Saturday, 06 July 2019 14:24

እያስመዘገብኩ ነው

Written by  አውግቸው ተረፈ
Rate this item
(5 votes)

“--ያንን ሁሉ ጩኸት ምን አመጣው? ሊቀ መንበሩ መጣና እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሰጥቶ ሄደ፡፡ እኛም ወጣንና እደጅ ቆመን ዝናብ
ይቀጠቅጠን ጀመር፡፡ ታዲያ ይህ ተገቢ ነው? ይህንንም እያስመዘገብኩ ነው፡፡--”
                   


            ዛሬም እንደ ወትሮው የደንቧን ቀምሼ ለመመለስ ከሠፈራችን ጠጅ ቤቶች አንደኛው ዘንድ ጐራ አልኩ፡፡ ስገባም አግዳሚ ወንበር ላይ ጥግ ይዤ ተቀመጥኩ፡፡ ጠጅ ቀጅው አልቀዳልኝ ብሎ ስለነበር እጄ እስቲቃጠል አጨበጭባለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ አንዴ እፍ ቢሏቸው ተሽቀንጥረው እዚያ ማዶ ይወድቁ እሚመስሉ ሰውዬ መጡና ከፊት ለፊቴ ቆመው፣ አጠገቤ ወደ አለው ባዶ ቦታ እያመለከቱ፤ “ልቀመጥ?” አሉ፡፡ “እሺ” እንደ ማለት፣ አንገቴን ነቀነቅኩና ዝም አልኩ፡፡ አግዳሚውን ጠረጴዛ በጥንቃቄ ተራምደው ቁጭ ካሉ በኋላ ባርኔጣቸውን አውልቀው፣ ቀኝ እጃቸውን ለሰላምታ ዘረጉልኝ፡፡ ጨበጥኳቸው፡፡
ካናቴራና ሸሚዝ ስለአለበሱ አሮጌ ኮታቸው የደረታቸውን ክሳት አጋልጦ አጥንታቸው እስቲቆጠር ድረስ ያሳጣቸዋል፡፡ ጉንጫቸው ጐንና ጐኑ የተጠረመሰ የጉልት ጣሳ ይመስላል፡፡ ሱሪያቸው ከጉልበታቸው እስከ ቁርጭምጭሚታቸው ድረስ ተቀዷል፡፡ ጫማቸው ከተረከዛቸው ላይ ከመንሻፈፉም በላይ ሁለቱንም አውራ ጣቶቻቸውን አሾልኳቸዋል፡፡ አሮጌ የሰሌን ባርኔጣቸውን አውልቀው በእጃቸው ስለያዙት ሽፍ ብሎ የበቀለው ፀጉራቸው ከተላጨ ብዙ ጊዜ እንዳልሆነውና ሽበት የወረራቸው መሆኑን ያሳያል፡፡
ለብዙ ጊዜ ሌላ ሌላውን ጫጫታ እያዳመጥኩ ተቀመጥኩ፡፡ ሰውዬው የተቀዳላቸውን ጠጅ አልነኩትም፡፡ አየት አድርጌያቸው ዘወር ስል ጐሸም አደረጉኝና፤ “ጋሽዬ ይህ ጥሩ ሥራ ነው?” አሉኝ፡፡ እኔ ግን የጥያቄያቸው ሥረ መሠረት ስላልገባኝ ዝም አልኳቸው፡፡ “በእውነት በውነት…ይህ ጥሩ ሥራ ነው?” አሉኝ፣ ደገሙና፡፡ የባሰ ግራ ተጋባሁና ትኩር ብዬ አየኋቸው፡፡ ዓይናቸውን አፍጠው፤ መንጋጭላቸውን ኩርትም አድርገው፣ አንገታቸውን እያንዘረዘሩ፤ “ይገባል?” አሉኝ፡፡
“ምኑ?” አልኳቸው፡፡
“እኔ ቀለም ስቀባ ውዬ የሠራሁበትን ቆርጦ ማስቀረት ተገቢ ነው?”
