Saturday, 13 July 2019 11:43

“የጥላቻ ሐውልቶች በየቦታው ተገንብተዋል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)


    *የሴት ልጅ ጡት መቁረጥ የሚባል ነገር በኢትዮጵያ ታሪክ የለም
   *አፄ ምኒልክ ኦሮሞን በመበደል ስማቸው መነሳቱ አስገራሚ ነው
  *ፌደራሊዝም የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር የለም
  *የተስፋዬ ገብረአብ መጽሐፍ አደገኛ ልቦለድ ነው

         “መረራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘና በዋናነት አፄ ምኒልክ ጠል የሆኑ ትርክቶችን የሚሞግት መጽሐፍ ያሳተሙት የታሪክ መምህሩ አቶ ታየ ቦጋለ፤ በመጽሐፉ ውስጥ በተነሱት አንኳር ጉዳዮች፣ ያልተነገሩ ታሪኮችና በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ አቶ ታየ በአሁኑ ወቅት “የገዳ ስርአትና ዋቄፈና”፣ “መጽሐፈ ነገስት” እንዲሁም “የኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኙ ሦስት መጽሐፍትን እያዘጋጁ መሆኑንም ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡


              “መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ” ከሚለው የመጽሐፍዎ ርዕስ እንጀምር ---
የኢትዮጵያ ታሪክ የአፃፃፍ ስልት በአብዛኛው ከፖለቲካ ፍላጐት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በ1962/63 ሲቋቋም ነው፣ የስነጥበብ ስነጽሁፍና ታሪክ የሚባል የትምህርት ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርአት ውስጥ የገባው:: ከዚያ በፊት ዘመናዊ የታሪክ አፃፃፍ አልነበረም፤ የታሪክ ትምህርትም አይሰጥም ነበር፡፡ ትምህርቱ በተጀመረ ማግስትም የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ፍልስፍና ወደ አገራችን ገባ፡፡ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ደግሞ በአጠቃላይ ስርአቶችን ጨቋኝና ተጨቋኝ፣ ገዥና ተገዥ፣ በዳይና ተበዳይ በሚል በሁለት ብቻ ከፍሎ የሚያሳይ በመሆኑ  ያለፉ ገዥዎችን በሙሉ ጥላሸት የመቀባት ሂደት ታይቷል፡፡
 በሌላ በኩል፤ የኦነግና ወያኔ ድርጅቶች አነሳስ፣ በራሳቸው በኦሮሞ ወይም በትግራይ ልጆች አልነበረም፡፡ ህወኃት እንደሚታወቀው በሻዕቢያ ወይም ሙሴና ጃማይካ በተባሉ ሰዎች ነው የተመሠረተው፡፡ ኦነግ ደግሞ በጀርመን ናዚዎች አማካይነት የተመሠረተ ነው፡፡ ይሄን በሰፊው በመጽሐፉ ውስጥ አብራርቼዋለሁ፡፡ የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች አላማ ደግሞ ህዝብን መነጣጠል ነው:: ህዝብን ለመነጠል እንዲያመቻቸውም የውሸት ታሪክ ፈጥረዋል፡፡ ህዝቡን የውሸት ታሪክ ሲግቱት ነው የኖሩት፡፡ ይሄን ሲግቱት የኖሩትን የውሸት ታሪክ በእውነት ሲሞገቱ ይመራቸዋል፡፡ እውነታው ሲነገር ውስጣቸው መታመሙ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያን ለመበተን በውሸት ትርክት ላይ የተመሠረቱ ሃይሎችን መሠረት የሚያሳጣና በእውነተኛ ማስረጃ የሚሞግት መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ነው ርዕሱን “መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ” ያልኩት::
እነዚህ ሃይሎች የውሸት ታሪክ ፈጥረው ትውልዱን በትርክታቸው ሲያጠምዱት የታሪክ ምሁራን ለምን ዝምታን መረጡ?
የታሪክ ምሁራን በራሣቸው በአራት ይከፈላሉ:: ራሣቸውም የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል፤ መንግስትን የሚደግፉ የታሪክ ምሁራን አሉ፡፡ የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ አለምን የሚከተሉ አሉ፡፡ የዘውግ ፍቅር የሚያጠቃቸው የታሪክ ምሁራን (የትግራይ፣ ኦሮሞ፣ አማራ -- እያሉ ለጽንፍ የሚያደሉ) አሉ፡፡ ለክብራቸው የሚጨነቁ በፍርሃት ውስጥ የተዘፈቁ የታሪክ ምሁራንም  አሉ፡፡ በሌላ በኩል የስርአቶች ጉሸማም እንዳለ ይታወቃል፡፡ መንግስት የታሪክ ትምህርት ክፍልን በአይነ ቁራኛ ሲከታተል ነው የኖረው፡፡ እነዚህ ተደማምረው ምሁራኑ ሚናቸውን እንዳይወጡ አድርጓቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዋነኛነት ለክብር መጨነቅ፣ ቀጥሎ እርስ በእርስ ላለመነካካት መጣር፣ ከዚያም ደግሞ የመንግስትን ተጽእኖ የመፍራት ነገር አለ:: እነዚህ ሁኔታዎች፣ ምሁራን እውነትን ፊት ለፊት እንዳይጋፈጡና ዝምታን እንዲመርጡ  አድርጓቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡  
በመጽሐፍዎ  ይህቺን ሀገር የበጠበጡ “የፈጠራ ትርክቶች” ብለው ከጠቀሷቸው ጥቂቶቹን ይግለጹልኝ--?
አንዱ የአኖሌ ትርክት ነው፡፡ አኖሌ ከትርክት አልፎ በብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ ሃውልት ቆሞለታል፡፡ ለዘመናት የነበረን የፍቅር መስተጋብር፣ የአባት የእናቶቻችን የአብሮነት እሴት አንድም ቦታ ሐውልት ሳይቆምለት፤ በአንፃሩ የጥላቻ ሃውልቶች በየቦታው ተገንብተዋል፡፡ አኖሌን ብንመለከት፤አኖሌ በምትባለው ስፍራ ላይ አማራና ኦሮሞ ተጋጭቶ አያውቅም፡፡ ተስፋዬ ገብረአብ የፃፈው “የቡርቃ ዝምታ” አንድም አጣቃሽ ነገር ሳይኖረው ልብወለድ ነው፡፡ በድርሰቱ ቡርቃ የሚላት ወንዝ ባለችበት ቦታ፣ አማራና ኦሮሞ ተጣልቶ አያውቅም፡፡ የተስፋዬ አላማ ግልጽ ነው፤ ኦሮሞና አማራን በፈጠራ ማጋጨት ነው:: እዚያ ቦታው ላይ ያሉ ሰዎችን ሳነጋግር፣ ምንም ግጭት እንዳልተፈጠረ ነው የሚናገሩት፡፡ ግጭት በቦታው ፈጽሞ አልተፈጠረም፡፡ የተስፋዬ ገብረአብ መጽሐፍ አደገኛ ልቦለድ ነው፡፡
መጠነኛ ግጭት የነበረው ከዚያ አልፎ ባሉ እንደ አርባ ጉጉ፣ በደኖ የመሳሰሉ ቦታዎች እንጂ እዚያ አካባቢ አስከፊ ግጭት አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደግሞ የሴትን ጡት የመቁረጥ ነገር ፈጽሞ የለም፡፡ የወንድ ልጅ ብልት መስለብ፣ እጅ መቁረጥ ነበር፤ ነገር ግን የሴት ልጅ ጡት መቁረጥ የሚባል ነገር በኢትዮጵያ ታሪክ የለም፡፡ ሌላኛው የጨለንቆ ጉዳይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1887 ከሀረሩ ኢምር አብዱላሂ ጋር የተደረገ ጦርነት ታሪክ ነው፡፡ ጦርነቱ 1 ሰዓት ብቻ የፈጀ ምናልባትም በጦርነት ታሪክ አጭር ጊዜ ከወሰዱት አንዱ ነው፡፡ ወቅቱ የገና በዓል ስለነበር “የአፄ ሚኒልክ ጦር ምግብ በልቶ ይደክመዋል” የሚል ጥቆማ ኢምር አብዱላሂ ደረሳቸውና፤ መጥተው ግጭት ፈጠሩ፤ ነገር ግን የምኒልክ ጦር በተጠንቀቅ ላይ ስለነበር ኢምሩ ያሰቡት ሳይሆን ሽንፈት አጋጠማቸው፡፡ ይሄው ነው ታሪኩ፡፡ ሌላው በአኖሌ የዘመተውን የምኒልክ ሠራዊት ብንመለከት፤ 9/10ኛው የኦሮሞ ተወላጅ ነው፤ አማራ ጥቂት ነው፤ እሱም የሰሜን ሸዋ  እንጂ ጐንደር፣ ጐጃምና ሌላው ተሳትፎ አልነበራቸውም፡፡ እነዚህ ትርክቶች በአጠቃላይ በውሸት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ይሄን በማስረጃ አቅርቤያለሁ፡፡
ሌላው የጥላቻ ታሪክ ምኒልክ ኦሮሞን “ጋላ” ብለው ተሳድበዋል የሚል ነው፡፡ ይሄም ፍፁም ውሸት ነው፡፡ ታሪኩን ስንመለከተው፤ ጃንጀሮ (የም)ችን አፍቃላ የሚባል የኦሮሞ የባሪያ ነጋዴ አለ፤ እሱ ጃንጀሮዎችን ከሀገር እያወጣ በባርነት ይሸጥ ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ በወቅቱ ለአባ ጅፋር በላኩት ደብዳቤ፤ “ይድረስ ከልጄ ጂማ አባጅፋር፡- ይህን የጃንጀሮ ሰው ጋላውን በእጄ ገባ ብለህ ጭቡ አታድርገበት፤ እኔ ጋ የጐንደር ሰው መጥቶ ተሰብስቧል፤ ግፍ ብሠራበት መልካም