Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 09 June 2012 08:13

“መኖሬን የማውቀው ሌሎች እንዲኖሩ መርዳት ስችል ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ዕቅዴ ከአገር ለመውጣት በመሞከር ድንበር ላይ ወይም በረሃ ውስጥ ለመሞት ነበር፡፡  በሱማሌ በኩል በአርትሼክ ወደ የመን ያወጣል ስለተባልኩ፣ በዛው መንገድ ጉዞ ጀመርኩና አርትሼክ ድንበር ላይ በፖሊስ ተያዝኩ፡፡ አንድ አምስት ቀን ያህል ከታሰርኩ በኋላ በሥፍራው የነበረውን የመቶ አለቃ በያዘው ጠመንጃ እንዲገላግለኝ አለበለዚያ ደግሞ ወደምሄድበት እንድሄድ እንዲለቀኝ ጠየኩት፡፡ ምክንያቴን ሲጠይቀኝም እውነቱን ነገርኩት፡፡የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ በሆነችውና ከአዲስ አበባ በአንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዳማ ከተማ ውስጥ HIV ቫይረስ በደማቸው ኖሮ ረዳትና አስታማሚ በማጣት እጅግ የተጐዱ ወገኖችን የሚረዳና የሚንከባከብ ማዕከል መኖሩን ሰማንና ወደ ሥፍራው አመራን፡፡ በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በሰፈረው በዚህ ማዕከል በኤችአይቪ ተይዘው በሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች እጅግ የደከሙና ረዳትና አስታማሚ የሌላቸው ህሙማን ተኝተው ያገግሙበታል፡፡ በማዕከሉ የመጠለያ፣ የመኝታ፣ የምግብ፣ የህክምናና የመድሃኒት አቅርቦት ያገኛሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ህሙማን ወደ ማዕከሉ ከመጡ የስድስትና የሰባት ወራት ዕድሜን ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ በሸክምና በድጋፍ ገብተው የነበሩ ህሙማን ከቀናት እንክብካቤ በኋላ ራሣቸውን ችለው ሲንቀሳቀሱ ማየት ለማዕከሉ የተለመደ ጉዳይ መሆኑ ተነገረን፡፡ ለዚህ ደግሞ በማዕከሉ ውስጥ ያሉ በጐ ፈቃደኛ ዶክተሮች፣ የጤና መኮንንና ነርሶች ለህሙማኑ የሚያደርጉላቸው የህክምና ክትትል ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦቱ፣ የተመቻቸና ንፁህ የመኝታ አገልግሎት ማግኘቱ ለህሙማኑ ጤና ቶሎ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ማዕከሉ ከተቋቋመበት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከ5ሺህ ሶስት መቶ በላይ ህሙማንን ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡  ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ጤናቸው ተሻሽሎና አገግመው በተለያዩ የሥራ መስክ ውስጥ ተሰማርተዋል፡፡

ከበሽታቸው ማገገም ተስኖአቸው ህይወታቸው ያለፈ  ዘጠና ስድስቱ ብቻ ናቸው፡፡

በማዕከሉ ውስጥ ተኝተው በማገገም ላይ ያሉ ህሙማንን ለማየትና ለማነጋገር ከማዕከሉ መሥራች ከአቶ መስፍን ደምሴ ጋር በያዝነው ቀጠሮ መሠረት ማለዳ ላይ አዳማ ገባን፡፡

የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ከሊዝ ነፃ በሰጠው አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ1.6ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው “መስፍን ኢንሼቲቭ የኤችአይቪ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከል” አርባ የህሙማን አልጋዎች፣ ሶስት የምርመራ ክፍል፣ አንድ መድሃኒት ቤት፣ ካፌና የምግብ አዳራሽ፣ የምግብ ማብሰያ ክፍሎች፣ የሻወርና የመፀዳጃ ቤቶች እንዲሁም ማንኛውም በጐ ፈቃደኛ ወደ ማዕከሉ በመሄድ ለሚያከናውነው የጥናት ሥራም ይሁን ሌሎች ተጓዳኝ አገልግሎቶች የሚውል በኮምፒዩተር የተደራጀ ቢሮን አካትቶ ይዟል፡፡

