Saturday, 13 July 2019 11:23

የታሰሩ ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የመብት ተሟጋቾች ጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 በኢትዮጵያ ያለው የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ወደ አስጊ ሁኔታ እየተቀየረ መምጣቱን የጠቆሙት አለማቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች፤ መንግሥት በጋዜጠኞች መብት አጠባበቅ ላይ ተጨማሪ ማሻሻያዎች እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
አሁንም ሰበብ እየተፈለገ  ጋዜጠኞች እየታሰሩ መሆኑን፣ ለጋዜጠኞች አስጊና አሳቃቂ የነበረው የፀረ ሽብር ህግ በድጋሚ ስራ ላይ ውሎ፣ ጋዜጠኞች በሽብር እየተከሰሱ መሆኑን እንዲሁም የመረጃ ነጻነትን በሚያፍን መልኩ ኢንተርኔትን የማቋረጥ ተከታታይ እርምጃዎች መወሰዳቸው አሁንም አገሪቱ ለጋዜጠኞች ምቹ እንዳትሆን እያደረጋት ነው ብሏል - ሲፒጄ በመግለጫው፡፡
በአሁኑ ወቅት የ “አስራት” ቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ በሪሁ አዳነና የቀድሞ “እንቁ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፤ ታስረው በጸረ ሽብር ሕጉ መጠርጠራቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ ከዚህም በተጨማሪም በቅርቡ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ የሰጠው የኢፌዲሪ መከላከያ ኃይል በሰራዊቱና በሕዝቡ መካከል ጥርጣሬን ለመፍጠር ሰርተዋል ያላቸውን መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ለመክሰስ ተዘጋጅቻለሁ ማለቱ የአገሪቱን የሚዲያ ነጻነትና የጋዜጠኞች መብት አያያዝን መልሰው አስጊ ያደረጉ ጉዳዮች ናቸው ብሏል፡፡
አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች መታሰር እንዳሳሰበው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በሚዲያ ነጻነትና በጋዜጠኞች መብት አከባበር ላይ ከፍተኛ መሻሻል ተፈጥሮ እንደነበር የገለፀው አምነስቲ በቅርቡ ግን ነገሮች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሁኔታ እየተለወጡ መሆኑ አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡
በአዲስ መልኩ ጋዜጠኞችን ማሰርና በፀረ ሽብር ህግ መክሰስ እንዲሁም ማስፈራሪያዎችን መሰንዘር በአገሪቱ ታይቶ የነበረውን የፕሬስ ነጻነት ወደ ኋላ የሚመልስ እርምጃ ነው ያለው ተቋሙ፤ በሰበብ አስባቡ የታሰሩ ጋዜጠኞችን መንግሥት በአስቸኳይ እንዲፈታና ክሳቸውን ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቋል::

Read 7863 times