Monday, 15 July 2019 09:39

ለመሰላሉ ጫፍ…የመሰላሉ ስር ስዕል

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

“የፖለቲካን ነገር ካነሳን አይቀር…የእኛ ‘ክርከር’ እኮ ኮሚክ ነው፡፡ እኔ የምለው… ለምንድነው ሳንሰዳደብ መነጋገር ያቃተን! የምር ግን.. የሀሳብ ድህነት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው?--”
               
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ወዳጅነት፣ ቀላል ባቡር፣ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ምናምን ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ግን ስንትና ስንት ነገራችንን “በእናንተው መጀን…” እያልን የሰጠነው አይበቃም እንዴ! አሀ… እንስቶቻችንን ለቀቅ፣ ረጅሙን ድልድይ ጠበቅ! አሀ…ወዳጅ የሆነ መሰመር አለዋ! በቀደም ነው፣ ከሆነ የህንጻ ግንባታ ከሚካሄድበት ግቢ ሶስት ገደማ ቻይናውያን ይወጣሉ፡፡ እንዳጋጣሚ በአስራዎቹ መጨረሻ የሚሆኑ ሁለት ወጣት ሴቶች በዛው ያልፋሉ፡፡ ቻይናውያኑ ሊሄዱ የጀመሩበትን አቅጣጫ ትተው ተጠመዘዙና ልጆቹን እየተከተሉ ለከፋ ጀመሩ፡፡ ያው እንግዲህ እንግዳ ተቀባዮች አይደለን…ልጆቹም ፊት አልነሷቸውም፡፡ ተከታትለው ሄዱላችኋ! 
እናላችሁ… የወዳጅነት መገለጫዎቻችን ለየት ብለዋል ለማለት ያህል ነው፡፡ በነገራችን ላይ የማኦ ልጆች ‘ሲላከፉ’ ማየት እየተለመደ መጥቷል:: (ለግንዛቤ ያህል ማርና ወጥ እና ማረቆ በርበሬ ስላበዙ  ነው እንዳንል ገና የሳይንስን ድጋፍ እየጠበቅን ነው::) ታዲያላችሁ… ምን ያሳስባል አትሉኝም… ለዓይን በሚስብ ሁኔታ የሚሠሩ ህንጻዎች ነገር ያሳስባል፡፡ ልክ ነዋ… ሀሳብ ሲከፋፈልና የአእምሮ ብዙ ‘ፐርሰንት’ ላይ ‘የከፋ ሶፍትዌር’ ሲጫን፣ ሰዎቹ በባለ ሠላሳ ፎቁ ህንጻ፣ አስራ አምስተኛና ሀያ ሦስተኛ ፎቆቹን ረስተው ቢያልፏቸውስ! (ቂ…ቂ…ቂ…) ለነገሩ ምንም አይነት ግንባታ በተወሰነለት በጀት የማያልቅባት (ምናልባትም ‘እንዲያልቅ የማይፈለግባት’) ሀገር ስለሆነች ትርፉ “ማን ይሰማናል ብለው ነው የሚለፈልፉት” መባል ነው፡፡ 