በዚሁ ማዕከል ውስጥ የተገነባውና በርካታ የኤችአይቪ ህሙማን በባለውለታነት የሚያነሱት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ መኖሩን በመግለፅ ወደ ሚዲያ በመጣው የተስፋ ጐህ መሥራች በነበረው ዘውዱ ጌታቸው ስም የተሰየመው ዘውዱ መታሰቢያ ፋርማሲ አገልግሎት መስጠት አልጀመረም፡፡

“ኤችአይቪ ድብቅ በነበረበትና ማንም ስለበሽታው ለመናገር በማይደፈርበት ጊዜ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ በድፍረት በመናገር ወደ ሚዲያ የመጡት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለእኛ እዚህ መድረስ ትልቅ ባለውለታዎች ናቸው” የሚለው  አቶ መስፍን፤ ኤችአይቪ በደሟ ውስጥ መኖሩን በመናገር የመጀመሪያዋ ሴት ለሆነችው ወ/ሮ በላይነሽ ጥላሁንም በስሟ አዳራሽ  ሰይሞላታል፡፡

የማዕከሉ መሥራች አቶ መስፍን ደምሴ ኤችአይቪ በደሙ ውስጥ መኖሩን ያወቀው በ1992 ዓ.ም ነው፡፡ ወቅቱ ኤች አይቪ ድብቅ የሆነበትና ማንም ሰው በቫይረስ መያዙን በግልፅ የማይናገርበት ዘመን ነበርና ራሱን ሲያውቅ እጅግ በጣም ደንግጦ ነበር፡፡

ራሱን ለማጥፋት ሞክሯል፣ ተስፋ ቆርጧል፣ ከአመታት ድካምና ዕልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ግን ከራሱ አልፎ ለበርካቶች መድህን የሆነውን ይህንን የማገገሚያ ማዕከል ሊያቋቁም ችሏል፡፡ ማገገሚያ ማዕከሉን በጐበኘንበት ወቅት በማዕከሉ ያገኘናቸውን ህሙማን ያነጋገርን ሲሆን፣ ስለ ማገገሚያ ማዕከሉ፣ በማዕከሉ ውስጥ ለመግባት ስለሚጠየቀው መስፈርትና ስለወደፊት ዕቅዶቹ ከአቶ መስፍን ደምሴ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ቆይታ አድርጋለች፡፡

በ1992 ዓ.ም ኤች አይቪ በደምህ ውስጥ መኖሩን እንዴት ልታውቅ ቻልክ?

በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ በዳግም ጥሪ ወደ ኤርትራ ከዘመቱ አባላት ጋር ነበርኩ፡፡ የጦር ምርኮኛ ሆኜ ኤርትራ ከቆየሁ በኋላ በ1992 ዓ.ም ወደ አገራችን እንድንመለስ ሲደረግ የአለም ቀይ መስቀል የጤና ሁኔታችንን የሚገልፅ የታሸገ ፖስታ ሰጠን፡፡ ፖስታውን ቀድጄ ስመለከት ወረቀቱ አናት ላይ HIV Positive ይላል፡፡ ደስ አለኝ፡፡ Positive ማለት ከቫይረሱ ነፃ መሆን ማለት ስለመሰለኝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ካምፕ ከገባን በኋላ ትምህርት ሊሰጠን በተቀበላችሁት የጤና መረጃ ላይ HIV Positive የሚል የያዛችሁ ሰዎች ቫይረሱ በደማችሁ ውስጥ ያለ በመሆኑ፤ በቀጣይ ህይወታችሁ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ እያለ ሲናገር ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ፡፡ ከዛ የጦር እሳት ተርፌ የመጣሁት ለዚህ ነው ወይ ብዬ ተስፋ ቆርጬ በጣም አዘንኩ፡፡ ከዛ ግን ራሴን ማጥፋት እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩና ከጦር ሰራዊቱ ተሰናብቼ ወጣሁ፡፡

የት ሄድክ?