አይሆንም”  ነው ያሉት፡፡ እዚህ ጋ መመልከት ያለብን፤ አፄ ምኒልክ፤ ጐንደርን “የውጪ ሰው” ጅማ አባ ጅፋርን ግን “ልጄ” ነው የሚሉት:: ብዙ ቦታ ይተቹ የነበረውም “አፄ ምኒልክ ለኦሮሞ ብለው አማራውን እየገፉ ነው” በሚል ነበር:: “ምኒልክ ኦሮሞውን እንደ ሰው አልቆጠሩትም” የሚለው ትርክት ውሸት ነው፡፡ ምኒልክ ኦሮሞን እንደ ሰው እክብረውታል፡፡ እንደ ሰው ቆጥረው ተጋብተውታል፡፡ ምኒልክ እናታቸው ኦሮሞ ናት:: እንደ ሰው ቆጥረውት የልጅ ልጃቸውን ሸዋረጋን የዳሩት ለወሎ ኦሮሞ ኢማም መሐመድ አሊ ነው:: የጦር ሚኒስትራቸው ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ኦሮሞ ናቸው፡፡ የመስፋፋት ሚኒስትራቸው ጐበና ዳጨ ኦሮሞ ናቸው፡፡ ምኒልክን የከበቧቸው ወይም በዙሪያቸው ወሳኝ ቦታዎችን ይዘው የነበሩት ኦሮሞዎች ናቸው፡፡
ምኒልክ የከበቧቸው ኦሮሞዎች ሆነው መጀመሪያ የወጉት ጐጃምን ነው፡፡ ጐጃም እምባቦ ላይ በ1882 ዓ.ም የተደረገውን ጦርነት ማንሳት ይቻላል:: በእርግጥ እሣቸው ዛሬ የሉም፤ ሞተዋል፤ ነገር ግን ይሄን የፈጠራ ታሪክ ለማምጣት የተፈለገው በግልጽ ኦሮሞና አማራውን ለማጣላት ነው፡፡ የወያኔ ፀሐፊዎች የሚጽፉት ተረት ተረት፤ ሁለቱን በማጋጨት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ዋናው የሃሰት ትርክቶች ማጠንጠኛ ሁለቱን ህዝቦች ማጣላት ነው::
ምኒሊክ በመስፋፋት ሂደት ያደረጉትን ጦርነቶች ብንመለከት፤ በኦሮሞ ላይ ካደረጉት ይልቅ በከፋና ወላይታ ላይ የከፋ ጦርነት አካሂደዋል፡፡ ደም አፋሣሽ የነበሩት ጦርነቶች እነዚህ ናቸው፡፡ በተለይ የወላይታ ገዥ መደብ ከሆነው “የትግሬ” ስርወ መንግስት ጋር የተደረገው ጦርነት እጅግ ደም አፋሳሽ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በወላይታ በአፄ አምደጽዮን የሠፈሩት “ትግሬዎች” ናቸው ቋንቋውን ለምደው፣ በሂደት በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ የወላይታን መንግስት ገልብጠው፣ የትግሬ ስርወ መንግስትን ያቋቋሙት፡፡ ይሄ በበርካታ የታሪክ ፀሐፍት የተመዘገበ ነው፡፡ ይሄን ስርወ መንግስት ለማፍረስ ምኒልክ ደም አፋሻሽ ጦርነት አድርገዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አፄ ምኒልክ ኦሮሞን በመበደል ስማቸው መነሳቱ አስገራሚ ነው፡፡ አፄ ምኒልክ ኦሮሞን 150 አመት ወደ ኋላ አስቀርተዋል ሲባልም በጣም ነው የሚገርመው:: እሣቸው እንደውም ለኦሮሞ ያደሉ ነበር ቢባል ነው ትክክል የሚሆነው፡፡ አሁን የሚጠቅመው እውነተኛውን ታሪክ ገልጦ ወደ አደባባይ ማምጣት ነው፡፡ ምኒልክና አማራው በሃሰተኛ ታሪኮች የጦስ ዶሮ ለምን ይሆናሉ? ዛሬ በየቦታው የምናያቸው ጥላቻዎችና መፈናቀሎች ሁሉ የእነዚህ ሀሰተኛ ስብከቶች ውጤት ናቸው፡፡
ለምንድን ነው በመጽሐፍዎ ዋና ትኩረትዎን በአጼ ምኒልክ ላይ ያደረጉት?
