Saturday, 13 July 2019 11:23

ህወኃትና አዴፓ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(29 votes)

- አዴፓ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለበት - (ህወኃት)
      - ትህነግ/ህወኃት ከጥፋት ኃይሎች ጀርባ መሽጎ አመራር እየሰጠ ነው - (አዴፓ)


          የህወኃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ባወጣው የአቋም መግለጫ ለሰኔ 15ቱ የባለሥልጣናት ግድያ አዴፓ ኃላፊነቱን ወስዶ ሕዝቡን ይቅርታ ይጠይቅ ማለቱን ተከትሎ፤ አዴፓ በሰጠው ምላሽ፤ ‹‹ህወኃት ከተጠናወተው የሴራ ፖለቲካ እንዲታቀብ አሳስቧል፡፡ ትህነግ/ህወኃት፤ አገራዊና ክልላዊ ለውጡ በጥርጣሬ እንዲታይ፣ ከጥፋት ኃይሎች ጀርባ መሽጎ አመራር እየሰጠ እንደሆነም ገልጿል::
የመከላከያ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ግድያን በጽኑ ያወገዘው የህወኃት መግለጫ፤ የባለሥልጣናቱን ግድያ መነሻ በማድረግ የአገሪቱ የህልውና ሁኔታ በከፋ ደረጃ እንደሚገኝ ገምግሜያለሁ ብሏል፡፡
‹‹ትናንት የአገሪቱን ህልውናና ክብር አሳልፈው የሰጡና ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን የማይተኙ ሃይሎች፤ በስመ ለውጥ ግንባር ለመፍጠር፣ አሰላለፉ ባልለየ መልኩ ተደበላልቀው አንድ ላይ እንዲሆኑ በመደረጉ፣ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተደራረበ፣ አሁን ላለንበት ደረጃ በቅተናል›› ያለው የህወኃት መግለጫ በተቃራኒው ለዚች አገር ክብርና ህልውና ሲሉ ዕድሜ ልካቸውን የታገሉት የሚታደኑበት፣ የሚታሰሩበትና ጥላሸት የሚቀቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብሏል፡፡
በአገሪቱ ከምንጊዜው በላይ ሰላምና ሥርዓት ማስከበር አልተቻለም፤ አገሪቱ ጽንፈኛ ሃይሎች የሚፈነጥዙባት እየሆነች ፀረ ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ - ሥርዓት የሆኑ ጽንፈኛ የትምክህት ሃይሎች እንዳሻቸው የሚሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብሏል - የህወኃት መግለጫ፡፡
‹‹ተጀምሮ የነበረው ተስፋ ሰጪ ልማትና ዕድገት በአሁን ወቅት መሪ አልባ ሆኖ ቁልቁለት መውረድ የጀመረበት ሁኔታ ላይ ይገኛል›› ያለው ህውኃት፤ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ከምንም ጊዜ በላይ የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ አልቻሉም፤ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ግድያም ለዚህ ማሳያ ነው፤ በግፍና ጭካኔ የሥልጣን ፍላጎቶቻቸውን ማርካት የሚፈልጉ የትምክህት ሃይሎች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሽገው ሕገ መንግሥቱንና ማዕከላዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል›› ብሏል፡፡
ህወኃት በዚህ ዘለግ ያለ መግለጫው፤ አገሪቱ በየቀኑ ወደ ስጋት እያመራች እንደሆነና በቀጣይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የማይታወቅበት ሁኔታ መፈጠሩንም አመልክቷል፡፡ ‹‹የአገሪቱ ህልውና የከፋ አደጋ ላይ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ›› ያለው ህወኃት፤ አገሪቱ ወደ ቀድሞ መስመር መመለስ አለባት›› ብሏል፡፡
ህወኃት በዚህ መግለጫው ሰባት አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን አስቀምጧል፡፡ በመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ ላይ ማን ተሳትፎ እንዳለው በገለልተኛ አካል እንዲጣራ፣ የደህንነት አመራሮች በድርጊቱ የነበራቸው ሚና ወይም ግዴታን ባለመወጣታቸው በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የማጣራት ሂደቱ በየጊዜው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ እንዲደረግ ጠይቋል - ህወኃት፡፡
‹‹በዚህ ወቅት አገር እየተበታተነ ያለው ከዚህም ከዚያም በተሰባሰበው የትምክህት ሃይል ነው›› ያለው ህወኃት፤ ይህ ሃይል ዕድል አግኝቶ እንደፈለገ እንዲሆን እያደረገ ያለው ደግሞ አዴፓ ነው ብሏል፡፡ በመሆኑም አዴፓ በአጠቃላይ በተፈፀመው ጥፋት በተለይም በድርጅቱ አመራሮች ላይ ባጋጠመ ግድያ ላይ ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ፣ ግልጽ አቋም ወስዶ የኢትዮጵያን ህዝቦች ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብሏል፡፡
‹‹የውስጥ ችግሩን ለመሸፈንም ጥፋቱን በሶስተኛ ወገን ማሳበብና ረጃጅም እጆች አለበት በማለት ሕዝብን ማወናበድ ማቆም አለበት›› ያለው ህወኃት፤ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ግልጽ አቋሙን እንዲያሳውቅ፤ ካልሆነ ግን ህወኃት ከእንደዚህ ዓይነት ሃይል ጋር አብሮ ለመስራትና ለመታገል እንደሚቸገር መታወቅ አለበት ብሏል፡፡
ሕገ መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ሃይል ነኝ ያለው ህወኃት፤ ለወደፊት ሕገ መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ከሆኑ ሃይሎች ጋር ሰፊ መድረክ በመፍጠር ለመታገል በአስቸኳይ ወደ ተግባር እንደሚሸጋገርም አመልክቷል፡፡ ህወኃት በዚህ መግለጫው፤ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙም አሳስቧል፡፡ አያይዞም፤ የመከላከያ ሠራዊት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያስከብር ጥሪ አቅርቧል፡፡
መግለጫ ምላሽ የሰጠው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በበኩሉ፤ የህወኃት መግለጫ ‹‹በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት›› አይነት ነው ብሏል፡፡  
‹‹የሰኔ 15 የባለሥልጣናት ግድያን ተከትሎ ከገባንበት ትልቅ ሀዘን ባልተላቀቅንበት ሁኔታ ትህነግ/ህወኃት ያወጣው መግለጫ ትህነግ/ህወኃት የነበረውንና እየቀጠለ ያለውን አሳፋሪ የሴራ ፖለቲካ እርቃኑን በአደባባይ ያጋለጠ›› ነው ያለው አዴፓ፤ ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል እንዲሉ፣ አገራችን አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት እራሱ ዋና ተጠያቂ ሆኖ ሳለ፣ የአማራን ሕዝብና ህልውናና ክብር የማይመጥን መግለጫ አውጥቷል ብሏል፡፡
‹‹መግለጫው ከአንድ እህት ፓርቲ የማይጠበቅ ነው›› ያለው አዴፓ፣ መግለጫው የትህነግ/ ህወኃትን መሠሪና አሻጥር የተሞላበትን የዘመናት ባህሪውን ያጋለጠ ነው ብሎታል፡፡ ‹‹የአማራ ህዝብን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ባደረጉት ቆራጥ ትግል፣ የተገኘውን ህዝባዊ ድል ደግሞ ደጋግሞ በማንኳሰስና ፈጽሞ አክብሮት የማያውቀውንና እራሱ ሲጥሰው የነበረውን ህገ መንግሥታዊና መድሏዊ ሥርዓት ጠባቂ በመምሰል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ጭቁን ህዝቦችን በማደናገር ለዳግም ሰቆቃ እንዲዳረጉ እያደረገ ባለበት፤ በፀረ ለውጥ እንቅስቃሴው አገራዊና ክልላዊ ለውጡ በጥርጣሬ እንዲታይ ከጥፋት ሃይሎች ጀርባ መሽጎ አመራር እየሰጠ ነው›› ብሏል አዴፓ፡፡
ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የለውጥ ፍላጎት መነሻ ተደርገው የተወሰዱ አሳሪና ደብዳቢ፣ ፀረ ዴሞክራቶችን፣ ሕዝብና አገር በድፍረት የዘረፉ ሌቦችን፤ በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልጆች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አቅፎና ደብቆ በያዘበት ሁኔታ ትህነግ/ህወኃት ያወጣው መግለጫ፣ የድርጊቱን አስመሳይነት ያጋለጠ ነው ብሏል አዴፓ በመግለጫው፡፡
ትህነግ/ህወኃት ከምስረታው 1968 ዓ.ም ጀምሮ የአማራን ህዝብ በጠላትነት የፈረጀ፤ ከሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር ተከባብሮና ተሳስቦ በፍቅር እንዳይኖር ‹‹ትምክህተኛ እና ሌሎች አግላይ ስያሜዎችን እየሰጠ፣ ለዘመናት ግፍ ፈጽሟል›› ያለው አዴፓ፤ አሁንም የአማራን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት የተቀበረውን የትምክህት ትኩረቱን ዳግም ይዞ ብቅ ማለቱ ድርጅቱ መቼውንም ቢሆን መፈወስ የማይችል በሽታ ያለበት መሆኑን ያጋለጠ ተግባር ነው ብሎታል፡፡ ትህነግ/ህወኃት ለህዝቦችና ለአገር አንድነት የማይጨነቅ ድርጅት መሆኑንም አዴፓ በመግለጫው አትቷል፡፡