ዕቅዴ ከአገር ለመውጣት በመሞከር ድንበር ላይ ወይም በረሃ ውስጥ ለመሞት ነበር፡፡  በሱማሌ በኩል በአርትሼክ ወደ የመን ያወጣል ስለተባልኩ፣ በዛው መንገድ ጉዞ ጀመርኩና አርትሼክ ድንበር ላይ በፖሊስ ተያዝኩ፡፡ አንድ አምስት ቀን ያህል ከታሰርኩ በኋላ በሥፍራው የነበረውን የመቶ አለቃ በያዘው ጠመንጃ እንዲገላግለኝ አለበለዚያ ደግሞ ወደምሄድበት እንድሄድ እንዲለቀኝ ጠየኩት፡፡ ምክንያቴን ሲጠይቀኝም እውነቱን ነገርኩት፡፡ በጣም አዘነ፡፡ እናም ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ እንድሄድና በኤችአይቪ የተያዙ ሰዎች በካምፕ ተሰብስበው የሚረዱበት ቦታ እንዳለ ነገረኝ፡፡ ከጓደኞቹ ባሰባሰበው ገንዘብ ብርድልብስ ገዝቶና የኪስ ገንዘብ ሰጥቶ በኦራል አሣፍሮ ወደ አዲስ አበባ ላከኝ፡

ካምፕ የተባለውን ቦታ አውቀኸው ነበር?

አላወቅሁትም፡፡ አንድ ሆቴል ገብቼ ቁጭ ብዬ ቴሌቪዥን ስመለከት፣ ዘውዱ ጌታቸው “ትውልድ ይዳን፣ በእኛ ይብቃ ቫይረሱ በደማችሁ ውስጥ ያለ ወደ እኛ ኑ፣ ትውልድ እናድን” እያሉ አድራሻቸውን ሲናገሩ፣ ቀስ ብዬ ስልካቸውን ፃፍኩና በማግስቱ ደወልኩ፡፡ ያገኘሁት ዘውዱን ነበር፡፡ ወደ ቢሮው እንድመጣ ጋበዘኝ፡፡ ቢሮው ስሄድ የተመለከትኩትን ነገር ማመን አልቻልኩም፡፡ በጣም ያማረበት ወፍራም ሰው ሳይ ግራ ገባኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ Positive ሰው ያየሁት እሱን ነበር፡፡ ወደ ጦር ሀይሎች ሆስፒታል ላከኝና እዛ የምክር አገልግሎት በመስጠት እንዳገለግል ተደረገ፡፡

ምን አይነት የምክር አገልግሎት ነበር የምትሰጠው?

በህይወቴ እጅግ የማዝንበት አይነት የምክር አገልግሎት ነበር፡፡ ከጦሩ ተቀንሰው የሚሰናበቱ አባላት እየተመረመሩ HIV Positive የሆኑት አንድ ክፍል ይደረጉና እኔ ገብቼ “ለአገራችሁ እንደተዋጋችሁ አሁን HIV Positive በመሆናችሁ ኤድስንም ተዋጉ” እላቸዋለሁ፡፡  አጐንብሰው ይወጣሉ፡፡ አሁን ሳስበው ይህ አይነቱ የምክር አገልግሎት እጅግ የተሳሳተና ወደ ጥፋት የሚያመራ ነበር፡፡ በዚህ በጣም አዝናለሁ፡፡

ወደ ማገገሚያ ማዕከሉ ሥራና ወደዚህ አገልግሎት እንዴት ገባህ?

ቀስ በቀስ በማስተማሩ ዙሪያ ሰዎች እየተበራከቱ ሲመጡ እኔ ሰዎችን ለመርዳት የምችልበትን መንገድ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ 1997 ዓ.ም HIV እጅግ የተስፋፋበትና ህብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ እየጐዳ ያለበት ዘመን ነበር፡፡ በዚህ በሽታ መሞቱ የተጠረጠረን ሰው ቤተሰቦቹ እንኳን በእጃቸው መንካት ይፈሩ ነበር፡፡ ኑና ገንዙልን እያሉ ይጠሩን ነበር፡፡ አስከሬኑ ደርቆ ሰባብረን የገነዝንበት ሁኔታ ሁሉ ነበር፡፡ ይህ ነገር አእምሮዬን እጅግ ነካው፡፡