አንደኛ፤ የታሪክ ግጭትና የዚህ ሁሉ ውዝግብ ምንጭ አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ ግጭቱን ለመፍጠር የተፈለገው በአፄ ዮሐንስ ላይ አይደለም፤ በአፄ ምኒልክ ላይ ነው፡፡ ግጭቱን ለመፍጠር ሁኔታውን የጠቀሱ አካላት አንደኛ የምኒልክን ታሪክ አሟልተው አይነግሩንም፡፡ ሁለተኛ፤ ሚኒልክ ባይኖሩ ኖሮ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ምን ትመስል ነበር? ለምሣሌ የቦረና ኦሮሞ ዛሬ ከፊሉ ያለው ኬንያ ውስጥ ነው፡፡ የቦረና ኦሮሞ ተነጥሎ እንዴት ከፊሉ ኬንያዊ ሆነ ካልን፣ ምኒልክ በተለያዩ ምክንያቶች ተወጥረው፣ በሀገር አንድነት እንቅስቃሴያቸው በመዘግየታቸው የተከሰተ ነው፡፡ ምኒልክ ቢዘገዩም በኋላ ወደ ቦረና በመሄዳቸው ዛሬ የጉጂና የቦረና ኦሮሞዎች ከቅኝ ተገዥነት ተርፈዋል፡፡ እሳቸው ፈጥነው ወደ ወለጋና አካባቢው ባይንቀሳቀሱ ኖሮ፣ ሱዳንንና ግብጽን የሚያህሉ ሀገሮች የያዘችው እንግሊዝ፣ ወለጋን መያዝ አያቅታትም ነበር፡፡ አፄ ምኒልክን በዚህ መጽሐፍ እንዳጐላ ያደረገኝ አንዱ ትልቁ ነገር፣ ትልቅ ሀገር መመስረታቸው ነው፡፡ ሌላው ምኒልክ የተንቀሳቀሱበት ዘመን፣ በ1870ዎቹ መጨረሻ አካባቢ፣ አውሮፓውያን ሰፊ የቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበረበት ነው፡፡ ምኒልክ በ1870ዎቹ ከእነ ጐበና ዳጨ ጋር ከተገናኙ በኋላ፣ በ1882 ነበር ከጐጃም ጋር ግጭት የጀመሩት:: ይሄም ዙሪያቸውን ጠላት እንደከበባቸውና ይሄን ለመከላከል ሀገሩን አንድ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስቀድመው ተረድተው ነበር ማለት ነው፡፡ 1884/85 የበርሊን ኮንፈረንስ (አፍሪካን የመቀራመት ምክክር) የተደረገበት ወቅት ነው፡፡ እሣቸውም በዚህ ወቅት ነበር ሰፊ እንቅስቃሴ ያደረጉት፡፡ ስለዚህ ምኒልክ ይሄንን ህዝብ ከቅኝ ግዛት ታድገውታል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ በዚያን ዘመን እሣቸውን የሚያህል ብልህና አዋቂ መሪ አልነበረም፡፡ ህዝቡም “እምዬ” እያለ ነበር የሚጠራቸው፡፡ ይሄ በተአምር የሆነ አይደለም፡፡ የሚበሉት ከህዝቡ ጋር ነው፤ የወርቅ ጫማ ነበራቸው፤ ነገር ግን አድርገውት አያውቁም፤ በባዶ እግራቸው ነበር የሚሄዱት፡፡ የትምህርትን ብርሃን ለኢትዮጵያ አምጥተዋል፤ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ እንዲጋቡ እንዲዋለዱ፣ እንዲቀላቀሉ አድርገዋል፡፡ የባሪያ ሽያጭን ለማስቀረት በእጅጉ ጥረዋል፤ ጠንካራ አዋጅም አውጥተዋል፡፡
ምኒልክን ከዘመናቸው አንጻር ከተመለከትናቸው፣ ላናደንቃቸው የምንችልበት ምንም ምክንያት የለም:: “አባት እሆንሃለሁ ልጅ ትሆነኛለህ፤ እባክህን ህዝብ አታስጨርስ“ እያሉ ነበር በርካቶቹን በሠላማዊ ድርድር የግዛታቸው አካል ያደረጉት፡፡ ከጦረኞች ጋር ባደረጉትም ግጭት ቢሆን ሰብአዊ ኪሣራ እንዳይደርስ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር፡፡ ይሄን የውጭ ፀሐፍት ሳይቀሩ ይመሰክራሉ፡፡ በ1906 በመጨረሻው የህይወት ዘመናቸው፣ ታመው አልጋ ላይ ተኝተው እንኳ፣ ሀገር እንዳትከፋፈል ጠቃሚ ነው ያሉትን ስልት የነደፉ ሰው ናቸው፡፡ በወቅቱ ለንደን ላይ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣሊያን የቅኝ ግዛት የሶስትዮሽ ስምምነት ሲፈራረሙ፣ እሣቸው ይሄን አስቀድመው አውቀው፣ አልጋ ላይ ሆነው ሚኒስትሮችን በመሾም፣ ይበጃል ያሉትን አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ጣሊያን ፈረንሳይና እንግሊዝ በተፈራረሙት ስምምነት መሠረት ቢሳካላቸው ኖሮ፣ ከኤርትራ ጀምሮ እስከ ሶማሊያ ያለውን ጣሊያን፤ ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ ያለውን ፈረንሳይ፤የአባይ ተፋሰስን ደግሞ ብሪቴይን ለመውሰድ ነበር ያቀዱት:: በእነዚህ ሀገራት ቀመር መሠረት፤ ይህቺ ሀገር ዛሬ ላይ የለችም ነበር፡፡ ለዚህ ነው ምኒልክ ሀገር የፈጠሩ ሰው ናቸው የምለው፡፡ ሀገር መፍጠራቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡
በደንብ  ከመረመርነው የምኒልክ ተግባር ረቂቅ ነው፡፡ ስራቸው የገዘፈ ነው፡፡ ሃውልት ሊቆምላቸው፤ ሊመሰገኑና ሊከበሩ ሲገባቸው፣ እሣቸውን ለማፍረስ መሞከር አሳዛኝ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ምኒልክ ለሀገራቸው አንድነት የደከሙ ቢሆኑም፣ ታሪካቸው በሃሰተኛ ትርክት የተሸፈነ ነው፡፡
ማን ነው ለእነዚህ ታሪኮች መሸፈን ወይም ተጣሞ መቅረብ ተጠያቂው?