ምንም ሳልመልስላቸው ብርሌዬን አንስቼ አንደቀደድኩት፡፡ ቀጠሉና፤ “ይህማ ጣትን መቁረጥ ማለት ነው፡፡ ለመሆኑ ከትንሿ ጣት ላይ ምኗ ይቆረጣል?”
“ማነው የቆረጠብዎ?”
“ሌላ ማን ሊሆን ነው? ጌቶች ናቸዋ? ጌቶች? መሥራት አትፈልግም ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ና ደህና ገንዘብ እከፍልሃለሁ፡፡ እየጠጣህ ባትሰክር ኖሮ፣ በሥራ ማን አጠገብህ ይደርሳል?” አሉኝ:: “ምን ቆርጦኝ ነው ጌታዬ እሠራለሁ እንጂ፡፡ ከተገኘ ማንኛውንም ሥራ እሠራለሁ“ አልኳቸውና ቤታቸውን ስጠርግ አቧራውን ሳራግፍ፣ የሸረሪት ድሩም፣ ጥቅርሻውም፤ ምኑም ምኑም በዓይኔ፣ በጆሮ፣ በአፌ ሲገባ፣ ስሠራ፣ ስሠራ ውዬ የድካሜን ዋጋ ከለከሉኝ፤ የቀለሜንም ዋጋ አብረው አስቀሩብኝ፤ አስቀሩብኝ…ወይኔ መኩሪያ አዎ…ታዲያ ችላ ብዬ ያለፍኩት አይምሰልህ…እያስመዘገብኩ ነው፡፡”
ዓይናቸውን ግራና ቀኝ ከብለል ከብለል እያደረጉ አዘኔታና ፍትህ በሚለምን አመለካከት አዩኝ:: ዕውነትም ደም ሰርቧቸው ፍም የመሳሰሉት ዓይኖቻቸው፣ በአንድ በኩል በደል የተፈፀመባቸውና አግባብ አለመሆኑን ሲገልጹ፣ በሌላ በኩል እጃቸውን እያወዛወዙ ከንፈራቸውን ሲነክሱ “ቆይ ግድ የለም ይጠብቅ” የሚሉ ይመስላሉ፡፡
ብርሌዬን እያነሳሁ ጠጄን በማንደቅደቅ ማዳመጤን ቀጠልሁ፡፡
“ባልና ሚስት ሲጣሉ፣ ሲጨቃጨቁ፣ መሣሪያ መዞ መጥቶ በሰደፍ መማታት ተገቢ ነው? ይኸውልህ ለምን ከባለቤትህ ጋር ትጣላለህ ብሎ በሰደፍ የመታኝን ላሳይህ?” ብለው እጄን ጐተቱና፣ ጀርባቸው ላይ አንድ ያበጠ ነገር አስዳሰሱኝ፡፡
“ምንስ አብዮት ጠባቂ ቢሆን እንደኔ ድንጋይ ሲሸከም፤ ጭቃ ሲያቦካ፤ ቀለም ሲቀባ አደል እሚውለው፡፡ እያወኩት …ልክ አይደለም፡፡ ልክ አይደለም” እያሉ እጃቸውን በማወናጨፍ ብሶታቸውን ሁሉ ለመናገር ከመቸኮላቸው የተነሳ፣ የምራቃቸው ፍንጥርጣሪ እፊቴ ላይ ማረፉን ያጤኑት አይመስልም፡፡
ቅሬታና ብስጭታቸውን፣ ራሳቸውን ግራ ቀኝ በማማታት እየገለጹ፣ ተከዝ እንደ ማለት ብለው አቀርቅረው  ቆዩ፡፡
