Saturday, 09 June 2012 08:15

ተቃዋሚዎችን የማማከር አገልግሎት ልጀምር ነው! (በክፍያ)

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

ለባለስልጣናት የኑሮ ውድነት መመልከቻ “መነፅር” ይሰራላቸው

ማርሻል ቲቶ የዩጐዝላቪያ መሪ በነበሩበት ጊዜ ነው አሉ፡፡ ቲቶ የደህንነት ሚኒስትራቸው ራንኮቪክን አስከትለው በከተማዋ ጉብኝት ያደርጋሉ (የሥራ ልትሉት ትችላላችሁ!) መጀመርያ ወደ አንድ ወላጅ አልባ ህፃናት ማሳደጊያ ተቋም ነበር የሄዱት፡፡ በተቋሙ ውስጥ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ሊወጡ ሲሉ ህፃናቱ ያሉበትን ሁኔታ ለማሻሻል በሚል 10ሺ ዲናር ይለግሳሉ -ቲቶ፡፡ በመቀጠል ጋብቻ ሳይመሰርቱ የወለዱ እናቶች መጠለያ ይሄዱና 15ሺ ዲናር ይሰጣሉ - የእናቶቹንና የህፃናቶቻቸውን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል በሚል፡፡ የቲቶ ቀጣይ ጉብኝት ወህኒ ቤት ነበር፡፡ እዚያ ደግሞ 80ሺ ዲናር ሰጡ - የእስረኞች አያያዝ እንዲሻሻል በማዘዝ፡፡ እንደኛ መንግሥት ለሰብዓዊ መብት የሚቆረቆሩ ቢሆኑ ኖሮ ግን ወህኒ ቤቱን አፈራርሰው ጉደኛ ህንፃ ይገነቡበት ነበር፡፡
(ቻይና እንዳቆመችው የአፍሪካ ህብረት ህንፃ ማለቴ ነው!)
ወደ ቲቶ ታሪክ ልመልሳችሁ:-
ቲቶ ለወህኒ ቤቱ ባደረጉት የበዛ ልግስና የተገረሙት የደህንነት ሚኒስትራቸው፤ “ለምንድነው የእስረኞች አያያዝ እንዲሻሻል ያን ሁሉ ገንዘብ የሰጠኸው?” ሲሉ ይጠይቁዋቸዋል፡፡
ቲቶም ሲመልሱ፤ “ክፉ ቀን ቢመጣ እኔና አንተ ማረፊያችን የት ይመስልሃል? የህፃናት ማሳደጊያ ተቋም፣ የእናቶች መጠለያ ወይስ ወህኒ ቤት?”
ቲቶ አርቆ አስተዋይ ነበሩ (አርቆ አስተዋይነት ከተባለ) እውነትም ታዲያ የማታ ማታ ማረፊያቸው ወህኒ ቤት ነበር አሉ - የዩጉዝላቪያው የቀድሞ መሪ ማርሻል ቲቶ፡፡ በነገራችን ላይ አዲስ አዋጅም በሉት መመሪያ ሲወጣ ከዕለታት አንድ ቀን እኔም ላይ ተፈፃሚ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ቢቀር እንኳን መጠርጠር ክፋት የለውም (የፊተኛውን በምን አነቅከው በሻሽ፤ የኋለኛው እንዳይሸሽ” የሚል አገራዊ ተረትም አለ!)
እኔ የምለው …እዚህ አገር ዘመናዊ ወህኒ ቤቶች የመገንባት እቅድ አለ እንዴ? አይገርምም…  አንዱ ካድሬ ወዳጄ እኮ ነው ሹክ ያለኝ፡፡ ዘመናዊ ስላችሁ ታዲያ ፍላት ስክሪን ቲቪ ምናምን ያለው ማለቴ አይደለም፡፡ እንደሱ ከሆነማ እንደ ኮንደሚኒየመ በዕጣ ተከፋፍለነው የወህኒ ቤት እጥረት ተፈጠረ የሚል ዓለም አቀፍ ዘገባ መሰራጨቱ አይቀርም፡ እናላችሁ … ዘመናዊ ሲባልም “አንፃራዊ” መሆኑ ልብ ይባልልኝ፡፡