እናላችሁ…ስንቱ ለምድር ለሰማይ የከበደ የሀገሬ ሰው እኮ ጉድ የሆነው በ‘ራቭ ፎር’ ብቻ ሳይሆን በ‘ፎር ዲጂት’ ረብጣም ‘መላከፍ’ እንደሚቻል ከተገለጠለት በኋላ ነው፡፡ (እኔ የምለው…አንዳንዶቻችን እንደው ከመሬት ተነስተን እንዴት ነው ‘እንዲህ’ የምንሆነው! አሀ…ነገርዬውን ደንገት በምርምር ገና አሁን የተደረሰበት ‘የተፈጥሮ ጸጋ’ አስመስልነዋ! የፈለገ  ‘ሞርኒንግ አፍተር’ ነገርዬው እንደ ገብስ ቆሎ እንደ ልብ ቢገኝስ!)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ ‘ለከፋ’ የሚባለው ነገር ከተነሳ አይቀር… ‘ኢማንሲፔሽን’ ምናምን ስለሚባሉት ነገሮች ስናወራ መአት አስርት ዓመታት ሆኗል፡፡ ዘንድሮ ብዙ እንስቶች ወፍራም፣ ወፍራም ወንበር ላይ መቀመጣቸው አሪፍ ነው፡፡ በዚህ ዓለም አጨብጭቦልን የለ! ግን እኮ…አለ አይደል… ዋነው ነገር ያለው እዛ ላይ ሳይሆን መሀልና እታች ነው:: (ከፖለቲከኞቻችን ሺህ ምናምን ችግሮች መሀል አንዱ ትልቅ ችግር ምን መሰላችሁ… ‘ፐብሊክ ኦፒኒየን’ የምንለው፣ ማለትም የህዝብ አስተያየት ቅርጽ የሚይዘው በባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች አይደለም፡፡ በእንትን ከተማ ‘ሪዞርቶች’ አይደለም:: እነ አከሌ የሚባሉ የ‘ጉልቤ’ ሀገር ዲፕሎማቶች በሚያወሩት አይደለም:: ይልቁንም በየመንገዱና በየመንደሩ ነው፡፡ ‘መሰላል ጫፍ’ ላይ ላሉት ማርክ የሚሰጠው በመሰላሉ ታች ያሉት በሚገጥማቸው የኑሮ ውጣ ውረድ እንደሆነ ልብ ይባልማ! እግረ መንገድ ‘ተንፈስ እንበል ብለን ነው እንጂ… ጆሮ እናገኛለን፣ ‘ኢንቬስቲጌቲቭ ሪፖርተር’ ርእስ ያገኛል ብለን አይደለም፡፡ በነገራች ላይ…ተንፈስ ማለትን የሚገድቡ አዝማሚያዎች ቀና ባሉበት ያስቀርልንማ!)
እናማ… በከተማዋ መንገዶች የእለት ከእለት  እንቅስቃሴዎች እንስቶቻችን የሚገጥሟቸው ችግሮች የሚያስጨበጭቡ አይደሉም፡፡ ጉዳዬ ብለው የሚያወሩ ባለመገኘታቸው እንጂ ‘ለከፋ’ የሚባለው ነገር በጣም፣ እጅግ በጣም ተባብሷል፡፡ ጫማ ማሰር ከለመደ ሶስትና አራት ዓመት የሞላው ታዳጊ እኮ የሶስት ልጆችን እናት ‘የሚለክፍባት’ ከተማ ነች፡፡
ስሙኛማ የእንስቶችን ነገር ካነሳን አይቀር የሰሞኑን የሴቶች የዓለም ዋንጫ አያችሁልኝ! የእኛ ወንዶች ሜዳዋን ሶስቴ ከተመላለሷት ‘ሲሲፈስን’ ሲያግዙ ውለው የመጡ ይመሰል ቁና፣ ቁና ሲያስተነፍሳቸው፣ ዘጠና  ደቂቃ ሙሉ እንዲህ መሮጥ ይቻላል እንዴ! በችሎታስ ቢሆን! እውነት እንነጋገር ከተባለ ምናልባት ተፈጥሯዊ ከሆነ አካላዊ ጥንካሬ ይሆን እንደሁ እንጂ በኳስ ጥበቡ የአሜሪካ፣ የስፔይን፣ የፈረንሳይን የሌሎቹ ሴት ተጫዋቾች ውሀ፣ ውሀ አያሰኙንም! እናማ…ትንሽም ቢሆን ሲያስጨበጭቡን ለነበሩት ለሴት እግር ኳስ ተጫዋቾቻቸን ትኩረት ይሰጥልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የስፖርት ሚዲያችንን ታዘብነው፡፡ ስለ ሴቶቹ የዓለም  ዋንጫ ቢወራ እንኳን እግረ መንገድ አንጂ ጠለቅ ያለ ትንታኔ ብሎ ነገር የለም፡፡ ቆይማ… ለትንታኔ ቡድኖቹ፣ ውስጥ የሆነ ሳዲዮ ማኔ፣ የሆነ መሀመድ ሳላህ፣ የሆነ ፖል ፖግባ ምናምን መኖር አለበት እንዴ! የአሜሪካዎቹ ሜጋን ራፒኖና አሌክስ ሞርጋን፣ የፈረንሳዮቹ ለ ሶሜር፣ ካዲ ዲያኒና ቫለሪ ጎቫን፡ የእንግሊዞቹ ኋይትና ሚጢጢዋ ፓሪስ፣ የሆላንዶቹ ሜይነማ እና ግብ ጠባቂዋ… ምንስ ቢባልላቸው ያንሳቸዋል እንዴ! (ለነገሩ “እኛ ሀገር ጭራሽ የለም፣” በተባለ ነገር እጃችንን አናስገባም:: ቂ…ቂ…ቂ…)  
እግረ መንገድ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…መቼም አዲሰ አበባ በየመንገዱ ሰብሰብ ብሎ መቆም እንደ ልብ ነው፡፡ ‘የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ ይገድባል፣’ ‘ለሰዎች ዝውውር ችግር ይፈጥራል’ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሰሙኝማ… “ምነው በአፍሪካ ሰው ከምሆን በእነሱ ሀገር ተናጋሪዋን ወፍ ባደረገኝ፣” የምንልላቸው ሀገራት እኮ ህግና ስርአት የሚባል ነገር አለ፡፡ አይደለም እንደፈለጉ ‘እንስቶችን መልከፍ’ የሰዎችን እንቅስቃሴ በሚገድብ መልኩ እንደፈለጉ ተሰባስቦ መቆም አይፈቀድም፡፡ እናማ…በየመንገዱ ሰብሰብ ብሎ የመቆም ሱስ ያለባቸው የሌሎች ሀገራት ዜጎች ካሉ… አለ አይደል… ‘በመንገድ ተሰብስቦ የመቆም ቱሪዝም፣’ በሚል ለዓለምም ምሳሌ ልንሆን እንችላለን፡፡ አሀ…ልንቆጣጠረው ካልቻልን፣ ወይም ፍለጎቱ ከሌለን፣ ዶላርና ፓውንድ እናግኝበታ! እናላችሁ…እዚች ከተማ ውስጥ ግን እዚህ ስፍራ አስር ሆናችሁ የመንገዱን አጋማሽ ይዛችሁ ያለምንም ምክንያት ብትቆሙ ‘ዝምባችሁን እሽ የሚል’ የለም:: እዛኛው ማዶ ግን ማስቲካ የምትሸጥ  ሚጢጢዬ ልጅ  ትሳደዳለች፡፡
ኮሚክ እኮ ነው፤ የምግብ ዘር ካረፈበት ሶስትና አራት ቀን የከረመ ባዶና ሆድ ይዘን እኮ ምግብ ሲቀርብልን… “ክክ! ክክ! አንቺ ሴትዮ በክክ ሞልተሽ፣ ሞልተሽ  በኋላ በሲሚንቶ ልትለስኚኝ ነው እንዴ!” አይነት፣ ወይም “እርቦኝ ሹሮ ከምበላ ዶሮ ማነቂያ ሉካንዳ ቤት በር ላይ ቆሜ ሰልፊ ብነሳ ይሻለኛል፣” አይነት…ወይም የሁለት ዲጂት ‘እድገታችን’ መቀዝቀዝን ያላገናዘበ ተቃውሞ እናቀርባለን:: (“ኸረ የምግብ ጡር አለው፣ ሲቀለድበት እንዳይቀልድብን…” ቢባል ሀሳቡን እንደ ሀሳብ እቀበለዋለሁ፡፡ አሪፍ አይደል!…ኮሚክ እኮ ነው፣ ብዙ ስብሰባዎችና ስብሰባዎች ምናምን በሚመስሉ ነገሮች ላይ የምንሰማው ነው፡፡ “ሀሳቡን እንደ ሀሳብ እቀበለዋለሁ፣” ይባላል፡፡ ታዲያ እንዴት ልንቀበለው ኖሯል! ለአዲስ ሲንግል እንደተጻፈ ግጥም! ሰውየው እኮ “እኔ የማቀርበው ሀሳብ…” ብሎ ነው የተናገረው!)