“እንዴት ነው አንዱን ሳይጨርሱ ሌላውን የሚጀምሩት?” እያልኩ ሳምሰለስል፣ጐሸም ሲያደርጉኝና “ጋሽዬ አንተን ጨምሬ አስለቀስኩህ ልበል?” ሲሉ ነው እንደገና ቀና ማለታቸውን ያጤንኩትና ፍንጥርጣሪዎቹን በመሐረቤ ያባበስኩት::
“…ተመልክተው ይህን ደግሞ ከጓዳ የሚወጣውን…የሁለት ብርሌ የከፈልኩለት እኔ ነኝ:: በቀደም ጠመንጃህን አፈሙዙን ቀና አድርገህ ያዘው፤ ካርታ ሙሉ ጥይት እንደጐረሰ ምላጩን ነካ ካደረከው ሰው ትገላለህ አልኩት፤ ይህ መጥፎ አባባል ነው? ይህን በመናገሬ በጥፊ አጮለኝ…”
ግንባሬን ኮስተር አድርጌ፣ ዓይኖቼን ፊት ለፊት ካለው ግድግዳ ላይ ባለው የሥነ ስቅለት ሥዕል ላይ ተክዬ፤ “ታዲያ እኔን ምን አድርግ ይሉኛል?” እንደ ማለት ግዴለሽ ለመምሰል ጣርኩ፡፡ አጠገቤ የነበረው ሰውዬ፤ “ይህ መጥፎ ሽማግሌ ከያዘ አይለቅ? ምን አድርግ ነው የምትለው?” አላቸው “ድሃ ስለማይንቅ ከኛ ጋር ሲበላ ሲጠጣ ጊዜ፣ የሱ ቢጤ መሐይም መሰለው’ኮ እባካችሁ?” አፈርኩ፡፡
ሰምተው እንዳልሰሙ ሆኑና ቀጠሉ፤
“…አሁን ስብሰባ አለብኝ ብሎ ሄደ፡፡ ምን እሚመክር ይመስልሃል? በኔ ላይ እኮ ነው ምክራቸው:: የፈለገኝን ያህል ብጠጣ፣ የትስ ባድር ምን አገባቸው? የምሬንኮ ነው ጋሽዬ፤ “የት ዋልክ? ስንት ጠጅ ጠጣህ? ምን አወራህ?” ይህን ምን አባባላቸው? እኔ የምጠጣው ዛሬ ብቻ አይደለም፤ ሚስቴንም የምመታት ዛሬ ብቻ አይደለም፡፡ ዱሮ ጀምሬ ጠጅ እጠጣ ነበር፤ ሚስቴንም እመታት ነበር:: እሷም ልብሴን ትቀድብኝ ነበር፡፡ ተመልከተው:: ሸሚዝና ካናቴራ የለኝም፡፡ ባለቤቴ ቀዳብኝ ነው” ብለው አሮጌ ኮታቸውን ገለጡና፣ ያንን የከሳ ደረታቸውን አጥንት አስቆጠሩኝ፡፡ “ታዲያ የትናንቱ ጠብ አዲስ መሆኑ ነው፤ በሰደፍ እንድመታና እንድታሰር ያደረገኝ? ተገቢ ነው? ባጠፋስ በሕጉ መሠረት አልጠየቅም? ለምን ስም ወጣልኝ? ለቤቴስ ቁጥር ለምን ተሰጠው? መታወቂያስ ለምን ተሰጠኝ? ወንጀል ብሠራ በሕጉ መሠረት እንድጠየቅበት አይደለም? ሚስትህን መታህ ተብዬ በሰደፍ…ጋሽዬ ይህ ጥሩ ሥራ ነው…?”