እኔን የሚገርመኝ ምን መሰላችሁ? ፈጣሪ ለእነጃፓን ማለቂያ የሌለው የቴክኖሎጂ ፈጠራና ተሰጥኦ ሲያድላቸው ለምንድነው ለእኛ ክፋት፣ መጠላለፍ፣ ጥላቻና ሃሜት ከድርሻችን በላይ ያሻረን? ቀላል ጥያቄ እንዳይመስላችሁ፡ በምንም ጥያቄ አይበገሩም የሚባሉት ጠ/ሚኒስትራችን እንኳን አቅቷቸው ትተውታል አሉ፡፡ ወደ ቁምነገሩ ስንመጣ… አሁን ጃፓን የሰራችው አዲስ መነፅር የሚበሉትን ምግብ መመጠን እያቃታቸው ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት (obesity)  ለሚጋለጡ ሰዎች ሁነኛ መፍትሄ ነው ተብሏል፡ እንዴት መሰላችሁ? መነፅሩ ትንሿን ምግብ ቆልሎ የሚያሳይ ነው … ስለዚህም ተመጋቢዎቹ ገና ሲያዩት የምግብ ፍላጐታቸው ይቆለፋል፡፡ እንደድሮው እያግበሰበሱ የስጋ ክምር መስራት ቀረ ማለት ነው፡፡ ችግር ፈቺ መሆን ማለት እንግዲህ ይሄው ነው!
ባይገርማችሁ… ስለዚህ መነፅር ገና እንደሰማሁ ነው ለአገራችን የተመኘሁት፡፡ ለእኛ የሚያስፈልገን መነፅር ግን ትንሽ ለየት ይላል፡፡ ገና በምግብ ራሳችንን ስላልቻልን ከልክ በላይ ውፍረት ለጊዜው ችግራችን አይደለም፡፡ እኛ የሚያስፈልገን እርስ በርስ የምንተያይበት መነፅር ነው፡፡ እኛ የሚያስፈልገን ዲሞክራሲያችንን አጋንኖ የሚያሳየን መነፅር ነው፡፡ እኛ የሚያስፈልገን የፖለቲካ ምህዳሩን አገር አሳክሎ (ለጥጦ) የሚያሳየን መነፅር ነው፡፡
አንድ ባለፈረስ ምን አደረገ መሰላችሁ? ፈረሱ ያገኘውን ሁሉ ሳር ነው ብሎ እንዲግጥ መላ ሲዘይድ ቆየና አረንጓዴ መነፅር በትእዛዝ አሰራለት አሉ፡፡ ከዛ በኋላ ስለ ቀለብ መጨነቅ ቀረለት፡፡ ፈረስ ሆዬ ካርቶኑንም፣ ጫማውንም፣ ቡትቶውንም ሳር እየመሰለው ይጐሰጉሳላ! በእርግጥ ለእኛ የሚሰራው መነፅር ከዚህ ፍፁም ይለያል፡፡ (እኛ ፈረስ አይደለንማ!)
አያችሁ … የእኛ ችግር ሌላ ሳይሆን የአተያይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ኢኮኖሚው 11 በመቶ ዓመታዊ እድገት እያሳየ ነው ይላል፤ ተቃዋሚዎች ሃሰት ብለው ይሟገታሉ፡፡ ማነው ሃቀኛ ካላችሁኝ… መልሴ ሁለቱም የሚል ነው፡፡ (አዋቂ ይዋሻል እንዴ?) ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል ይላሉ፤ ኢህአዴግ የጠበበ ነገር የለም ባይ ነው፡፡ ማንን እንመን? ሁለቱንም፡፡ ለምን ብትሉ? የሁለቱም አመራሮች ነጭ ፀጉር ያበቀሉ አዛውንቶች ስለሆኑ ይዋሻሉ ልንል አንችልም፡፡ (በአገራችን ባህል ሽማግሌ አይዋሽማ!) ደሞስ ለፖለቲካ ምህዳር ብለው ነው የሚዋሹት! እኛ ግን ትክክለኛውን እይታ ማግኘት እንድንችል በልዩ ትእዛዝ መነፅሩ ይሰራልን፡፡ ጃፓን ስሪት ቢሆን ደግሞ ይመረጣል፡፡ የቻይናው ችግር አያጣውም ብዬ እኮ ነው፡፡
እኔ የምለው… እዚሁ ጋዜጣ የነገር ጥግ ላይ “ድሃ በግ ሲያርድ የሚያሳይ መነፅር አስመጥተናል” የምትል ማስታወቂያ አላነበብኩም እንዴ? እሷ መነፅር የጃፓን ናት የቻይና ስሪት? እስቲ አጣሩልኝ፡፡ ሌላ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? ለመንግሥት ባለስልጣናት የደሃውን ኑሮ የሚያዩበት ልዩ መነፅር በትእዛዝ እንዲሰራላቸው! እሱ ብቻ አይደለም… የኑሮ ውድነት መመልከቻ ልዩ መነፅርም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያለመነፅሩ መግባባት እንደማንችል አየነዋ! ተቃዋሚዎች ደግሞ የኢህአዴግ ሥልጣን ምን እንደሚመስል የሚያዩበት ልዩ መነፅር በትእዛዝ ሊሰራላቸው ይገባል (ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር እንዳይሆንባቸው ብዬ እኮ ነው) አያችሁ… ሁላችንም መነፅራችንን ካገኘን የኢትዮጵያ ችግር ተፈታ ማለት ነው፡፡ (ያው ጊዜ መውሰዱ ግን አይቀርም)