ይሄ ግልጽ ነው፤ ወያኔ ነው፡፡ ከወያኔ ጀርባ አለማቀፍ አካል እንዳለም ግልጽ ነው፡፡ አፄ ዮሐንስን ብንወስድ፤ በ1889 ነው መተማ ላይ የተሰዉት፡፡ አፄ ዮሐንስ፤ 17 ሺህ ጐጃሜ በግፍ ገድለዋል፡፡ ከ30 ሺህ ያላነሰ የወሎ ሙስሊምና የቅባት ክርስቲያኖችን ገድለዋል፤ ምላስ ቆርጠዋል፤ መሬት ላይ አስተኝተው ከብት ነድተውባቸዋል፤ በጣም አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፡፡ እነዚህ በጽሑፍ የተቀመጡ ታሪኮች ናቸው፡፡ ይሄ የእሣቸው ታሪክ እንዲነገር አይፈለግም:: ሆነ ተብሎ በአፄ ቴዎድሮስና በአፄ ምኒልክ ላይ ነው ዘመቻው የተከፈተው፡፡ እነዚህን ነገስታት የአማራ ገዥዎች አድርጐ ለማቅረብ ነው ጥረት የሚደረገው:: ይሄን ትርክት የፈጠረው ደግሞ ወያኔና ከጀርባው ያሉ አለማቀፍ አካላት ናቸው፡፡ ከወያኔ ጋር ሃሳብ ተጋርቶ የተፈጠረው ሌላኛው ድርጅት  ደግሞ ኦነግ ነው፡፡ ሁለቱም የተፈጠሩት አንድ ዘመን ላይ ነው:: በ1871 ነው “የኢትዮጵያ ህዝቦች አርነታዊ ግንባር” በበርሊን የተመሠረተው፡፡ “ህዝቦች” እና “ግንባር” የሚለውም እንግዲህ የመጣው ያኔ ነው፡፡ እነዚህ ግንባሮች አሁንም አብረው ናቸው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት 27 አመታት ምን አይነት አሰቃቂ ግፍ እንደደረሰበት ይታወቃል፡፡ አንድ በአንድ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አርቲስት ኤቢሣ አዱኛ፤ ከእነ ህይወቱ በመኪና ተጐትቶ እንዲገደል ተደርጓል፤ ነቀምት ውስጥ እናት የልጇ አስከሬን ላይ ተቀምጣለች፤ ኢሬቻ ላይ በታቀደ መልኩ ሰዎች ገደል ገብተው እንዲሞቱ ተደርጓል፤ አምቦ ለ27 አመት አልቅሳለች፤ ሻኪሣ፣ ወለጋ፣ ሻሸመኔ -- የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግፎች በወያኔ ተፈጽመዋል:: ነገር ግን ኦነግ ወደ ሀገር ቤት ሲገባ፣ ይሄን ግፍ ከፈፀሙ ሰዎች መቀሌ ላይ የቀረበለትን ግብዣ ተቀብሏል፡፡ ይሄ በኦሮሞ ህዝብ ላይ መሣለቅ ነው:: በሌላ በኩል ሁለቱ የአላማ አንድነት እንዳላቸው ማሳያም ነው:: ኦነግ ከዚህ አንፃር የኦሮሞ ህዝብ ተወካይ ሊሆን አይችልም፡፡  
በመጽሐፍዎ “አፄ ኃይለሥላሴ ሙሉ ለሙሉ ኦሮሞ ናቸው፤ ምኒልክ በከፊል ኦሮሞ፣ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያምም ኦሮሞ ናቸው” ብለዋል፡፡ ይህን ያሉት ኦሮሞዎችም ሀገር መርተዋል ለማለት ይመስላል--?
