Sunday, 07 July 2019 00:00

በአለማችን በየአመቱ ከ2 ቢሊዮን ቶን በላይ ቆሻሻ ይፈጠራል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 የአለማችን አገራት ፕላስቲክና የምግብ ትራፊዎችን ጨምሮ በየአመቱ በድምሩ ከ2 ቢሊዮን ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ እንደሚፈጥሩ በ194 አገራት ላይ የተሰራና ባለፈው ረቡዕ ይፋ የሆነ የጥናት ሪፖርት መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአለማችን በየአመቱ ከሚመነጨው 2 ቢሊዮን ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ ለመልሶ መጠቀም የሚውለው 16 በመቶው ብቻ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ቀሪው 950 ሚሊዮን ያህል ቆሻሻ ግን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደሚወገድ ጥናቱን በመጥቀስ አመልክቷል፡፡
ከህዝብ ብዛታቸው አንጻር ከፍተኛ መጠን ያለው ደረቅ ቆሻሻ ከሚያመነጩ ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት መካከል አሜሪካ በአንደኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ህንድና ቻይና በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ሶስቱ አገራት በድምሩ ከአለማችንን አጠቃላይ ቆሻሻ 39 በመቶ ያህሉን እንደሚያመነጩም ገልጧል፡፡
ከምታመነጨው ቆሻሻ ውስጥ 68 በመቶውን መልሳ የምትጠቀመው ጀርመን፤ ቆሻሻዎችን መልሶ በመጠቀም ረገድ ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት ተቀምጣለች ያለው ዘገባው፣ በአብዛኞቹ አገራት ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም አዝማሚያ እየቀነሰ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
ጥናቱ የተሰራባቸው አገራት በየአመቱ የሚያመነጩት አጠቃላይ ቆሻሻ 820 ሺህ የኦሎምፒክ የመዋኛ ገንዳዎችን የመሙላት አቅም እንዳለው የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ቻይናንና ታይላንድን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ከውጭ አገራት እየገዙ መልሰው ይጠቀሙት የነበረውን ቆሻሻ መግዛት ማቆማቸው ቆሻሻ በከፍተኛ መጠን እንዲጠራቀም ሰበብ መፍጠሩንም አመልክቷል፡፡
በአለማችን የተለያዩ ውቅያኖሶች ውስጥ 100 ሚሊዮን ቶን የሚገመት ቆሻሻ እንደሚገኝ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ይህም የውሃ አካላትን ህልውና በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳውና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ገቢን በእጅጉ እንደሚቀንሰው ገልጧል፡፡

Read 3191 times