Saturday, 13 July 2019 11:36

በእርግዝና ወቅት ሰውነት ይ ላላል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  ባለፈው ሳምንት እትም ለንባብ ያልነው እስፖርትንና እርግዝናን የሚመለከት ርእሰ ጉዳይ ነው፡፡ የሴቶች ገጽ የተባለው ድረገጽ ያወጣቸው መረጃዎች በአጭሩ ተቀንጭበው ማለትም ዋና ዋና የተባሉት ቁምነገሮች ተመርጠው እንጂ የቀረቡት ነጥቦች ብቻ አይደሉም ለንባብ የወጡት፡፡ በዚህ እትምም ቀሪዎቹን ጠቃሚ ነገሮች እናስነብባችሁዋለን፡፡
አንዲት ሴት ከማርገዝዋ በፊትና ካረገዘችም በሁዋላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚጠቅማት ሲሆን እንደ እርግዝናው ወቅት እና እንደ ጤንነትዋ ሁኔታም የምትሰራቸው እስፖርቶች ይለያያሉ፡፡ የእርግዝናው ጊዜ በሶስት ቢከፈልም ባገኘነው መረጃ ግን በሁለት ተከፍሎ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
የመጀመሪያው የእርግዝና ወቅት (ከ1-12) ሳምንታት፤
በዚህ ወቅት የሚሰሩ የእስፖርት አይነቶች ከልክ በላይ ሙቀት የሚያስከትሉ ከባድ የእስፖርት አይነቶች መሆን የለባቸውም፡፡ ይህ ጥንቃቄ ያረገዘችውን ሴት እንዲሁም የጽንሱን ደህንነት ለመጠበቅ ይረዳል፡፡  ስለዚህ…
ከፍተኛ ሙቀት ወይንም ወበቅ ባለበት ሰአት እስፖርት መስራት አያስፈልግም፡፡
ሰውነትን የማያጣብቅ (ለቀቅ) ያለ እና ለእስፖርት እንቅስቃሴው የሚመች ልብስ መልበስ ጥሩ ነው፡፡
እስፖርትን በሚሰሩበት ገዚ ውሀ በአስፈላጊው መጠን መጠጣት ተገቢ ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛው የእርግዝና ወቅት (ከ13-40) ሳምንታት፤
በዚህ ወቅት ጽንሱ አቀማመጡን ወደላይ የሚያደርግበት በመሆኑና የጀርባ አጥንት ሊከላከለው ወይንም ሊጠብቀው የማይችልበት አቀማመጥ በመሆኑ ከበድ ያለ የእስፖርት አይነት ቢሰራ ልጁ በእንቅስቃሴው ምክንያት ሊመታ ይችላል፡፡ ስለዚህ በእርጋታ የሚሰሩ የእስፖርት አይነቶችን መምረጥ ይገባል፡፡
ያረገዘችው ሴት ሰውነት እራሱ በእንቅስቃሴው ምክንያት ወደፊት ወይንም ወደሁዋላ የሚገፋና  ልትወድቅ የምትችልበት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል ደህንነትን ማረጋገጥና አለመመቸትን ማስወገድ ይገባል፡፡
የሰውነት መገጣጠሚያዎች ጡንቻዎች አቅም ሊያጡና ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ክብደት ያላቸውን ወይንም ድንገተኛ እንቅስቃሴዎችን፤ አቅጣጫ በድንገት የሚያስለውጡ እንቅስቃሴዎችን ማስወገድ ይገባል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት የደም ግፊት የመቀነስ ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል በመቀመጥ መነሳት ወቅት መጠንቀቅ ያሻል፡፡
ጽንስ ከተፈጠረ ከ16/ ሳምንታት በሁዋላ በጀርባ ተኝቶ የሚሰራ እንቅስቃሴን ማድረግ አይገባም፡፡ የዚህ ምክንያትም ከእናትየው ወደልጁ የሚሄደውን የደም ስርጭት ሊያውክ እና እናትየውንም እራስዋን መቆጣጠር እንዲያቅታት ሊያደርግ ስለሚችል ነው::
በእርግዝና ወቅት ምን ያህል ጊዜ እስፖርት መስራት ያስፈልጋል?