ዶ/ር ኦርሲዶ ከተባሉ ሰው ጋር ስለዚሁ ጉዳይ አንስተን ስንወያይ፣ አንተ እስከ አሁን አስተምረሃል ከዚህ በኋላ የኤችአይቪ ህሙማን የሚያገግሙበት ማዕከል ማቋቋም አለብህ ብለው መከሩኝ፡፡ ጊዜ አላጠፋሁም፣ በወሩ አዳማ መጥቼ በአንድ ሺህ ብር ቤት ተከራየሁና ህሙማኑን መሰብሰብ ጀመርኩ፡፡

ስትጀምር ምን ያህል ህሙማን ነበሩህ? በምን ሁኔታ ላይስ ነበሩ?

ሃያ የሚሆኑ በሽታው እጅግ የጐዳቸውና ረዳትና አስታማሚ የሌላቸውን ሰዎች ነው ከየመንገዱና ከየቤተስኪያኑ ደጃፍ የሰበሰብኩት፡፡ እነዚህን አስተኝቼ እያስታመምኩና እየደገፍኩ ቆየሁ፡፡

ድጋፍ የሚያደርግልህ ነበር?

በወቅቱ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ከአብኮ ጋር በትብብር ኬር ኤንድ ሰፖርት ለእያንዳንዱ የኤችአይቪ ህመምተኛ 100 ብር ይሰጡ ነበር፡፡ ነገሩን ሳስበው የማይሆን ነገር ነው፡፡ ይህ ገንዘብ አንድ ቀን ሊቁዋረጥ የሚችል ገንዘብ ነው፣ እኛ ደግሞ መስራት እንችላለን፡፡ ገንዘቡን ስጡንና እንስራበት የሚለውን ሃሣብ አቀረብኩና አባላቱን አሳምኜ፣ የአንድ አመት ክፍያውን ወደ መቶ ምናምን ሺህ ብር ተቀብለን ከተወሰኑ አባላት ጋር ቦረና ሄደን ከብት በመግዛት ማድለብ ጀመርን፡፡ በወራት ዕድሜ ትርፋችን ከፍ አለ፣ የተበደርነውን ገንዘብ መልሰን ሱቆችና የቤት ዕቃ ማምረቻ ድርጅቶች ሠርተን ሥራችንን ማስፋፋት ጀመርን፡፡

በማገገሚያ ማዕከሉ ውስጥ በመግባት አገልግሎቱን ለማግኘት የሚፈልጉ ህሙማን ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጣ፡፡ በኪራይ የተያዘችው ቤትም ልትበቃን አልቻለችም፡፡ ሁኔታውን የተመለከቱት የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ባለስልጣናት፣ ማዕከሉን ጐብኝተው ለማዕከል ግንባታ የሚሆን ገንዘብ የምታገኝ ከሆነ መሬቱ ከሊዝ ነፃ ይፈቀድልሃል ብለው 1ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ሰጡኝ፡፡

ለማዕከሉ ግንባታ የሚሆነው ገንዘብ ከየት ተገኘ?

የማንም እርዳታ የለበትም፡፡ መሬቱ ሲሰጠን ማዕከሉን ለመገንባት እንደምንችል ፅኑ እምነት ነበረኝ፣ ህዝቡ ይገነባዋል እል ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሱቆቹን እተማመንባቸው ነበር፡፡ አሁን በመንገድ ሥራ ምክንያት እንዲፈርሱ የተደረጉት እነዚያ ሱቆች፣ ለማዕከሉ ግንባታ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በሚሆን ወጪ ማዕከሉን ገንብተን ስናጠናቅቅ የአለም ጤና ድርጅት ደግሞ በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ የህሙማን አልጋዎችን፣ የህክምናና የላብራቶሪ መሣሪያዎችን በሙሉ አሟላልን፡፡ አንድ አምቡላንስም ሰጠን፡፡

ወደ ማዕከሉ ለመግባት መስፈርቱ ምንድነው?