‹‹ትህነግ/ህወኃት ይቅርታ እንድንጠይቅ መግለጫ ማውጣቱ ተጨማሪ ታሪካዊ ስህተት ነው›› ያለው አዴፓ፤ ‹‹ይህንን ወቅታዊ ሁኔታ የራሱን የዘመናት ወንጀሎች ለመሸፋፈን ተጠቅሞበታል›› ብሏል::  እውነትና ፍትህ ቢኖር ኖሮ፣ ባለፉት ዘመናት በትህነግ/ ህወኃት የሴራ ፖለቲካ ምክንያት ለተለያየ ጥፋትና እንግልት በተዳረገው መላው ሕዝብና አደጋ ውስጥ በወደቀው አገራዊ አንድነታችን ምክንያት ከወገቡ ዝቅ ብሎና ከልቡ ተፀፅቶ የተበደለውን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት ዋነኛው ተጠያቂ ትህነግ/ህወኃት ነው›› ብሏል - አዴፓ በዚህ መግለጫው፡፡
በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢና አጎራባች አገሮች ክልሎች ከሚከሰቱ ግጭቶች ጀርባ ትህነግ/ህወኃት እጁ እንዳለበት በርካታ ማስረጃዎች እንዳሉትም አዴፓ አስታውቋል፡፡
አዴፓ በዚህ መግለጫው በ6 ነጥቦች ባስተላለፈው የአብሮነትና የአጋርነት ጥሪውም፤ ‹‹አዴፓ ለህዝባዊ አላማዎች ግብ መሳካት መስዋዕትነት የከፈሉ ጓዶቹን አላማ ዳር ለማድረስ በፅናት የሚታገል የአማራ ህዝብ ፓርቲ እንጂ፣ እንደ ትህነግ/ህወኃት ላሉ የሴራ ሃይሎች የሚያጎበድድ ፓርቲ አይደለም›› ብሏል፡፡ ከሰኔ 15ቱ ክስተት በኋላም ከአደጋውና ከችግሩ ፈጥኖ በመውጣት ህዝቡን የማረጋጋት ሥራውን በላቀ ጥንካሬ እየተወጣ ወደ ላቀ ጥንካሬ እየተመለሰ መሆኑን አስገንዝቧል - አዴፓ፡፡
የትናንት እኩይ ሴራቸውን ዛሬም ማዳረሱ ወቅታዊ ችግሮቻችን እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም አንገት ሊያስደፉን ከሚፈልጉ ትህነግ/ህወኃትና መሰል የጥፋት ሃይሎች የማንበገር መሆናችንን በጽናት እየገለጽን፣ መላው የአማራ ህዝብና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችን እንድትሰለፉ እንጠይቃለን ብሏል አዴፓ፡፡
ለብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች እኩልነት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ለእውነተኛ ዴሞክራሲና የፌዴራሊዝም ሥርዓት እንዲሁም ለሃቀኛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንደሚታገል ያስታወቀው የአዴፓ መግለጫ፤ ትህነግ/ህወኃት የዘመናት ወንጀሎቹን በመሸፋፈንና ድርጅታችን አዴፓና የአማራ ህዝብን የሌሎች ህዝቦች ጠላት የሚያደርግ የተሳሳተ አስተምሮህ ዛሬም በጥርጣሬ እንድንተያይ የሚነዛውን የማደናገሪያ ትርክት መሠረተ ቢስ መሆኑን እንድትገነዘቡና ከጎናችን ሆናችሁ በፅናት እንድትታገሉ ጥሪ አቀርባለሁ›› ሲል ለኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ህዝቦችም አዴፓ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ለትግራይ ህዝብ ባስተላፈው መልዕክት፤ የአማራና የትግራይ ህዝቦች ታሪካዊ አንድነትና ውህደት ያላቸው ባህላዊና ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እሴትን የሚኖሩ መሆናቸውን በመግለጽ ትህነግ/ህወኃትና መሰል ድርጅቶች የሕዝቦችን አንድነት አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉትን ሴራ እንድትታገሉ ጥሪ አቀርባለሁ ብሏል፡፡
አዴፓ በመጨረሻም፤ ለፖለቲካ ሃይሎች ባስተላለፈው መልዕክቱ፤ በአማራም በክልሉ ህዝቦች ስም የምትንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ሃይሎች እየሰፋና እየጠነከረ በመጣው የፖለቲካ ምህዳር አዎንታዊ ሚና እንድትጫወቱ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤ በሌላ በኩል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የትህነግ/ህወኃት የፖለቲካ ደባ የምታስፈጽሙ ተላላኪ የፖለቲካ ሃይሎችና ቡድኖች፤ ከእኩይ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ በጥብቅ አሳስባለሁ ብሏል፡፡    

Read 9427 times