Print this page
Saturday, 06 July 2019 14:30

የሰጎን መላ! - (ወግ)

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ /አተአ/
Rate this item
(3 votes)

ሰሞኑን ሄድ መለስ የሚል በሽታ ይዞኛል፡፡ ለሊት ለሊት በላብ ይዘፍቀኝና ሰውነቴን ይቆረጣጥመኛል፤ ቀን ቀን ይጠፋል፡፡ ሃኪም ዘንድ መሄድ ግን አልወድም፡፡ በጣም ያስጠላኛል፡፡ ጓደኞቼ ሲተርቡኝ “የጋርዮሽ ዘመን ሰው ነህ፣ ስለዚህ ዳማከሴ ነገር ጠጣበት” ይሉኛል፡፡ እናም ባለፈው እርሜን ከአንድ ታዋቂ ሆስፒታል በር ላይ ቆሜ የሚንከራተተውን ታማሚ ሳይ ወደ ሃሳቤ የመጡት እነዚያው የልጅነት ትዝታዎቼ ነበሩ፡፡  ተማሪ እያለሁ የተወጋሁት መርፌ ህመም አሁን ድረስ አጥንቴ ውስጥ የሚሰማኝ ሲሆን ሌላ ጊዜ ያጋጠመኝ ደግሞ ሃኪም ዘንድ ሁለተኛ እንዳልመለስ ፍርሃት አድርጎብኛል፡፡ አንዳንዴ ቀላላል ማስታገሻዎችን ከፋርማሲ እገዛለሁ እንጂ ሃኪም ፊት አልደርስም፡፡
ምን አጋጠመኝ!?
የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ እኛ ቤት እንግድነት ከገጠር የመጡ አንድ አዛውንት ዘመዳችን ታመሙ፡፡ ለፍርድ ቤት ክርክር ቀጠሮ ሲጠባበቁ ነበር፡፡ በታመሙ በሁለተኛው ቀን በሃይለኛው መቃዠት ጀመሩ፡፡ አባቴ በጠዋት ከእንቅልፉ እንደተነሳ ወደ እኔ መጣና ሃኪም ቤት ወስጄ እንዳሳክማቸው ነግሮኝና ብር አስቀምጦልኝ ወጣ:: ቁርሴን ከበላሁ በኋላ እየደበረኝ ከተኙበት አልጋ ግርጌ ቆሜ በትካዜ አየኋቸውና በቀስታ መጠየቅ ጀመርኩ፡፡
‹‹አባባ በጎ አደሩ?…››
እያቃሰቱ … ‹‹ማነህ?… ታምሜያለሁ … ለሊቱን ሁሉ ሰራዊት ከላይና ከታች ከቦኝ ነው የሚያድረው:: እንዲሁ ሲያሳቅቁኝ … ተነስ … ተኛ ሲሉኝ ነው ያደሩት…›› አሉኝ፤ በሚንቀጠቀጥ ድምፅ፡፡ ግራ ገባኝ:: እውነቱን ለመናገር አንድ ቤት ነበር ያደርነው:: ምንም አይነት ሰራዊት ከእኛ ቤት ሲመጣ አላየሁም:: ሰውየው ስምጥ ብለው ከተጠቀለሉበት አልጋ መሃል መንዘርዘራቸውን ቀጠሉ፡፡ የመጡት ከቆላ (ሞቃታማ) አገር ስለነበር ወባ መታመማቸውን ቤተሰቡ ሁሉ ስለ ደመደመ የሆነ አገር ባህል ነገር ሲያደርጉላቸው ነበር፡፡