ከዚህ በፊት ያወራናትን ነገር እንድገማትማ… ሰውየው ለሆነ ወንበር ቀርቦ የምረጡኝ ንግግር እያደረገ ነው፡፡ “ወገኖቼ ለሀገሬ ተዋግቻለሁ፣ አልጋዬ ጦር ሜዳ ነበር፣ እያንዳንዱ ኮቴዬ የደም ማህተም እስኪያኖር ድረስ ቁርና ውርጭ በሆነው መንገድ ስጓዝ ኖሬለሁ፡፡ ስለዚህ ለሀገሬ የለፋሁትን አይታችሁ ምረጡኝ፣” ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሳታፊዎች አንዱ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ለሀገርህ ከሚገባህ በላይ አገልግለሀል፡፡ አሁን አንተ አረፍ በልና ሌላ ሰው እንመርጣለን፣” አለው አሉ:: (ምናልባት ያስፈልገን እንደሁ ‘ለማስታወስ’ ያህል ነው፡፡)
የፖለቲካን ነገር ካነሳን አይቀር…የእኛ ‘ክርከር’ እኮ ኮሚክ ነው፡፡ እኔ የምለው… ለምንድነው ሳንሰዳደብ መነጋገር ያቃተን! የምር ግን.. የሀሳብ ድህነት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው? የሆነ ሰው የሆነ ህትመት ውጤት ላይ ‘የግል ሀሳቤ’ የሚለውን ነገር ይጽፋል፡፡ የእኔ ቢጤው መልስ የሚለውን ሲጽፍ ምን ይል መሰላችሁ… “የግለሰቡ ጽሁፍ ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት የረጩት መርዝ ነው፡፡ እሳቸውና መሰሎቻቸው አይዟችሁ በሚሏቸውና ከትናንት ናፋቂዎች በሚጣልላቸው የገንዘብ ድርጎ እኩይ  አጀንዳቸውን በህዝቡ ላይ ለመጣል...”  እያለ ይቀጥልላችኋል፡፡ አንድም ቦታ ላይ ከተባለው ጽሁፍ አንዲት ዓረፍተ ነገር እንኳን መዞ የሚሞግትበት የለም፡፡
ይቀጥላል… “ልናረጋግጥላቸው የምንወደው የእሳቸውና የመሰሎቻቸው እኩይ ድብቅ አጀንዳ መቼም እንደማይሳካ ነው፡፡” “ቲቸር ጥያቄ አለኝ…” እንደሚባለው እኛም ጥያቄ አለን፤ አጀንዳው ‘ድብቅ’ ከሆነ እኩይነቱን የተናገረችው የሌሊት ወፍ አድራሻዋ የት እንደሆነ ይነገረና! ግራ ገባን እኮ… በአደባባይ የሚሳደብ፣ በአደባባይ የሚፎክር፣ በአደባባይ “እስቲ ወንድ ከሆንሽ ጫፌን ንኪኝና እንተያያለን!” የሚል አይነት በዝቶብን ግራ ገባን እኮ!
እናማ…እንስቶቻችንን በማንኛውም መልኩ ማክበሩና መንከባከቡ በቴሌግራም መልእክትና ፎቶ ከመለዋወጥ የበለጠ የስልጣኔ ምልክት ነው:: ለክፉም ለደጉም… ለመሰላሉ ጫፍ ማርክ የሚሰጠው፣ በመሰላሉ ስር በሚኖረው ስእል እንደሆነ ልብ ይባልማ! ምነው ሸዋ!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2637 times