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አሊ ኦሮሞ መሆናቸውን ራሣቸው ተናግረዋል፡፡ ከእሣቸው በፊት ያሉት ኃይለማርያም ደሣለኝ ቦሼ፤ ወላይታ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ አስረስ “ትግሬ ነኝ፤ ወርቅ ከሆነው የትግራይ ህዝብ በመፈጠሬ እኮራለሁ” በማለት ትግሬነታቸውን አስረግጠውልናል፡፡ መንግስቱ ኃ/ማርያም ወልዴ አያና፤ የሸዋ ኦሮሞ ናቸው፤ በመጽሐፋቸውም ላይ ገልጸውታል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ውልደታቸው ኤጀርሳ ጐሮ ነው፡፡ ኤጀርሣ ጐሮ የኦሮሞ ሀገር ነው፡፡ አባታቸው መኮንን ወ/ሚካኤል ጉዲሣ ናቸው፣ እናታቸውም ከአባ ጅፋር ዘር የሚመዘዙ ኦሮሞ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ አፄ ኃይለሥላሴ ኦሮሞ ናቸው፡፡ በስነልቦናም ተሳስረው የነበረው ከኦሮሞ ጋር ነው፡፡ የደርጉ ደበላ ዲንሣም (ም/ሊቀመንበሩ) ኦሮሞ ናቸው፡፡ አፄ ምኒልክ በከፊል ኦሮሞ ናቸው፤ በእናታቸው በኩል:: በስልጣን ዘመናቸውም ዙሪያቸውን የከበቧቸው ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ምኒልክ ያላቸው የሸዋ ስነልቦና እንጂ የአማራ ስነልቦና አይደለም ማለት ነው፡፡ የሸዋ ስነልቦና ራሱን የቻለ ነው፡፡ ጅማ አባ ጅፋርን ልጄ እያሉ እያቀረቡ፣ ጐንደሮችን እንግዶች አድርገው ነበር የሚመለከቱት፡፡ ይሄን የፈጠረው የሸዋ ስነልቦናቸው ነው፡፡ አፄ ምኒልክ የአማራ ስነልቦና ኖሯቸው አያውቅም፡፡ ከሸዋ ስነልቦና በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ስነልቦና ነው የነበራቸው፡፡ ስነልቦና የሰዎችን ማንነት በሚገባ ይቀርፃል፡፡ እኔ አሁን በማንነቴም ሆነ በስነልቦና ኦሮሞ ነኝ፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያዊነትን ለአማራ ስነልቦና ሰዎች ሲሰጡ ይስተዋላል፤ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ሥነልቦና የአማራ ሥነልቦና አይደለም፡፡ እንደውም ኢትዮጵያዊ ሥነልቦናን ለአንድ ማህበረሰብ ብቻ ማሸከም ለኔ በደል ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የነበራቸው ስነልቦና ከፍ ሲል ኢትዮጵያዊ ነው:: እነዚህ ሰዎች አማራ አይደሉም፡፡ እንደውም የአማራ ብሔርተኝነትን ማፋፋት እንዳይሆን እንጂ በእነዚህ ነገስታት ዘመን ከፍ ያለ በደል የደረሰበት አማራው ነበር፡፡ በየትኛውም ሥርአት ከፍ ያለ በደል የደረሰበት አማራው ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያደረጉትን ጦርነትና አብርሃም ሊንከን አሜሪካን አንድ ለማድረግ ያደረገውን ጦርነት ለማነጻጸር ሞክረዋል ---
አዎ፤ ይሄ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡ አብርሃም ሊንከን እንደተመረጠ ባርነትን ለማጥፋት ነው ቃል የገባው፡፡ ቢያንስ ጥቁሮች ከባርነት ነፃ መውጣት አለባቸው፤ መሬት ተሰጥቷቸው ይኑሩ ብሎ ነው የተነሳው፡፡ ይሄን ለምርጫ ውድድርም ተጠቅሞበታል፡፡ የደቡቦቹ ግዛቶች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ባሪያ አሳዳሪ ነበሩ፡፡ የሰሜን አሜሪካ ሰሜናዊ ክፍል በአሠራሩ የተሻለ ነበር፡፡ የደቡቡና የሰሜኑ ስርአቶች በባህሪያቸው የማይጣጣሙ ነበሩ፡፡ በ1861 አብርሃም ሊንከን ሲመረጥ፣ ባሪያ አሳዳሪ የሆኑት የደቡቦቹ ግዛቶች ኮንፌደሬት ስቴትስ ኦፍ አሜሪካንን በካሮሊና መሪነት መሠረቱ፡፡ ከእነዚህ የደቡብ አካባቢዎች ውስጥ 11ዱ ደግሞ ጀፈርሰን ዴቪሰንን በፕሬዚዳንትነት መርጠው ተገነጠሉ:: የሀገርን አንድነት ማስጠበቅ ስለነበረበት በዚህ ወቅት አብርሃም ሊንከን ትግሉን ጀመረ፡፡ ከ1961 እስከ 63 ባለው ጊዜ ደቡቦቹ አሸነፉ፡፡ በ1963 ላይ ግን “ጥቁሮች ነፃ ይውጡ፤ ከዛሬ ጀምሮ ጥቁር ባሪያ የሚባል የለም” ብሎ ሊንከን  አዋጅ አወጣ፡፡ ከዚያም  ጥቁሮች መሬት ይሠጣቸው አለ፡፡ ጥቁሮች መሬት የሚሰጠን ከሆነ ብለው ወደ ሰሜኑ ፈለሱ:: ይሄን የፈለሰ ሃይል ተጠቅሞም ብላክ ሬጅመንት (ጥቁር ጦር) የሚባለውን ጦር አቋቋመ፡፡ በወቅቱ በተደረገው ጦርነት 360 ሺህ ከሰሜኑ፣ 260 ሺህ ከደቡቡ ሞተው፣ በድምሩ 620 ሺህ ተሰውተው ነው የሀገር አንድነትን ያረጋገጠው፡፡ ምኒልክ ግን ጐራዴና ጦር ተጠቅመው ነው በጥቂት መስዋዕትነት ሀገርን አንድ ያደረጉት፡፡ ከወላይታና ከፋ በስተቀር ደም አፋሳሽ የሚባል ጦርነትም እምብዛም አልተካሄደም:: ምኒልክ በወቅቱ ብልሃትንም ተጠቅመዋል፡፡  
አንዳንዴ ወለጋ አካባቢ የከረረ የምኒልክ ጠል ትርክት ሲፈጠር ያስገርመኛል፡፡ ወለጋ ማለት እኮ ምኒልክ ማለት ነው፡፡ ምኒልክ ለሚወቀሱበት ነገር በሙሉ ወለጋ ተወቃሽ ነው፤ የሸዋ ኦሮሞ ተወቃሽ ነው፡፡ የወለጋ ልሂቃን እንደውም ሸዋን “ጐበና” እያሉ ነበር የሚጠሩት፡፡ ተወቃሹ ነው ዋናው ወቃሽ ሆኖ የቀረበው፡፡ ይሄ ሁሉ ትርክት የመጣው ከጀርመን ናዚ ነው የምለው ለዚህ ነው፡፡ በመጽሐፉ ላይ ይሄን ጉዳይ አብራርቼዋለሁ፡፡
ህገ መንግስቱን  አምርረው ይተቻሉ፤ “ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች” የሚለውን ፍልስፍናም ጥመት ያለበት ነው ይላሉ፡፡ እስቲ ይሄን ጉዳይ ያብራሩት--    
ብሔርና ብሔረሰብ በአዲሱ የወያኔ ትርጉም አንድ የሚያደርጋቸው፤ ብሔርም ብሔረሰብም አንድ አይነት ቋንቋ ነው የሚናገሩት፤ ያላቸው መልክአ ምድር ተመሳሳይ ነው ይልና፤ ልዩነታቸውን ሲያስቀምጥ፤ ብሔር በተሻለ የምጣኔ ሀብት ደረጃ የሚገኝ ነው ይላል፤ ብሔረሰብ ደግሞ በዝቅተኛ ምጣኔ ደረጃ የሚገኝ ነው ይላል፡፡ ለምሣሌ ትግራይ ውስጥ ሶስት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች አሉ:: ትግራይ፣ ኩናማና ኢሮብ፡፡ ትግራይን ብሔር ይለዋል፤ የምጣኔ ሃብት ደረጃውና የተማረ ሃይሉ ሰፊ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ኩናማና ኢሮብን ደግሞ ብሔረሰብ ይላቸዋል፡፡ ኦሮሞ፤ አማራ ክልል ውስጥ አለ፡፡ አማራ ክልል ውስጥ ያለው ኦሮሞ በምጣኔ ደረጃ አናሣ ስለሆነ ብሔረሰብ ይባላል፤ ኦሮሚያ ሲመጣ ደግሞ ብሔር ይባላል፡፡ ስለዚህ ብሔርና ብሔረሰብ ልዩነታቸው የምጣኔ ሀብት ሁኔታ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ አሁን ስናየው አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራይ ብሔሮች ይሆናሉ፤ በውስጣቸው ያሉት ኩናማ፣ አገው፣ ቅማንት የመሳሰሉት ደግሞ ብሔረሰብ ይባላሉ ማለት ነው፡፡ ኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነው ህዝብ አንዱ ጋ ብሔር፣ ሌላው ጋ ብሔረሰብ የሚሆንበት ቅጥ አምባሩ የጠፋበት ስርአት ነው:: ብሔር ሀገር ማለት ነው፡፡ አሁን ብሔር ብለን ስንነሳ ለመገንጠል ተመቻችቶ የቀረበ ብያኔ ነው፡፡ ህዝቦች የሚል ነገርም አለ፤ ይሄ ሰዎችን በስነልቦና ለመገነጣጠል የተደረገ ነው፡፡ እንጂ በየትኛውም ሁኔታ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ፤ ህዝብ እንጂ ህዝቦች ሊባል አይገባውም፡፡ በሌላው አለም ህዝቦች የሚል መጠሪያ በህገ መንግስት የለም፡፡ አጠቃላይ ሴራው የመገነጣጠል ስነልቦናን ማስረጽ ነው፡፡ እንስሳዎችም አልመች ብለው እንጂ የእነሱም እጣ ፈንታ ይሄ መሆኑ አይቀርም ነበር፡፡
እርስዎ የጠቀሱት “የመገነጣጠል ስነልቦና” እና የመከፋፈል አደጋ እንዴት ሊታከም ይችላል ብለው ያስባሉ?