በነገራችሁ ላይ አዲስ የቢዝነስ ፕሮፖዛል እያረቀቅሁ ነው፡፡ አይዲያዋ የተኮረጀች ብትሆንም ሃይለኛ ቢዙ ያላት ናት፡፡ ምን መሰላችሁ? ተቃዋሚዎችን የማማከር አገልግሎት ነው፡፡ እኔ የማማክረው ታዲያ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ፓርቲዎች፣ ግንባሮች ወዘተ ብቻ ነው፡፡ “ዱር ቤቴ” ብለው ጫካ የገቡ ካሉ ሥራቸው ያውጣቸው፡፡ አያችሁ … እንዲህ ራሴን ግልፅ ካደረግሁኝ ካድሬውም ሥራ አይፈታም - የእኔን የጀርባ ማንነት በማጥናት፡፡
የቢዝነስ ሃሳቡ ከየት መጣ አትሉም? ከአንድ የሰርብ ተወላጅ ነው፡፡ የተመረቀው በባዮሎጂ ቢሆንም ሙያው ግን ሰላማዊ አብዮት መጀመር የሚፈልጉ ወገኖችን ማሰልጠንና ማማከር ነው፡፡ “ኢንተለጀንት ላይፍ” ከተባለ እውቅ መፅሄት ላይ ባገኘሁት መረጃ SRDJA popovic የተባለው የሰርብ ተወላጅ በዓለማችን 40 አገራት ላይ የሚገኙ አማፅያንን ያማክራል፤ ያሰለጥናል፡፡ ፖፖቪክ የሰርቢያ አምባገነን መሪ የነበሩትን ስሎቮዳን ሚሎሶቪች ከስልጣን ለመገርሰስ በተደረገው ትግል ውስጥ ተሳትፏል ይላል - መፅሄቱ፡፡ (በ18 ዓመቱ!)
ከሦስት ዓመት በኋላ እሱና ሌሎች ወጣቶች መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሰረቱ - Center for applied non violent Action and Strategies የሚባል፡፡ Canvas ይሉታል በአጭሩ ሲጠሩት፡፡
ይሄ ድርጅት በሰላማዊ ትግልና አብዮት ለሚያምኑ ዲሞክራሲ - አፍቃሪ ቡድኖች ሥልጠና በመስጠት ይታወቃል፡፡ ፖፖቪክም የአረብ አብዮት (Arab Spring) ቀያሽ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ የአረብ አብዮት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ ከቱኒዝያ፣ ከሊባኖስና ከግብፅ የተውጣጡ ታጋዮችን አሰልጥኗል - የእነ ፖፖቪክ ድርጅት Canvas. በካይሮ የታህሪር አደባባይ የህዝብ አመፅ እንደው በግብታዊነት የተካሄደ አልነበረም የሚለው ኢንተለጀንት ላይፍ መፅሄት፤ ህዝባዊ አመፁን የመሩት ቤልግሬድ ድረስ ሄደው የእሱን ስልጠና ያገኙ ናቸው ብሏል፡፡ (የእሱ ምልምል ልትሏቸው ትችላላችሁ፡፡) ነገሩን ግልፅ ለማድረግ የፖፖቪክ ሥልጠና በሰላማዊ ተቃውሞ አምባገነን ከሥልጣን ማውረድ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ አንዳች መሳሪያ በትግል ስልቱ ውስጥ የለም - ምላጭም ቢሆን፡፡ የፀጥታ ሃይሎች ጥቃት ቢሰነዝሩም እንኳን ምላሽ መስጠት ክልክል ነው፡፡ የትግሉ ሥልት አይፈቅድም፡፡ በዘፈን፣ በከበሮ፣ በግጥም፣ በፉከራ፣ በቀልድ፣ በተረብ፣ በሹፈት፣ በስላቅ ነው ተቃውሞው የሚካሄደው ይላል መፅሄቱ የትግሉን ካሪኩለም የቀረፀውን የ39 አመቱን