ቆየት ብለው … ‹‹…አየህ ልጄ!… ወባ አራት ደረጃዎች አሉት፡፡ አራተኛው ደረጃ ላይ ሲደርስ ጭንቅላትህ ላይ ይወጣል … ጭንቅላትህ ላይ ሲወጣ በቃ መመለሻ የለውም ይባላል፡፡ … ማለፍ ነው … አይ ሰው ከንቱ … አይ ሰው መሆን … አይ አገር .. አይ ዘመድ … ብቻ ለአገሬ አፈር አብቁኝ አደራ!…›› እያሉ መብሰክሰክ ቀጠሉ፡፡ አሳዘኑኝ፡፡ ሰውየው በጣም ታመው ነበር፡፡
ቀኑ ሞቅ እንዳለ ደግፌ ሃኪም ቤት ወሰድኳቸው:: ሁሉን ነገር አሟልተን ስንጨርስ በየጥጋ ጥጉ ከተኮለኮሉት በሽተኞች ተርታ ቆመን፣ አልኮልና መድሃኒት መድሃኒት የሚሸት ኮሪደር ውስጥ ግማሽ ቀን ወረፋ ጠብቀን ሃኪሙ ዘንድ ቀረቡ፡፡ ወደ ወጣቱ ሃኪም ጠባብ ቢሮ እየተጓተትን ዘለቅን፤ ጠባቧ ፊቱ ላይ ትልቅ መነፅር የሰካ ዶክተር ከጠረጴዛው ላይ ተደፍቷል፡፡ ቀና ብሎም አላየን፡፡ ሽማግሌውን እንደ ደገፍኩ ጥቂት ቆምኩ፡፡ የቆሸሸ ልብስ ለብሰው ስለነበር እኔም ደብሮኛል፤ አሁንም አሁንም እንቅ እንቅ የሚያደርጋቸው ሳል ልጃገረድ ጀረባ ላይ እንደተደላደለ እንስራ ይንጣቸዋል፡፡ ሲያስነጥሱ ፊቴን ባዞርም ፍንጥቅጣቂውን ይበትኑብኛል፡፡ ቆዳዬ ላይ ይታወቀኛል፡፡ ያሳክከኝና አሁንም አሁንም ፊቴን እዳብሳለሁ፡፡ እየቆዩ እየቆዩ ያቃስታሉ፡፡ እኔ በአባቴ በጣም ተናድጃለሁ፡፡ ከትምህርት ቤት ቀርቼ ሽማግሌ እንደሸከም የፈረደብኝ እርሱ ነውና፡፡
ጥቂት ከቆምን በኋላ ከዶክተሩ ፊት ከተቀመጠች ወንበር ላይ አሳረፍኳቸው፡፡ ቀና ብሎ አየን፡፡ ከዚያም ስማቸውንና እድሜያቸውን ቢጠይቃቸው ሰውየው ሌላ ነገር ይዘበራርቃሉ፡፡ እናቴ እንደነገረችኝ ህመሙ ያስቃዣቸዋል፡፡ ቀጥሎ ድንገት ያብራሩለት ጀመር፡ ‹‹…አየህ!… ወባ አራት ደረጃዎች አሉት፡፡ አራተኛው ደረጃ ላይ ሲደርስ ጭንቅላት ላይ ይወጣል … ጭንቅላትህ ላይ ሲወጣ በቃ መመለሻ የለውም … ያው ማለፍ ነው፡፡ እናም አሁን አንተ ጋ የመጣሁት ስንተኛ ደረጃ ላይ እንዳለ እንድታረጋግጥልኝ ነው…››:: እኔ እጅ በደረት እንዳደረግሁ ቆሜያለሁ፡፡
ዶክተሩ በንዴት ገላመጣቸው፡፡ … ‹‹ሰውየ አሁን ዝም ብለው አይዘባርቁ … ምንዎትን እንደሚያምዎት ብቻ ይንገሩኝ…›› አለና ማዳመጫውን ይዞ ቀረበ:: ከላይ የለበሱትን ጭርንቁስ ገልቦ ጀርባቸው ላይ ደገነው፡፡ የሰውየውን ገላ እያየሁ አፌን በጠባቡ እንደከፈትኩ ቆምኩ፡፡ ጀርባቸው ከጣውላና ከሽቦ እንደተሰራ የሰው ልጅ የአጥንት ሞዴል ይመስላል፤ ገላቸውን ታጥበው የሚያውቁ አልመሰለኝም፡፡ እጅግ ከመቆሸሹ የተነሳ በጥፍሮቻቸው የፈተጉበት መስመር እንደ ጠባሳ  ደምቆና የተቆፈረ ቦይ መስሎ ይታያል፡፡