ቀደም ሲል በኤች አይቪ ተይዘው የተዳከሙና ረዳትና አስታማሚ የለንም ያሉንን ህሙማን ሁሉ እንቀበል ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ህሙማን ቁጥር ከእኛ አቅም በላይ እንዲሆን አደረገው፡፡ ስለዚም ከሆስፒታሎች ወደ እኛ ማገገሚያ ማዕከል ሪፈር የተደረጉና ከጤና ኤክስቴንሺን ባለሙያ ጋር ወደ ማዕከላችን የሚመጡትን ህሙማን ብቻ መቀበል ጀመርን፡፡ ህሙማኑ ወደ ማዕከላችን ሲመጡ ሪፈር ከሚደረጉበት ሆስፒታል የጤና ሁኔታቸውን የሚገልፅና ምን አይነት መድሃኒት እየወሰዱ እንደሆነ የሚያስረዳ መረጃ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ይህም በሽተኛውን ለመከታተልና በጤንነቱ ላይ እየተከሰተ ያለውን ለውጥ ለማጥናት ይረዳል፡፡

በማዕከሉ ውስጥ ያሉ ህሙማንን የጤና ሁኔታ የምትከታተሉበት መንገድ ምንድነው?

በማዕከሉ የህሙማኑን ጤና የሚንከባከቡ አንድ የጤና መኮንን፣ 2 ቅጥር ነርሶች፣ 3 በጐ ፈቃደኞች ነርሶችና በርካታ በጐ ፈቃደኛ ዶክተሮች አሉ፡፡ እነዚህ የጤና ባለሙያዎች ህሙማኑ ያለባቸውን የጤና ችግር በማየት ለተጓዳኝ በሽታዎች የሚረዱ መድሃኒቶችና ህክምናዎችን ይሰጧቸዋል፡፡ የነርቭ ችግር ያለባቸውን ህሙማን ደግሞ በማሣጅ ቴራፒ እንዲረዱ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአንቡላስ እየወሰድን ስፖርት እናሰራቸዋለን፡፡

ለህሙማኑ ምን አይነት ምግቦች ነው የምታቀርቡት? ወጪውስ?

በማዕከሉ ውስጥ ተኝተው ከምናስታምማቸው ህሙማን ሌላ 50 ሰዎች በተመላላሽነት እየመጡ ቁርስ፣ ምሣና እራት ይመገባሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት የጀመሩ ሆነው የሚበሉት የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ አልጋ አልያዙም ይንቀሳቀሳሉ፣ ግን ምግብ ማግኘት አልቻሉም፡፡ መድሃኒቱ ደግሞ ምግብ መመገብ ይፈልጋል፣ ስለዚህም ሐኪሞቻቸው ሪፈር እያደረጉልን እኛ ጋ ምግብ ይመገባሉ፡፡ ምን አይነት ምግብ ነው ላልሽኝ ሁሉንም አይነት የተመጣጠነ ምግብ ነው የምናቀርበው፡፡ ህመምተኛው በራበውና ምግብ በፈለገ ጊዜ ሁሉ ይመገባል፡፡ ምሣ ሰዓት ገና ነው እራት አልደረሰም የሚባል ነገር የለም፣ በምግብ ቤት ውስጥ ያሉ እናቶች ከበሽታቸው አገግመው የተነሱ በመሆናቸው ስለ ህመሙ እና ስለሚፈልገው ነገር ያውቃሉ፡፡ ፈፅሞ ምግብ አይከለክሉም፡፡ የምግብ ወጪያችንን በተመለከተ አሜሪካ አገር ሜኖሶታ ግዛት የሚገኝ ህሙማንን ምግብ የሚያበላ ድርጅት፣ 25ሺህ ብር በየወሩ ለምግብ ወጪያችን ይሰጠናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአዳማ ህዝብ በየዕለቱ ወደ ማዕከሉ እየመጣ ህሙማኑን መጠየቅና ሰርግ ልደት ተዝካር ሲኖርበትም እዚሁ ግቢ መጥቶ ከህሙማኑ ጋር በመብላትና በመጠጣት ማሳለፍን እንደ ባህል ስለያዘው የምግብ ችግር በፍፁም የለብንም፡፡

የመድሃኒት አቅርቦቱስ?

