቅት ፈተና ሆኗል:: ወላጆቹን የማይሰማ ልጅ ወደፊት ሲሉት ወደ ኋላ፣ ወደ ት/ቤት ሲልኩት ወደ ጫት ቤት፣ ወደ ሥራ ሲያሰማሩት ወደ መሸታ ቤት፣… መሄድ የእለት ተእለት ትእይንት መሆኑም ሌላ የስጋት ምንጭ ነው:: ወላጆቹን የማያከብር ወጣት፣ የሀገር ሽማግሌዎች የሚሉትን ሊቀበል አይችልም፡፡ የወላጆቹን ምክር የማይሰማ ወጣት፣ የሃይማኖት አባቶች ግዝት ሊያቆመው አይችልም፡፡ ወላጆቹን የማይፈራ ወጣት፣ መንግስትን አይፈራም፣ ህግን አያከብርም፣ ፖሊስን ከመጤፍ አይቆጥርም፡፡
በአጠቃላይ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በብዙዎቹ አካባቢዎች ፈጣሪን መፍራት ቀርቷል:: ትልቅ ሰው ማክበር ብርቅ ሆኗል፡፡ ፍቅርና መተሳሰብ ርቋል:: ይሉኝታ የሚባል ነገር ተረት ተረት ሆኗል:: ይህ ሁሉ የሚያሳየው በአጭሩ መደማመጥ መጥፋቱን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ “ገሀነም” የሚወስዱ መንገዶች ወለል ብለው ተከፍተዋል፡፡ ከተደማመጥን በብልሃት እንሻገራቸዋለን፡፡ ካልተደማመጥን ግን ባልታሰበ ሰዓት፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ “ሶሪያን የምትመስል” ምድራዊ ሲዖል ውስጥ ራሳችንን ልናገኘው እንደምንችል በሃዘን ስሜት አስባለሁ፡፡ እናም “እንደማመጥ!!!” - እላለሁ ደግሜ ደጋግሜ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2863 times