Saturday, 06 July 2019 14:35

ቃለ ምልልስ አጭር ቆይታ ከአዲሱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ጋር

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

ሥራዬን የምጀምረው ከማዳመጥ ነው

          የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ የቀድሞው ኮሚሽነር አቶ አዲሱ ገ/ እግዚአብሔር አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ለበርካታ ወራት ኃላፊ ሳይመደብለት ቆይቷል፡፡ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ህግ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ከሰብአዊ መብት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለበርካታ ዓመታት በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ አገልግለዋል፡፡ የ“ሂዩማን ራይትስዎች” የአፍሪካ ሰብአዊ መብት ከፍተኛ አማካሪና የአፍሪካ ሰብአዊ መብት ዲዥን ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ በዓለም ባንክ፣ በኦክስፋም፣
በዩኤስ ኤይድና በሌሎች ድርጅቶችም በአማካሪነት፣ በአሰልጣኝነትና በተመራማሪነት መስራታቸውን የሥራና ልምድ ማስረጃቸው ይጠቁማል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት የቀረቡት ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሾመዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው፤ ከዶ/ር ዳንኤል በቀለ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡


          አሁን በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ምን ይመስላል?
የሰብአዊ መብት አያያዝ በኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት እጅግ በጣም አሳሳቢ ነበር፡፡ በታሪካችን እንደሚታወቀው፤ የሰብአዊ መብት ቀውስ አለባቸው ከሚባሉት አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች:: ነገር ግን ከአንድ ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የለውጥ አጀንዳ፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል ብዬ አምናለሁ፡፡ ብዙ የማይከበሩ የነበሩ የሰብአዊ መብቶች አሁን መከበር ጀምረዋል፤ ትልቅ እርምጃ ተራምደናል ብዬ አምናለሁ ይሄ ማለት ግን የሰብአዊ መብት ችግሮች በሙሉ ተፈተዋል፤ የሰብአዊ መብት ችግር የለም ማለት አይደለም፤ ይልቁኑም እጅግ በጣም ሰፊ፣ ውስብስብ የሆኑ፣ አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡
ለምሳሌ ከግጭት ጋር በተያያዘ የመፈናቀል ሁኔታን መውሰድ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰፊ ሰብአዊ መብት ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈቱ ሳይሆን በረጅም ጊዜ የሚፈቱና ስራ፣ ጥረት፣ እቅድ፣ መፍትሄ … የሚፈልጉ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ይሄንንም ለማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ምቹ ሁኔታ አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ትልቁ ነጥብ የሚመስለኝ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ የሚለየው፣ አሁን እነዚህን ችግሮቻችንን እያነሱ መፍትሄ ለመፈለግ ምቹ ሁኔታ መኖሩ ነው፤ ስለዚህ ይሄ በጣም ያበረታታል፤ ተስፋ ይሰጣል፡፡
እስካሁን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአብዛኛው የሚፈፀመው በምን ላይ ነበር?
ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው የፖለቲካ አስተዳደር የተነሳ፣ ከፖለቲካ ቀውሳችን ጋር፣ ከኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የተነሳ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት የነበረበት አገር ነው፡፡ የዜግነት እና ፖለቲካ መብቶች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ መብቶች ሁሉም ዓይነት መብቶች ማለት ይቻላል በአግባቡ ሳይከበር የኖረበት አገር ነው፡፡ በተለይ በተለይ ግን የማህበረሰብና ፖለቲካ መብቶች በተለየ ሁኔታ ብዙ ገደብ ሲደረግባቸው ነበር፤ ከዚህ በፊት በነበሩ አስተዳደሮች፡፡ አሁን ግን የተለየ ሁኔታ ማየት ጀምረናል፡፡ ይሄ ደግሞ በጣም ያበረታታል፤ ተስፋ ይሰጣል፤ በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ የተገኘው ውጤት የበለጠ  እየሰራን የበለጠ እየገነባን ከሄድን የሰብአዊ መብት ይሻሻላል፡፡
የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ከመንግስት ኃላፊዎችጋር የተያያዙ ከመሆኑ አንፃር የመንግስት ጫናና ተፅዕኖ ሥራውን እንዳያደናቅፍ አያሰጋዎትም?
