በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው እለት የሚያስመርቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ለኢትዮጵያ እስላማዊ ም/ቤት (መጅሊስ) ዋና ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ሁመር ኢድሪስ እና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም የክብር ዶክትሬት ይሰጣል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር የክብር ዶክትሬቱን የሚሰጠው ለህዝብ ሠላምና አንድነት ላበረከቱት የእድሜ ዘመን አገልግሎት ነው ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም አየር መንገዱን የላቀ ውጤታማ በማድረጋቸው የክብር ዶክትሬት ባለቤት እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር የክብር ዶክትሬቱ እንዲሰጣቸው ማመልከቻ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ኢ/ር ታከለ ኡማ እንደሆኑ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር ኢንድሪስ ደመቀ በወሎ ክ/ሀገር ለጋምቦ ወረዳ ገነቴ በምትባል መንደር ግንቦት 21 ቀን 1929 የተወለዱ ሲሆን በእስልምና እምነት መምህርነታቸውና መሪነታቸው ይታወቃሉ:: ከ50 በላይ ሃይማኖታዊ መጽሐፍት እንደፃፉም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