የፀረኤችአይቪ መድሃኒቱ የሚገኘው ከሆስፒታሎች ነው፡፡ እኛ በማዕከላችን ይህንን መድሃኒት አንሰጥም፣ ለተጓዳኝ በሽታዎች የሚረዱ መድሃኒቶችን ግን በግዢ ነው የምናገኘው፡፡ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀንም ለከፍተኛ ህክምናዎች እንደ ሲቲ ስካን ላሉ ምርመራዎችና ለመድሃኒቶች መግዣ የምናወጣው ወጪ ነው፡፡

ከማዕከሉ አገግመው የሚወጡ ሰዎች የት ነው የሚሄዱት?

በዚህ ማዕከል ውስጥ በተለያየ የሥራ መስክ ተቀጥረው የሚሰሩት ሁሉ በማገገሚያ ማዕከሉ ተኝተው የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ አምሣ አንድ ያህል ሰዎች በዚህ ማዕከል ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው ይሰራሉ፡፡  ከበሽታቸው አገግመው ከሚወጡ ሰዎች መካከልም መቋቋሚያ እስከ ሁለት ሺህ ብር እየሰጠን ሥራ እየፈጠሩ እንዲሰሩ እያደረግናቸው ነው፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ባሉ ሰዎች ቤትም በሠራተኝነት የምናስቀጥራቸው ሰዎችም አሉ፡፡ በተለይ በለጋ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆች ከማዕከሉ ወጥተው ዝም ብለው እንዲሄዱ አንፈቅድላቸውም፡፡ ጥበቃ በሚያስፈልጋቸው አካባቢ ውስጥ ሆነው ስነልቦናቸውን የማስተካከል ሥራ እየሠራንባቸው ነው፡፡ ሃላፊነት እንዲሰማቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንመክራቸዋለን፡፡

በአሜሪካ አገር ሜኖሶታ ከተማ ጥሪ ተደርጐልህ ሄደህ ነበር?

አዎ፡፡ በ2001 ዓ.ም የእኔን ሥራ የሰሙ ሜኖሶታ ያሉ በተመሳሳይ ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች /ኦፕን አረም እና ናስታድ/ የተባሉ ሥራቸውን እንድጐበኝ ጥሪ አቀረቡልኝና ወደዚያው ሄድኩ፡፡ ሥራቸውን ጐብኝቼ ከተመለስኩ በኋላ በወሩ ደግሞ እነሱ የእኔን ለማየት መጡ፡፡ ከዛ በኋላ ነው ለምግብ ያልኩሽን ብር 25ሺ የሰጡን፡፡ አሁንም በዚህ በያዝነው ወር መጨረሻ ድጋሚ ወደ ሜኖሶታ ከተማ ተመልሼ እሄዳለሁ፡፡

ለዚሁ ሥራ ነው በድጋሚ የምትሄደው?

አዎ፡፡ ባለፈው እዛው ሄጄ ያየኋቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ በየቤታቸው ዞሬ አይቼአቸዋለሁ፡፡ እጅግ በጣም የሚያሣዝኑ ናቸው፡፡ ታመው አልጋ ላይ የቀሩ ናቸው፡፡ ማንም ማንንም አይረዳም፡፡

አይጠያየቁም፡፡ እርስ በርሣቸውም አይገናኙም፡፡ ሰው ይናፍቃቸዋል፡፡ በዚህ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ እርስ በርሳቸው የሚገናኙበት መድረክ ቢፈጠር የትዳር አጋር እንኳን ማግኘት ይችሉ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ግን የለም፡፡ በዚህ ላይ መሰራት አለበት፡፡ ለዚህና ከዚሁ ጋር ተያያዥ ለሆኑ ጉዳዮች ነው የምሄደው፡፡

ምንድነው ለወደፊቱ ያቀድከው?