“ታዲያ ሚስትህን እንድትደበድብ ተፈቅዶልሃል?” አላቸው፤ አጠገቤ የተቀመጠው ሰውዬ፡፡ ቀና ብለው እንኳ ሳያዩት ቀጠሉ፡፡
“አትዘክርብኝ ጋሽዬ፣ ተበሳጭቼ ነው፡፡ ግን የሰከርኩ እንዳይመስልህ” ቀጠሉ “ትናንት እኛ ቀበሌ ሳሙና መጣ፤ ጦርነት የተነሳውም በሱ ነው:: ትግል፣ ትንንቅ፣ ግብ ግብ ተነሳ፡፡ ልጅ አዋቂው ዋይ፣ ዋይ አለ፡፡ ይኸውልህ ኮቴን ይዘው ሲጐትቱኝ ቀደዱት” ኮታቸውን አሳዩኝ፡፡ “ያንን ሁሉ ጩኸት ምን አመጣው? ሊቀ መንበሩ መጣና እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሰጥቶ ሄደ፡፡ እኛም ወጣንና እደጅ ቆመን ዝናብ ይቀጠቅጠን ጀመር፡፡ ታዲያ ይህ ተገቢ ነው? ይህንንም እያስመዘገብኩ ነው፡፡”
ጠጅ ቀጅው አልቀዳልኝ ብሎ በብርሌ ጠረጴዛውን እቀጠቅጣለሁ፡፡ የሰው ጩኸት ጆሮ ቢቆርጡ አያሰማም፡፡
“…ዱሮ የነበርኩበትን ቤት ባለቤት ታውቀው የለ?” አሉኝ፤ የብዙ ጊዜ እውቂያ ያለን ይመስል:: ቢሆንም ቶሎ ጨርሰው ብገላገል ብዬ “አዎ” አልኳቸው፡፡ “ይኸውልህ እሱ ነው፣ ያኔ አሥራ አምስት ብር የሚሸጠውን ጫማ ዛሬ አርባ ብር፣ ሃምሳ ብር፣ የሰባት ብር ሸሚዝ ሠላሳ ብር፣ የአርባ ብር ኮት፣ መቶ ሃምሳ ብር የሚሸጥ፤ ላንተ ምን እነግርሃለሁ፡፡ ህብረት ሱቅ የሚያስመጣውን ዕቃ ሁሉ ባሽከር፣ በገረድ፣ በሚስት፣ በዘመድ አዝማድ አስገዝቶ ይወስደዋል፡፡ የሳሙናውንም ጦርነት ያስነሳው እሱ ነው፡፡ ለመሆኑ ያ ሁሉ እረብሻና ጩኸት ከየት መጣ? ሕብረት ሱቁስ ለምን ተዘጋ? እንደሚባለውማ ከሊቀ መንበሩ ጋር ተሻርኮ አዘግቶ ሲያበቃ በጐን ያስወስደዋል፡፡ ከዚያ ሳሙና አለቀ ይባልና፣ ስኳር አለቀ ይባልና…እንደገና እስቲመጣ ጠብቁ ይባላል፡፡ ለነገሩማ የአንድ ሣሙና መግዣ አጥቼ ተበድሬ አልነበር የሄድኩ፡፡ ብገዛውስ ምኑን ላጥብበት ነው? ኧረ ለምን…ይሄንንም እያስመዘገብኩ ነው፡፡”
ዓይናቸውን እያጉረጠረጡ፣ እጃቸውን እያወናጨፉ፣ በንዴት፣ በችኮላ ሲናገሩ፤ አሁንም ምራቃቸው እየተፈናጠረ፣ ፊቴን ሲያለብሰው፣ እኔ ስጠርግ አልተገነዘቡትም፡፡ የደም ሥራቸው በቁጣ ተገታትሮ፣ የሲቃና የእልህ እሮሮአቸውን ቀጥለዋል፡፡
“ጋሽዬ፣ መኩሪያ ብለው ስም ያወጡልኝ ለምንድ ነው? ከሌሎች ሰዎች ተለይቼ እንድታወቅበት አይደል፡፡ ለቤቴስ ቁጥር ለምን ተሰጠው? አጥፍቼ ብከሰስ የትም ሄጄ እንዳላመልጥ አይደል? ገና ለገና ቤት ኪራይ ከፍያለሁ ብዬ ባልከፈሉት ሰዎች ላይ መኩራትና መሣቅ ይገባኛል? ቤት በሌላቸው ላይ መኩራት ይገባኛል?....