እርጉዝ ሴት ከሕክምና ባለሙያ ጋር ተመካክራ የምትሰራቸውን የእስፖርት አይነቶች በቀን ለ30 ደቂቃ በሳምንት ለአራት ቀን ማድረግ ትችላለች፡፡ ከእርግዝናው ጋር በተያያዘም ሆነ ያረገዘችው ሴት አስቀድሞውኑ ያሉአት የተለያዩ የጤና እክሎችን መሰረት ባደረገ እና የሕክምና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር መሰረት እንዲሁም እናቶቹ ያላቸውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልምድ መሰረት ባደረገ የእስፖርት እንቅስቃሴው ፕሮግራም ሊለዋወጥ ይችላል፡፡ ለሁሉም ነገር የሕክምና ባለሙያ ምክር አስፈላጊ ነው፡፡
የሚመከሩ የእስፖርት አይነቶች፤
የእግር ጉዞ፤ የእግር ጉዞ ማንኛዋም እርጉዝ ሴት ልታደርገው የምትችለው ጠቃሚ የእስፖርት አይነት ነው::
የውሀ እስፖርት፤ የውሀ እስፖርት ማለት እንደ ዋና፤ ውሀ ውስጥ ኤሮቢክስ እስፖርት መስራት፤ ውሀ ውስጥ የእግር ጉዞ ማድረግ ማለት ሲሆን እርጉዝ ሴቶች ይህን ቢያደርጉ ምንም ክልከላ የለባቸውም፡፡ በተለይም ዋና ሁሉም ጡንቻዎች በደንብ እንዲሰሩ እና እንዲጠነክሩ ስለሚያስችል እና ከልብ ጋር በተያያዘ የጤንነትን ብቃት ለማረጋገጥ ሲባል መስራት ጠቃሚ ነው፡፡ ውሃ ዋና በእርግዝና ጊዜ ለሚከሰት የጀርባ እና የእግር ሕመም እንደ መፍትሔም ይቆጠራል፡፡
የማይንቀሳቀስ ብስክሌትን መንዳት፤ ለእስፖርት የተዘጋጀ ብስክሌት ላይ ማለትም መንገድ ላይ ሳይወጡ ባለበት ቦታ መጋለብ ወይንም መንዳት ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይም እርግዝናው ወደመጨረሻው ሳምንት ከሆነው ብስክሌት ላይ ለመሆን ሚዛንን መጠበቅ ስለሚያስቸግር የማይንቀሳቀስ ብስክሌትን መጠቀም ጠቃሚ ነው፡፡
ሩጫ፤ እርጉዝዋ ሴት ከማርገዝዋ በፊት ሩጫን የተለማመደች እና ትሮጥ የነበረች ከሆነች  በእርግዝናዋ ወቅት መሮጥ አያስቸግራትም፡፡ ነገር ግን ከእርግዝና በፊት ሩጫን ያልሞከረች ሴት በእርግዝናዋ ወቅት እንድትሮጥ በፍጹም አትመከርም፡፡ ልምምድ ያላት ሴት ለስንት ሰአት እና በሳምንት ምን ያህል ቀን ትሩጥ ለሚለው እንደሴትየዋ ሁኔታ ይወሰናል፡፡
በእርግዝና ጊዜ እስፖርት እንዳይሰራ ከሚከለከሉባቸው ምክንያቶች መካከል፤
የስኩዋር ፣የታይሮይድ፣የደም ግፊት የመሳሰሉት ችግሮች የሚታዩባቸው እርጉዝ ሴቶች እስፖርት መስራት አይመከሩም፡፡
እርግዝናው የመጀመሪያ ካልሆነ በቀደመው ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ልብ ብሎ ማስታወስ ይገባል:: ለምሳሌም ባለፈው እርግዝና ምጥ ያለጊዜው በመምጣት አስቸግሮ ከነበረ በቀጣዩ እርግዝና ጊዜ እስፖርት ብትሰራ ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥማት ስለሚችል ካለሐኪም ምክር እንዳትሰራ ትመከራለች፡፡
