Saturday, 13 July 2019 11:11

ኦፌኮ፤ በኦሮሚያ አመራርና አባላቶቼ እየታሠሩብኝ ነው አለ

Written by 
Rate this item
(4 votes)


             በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች አመራሮቹና አባላቱ በሰበብ አስባብ እየታሠሩበት መሆኑን የገለፀው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፤ በየአካባቢው ህዝባዊ ውይይት ለማካሄድ መቸገሩንም አስታውቋል፡፡
በነቀምት የዞኑ የአፌኮ ጽ/ቤት አደራጅና ሰብሳቢ፣ በሆሮ ጉዳሩ የጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ በኢሊባቡር፣ በምዕራብ ሀረርጌ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በቄለም ወለጋና በተለያዩ አካባቢዎች ከ20 በላይ አመራሮችና አባላት ከሰሞኑ እንደታሠሩበት ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
እስሩ እየተፈፀመ ያለው የተለያዩ ሰበብ አስባቦችን በመፈለግ ነው ያሉት የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ አመራርና አባላቶቻችን ለምን ታሠሩ ብለን ስንጠይቅ፤ “ግማሾቹ በቤታቸው የጦር መማሪያ አከማችተው ተገኝተዋል፣ ግማሾቹ በመኖሪያ ቤታቸው ህገ ወጥ ስብሰባ አድርገዋል፤ በህገ ወጥ መንገድ አባላትን አደራጅተዋል” የሚል ምላሽ ይሠጠናል ብለዋል፡፡
የለውጥ ሂደቱን ተስፋ በማድረግ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በመላ ኦሮሚያ በሚገኙ 20 ዞኖች ውስጥ ጽ/ቤት መክፈቱንና በየወረዳዎቹም በርካታ የወረዳ ጽ/ቤቶችን በአንድ አመት ጊዜ ማደራጀቱን የገለፁት፤ አቶ ሙላቱ፤ ጽ/ቤቶቹን ብናደራጅም በየዞኖቹና በወረዳዎቹ ህዝባዊ ውይይቶችን ማድረግ ተቸግረናል ብለዋል፡፡
በኛ የፓርቲ ስብሰባ ላይ የተገኙ ግለሰቦች በወረዳና አካባቢ አመራሮች ወከባና እስር እየተፈፀመባቸው መሆኑን ያስታወቁት ም/ሊቀመንበሩ፤ በተለይ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጽ/ቤታችንም በሃይል እንዲዘጋ ተደርጐብናል ብለዋል፡፡
አባሎቻችንና አመራሮቻችን ለምን ይታሠራሉ ብለን መንግስትን ስንጠይቅ፤ ህግን የማስከበር እርምጃ ነው የተወሰደው” የሚል ምላሽ ይሰጠናል ያሉት አቶ ሙላቱ፤ ማጣራት ሳይደረግ በስመ ህግን ማስከበር ዜጐችን በጅምላ ማሰር፣ ለሀገር ሠላም ጠቃሚ አይደለም፤ በመንግስት በኩል አስቸኳይ እርምት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል፡፡
የቀድሞውን አካሄድ በሚያስታውስ መልኩ ፖለቲከኞች በሰበብ አስባቡ መታሠራቸው በታችኛው የመንግስት መዋቅር ላይ ባሉ አመራሮች ዘንድ የአስተሳሰብም ሆነ የአሠራር ለውጥ ባለመፈጠሩ የተከሰተ ነው ብለዋል - አቶ ሙላቱ፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢ በመከላከያ ቁጥጥር ስር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙላቱ፤ መከላከያ ወጥቶ በመደበኛ የፀጥታ ሃይል ሠላም መረጋገጥ አለበት ይላሉ፡፡
ከኦፌኮ አባላትና አመራሮች በተጨማሪም “የኦነግ ደጋፊ ናችሁ” በሚል ሰዎች እየታሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጠው የክልሉ ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ፤ በህግ ማስከበር ሂደት ሰዎች እየታሠሩ ያሉት በወንጀል ብቻ ተጠርጥረው ነው ብሏል፡፡   

Read 7063 times