የመጀመሪያው ማስተማር ነው፡፡ አሁን ፌደራሊዝም የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር የለም፡፡ በደቡብ  ስራ ላይ አልዋለም፡፡ ሀረሪ ደግሞ ህዝቧ የቦሌ ክፍለ ከተማ ያህል አይሆንም፤ ግን ክልል ሆናለች፡፡ ትግራይ ውስጥ ኩናማዎች አሉ፤ የራሣቸው ክልል የላቸውም፤ ተደፍጥጠዋል፡፡ አርጐባ፤ አፋርና አማራ ክልል ውስጥ ተከፋፍሎ እንዲኖር ተገድዷል፡፡ ታዲያ ይሄን ምን ብለን ነው ፌደራሊዝም የምንለው? አማራ ክልል ውስጥም  አገው፣ ቅማንቱ፣ አርጐባው፣ ኦሮሞው በአማራ ማንነት ውስጥ ተውጦ ነው ያለው:: ኦሮሚያ ውስጥ በታሪካዊ መስተጋብር የመጣው 15 ሚሊዮን ህዝብ፣ በኦሮሞ ማንነት ተውጦ ይገኛል፡፡ ታዲያ ፌደራሊዝሙ ምንድን ነው? አንደኛና ሁለተኛ ዜጋን የፈጠረ ፌደራሊዝም ነው፡፡ ፌደራሊዝም የተባለው ራሱ ብዙ ችግር የፈጠረ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ሁኔታ በአንድ ጀንበር ይስተካከል ማለት አንችልም፡፡ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ዲሞክራሲ ራሱ “ኢቮሉሽነሪ” እንጂ “ሪቮሉሽነሪ” አይደለም:: ይሄም ዝግመተ ለውጣዊ በሆነ ሂደት ነው መስተካከል ያለበት፡፡ በአለም ላይ 28 ሀገሮች ናቸው ፌደራሊዝምን የሚከተሉት፡፡ የእነሱም በአብዛኛው ጂኦግራፊያዊ ፌደራሊዝም ነው፡፡ የኛም በሂደት መምጣት ያለበት ወደ ጂኦግራፊያዊ ፌደራሊዝም ነው፡፡ ስዊዘርላንድ ውስጥ ተማሪዎች እስከ 6ኛ ክፍል በራሣቸው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ይማራሉ፤ ከዚያ በኋላ ግን በስፋት የሚነገሩ አራት ቋንቋዎችን ነው የሚማሩት፡፡ ይሄ በኛም አገር ቢጀመር፤ ሰዎች ቋንቋን መገደቢያ ከማድረግ ስነልቦና እየተላቀቁ ይሄዳሉ፡፡ በዚህ አይነት ስልት ነው ወደተሻለው መንገድ ልንሄድ የምንችለው፡፡
እንዴት ነው በታሪክ ጉዳይ ላይ አገራዊ መግባባት የሚፈጠረው? የታሪክ ምሁራን ሚናስ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
በመጀመሪያ ለታሪክ ትምህርት ቤት ሥነምግባርና መርሆ ተገዥ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ምሁሩ ለዚያ መርሆ ተገዥ ከሆነ የራሱን መሻትና የራሱን ብሔር አይደለም የሚያስቀድመው፤ ከታሪክ ትምህርት አላማ ነው የሚነሳው፡፡ አላማው ያለፈውን አጥንቶ፣ ዛሬና ነገን የተሻለ ማድረግ የሚል ነው፡፡ አሜሪካኖችን ያሳደጋቸው የመጀመሪያው አንድነታቸውን የሚያፀና ነገር ማድረጋቸው ነው፡፡ መጀመሪያ አንድነትን የሚያመጣ ነገር መመርመር ነው፡፡ ለምሣሌ ምኒልክ የነበራቸው ድክመት ላይ ከማፍጠጥ ይልቅ በዚህ በዚህ ጉዳይ ጠንካራ ነበሩ ብሎ መዘገብ፤ እዚህ ቦታ ግጭት ፈጥረዋል፣ ባይፈጥሩ ግን ጥሩ ነበር ብሎ ማለፍ እንጂ ቂምን መትከል ተገቢ አይሆንም:: በዚህ ቅንነትና ስነምግባር ውስጥ ካልገባን ዋጋ የለውም፡፡ ምኒልክ በመሞገሳቸው ወደ ላይ የሚወጣ የህብረተሰብ ክፍል የለም፤ ሲወቀሱም አብሮ የሚወርድ ማህበረሰብ የለም፡፡ ይሄን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ የዛሬዎቹ እንግሊዞች እኮ ታሪክን መማሪያ ብቻ ስላደረጉት እንጂ ታሪካቸው እኮ በእጅጉ የጨቀየ ነው፡፡ እነሱ ግን እንደኛ ጭቃውን ማንሳት አይፈልጉም፤ ለመማሪያነት ይወስዱና ስነልቦናቸውን የሚገነባውን ያጐላሉ፡፡ የኛ ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ የታሪክ ምሁራን ይሄን የማረቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለአሁኑ ዘመን እንድንመጥን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በብሔር ሳይሆን በሀገር እንድንግባባ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ለመንጋ ከመቆም ይልቅ ለሀገር መቆም  አለባቸው፡፡


Read 9093 times