ፖፖቪክ በመጥቀስ፡፡ በእርግጥ ፖሊስ ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው የሚል ነገር በትግል ስልቱ ውስጥ አልተካተተም፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞ አድራጊዎች እንዴት ጥቃቱን ያለጥቃት እንደሚከላከሉ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የእግር ኳስ ቲፎዞዎችና ሥልጠና ያልወሰዱ ጐረምሶች በሰላማዊ ተቃውሞው እንዳይሳተፉ ካሪኩለሙ ይመክራል፡፡ ትንሽ ስህተት ቀውጢ ትፈጥራለችና (ፖፖቪክ እንደሚለው)
አንዳንድ ፀብ ያለሽ በዳቦ የሚዳዳቸው የኢህአዴግ ካድሬዎች ይሄን ሰው ቢያገኙት ዓለም አቀፍ ሽብርተኛ ብለው ወህኒ ቤት ሊወረውሩት ይችላሉ፡፡ ሰውየው ግን የሰላም የኖቤል ሽልማት እጩ እንዲሆን ወረፋ እንደተያዘለት የ”Peace Research Institute OSLO” ዳይሬክተር ለመፅሄቱ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ እውቅ ጆርናል የሆነው Foreign Policy በ2011 ዓ.ም 100  ምርጥ ዓለም አቀፍ አብሰልሳዮች (Thinkers) በሚል ካወጣቸው በአንደኝነት “የአረብ አብዮተኞችን” ያሰፈረ ሲሆን ፖፖቪክንም ከእነዚህ አብዮተኞች አንዱ አድርጐ ሰይሞታል፡፡
የዚህን የሰላማዊ አብዮት መሃንዲስ ታሪክ ሳነብ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የ97 ግርግር! ምናልባት ይሄ ሰው ሥልጠና ቢሰጥ ኖሮ እኮ ለፖለቲካ ቀውስ አንዳረግም ነበር (ግምቴ ነው) ሌላ ጥርጣሬዬን ደግሞ ልንገራችሁ፡፡ በG8 አገራት ስብሰባ ላይ ድንገት ተነስቶ ተቃውሞውን ያንበለበለው ጋዜጠኛ አበበ ገላው የፖፖቪክ ምልምል ይሆን እንዴ? (እሱ ብቻ ነው የሚያውቀው!)
በነገራችን ላይ የእኔ ቢዝነስ ለትርፍ የሚሰራ ስለሆነ እንደ ፖፖቪክ በነፃ ምክር አይሰጥም፡፡ ተቃዋሚዎችን እያማከረ የአገልግሎት ክፍያ ይቀበላል - በሰዓት እያሰላ፡፡ ቢዝነሴ ለኢህአዴግም እንደማያንስ ላሳውቀው እፈልጋለሁ፡፡ አያችሁ … የእኔ ምክር በሰላማዊ ትግል ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ ኢህአዴግ ከእኔ ብዙ ይጠቀማል ብዬ አስባለሁ፡፡ የእኔ አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ የአድማ መበተኛ ጭስ ስላለቀብኝ ሽጉጥ ተኮስኩ ምናምን የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ እንደ 97 ዓ.ም በቂ የሰለጠኑ ፖሊሶች ስለሌሉኝ ነው ህይወት የጠፋው የሚለውም አይሰራም፡፡ የሆነስ ሆነና የንግድ ፈቃድ የሚሰጠኝ የትኛው የመንግሥት አካል ይሆን? ገና ተጠንቶ ነው ከተባለ ግን በህቡዕ ሥራዬን መጀመሬ አይቀርም፡፡ (ሽብር ሳይሆን ቢዝነስ እኮ ነው!) ይሄም ህገወጥ ነው ከተባልኩኝ ግን በ1ለ5 ተደራጅቼ ኮብልስቶን አነጥፋለኋ! (ፈጠራ ካልተበረታታ ምን አደርጋለሁ?)

 

 

Read 3666 times Last modified on Saturday, 09 June 2012 08:24