ዶክተሩ ወዲያውኑ ጥያቄውን ያዘንበው ጀመር:: ‹‹…እስኪ በደንብ ይተንፍሱ፤ አዎ! … ወደ ውጪ … ወደ ውስጥ … ምንድነው የሚሰማዎት፤ ስሜትዎን በትክክል ይግለጹልኝ…››
‹‹አየህ ሃኪም … ይገርምሃል! ዛሬ ለሊቱን ሰራዊት ከቦ ሲያዋክበኝ ነው ያደረው፡፡ ግራ ቀኝ እያለ … ተነስ፣ ተኛ እያለ…››
ግንባሩን ከስክሶ አስተዋለኝና … ‹‹አሁን ይሄ ምን ማለት ነው!?…›› ሲል አምባረቀብኝ፡፡ ደንግጬ ትንሽ ካፈጠጥኩ በኋላ … ‹‹ያስቃዣቸዋል… ቅዠት ማለታቸው ነው…›› ስል መለስኩለት፡፡
‹‹…አየህ ሃኪም … ይገርምሃል … ውድቅት ላይ መጥረቢያውን ስሎ መጥቶ ከዚህ ከሽሉዳዬ ዠምሮ ሲከተክተኝ አደረ … እኔምልህ ሃኪም! ደረጃ አራት ደረሰ ወይ?… ጭንቅላቴ ላይ ከወጣ ያው አብቅቶልኛል ማለት ነው!…››
ለእኔ ባልገባኝ መልኩ ሃኪሙ እጅግ ተናደደ፤ እናም በስድብ ከፍ ዝቅ ካደረገንና ጥቂት ነገሮች ከጻፈ በኋላ ደም እንዲሰጡ አዘዘና አስወጣን፡፡ ከደም ምርመራው በኋላ የታይፎይድና የታይፈስ መድሃኒት ተሸክመን ሲመሻሽ ተመለስን፡፡ ከቤት እንደተኙ ሰውዬው መጮህ ጀመሩ፤ ‹‹…አገሬ ውሰዱኝ፣ ዘመዶቼ ጋ አድርሱኝ፣ ለቀየዬ አብቁኝ…›› ጥቂት እንደቆዩ እየተንቀጠቀጡ መንሰቅሰቃቸውን ቀጠሉ፡፡ እናም አባቴ በለሊት ተነስቶ ወደ አገራቸው ይዟቸው ሄደ፡፡ በሁለተኛው ቀን አድርሷቸው ተመለሰ፡፡ በተመለሰ በሶስተኛው ቀን ሰውየው ማረፋቸውን ሰማን፡፡
እናም በልጅነት አዕምሮዬ ለሞት አልደነገጥኩም:: ለእኔ ሞቱ! …  በቃ  ሞቱ!  ነው፡፡ … አባቴ ግን ሲያለቅስ እያየሁት ነበር፡፡ በጣም አዝኖና ተፀፅቶ፣ “ጓዴ፣ ወንድሜ፣ ወዳጄ … ገደልኩህ” እያለ ነበር፡፡በዚያኑ ሠሞን ትምህርት ቤት እንግሊዝኛ አስተማሪያችን ከሼክስፒሩ ማክቤዝ እንዲህ የሚል ቃለ ተውኔት አነበበልን፡፡ ማክቤዝ ሚስቱ መሞቷን እንደሰማ እንዲህ ሲል አዝኖ ነበር፡፡ ይህን ቃለ ተውኔት አልረሳውም፡፡ ጥልቅ ሃዘን ሁሉ የሚገለጸው እንዲህ ነበር የሚመስለኝ፤ (አሁንስ ቢሆን!)