የተረገዘው ልጅ በክትትሉ ወቅት ሲታይ በጣም ቀጭን ወይንም የጫጨ ከሆነ ምናልባትም እስፖርቱን እናትየው ብትሰራ የበለጠ ሰውነቱ አንዳይጎዳ ሲባል ለእነዚህ ሴቶች  እስፖርት አይመከርም፡፡
በእርግዝና ጊዜ የደም መፍሰስ ካለ ሁኔታው በሐኪም ሳይጣራ እና ሳይፈቀድ ወደ እስፖርት መሄድ አይገባም፡፡
እርግዝናው መንትያ ከሆነ በተለይም ሶስት እና ከሶስት በላይ ከሆነ እስፖርት መስራት ይከብዳል፡፡
ማህጸናቸው ልጅ የመሸከም ችግር ያለባቸው ሴቶች በእርግዝና ወቅት እስፖርት እንዲሰሩ አይመከርም::
‹‹…አንዲት ሴት በምትጸንስበት ጊዜ የሚታዩ የተለያዩ አካላዊ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ ከሰውነት መጠቁዋቆር ጀምሮ በእግር እጅና ፊት እንዲሁም ሰውነት የማበጥ ሁኔታዎች ይከሰታሉ፡፡ እብጠቱ የሚከሰትበት ምክንያት እርግዝናው እያደገ ሲመጣ የደም መልስ የሚባለውን ከእግር ወደልብ ደምን የሚመልሰውን የደም ቡዋንቡዋ ስለሚጫነውና የደም ዝውውሩን ሰለሚያውከው ነው፡፡ በእርግዝና ጊዜ ፈሳሽ በሰውነት ውስጥ ይጨምራል፡፡ ያ ፈሳሽ በሚጨምርበት ጊዜ ከደም ቡዋንቡው እየወጣ በቆዳ ስር ይከማቻል፡፡ ይሄ ነገር በብዛት የሚከሰት ሲሆን ከሌሎች ሕመሞች ጋር በተያያዘ ካልሆነ በስተቀር እንደ ችግር አይቆጠርም፡፡ ነገር ግን የደም ግፊት ፣ኩላሊት ከመሳሰሉት ሕመሞች ጋር የሚያያዝ ከሆነ አሳሳቢ ይሆናል፡፡ በህመም ምክንያት ማለትም የልብ የኩላሊት የጉበት የመሳሰሉት በሽታዎች ያሉባት ሴትም በእግሩዋ ወይንም በሰውነትዋ ላይ እብጠት ሊኖራት ይችላል፡፡ በእርግዝናው ምክንያት የሚከሰተው ግን አሳሳቢ አይደለም፡፡ የሰውነት መጠቋቆር የሚከሰተው ደግሞ ኢስትሮጂን እና ፕሮጀስትሮን የተባሉት ሆርሞኖች (ቅመሞች) መጠናቸው ስለሚጨምር ነው፡፡ በእርግዝና ጊዜ የልብ ሕመም፣ የደም ዝውውር ችግር ፣ስኩዋር የመሳሰሉት ሕመሞችም ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በእርግዝና ጊዜ ሴቶች የደማቸው መጠን ብዛቱ ማለት ነው ሊጨምር ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ወቅት ደግሞ ልብ ስራው ይጨምራል፡፡ በደቂቃ የሚተነፈሰው ትንፋሽም በደቂቃ መጠኑ ከፍ ይላል፡፡ በእርግዝና ጊዜ የሰውነት መገጣጠሚያዎች እና የወገብ አጥንት በዳሌ አካባቢ ያሉ አጥንቶችና መገጣጠሚያዎች ልጅ በሚወለድበት ጊዜ ሰውነት እንዳይጠብቅ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ሰለሚያደርጉ ይላላሉ፡፡ እርግዝናው የሰውነት አቋምን አለመስተካከል፣ድካምን እንዲሁም የተለያዩ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን እነዚህን ለማቃለልም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በባለሙያዎች ይመከራል፡፡››
ዶ/ር ደሴ እንግዳየሁ
በአንድ ወቅት የሰጡት ማብራሪያ

Read 11999 times