“ይችን ደባላችንን፣ አሁን እንዲህ መከራችንን ልታሳየን፣ መጀመሪያ ብታያት እንዴት ታሳዝን ነበር መሰለህ፡፡ ረስተኸው ካልሆነ የመጣች ዕለት ከባድ ዝናብ ይዘንብ ነበር፡፡ ታዲያ ልጅዋን አዝላ መጣችና ከዝናቡ ለመጠለል እጥግ ቆመች፡፡ የኛን ቤት ታውቀው የለ? በረንዳ የለው፤ ምን የለው፤ እንዲያውም ቆርቆሮው አርጅቶ፣ ወንፊት ሆኖ የቤቱን ግድግዳ ስለማያስጥለው ከላይ ዝናቡ፣ ከታች ጐርፉ ተጋግዘው ሊጥሉት እንደ ሐምሌ ደመና ከብዶ ያስፈራራል፡፡
“ሴትዮ ምን ትፈልጊያለሽ? መቼም በዚያ ዝናብ ጤነኛ ሰው እደጅ አይቆምም፡፡ በዚያ ላይ ብርድ አንጀቷ ድረስ ገብቶ ያንቀጠቅጣታል፡፡ ከውሃ የወጣች አይጥ መስላ ሳያት በጣም አሳዘነችኝ፡፡ የኋላውን ምኑን አውቄ፣ እንዲያው ሆዴ ስለማይችል ብቻ ነው፡፡
“ሴትዮ ልጅሽን ጨምረሽ በዝናብ አትግደይ:: ግቢና አባሪው፡፡ ምንም ቢሆን ውስጡ ከውጩ ሳይሻል አይቀርም” ስላት እያፈረች ገብታ ተቀመጠች፡፡ ባለቤቴ ደግሞ “ይህን ያህል ዝናብ ከሚያበሰብስሽ ለምን አንዱ ቤት አትጠለይም ኑሯል?” ብላ ለቡና ማፍያ ያቀጣጠለችውን ከሰል እንድትሞቅ አቀረበችላት፡፡
“ኋላ ብናያት አትሄድም፡፡ ብናያት አትሄድም:: ሴትዮዋ ምን ሆናለች፣ ከባሏ ተጣልታ ይሆን? አልኩና “እምይ ዝናቡ አባርቷል፡፡ ሂጅና ለባለቤትሽ ምናምን አብስይለት” አልኳት፡፡
አንገቷን ቀና አደረገችና፤ “አሄሄ ባል እንዳለው ሰው ሁሉ” አለች፡፡
“ባል የለሽም እንዴ?”
 “የለኝም”፡፡
“ቤትሳ? ባል ባይኖርሽ ወደ ቤትሽ አትሄጅም?” አልኳት፡፡
“የለኝም” አለችና ዓይኗን ባዶው ግድግዳ ላይ ሰክታ ልጅዋን ማጥባት ቀጠለች፡፡ እንግዲህ ሲመሽ የት ትሄዳለች? ባይሆን አድራ ነገ ትሄዳለች ብለን አሳደርናት፡፡ በበነጋታው ብንጠይቃት “ምን መሄጃ አለኝ፡፡ ይሄን ሰሞን ብርድ ሲሆን ጊዜ ልጄን አመመብኝና ምን አልባት ብርዱ ይሆናል፣ ትንሽ እስቲሻለው የሚያስጠጋኝ ሰው ባገኝ ብዬ ስፈልግ፣ እግሬ እናንተ ቤት አደረሰኝ” ብላ ልጁዋን ታቅፋ ለመሄድ ስትነሳ ሆዴ ተንቦጫቦጨ፡፡
ባለቤቴ ደግሞ አብራን እንድትሰነብት ስለማትፈልግ በክፉ ዓይኗ አየቻት፡፡ ፊት ነሳቻት፡፡ ወንድ ነኝ ብዬ የባለቤቴን ቁጣ ንቄ፣ እንግዲያውስ ትንሽ ቀን ተቀመጭ ብዬ ወጥቼ ሄድኩ፡፡ የባለቤቴን ቁጣ ለማብረድ ስል፡፡
(ከደራሲ አውግቸው ተረፈ “ወይ አዲስ አበባ” የአጭር ልብወለዶች ስብስብ፤”እያስመዘገብኩ ነው” ከሚለው ታሪክ የተወሰደ)

Read 1196 times