Print this page
Saturday, 13 July 2019 11:06

መልክቶቻችሁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በ‹‹ሰሎሜ›› ቶክሾው የታዘብኩት!


           የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ የነበረችውና በጣቢያው ላይ አስደማሚ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣችው ሰሎሜ  ታደሰ፤ በፋና ቴሌቪዥን እያዘጋጀች የምታቀርበውን ‹‹ሰሎሜ›› የተሰኘ ቶክሾው ሁሌም በፍቅርና በጉጉት ነው የምመለከተው:: በፕሮግራሙ የምትዳስሳቸው ርዕሰ ጉዳዮችና የምትጋብዛቸው እንግዶች (ብዙ ጊዜ ወጣቶችና ታዳጊዎችም ይሳተፋሉ) እንዲሁም የፕሮግራሙ አቀራረብ ይማርከኛል፡፡ ለኔ ዘና የሚያደርግም ትምህርት የሚሰጥም ነው የሰሎሜ ቶክሾው፡፡ ስለ አዘጋጇና ፕሮግራሟ ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ፡፡ ለዛሬ ግን ባለፈው ረቡዕ በቀረበው ሳምንታዊ ፕሮግራሟ ላይ ብቻ አተኩሬ ትዝብቴን እገልጻለሁ፡፡
ፕሮግራሙ ላይ የደረስኩት ከጀመረ በኋላ ቢሆንም የዕለቱ ርዕሰ ጉዳይ በትምህርት ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን ተገንዝቤያለሁ:: በትምህርት ፍኖተ ካርታው፣ በትምህርት
ጥራት፣ በማስተማር ዘዴ፣ በኩረጃ ባህል… ወዘተ ስማቸውን ከማላስታውሰው፣ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጋር ሁነኛ ውይይት እያደረገች ነበር፡፡
እንደተለመደው መሃል ላይ እሳት የላሱ የዘመኑ ታዳጊዎችና ወጣቶችን በማስገባት፣  ከዕድሜያቸው በላይ የበሰለና የጠለቀ አስተያየት አስደምጣናለች - በኩረጃና በትምህርት ዙሪያ፡፡ እስከዚህ ድረስ የታዘብኩት የለም፡፡
በፕሮግራሙ መገባደጃ ላይ፣ ፕሮሰፌሰሩ በሰጡት ምላሽ ላይ ነው ትዝብቴ፡፡ ሰሎሜ የኤሊት (Elife) ት/ቤቶች የሚል ነገር አንስታ ማብራራት ጀመረች፡፡ እነ ዊንጌትን፣ ተፈሪ መኮንን… ወዘተ ለአብነት ጠቀሰች፡፡ ባህር  ማዶም ተሻግራ እነ ሃርቫርድን የመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎችን በምሳሌነት አቀረበች:: የኤሊት ት/ቤት ስትል፣ የ‹ሃብታም ወይም ወድ› ት/ቤትን ሳይሆን ምርጦችንና የላቁ ተማሪዎች ማዕከል (Center & excellence) ማለቷ እንደሆነ በቅጡ በማስረዳት… በአሁኑ ዘመን ተማሪዎች የላቀ ብቃትና አቅም ያላቸው ተማሪዎች ለማፍራት፣ ተመሳሳይ የኤሊት ት/ቤት ወይም ተቋሙ ቢኖርስ…? የሚል አስተያየት አቀረበች ጥያቄው ቀላልና ይመስላል፡፡ በተለይ እንደ ፕሮፌሰሩ ላሉ የቀለም ቀንዶች!! ግን ተሳስቼአለሁ፡፡
ፕሮፌሰሩ የሰጡት ምላሽ አስገርሞኛል፡፡ የኤሊት ት/ቤት የሚለውን ነገር…  የተቀበሉት አይመስልም፡፡ ልብ ብሉ! የኤሊት የሚለውን ‹‹የልህቀት ማዕከል›› ስትል ሰሎሜ በግልፅ አብራርታዋለች፡፡ ፕሮፌሰሩ ግን በአሁኑ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የኤሊት ት/ቤት (ተቋም) የሚለው ሀሳብ… የሚተገበር ወይም የሚቻል እንዳልሆነ ነው የገለጹት፡፡ ይልቁንም በመንግሥት የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተመሳሳይ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ  ከጉዳዩ ለመሸሽ ሞከሩ፡፡
እንግዲህ የትምህርት ፖሊሲን እንዲቀየር ወይም ሥር ነቀል የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ እንዲደረግ… ሀሳብ፡፡ ጎበዝ ተማሪዎች የሚበራከቱበትና የሚበረታቱበት የልህቀት ማዕከል ቢቋቋምስ? ነው የተባለው፡፡
በመጨረሻ ላይም ፕሮፌሰሩ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በሌላ ጊዜ በስፋት ተዘጋጅተው እንደሚወያዩ ቃል ገብተዋል።  
ፕሮፌሰሩ፤ ይህን ሀሳብ ለምን ሸሹት? ለምንስ እንደ ከባድ ነገር ለሌላ ጊዜ አስተላለፉት? ለእኔ አሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ ነው፡፡
የአገራችንን እንቆቅልሽ ይፈቱልናል ብለን የምንጠብቃቸው ምሁራን ጭራሽኑ ተጨማሪ እንቆቅልሽ እየፈጠሩብን ነው ልበል? ከእንቆቅልሽ ያውጣን!!
ትዕግስቱ ከአብነት      

Read 2998 times
Administrator

Latest from Administrator