እንግዲህ እስከ ዛሬ ባለው ህይወቴ ብዙ ውጣ ውረዶችን ብዙ ፈተናዎችን አልፌ ከዚህ ደርሻለሁ፡፡ በኤች አይ ቪ ህሙማን ላይ የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች በሙሉ ከህሙማኑ ፍላጐትና ስሜት ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማስቀረት ብዙ ትግል አድርጌአለሁ፡፡ በህልም ይመስል የነበረውን ሃሳቤን ዕውን ሆኖ አይቼዋለሁ፡፡ በርካታ አገር አቀፍና አለም አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝቻለሁ፡፡ ግን ይኼ ሁሉ ለእኔ አያረካኝም፡፡ ገና ይቀረኛል፡፡ ይህንን ማዕከል ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ህሙማን የሚታከሙበት ትልቅ ሪፈራል ሆስፒታል የማድረግ ህልም አለኝ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ማዕከል ውስጥ ከተለያየ አካባቢ የመጡ በተለያዩ የአመጋገብና የአኗኗር ባህል ውስጥ የኖሩ፣ የተለያየ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ስለአሉ ትልቅ የጥናት ማዕከል ሆኖ የበሽታው ምንጭ የሚገኝበትና ለበሽታው መድሃኒት የሚፈጠርበት ማዕከል ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

ከአቶ መስፍን ጋር ውይይታችንን ስንቋጭ በማዕከሉ ያሉ ህሙማንን ለማነጋገር ገባን፡፡ አብዛኛዎቹ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ በተለያየ የኃላፊነት ሥራ፣ በተለያየ ሙያ፣ በሹፍርና፣ በረዳትነት፣ በቤት ሠራተኝነት፣ በቡና ቤት ህይወት ውስጥ ያለፉ ህሙማንን አግኝተናል፡፡

ሁሉም ህሙማን ግን በአንድ ቃል የሚናገሩት ይህ ማዕከል ባይኖር ኖሮ ሜዳ ላይ ወድቀው ይቀሩ እንደነበርና አሁን ግን በማዕከሉ በሚሰጠው እርዳታ አገግመው ከሞት መትረፋቸውን ነው፡፡

ከሶስት ዓመታት በፊት ወደ ማዕከሉ መጥተው እንደነበር ያወጉኝና በምግብ ክፍል ተቀጥረው የሚሠሩት ሁለት እናቶች፣ በማዕከሉ ተኝተው ካገገሙና ከተሻላቸው በኋላ ባገኙት የሥራ ዕድል በዚሁ ማዕከል ውስጥ ደመወዝተኛ ሆነው መቀጠራቸውን ነግረውኛል፡፡ ግብፅ አገር ለስድስት ዓመታት መኖሯን ያጫወተችኝ አንዲት ወጣት በርካታ ተስፋ አስቆራጭ ጊዜያትን ካለፈች በኋላ ወደዚህ ማዕከል በመምጣት እንደ እሷ በደማቸው ኤችአይቪ ቫይረስ ያለባቸውን ሰዎች በማግኘቷ፣ ከበሽታዋ ለማገገም እንደቻለች  ገልፃልኛለች፡፡

ህሙማኑ ለማዕከሉ መሥራች ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት የሚገልፁት መንታ መንታውን በሚወርድው እንባቸው ነው፡፡ ከፈጣሪ በታች የህይወታችን ጠባቂ ነው ይሉታል አቶ መስፍንን፡፡ በቡና ቤት ህይወት ለበሽታው የተጋለጡ ወጣቶችም በማዕከሉ አግኝቻለሁ፡፡ ወጣቶቹ ከበሽታው ቢያገግሙም መሄጃ ቦታ የላቸውም፡፡ ተመልሰው ወደቀደመው ህይወት እንዳይገቡ ጥረት እንደሚደረግና የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደሚሞከር አቶ መስፍን ነግሮናል፡፡ ጉብኝታችንን አጠናቀን ከማዕከሉ ስንወጣ አቶ መስፍን አንድ አሣሣቢ ጉዳይ ነገሩን፡፡

በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ካሉ ህሙማን አብዛኛዎቹን ጨምሮ በርካታ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ህሙማን የሚወስዱት መድሃኒት ከበሽታው ጋር እየተለማመደ በመሆኑ፣  የህሙማኑ የወደፊት እጣ ፈንታ እጅግ አሣሣቢ ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸውን አነጋግረን በቀጣዩ ሣምንት ምላሽ ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን፡፡

 

 

Read 3730 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 08:23