Life’s but a walking shadow, a poor player,
That struts and frets his hour upon the stage,
And then is heard no more. It is a tale
Told by an idiot, full of sound and fury,
ህይወት! …
ህይወትማ ከንቱ ጥላ ነው፤ ከንቱ የመድረክ
ተዋናይ
ሃዘኑን ከራሱ ገምዶ ሲያበቃ፣ ደስታን በደቂቃ
የሚያሳይ
ህይወት ማለት በእውነት ተረት ነው፤ አፌን በዳቦ
አብሱ አይነት
በሞኝ የተመደረከ ጩኸት፣ ልቅሶና ዋይታ
የበዛበት፡፡
(በደምሳሳው የተተረጎመ)
***
እናም በዘመናት ልዩነት በድጋሚ ሀኪም ቤት ተገኘሁ፡፡ ገብቼም ደሜ ተቀዳ፡፡ ከምርመራውም በኋላ የመድሃኒት ማዘዣውን የፃፈውን ሃኪም መመልከት አልደፈርኩም፡፡ መነፅር አድርጎ ነበር:: ላቤ እየተንዠቀዠቀ ወጥቼ ወደ መድሃኒት ቤቱ ዘለቅሁ፡፡ ባለሙያውም ወረቀቱ ላይ የተጻፈውን ጥቂት ካስተዋለ በኋላ የራሱን መጠይቅ ጀመረ፡፡
‹‹ከዚህ በፊት እንዲህ አሞህ ያውቃል እንዴ!››
‹‹አያውቅም…›› ወገቤን እንደ ደገፍኩ ላቤን ጠራረግሁ፡፡
‹‹በጣም ከባድ ነው …  አምስት መቶ ሃያ ስድስት ብር…›› አለኝ፡፡ ቆጥሬ አስረከብኩ፡፡
ብዙ እሽግና ጥቅልል መድሃኒቶች ከፊቴ ዘርግፎ ሲያበቃ፣ እየቆጠረና አወሳሰዳቸውን እያብራራ፣ በፌስታል አጉሮ ፊት ለፊቴ አኖራቸው፡፡ ብድግ አድርጌ መንገዴ ቀጠልኩና አንድ ሁለት ተራምጄ ተመለስኩ፡፡ በድካም፣ በጥርጣሬና በፍርሃት መሃል ቆሜ ጠየኩት፤ ‹‹…ለመሆኑ ግን ህመሜ ምንድነው?!…››
ፈገግ ብሎ ያስረዳኝ ጀመር፡፡ ቀይ ድዱን በጥቁር ቀለም መወቀሩን ገና አሁን ነበር ያየሁት፡፡ ‹‹ይህንንማ ሃኪምህን ነበር መጠየቅ የነበረብህ … ለማንኛውም መድሃኒቱ የታዘዘልህ ለታይፎይድና ለታይፈስ ነው … መርፌውም ጠዋትና ማታ 7 ቀን ይወስድብሃል::
ተከታትለህ ካልጨረስከው አደገኛ ነው … እናም…››
ፊቴን አዙሬ መንገዴን ቀጠልኩ፤ ምን አይነት አጋጣሚ ቢሆን ነው፡፡ የመድሃኒት ቤቱን ደረጃ እንደወረድኩ ከሚገኘው የቆሻሻ በርሜል ውስጥ ፊስታሉን ወርውሬ፣ ወደ ቤታችን የሚወስደውን ኮረኮንች አቀላጥፈው ጀመር፤ አሁን ህመሙ ሁሉ ለቆኝ ነበር፡፡ ነጭ ሽንኩርትና ጤና አዳም ገዝቼ እገባለሁ እያልኩ እያሰላሰልኩ አፈጠንኩት፡፡
በሶስተኛው ቀን ከመኝታዬ ተነስቼ ስወጣ በር ላይ ወደቅሁና ከሰዓታት በኋላ ራሴን ከዚያው ሃኪም ቤት አልጋ ላይ፣ በቀጫጭን እጆቼ ላይ እንደ መዥገር የተጣበቀ የግሎኮስ መርፌ በደም ስሬ ውስጥ ሰምጦ አገኘሁት፡፡ ከግርጌ በኩል ትልቅ መነፅር የሰካ ሃኪም በፈገግታ ሲያስተውለኝ፣ ብርድ ልብሱን ጎትቼ በጭንቅላቴ ላይ አኖርኩና በጭለማው ማሰላሰሌን ቀጠልኩ፡፡ የሰጎን መላ መሆኑ ነበር፡፡ ሰጎን አንዳንድ ጊዜ ሃይለኛ ጠላት ሲያጋጥማት ጭንቅላቷን አሸዋ ውስጥ ትቀብራለች፡፡ ካላየሁት ነገርየው የለም እንደ ማለት፡፡ የሽማግሌው ልም አይኖችና የጀርባቸው ላይ መስመሮች የሁልጊዜ የሀሳብ መነሻዬ ነውና በጨለማው ብልጭ አለብኝ፡፡ እናም ለጥቆ እንዲህ የሚል ስንኝ፣
አይ ህይወት!
ህይወት ማለት በእውነት ተረት ነው፤ አፌን በዳቦ
አብሱ አይነት
በሞኝ የተመደረከ ጩኸት፣ ልቅሶና ዋይታ
የበዛበት፡፡


Read 1567 times