የሰብአዊነት መስፋፋት፣ የሰብአዊነት ማስከበር፣ የሰብአዊ መብት ማስጠበቅ ስራ ውስብስብ መሆኑን ብገነዘብም፤ የሚያሰጋኝ ነገር ግን የለም፡፡ በሙሉ ነፃነት፣ በራስ መተማመን መስራት እንደምችል አምናለሁ፡፡ ይሄን የሚስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ፍርሃት የለብኝም፤ የሚያሳስቡኝ ነገሮች ግን አሉ፡፡ የምንፈልጋቸውን ለውጦች፤ የምንፈልገውን አይነት የሰብአዊ መብት መከበር በአጭር ጊዜ የሚለወጥ ነገር አይደለም:: ስለዚህ በምን ያህል ፍጥነት ማስኬድ እንችላለን? ይሄንን ለመስራት የሚያስፈልገን የሰው ኃይል፣ ሀብት፣ ተቋማት፣ ሲስተም … የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ ተሟልተዋል ወይስ አልተሟሉም? አሉ ወይስ የሉም? የሚለው ነገር የሚያሳስብ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ግን የረጅም ጊዜ ስራ ስለሆነ፣ ደረጃ በደረጃ፣ ወደፊት መራመድ እንቀጥላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ወደ ስራ ስገባ መጀመር የፈለኩት ከማዳመጥ ነው፡፡ ችግሮቹ ምንድናቸው? የሚያጋጥሙ ነገሮችን እንዴት ልንወጣቸው እንችላለን የሚሉትን ነገሮች ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖረኝ፣ በቅድሚያ ለማድረግ ምፈልገው ከማዳመጥ ለመጀመር ነው:: ተቋም ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ባለድርሻ አካላት ናቸው ከተባሉ፣ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ መ/ቤቶች ጭምር በቅርበት ለመወያየት ለማዳመጥ፣ ችግሮች ምንድናቸው የሚለውን ለመጠየቅ ፍላጎት አለኝ:: ህብረተሰቡንም ጭምር ለመጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ገና ስራውን እየጀመርኩ ስለሆነ ችግሮቹ እነዚህ ናቸው ብዬ በመዘርዘር ሳይሆን በመጀመሪያ በማዳመጥ ለመጀመር፤ ከነዚያ ውስጥ ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጣቸው ለይቶ ለማውጣት እንዲያመቸን ነው:: ከታሪካችን ከፖለቲካ ቀውሳችን፣ ከማህበራዊና ከኢኮኖሚ ችግራችን የሚመነጩ ችግሮች አሉ:: ከተቋሞች ጠንካራ አለመሆን፣ የሚያስፈልጉት አይነት የህግ ማዕቀፎች ካለመፈጠር አንዳንዶቹ ህጎቻችን የሰብአዊ መብቶች ከግዴታዎች ጋር በተስማማ መልኩ የተቀረፁ ባለመሆናቸው መዋቅራዊም ኢኮኖሚያዊም ችግሮችና እንቅፋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገነዘባለሁ፡፡
በሰብአዊ መብት ኮሚሽን እምነት የለንም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች … ይሄን ተዓማኒነት መገንባት አያስቸግርም?  
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተአማኒነትና በቅቡልነት ከዚህ በፊት ችግር እንደነበረበት በገሀድ የሚታወቅ ነው ብዙ የሚያከራክር አይደለም:: ይሄንን ደግሞ በዚህ ተቋም ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ብዙ ተቋማት ላይ የነበረ ችግር ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ፣ ፍ/ቤቶች፣ ሌሎች የዲሞክራሲ ተቋሞችም ቢሆን ከዚህ በፊት በነበረው የፖለቲካ አስተዳደር ስር ወድቀው ሲሰሩ የነበሩ በመሆናቸው ተአማኒነታቸው፣ ቅቡልነታቸው፣ ውጤታማነታቸው ሰፊ ጥያቄ ሲነሳበት የቆየ ነው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተወሰደ ባለው እርምጃ፤ እነዚህ ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ተአማኒነት እንዲያገኙ ከአመራር ጀምሮ ለውጥ መደረግ ጀምሯል፡፡ በምርጫ ቦርድ በፍ/ቤቶች … እንደሚታየው የሰብአዊ መብት ኮሚሽንንም ሊረዳ የሚችል ለውጥ መደረግ ተጀምሯል፡፡ ጥሩ ጅምር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይሄ ጅምር ነው እንጂ ተቋሙ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ተአማኒ፣ ተቀባይ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስፈልገው ስራ ተጠናቋል ማለት አይደለም:: ገና የመጀመሪያ አንድ ድንጋይ፣ አንድ ብሎኬት ናት የተቀመጠችው፤ ይሄ ረጅም ስራ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮያውያኖች በመተጋገዝ አብረን ከሰራን፣ ጠንካራ ተቋማት ለመመስረት እንችላለን ማለት ነው፡፡
ከተሰጠህ ኃላፊነት ጎን ለጎን ተጨማሪ ስራ ለመሥራት ፓርላማውን ጠይቀህ ነበር፡፡ አይከብድም?
አይከብድም፡፡ ተጨማሪ ስራ ሙሉ መረጃው አልተገለፀ ይሆናል እንጂ የሰብአዊ መብት ማቋቋምያ አዋጅ ላይ የሚደነግገው ነገር አለ፡፡ በዋና ኮሚሽነርነት የሚመደበው ሰው ካለው ሙያና ከስራ ልምዱ አንፃር፣ በሌሎች ስራዎችም ላይ ቢሰማራ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ሲታመን፣ ምክር ቤቱ ተጨማሪ ስራ እንዲሰራ ሊፈቅድለት ይችላል ይላል፡፡ ይሄ አንቀፅ ህጉ ላይ የተቀመጠው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከሙያቸውና ከስራቸው አንፃር በሌላም ጉዳዮች ላይ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ከማድረግ አንፃር ነው፡፡ ይሄ የህግ ማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ቢኖርም፣ ከዚህ በፊት ስራ ላይ ውሎ አያውቅም፤ አሁን ግን በተለይ እኔ ከዚህ በፊት በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ካለኝ ልምድና ሙያ አንፃር አስተዋፅኦ ላደርግባቸው የምችላቸው የስራ ዘርፎች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ሳስበው የነበረው ነገር ነበር፡፡ ለምሳሌ አንዱ ማስተማር ነው፡፡ ማስተማርና ኮሚሽኑን መምራት አብረው ሊሄዱ የሚችሉ ስራዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ውስን የተማረ የሰው ኃይል ስለሆነ፣ ያለንን ውስን የሰው ሀይል በተለያዩ ዓይነት ጉዳዮች በአግባቡ መጠቀም መቻል አለብን ከሚል አንፃር የታሰበ ነገር ነው፡፡
አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ከስራ ብዛት አንፃር ስጋት እንዳደረባቸው ተረድቻለሁ፡፡ ይሄንን ወደፊት በተረጋጋ ሁኔታ እንነጋገርበታለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡   


Read 1394 times